የኛ ቤት ጀበና

እሳት ያተከነውን ጀበና ከምድጃው ላይ መንጥቃ አወጣችው። ቻይነቱ ይገርማል፤ እየተጠበሰም ቢሆን ፍልቅልቅ ፈገግታውን ይጋብዛል። ቡና ቀዳችና ከቆሎውም፣ ከቂጣውም፣ ከልስሱም ቆንጥራ ቆሌ ተቋደስ ብላ በአራቱም ማዕዘን ረጨችው። ይህን ያደረገችው ከቆሌ በፊት ሰው ከቀመሰው አዝመራውን፣ ልጅና ከብቱን ይጣላልና ነው። አቦል ጀባ አለችና የጀበናውን ጆሮ ስማ ወስከንባዩን ብትከፍተው ሞሰብ ወርቁ በህብስት ተጨንቋል። “የቆራሽ ያለህ …” አለች እንዴ ደጁን አንዴ ህብስቱን አትኩራ እያየች።

በባህሉ በቤቱ አባወራ ከሌለ ሌላ ወንድ ቡና ጠጭ መጠበቅ ግድ ነው። በስመ ስላሴ ባርኮ ከሰጣት በኋላ እንጂ ሴት ልጅ ከወንድ ቀድማ እጇን ወደ ሞሰቡ አትሰድም፤ እማማ ጦቢያውንም የጠበባት ይህ ነው። እንኳን በበዓል ወቅት ባዘቦትም ሰው የማይለየው አዳራሽ ወና ሆኗል። ተራውጠው ያደጉበት ልጆች ዛሬ የሉም፤ መብሉ መጠጡ ሞልቶ ተርፎ ሳለ አይኗን ሰው እራበው። ደጅ ደጁን ብታይ ዝር የሚል ጠፋ፤ ተንገበገበች። “ለካ… ጊዜ ሲጥል እንዲህ ነው¡ ተናፋቂ እንዳልነበርኩ ናፋቂ ልሁን?” አለች ከንፈሯን ነክሳ። “ልጆቼን የሰው ሰራሽ ወረቀት ቢያስኮበልላቸው የወላድ መካን ተባልኩ” ውጋት እንደያዘው ወዲያ ወዲህ እየተንቆራጠጠች “ምነው ጌታዬ… ብትወደኝ ነው ብትጠላኝ ፈተናዬ መብዛቱ? ባውዳመቱ ምድር ባይተዋርነት ቤቴን ሲወረው እንዴት ፈቀድክ?” ከደም የወፈረ እንባ ጉንጯን አራሰው። በሐዘን ብዛት ደንዝዛለች፤ ከቀልቧ አልነበረችም። ተንጋግተን ከቤቷ ስንገባ እንኳን አልሰማችም። ሴት ልጇ ከወደ ኋላ ቆማ እጇን በፊት ለፊት ሰዳ አይኗን በመጨፈን “እንኳን አደረሰሽ እናቴ” ስትላት ከሰመመን ነቃች።

ያብራኳ ክፋዮች እጅ እየነሳናት ስታይ ዳግም የደስታ እንባ አነባች። ለቅሶ ቤት ነው እንዴ የመጣነው? ብዬ ገሰፅኳት። እንባዋን አደራርቃ የበረደውን ቡና ጣደችና የዶሮ አይን የመሰለ ጠላ አሲይዛን ከበናት ተቀመጥን። ቤት ያፈራውን ስታቋድሰን እኛ ደግሞ ስጦታ አበረከትንላት። የመጀመሪያውን ሀጎስ “እናቴ ላውዳመቱ እንኳን አደረሰሽ” ብሎ የያዘውን ሻማ ዘረጋላት።

አንዴ ሻማውን አንዴ እሱን እያች “ሻማ በቀን ምድር ምን ይሰራል?” አለችው። “በቃረምኩት እውቀት የጋረደንን ያስተሳሰብ ጨለማ እንደሻማ ቀልጬ እገፈዋለሁ” ብሎ ቃል በመግባት ጫንቃ ሳመ። አጫሎ ደግሞ ከደጅ ያኖረውን በትር አምጥቶ አስረከባት። “አቅሜ ሳይዝል መቋሚያ ለምኔ?” ብትለው ታናሾቹ የሚደገፉት፣ ታላቆቹ የሚመረኮዙት ጠንካራ ትውልድ እንደሚሆን ቃሉን ሰጣት። እኔም የበኩሌን ሰነዘርኩ። የታሸገውን ካርቶን ብትፈታው መአት ኮንዶም ነው፤ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ… ለኔ ኮንዴቭ?” አለችና አሽቀነጠረችው። እታተይ ብዬ ጠራኋትና እራሴን ከበሽታ በመጠበቅ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር እጥራለሁ በማለት ኪዳን አሰርኩ። ቀጥላ እህታችን ጅንስ ሱሪ አሳቀፈቻት። ምን አልኩሽ ልጄ? በሚል አስተያየት ተመለከተቻት። “ጥበብ ቀሚሱን አሽሞንሙኖ ያለበሰኝ እጅሽ እንዳይገፋኝ ከእንግዲህ ወዲያ ሱሪ አልደነቅርም ብላ ጉልበት ሳመች። በመጨረሻም ሁሴን ባንዲራና ጩቤ ይዞ ከፊቷ ቆመ። “ደግሞ ምንድን ነው እሱ?” አለች አይኗን ተክላበት። “ የክብር ልብስሽን ለማውለቅ ከሚያሴሩት ጋር አብሬ የበላሁ እንደሆነ ያባቴ ቃል እርግማን ይሁንብኝ፣ አጥንቱ እሾህ ሁኖ ይውጋኝ” አለና ፉከራ ቢጤ አስከተለ።

“እውነት ከእውነትነቱ ለማይሻገር፣

ለሰው ሰራሽ ወረቀት ከምግደረደር፣

የድሃ ልጅነቴን ይዤ ልቀበር። ”

ወደኛ እየጠቆማት የቱንም ያህል ከባድ ችግር ቢሆን በውይይት ከመፍታት በቀር ከወንድሞቼ ጋር ደም ላልቃባ ቃል እገባልሻለሁ ብሎ የያዘውን ጩቤ ሰባብሮ እግሩ ስር ጣለና የክብር ልብስ አጎናጸፋት

እየተፍለቀለቀች “ልጆቼ ማለፊያ እውቀት ገብይታችሁ መጥታችሁልኛላ!” አለችን።

የበዓሉን ሽርጉድ እንዳዲስ ጀመረችው። ቆራሽ ያንቃቃ የነበረውን ህብስት ከፊታችን ሰየመችው። ሁላችንም ተፈራራን። ከተለያየ አባት መወለዳችንን እንጂ አንድም ቀን የአንድ እናት ልጆች መሆናችንን አስበን ተፈቃቅደን አናውቅም። አማትቤ ድፎውን ልቆርጥ ቢላ ሳነሳ ሀጎስ እጄን ያዘኝ።

ኧረ ተይ እገሊት ጡር ፍሪ ጡር ፍሪ፣

ታላቅ ተቀምጦ ታናሽ አትዳሪ።

ተብሎ መዘፈኑን አጣኸው?“ አለ ሞሰቡን ወደ ራሱ እየሳበ። ታላቁ ያላገባ እንደሆነ ታናሹ ቁሞ መቅረት አለበት? ብዬ አሾፍኩበትና ተራዬን እጁን ይዤ “አንተስ ማን ስለሆንክ ትቆርሳለህ? ብዬ ከለከልሁት።

በመልካም ስራ ለተምሳሌትነት የበቃ ዕድሜ ሲያስከብር የእንጨት ሽበት የወረሰው ዕድሜ ባንጻሩ ያስንቃል። ወጣቱ ኃይል የሚሰደደው በሀገሩ መኖር ጠልቶ መሰለህ? ቀድሞ በመወለድ የሚያምነው የዕድሜ ክልል ጥቅሙን ላለማጣት ሲል ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም፣ ልጅ ቢሮጥ አባቱን አይቀድምም እያለ ያሸሸዋል እንጂ አያቀርበውም፣ እና… ብሶቴን በዳቦው ብገልጽ ምን ይመስልሀል? አልኩትና ሞሰቡን ወደኔ አንኳተትኩት። ሽንፈት መስሎት እልህ ተጋባ፤ መልሶ አንሻቶ ወሰደው። ሁሴንም ጣልቃ እየገባ “እናንተ ከምትጣሉ ከሁላችሁም እኔ ቀይ ስለሆንኩ ልቁረሰው” ብሎ እጁን ሲያሾል ማንነት ባስተሳሰብ እንጂ በቀለም አይለካም ብዬ ዝም አሰኘሁት። አጫሎ እኔም ይድረሰኝ ይመስላል፤ “ከሁላችሁም ወፍራሙ እኔ ስለሆንኩ ብቆርሰውስ?” አለ በተራው። የአፈር ክምር ገለባው እንጂ ፍሬው መቼ ታይቶ ያውቃል? በማለት በነገር ጎሸምኩት።

ኡፋይሴም “ቅድሚያ ለሴት” ብላ ልትቆርስ ቢላውን ጨበጠች። እጇን አረገፍኳትና የምናከብረው ማርች ኤይት አይደለም አልኳት። “ማለት?” ብላ ነገር ልታከር ስትል ማለት ተብሎ አረፍተ ነገር አይጀመርም ብዬ ደሰኮርኩና ዝም እንድትል ባይኔ ዛትኩባት። እናታችንም ሁኔታችን አልጥምሽ ቢላት በትዝብት ታየናለች። ከፊቷ ጥሩ ስሜት አይነበብም፤ ግንባሯ ተኮሰታትሯል። ዳቦውን ለመቁረስ ሁሉም የሰጡት ምክንያት አሳማኝ ባለመሆኑ እራሴው ልቆርሰው ካራውን ሳሰናዳ እነሱም ግንባር ፈጥረው አበሩብኝ። እቆርሳለሁ አትቆርስም ስንጓተት ሞሰቡ ተከነበለ። በድርጊታችን የእናታችን ሐዘን አገረሸ። እናታችን “በጠባችሁት ጡቴ ይዣችኋለሁ፤ …

የእሳቱ ፍም ጀግንነታችሁ፣

የጀበናው ገላ ጥቁር እንቁነታችሁ፣

የፍንጃሉ መልክ ዘላቂ ሰላማችሁ፣

ይሁነኝና ለሀሳቤ አንድምታ፣

ማህጸኔ እንዳይረገም የማታ ማታ፣

እንድኖር ብትሹ እድሜ ልኬን ተደስቼ፣

በአድባሩ ፊት ይቅር ተባባሉ ልጆቼ።

አለችን ተስፋ ሰንቃ፣

እያየችን አፈራርቃ።

እኛ ግን የጋለበን ሰይጣን ከላያችን አልወርድ ብሎ መናቆሩን ቀጠልን።

ስንብላላ የሰሙ አንድ አዛውንት “ቤቶች እንኳን አደረሳችሁ” ብለው ገቡ። ጩኸታችን መበርከቱን ገልጸው ምን እንደሆን እናታችንን ጠየቋት። እሷም የለቅሶዋን ሰበብ አንድም ሳታስቀር አዋየቻቸው። አዛውንቱም “ልጆቼ…ቀርቦ ከመገፋት ተወዶ ከመጠላት ይሰውራችሁ፣ታምኖ ከመጠርጠር አግኝቶ ከመቸገር ይጠብቃችሁ፣ የራስን ከመዘንጋት የሰውን ከመመኘት ያውጣችሁ፣ ብዙ ከማውራት ብዙ መስራት ያልምዳችሁ፣ አዋቂ እንጂ ታዋቂ ለመሆን አትጣሩ፣ ስራችሁ አፍ አውጥቶ ይናገራልና ” እያሉ ምርቃትና ምክር ቀላቅለው ሲገስጹን ቆይተው ጦቢያ ትቅደም ብለን ህብስቱን በጋራ እንድንቆርሰው አዘዙን፤ እንዳሉን አደረግን። የእናታችን ፈገግታ እንደ ጸሀይ ብርሀን ሞቀን። እንትፍ እንትፍ ተብሎብን ቆሌ እርቀ ሰላም ሲያወርድ አዛውንቱንና እናታችንን ከመሀል አድርገን በእጃችን እንግጫ ይዘን…

አንቺ ኢትዮጵያ… ውዲቷ ቆንጆ ሀገራችን፣

በሦስቱ ቀለም ሰንደቅ አላማችን፣

እንዘምርልሻለን በሙሉ ልባችን፣

ሀሳብሽን እንፈጽመው በትግላችን።

ኢትዮጵያ እናታችን ደግ ወላድ እናት፣

ወልዳ የምታሳድግ በማር በወተት፣

ልጆቿ ፋፍተዋል በእርሷ አሳቢነት፣

ይኸው ተሰብስበው ያሳያሉ ህብረት።

ህብረታቸው ፅኑ ሰውን የሚያስቀና፣

ኢትዮጵያም ደስ አላት በእነርሱ ትህትና።

ኢትዮጵያ እምነቷን ስትጥል በእኛ ላይ፣

መበርታት አለብን እንዳንሆን አባይ።

አፍ የፈታንበትን ዜማ ዳግም አንቆረቆርነው። ድንገት እትዬ ባንቺ አይሞሉ በሬን ሲያንኳኩ ከእንቅልፌ ነቃሁ። የቅዥቴን ምንጭ ሳስስ ከራስጌ አገኘሁት፤ ለካስ አያቴ ስትነግረኝ አልሰማ ብዬ ሱሪዬን ተንተርሸው ኖሯል። በህልሜ የዘመርኩላትን ውብ ኢትዮጵያዬን ብፈልጋት ከልቦለድና ከዘፈን ውጪ አጣኋት።

ሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም

Recommended For You