ስለ ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ወዳድነት መናገር ለቀባሪ የማርዳት ያህል ነው። ኢትዮጵያውያን ለእግር ኳስ ምን ያክል ዋጋ እንደከፈሉና እየከፈሉ እንዳሉ ከአፍሪካ ዋንጫ፣ እስከ ካፍ ምስረታ፣ ከካፍ ፕሬዚዳንትነት አሁን እስካለንበት የደጋፊ ስሜት ድረስ ያለውን መረዳት በቂ ነው። ከቀጠናዊ እስከ አህጉራዊ ብሎም እስከ ዓለም አቀፍ የሚደርሰው የደጋፊ ስሜት ኳስ ወዳድነታችንን ከማሳየቱ በላይ በእግር ኳሱ ላይ ያለንን ተስፋ የሚያሳይ ነው።
ታሪክ በእግር ኳሱ ላይ የኋሊት ቢምዘገዘግ በሆነ ዘመን ላይ ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር ያገኛል። እንደ ነጻነትና ስልጣኔ፣ ጥበብና ጀግንነት ሁሉ በአፍሪካ እግር ኳስም ቀደምት ታሪክ አለን። ዛሬ ላይ ያ ስም በነበር ተውጦ ድሮ ተብሎ የሚገለጽ ሆኗል። ካፍን ከመጀመር እስከ አፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት ከፍ ሲልም ዋንጫ እስከ መብላት የደረሰ ድላችን ነፍስ አልዘራ ብሎ በመድረኩ ቀላዋጭ ካደረግን ብዙ ዓመታት አለፉ።
ከግብጽና ሱዳን ጋር ተቧድነን የመጀመሪያውን የአፍሪካ ዋንጫ ለዓለም ያስተዋወቅን እኛ ነበርን። በማዘጋጀትና ዋንጫውንም በማስቀረት ስም ነበረን። ከዛ በኋላ በነበሩት የእግር ኳስ ታሪኮች ግን ተሳትፏችን እየቀነሰ ዋንጫ መብላት አይደለም ተሳትፎ ብርቅ እስኪሆንብን ድረስ ከታሪካችን ተለያየን።
ካፍ እና የአፍሪካ ዋንጫ ሲነሳ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚታወስ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚዎቹ የሚለው ብኩርና ለኩራትና እንደ አፍሪካ ትልቅ ክብር የሚያሰጠን መሆኑ ባይካድም አሁን ላለንበት የኳስ ደረጃና የደጋፊ ስሜት ምላሽ መስጠት ግን አልቻለም። እንደ አጀማመራችንና አስተዋጽኦአችን ለምን በከፍታ እንዳልተጓዝን የተለያዩ ምክንያቶች ቢነሱም በሂደት እነዚህ ተቀርፈው ወደነበርንበት የከፍታ ማማ እንደምንመለስ ተስፋ እናደርጋለን።
ለዚህ ጽኑ ስሜታችን ተጠቃሽ በመሆን የሚነሳው ከአስር ዓመት በፊት ከሰላሳ አንድ ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችንን ተከትሎ የነበረው የሕዝብ ስሜት አይረሳም። ያ ጊዜ ሕዝባችን ለኳስ ያለው ፍቅር እስከየት እንደሆነ ያየንበት ከመሆኑም በላይ የሀገር ፍቅር ስሜት የተንጸባረቀበትም ነበር። ሁሉንም ትተን በዛ ስሜት ብቻ ለኳስ ያለንን ስሜት መመዘን እንችላለን። ከዛ ከዛ በኋላም ስምንት ዓመት ጠብቀን ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ በቅተናል። ከዚህ በኋላ ባሉት ጊዜያቶች ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ጉጉታችን ያልሰመረ ቢሆንም አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ ውስጥ እንገኛለን።
ይህን ተስፋ ከፍ የሚያደርግ ለተዳከመው እግር ኳሳችንም መነቃቃት የሚፈጥር አንድ ትልቅ ርምጃም በመንግስት በኩል ሰሞኑን ተወስዷል። ይህም በካፍ እና በፊፋ ፕሬዚዳንቶች ፊት በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተነሳው የአፍሪካ ዋንጫን የእናዘጋጅ ጥያቄ ነው።
46ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ)ና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቶቹ በጥቂት ቀናት ቆይታቸው ወቅት ስለኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ፍቅር ብዙ ተገንዝበው ተመልሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለልዑካኑ በታላቁ ቤተ-መንግስት የእራት ግብዣ ባደረጉበት ምሽትም ‹‹ኢትዮጵያ በ2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት አቅም አላት› ሲሉ የፊፋና የካፍ አመራሮች ፊት የኢትዮጵያውያንን ስሜትና ፍላጎት አንጸባርቀዋል።
ይሄን ጥያቄ ተከትሎም የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሙትሴፔ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልና መስተንግዶ ምስጋና በማቅረብ በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነትና የትስስር እሴት መደነቃቸውን ገልጸው፣ በዚህም ኢትዮጵያ ቤታችን እንደሆነች እንዲሰማን ሆነናል ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም የተነሳው የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት መሻት ካፍ ከኮሚቴው ጋር እንደሚወያይበት አሳውቀዋል።
ስለነበረው ኢትዮጵያዊ ድባብ ንግግር ያደረጉት የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ‹የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የኛም ሀገር ነች› ሲሉ ስሜታቸውን አጋርተዋል። በመርሀ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሁለቱ ፕሬዚዳንቶች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን መለያን በስጦታነት አበርክተዋል። በተመሳሳይ የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኔ ኢንፋንቲኖ 2029 የሚል ፊርማቸው ያረፈበትን ኳስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አበርክተዋል።
በመንግስት በኩል የተነሳው የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ጥያቄ ምክንያታዊ እንደነበር ብዙዎች ስሜታቸውን አንጸባርቀዋል። በተሰሩትና እየተሰሩ ባሉት ስታዲየሞችና መሰረተ ልማቶች የተደነቁት የካፍ ልዑካን ቡድኖች በእርግጥም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት አቅምና ሞራል እንዳላት ምስክርነታቸአውን ሰጥተዋል። ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላም መሰል አንቂና ሞራል ሰጪ ንግግሮች ከተሳታፊዎች ተደምጠዋል። የፊፋ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሲፔን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችም ጠቅላላ ጉባኤውን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ይሄንኑ መስክረዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ታሪካዊ ሚና እንዳላትና የካፍ መስራች አባል መሆኗን በተጨማሪም ለአፍሪካ ነጻነት ትልቅ ሚና የተጫወተች እንደሆነች ያነሱት የካፍ ፕሬዚዳንት፣ የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ ጥያቄዋም ወቅቱን የጠበቀና ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነ በመጠቆም በጎ ምላሽ እንደሚኖረው አመላክተዋል።
ሌሎች ተሳታፊ የቀድሞ ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቾችም ባዩት ነገር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካን ዋንጫ የማስተናገድ አቅም እንዳላት ተመልክቻለው›› ያለው የቀድሞ የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አልሀጂ ዲዩፍ በእግር ኳሱ ላይ እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ኢትዮጵያ ላነሳችው የአዘጋጅነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በቂ ነው የሚል ሀሳቡን አጋርቷል። በእግር ኳሱ ላይ የነበረንንና ያለንን ጉልህ ሚና በመጥቀስም ሕዝቡ ለእግር ካሷ ያለውን ጽኑ ስሜት አድንቋል።
በተመሳሳይ የቀድሞ የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ተወዳጁ ጄይጄይ ኦካቻ ‹ኢትዮጵያ የትልቅ ስፖርት ሀገር በመሆኗ አፍሪካን በትልቅ የመወከል አቅም አላት› ያለ ሲሆን በተደረገላቸው አቀባበልም መደሰቱን ገልጿል። የሀገራችን የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችም የዚህ ስሜት ተጋሪ በመሆን ሀሳባቸውን አካፍለዋል። ሳላሀዲን ሰይድ፣ ምን ያህል ተሾመና አዳነ ግርማ የካፍ መስራችነታችንን በማውሳት ለእግር ኳሱ እድገት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በማድነቅ ተስፋ ሰጪነታቸውንም አያይዘው ተናግረዋል።
እኚህ የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ጥያቄው ተገቢ እንደሆነ፣ እየተሰሩ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያዎችም ለዚህ ጉልበት እንደሚሆኑ በመግለጽ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንን ማዘጋጀታችን ደግሞ የበለጠ ዋጋ የሚያሰጠን ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ይሄን መሰሉን ሀሳብ ሌሎች አዲስ እና ነባር ተጫዋቾችም የሚጋሩት እንደሆነ መረዳት ቀላል ነው።
በነበረን ቁጭትና ለእግር ኳስ በከፈልነው ዋጋና ባለን ብርቱ ስሜት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሀገር በስፖርቱ ዘርፍ የተሻሉ ነገሮችን በመስራት ላይ እንገኛለን። በካፍ ስታንዳርድ መሰረት ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞችን መገንባት፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ማስፋፋት፣ የታዳጊ የስፖርት አካዳሚዎችንና ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት ነገን ዛሬ ላይ እያለምን እንገኛለን።
ዝግጅታችንን ጨምሮ ያለው ነባራዊ ሁኔታና የአፍሪካ የኳስ ታሪካችን የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት እንደምንችልና ከዚህም ላቅ ላለ ኃላፊነት መብቃት እንደምንችል ዋስትና መሆኑ በብዙዎች ዘንድ አመኔታን መፍጠሩ አጠራጣሪ አይሆንም። ለአፍሪካ የኳስ ትንሳኤ አድባር መሆናችን፣ የደጋፊዎቻችን የኳስ ፍቅር፣ በካፍ ላይ የነበረን አስተዋጽኦ ተደማምረው ጥያቄዎቻችን በጎ መልስ እንደሚያመጡ ይታመናል። ራስን እንዲህ ባለው የካፍና የፊፋ አመራር ልዑክ ማስተዋወቅ ዋጋው ትልቅ ነው። ታዋቂ ሰዎችን ጋብዞ ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ እንዲረዱ ማድረግ፣ በፊፋና በካፍ አመራሮች ዘንድ ማንነትን ማሳየት ትልቅ ተነሳሽነት እንደሆነ መረዳት ተገቢ ነው።
በዚህ ልክ ሌሎች እንዲረዱን መሆኑ ከኳስ ባሻገር እንደሀገር በርካታ ጥቅሞችን ይዞ የሚመጣ ነው። በእግር ኳሱ ረገድ ይዞት የሚመጣው መነቃቃት ዋነኛው ሲሆን ከዚህ ጋር አብረው የሚመጡ በርካታ በረከቶችም አሉ። ሌላ ሌላውን ትተን እንኳን በነበረው የብሔራዊ ስቴድየም ግንባታ የመስክ ጉብኝትና በልዑካን ቡድኑ የተሰጠን ገንቢ አስተያየት ቀላል አይደለም። በእግር ኳሱ መሰረተ ልማት ተስፋ ሰጪ ነገሮች እንዳሉ ከማሳየት ባለፈ ወደቀደመ ክብራችን ለመመለስ እያደረግነው ያለውን ተጋድሎ የሚያሳይም ነው። በእግር ኳሳችን ላይ በተለይም ደረጃውን የጠበቀ ስቴድየም ባለመኖሩ ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ። እኚህ ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል በቅርብ ጊዜ እልባት እንደሚያገኙ የማይካድ ቢሆንም ወደፊት ከዚህ የተሻለ ሰርተን ከአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት ወደሌሎችም ታላላቅ መድረኮች አዘጋጅነት መሸጋገር እንችላለን።
ብሔራዊ ቡድናችን በባዕድ ሀገርና ሜዳ ያለደጋፊ ሄዶ እንዲጫወት የሚገደድበት ደረጃውን የጠበቀ ስቴድየም ችግር አሁንም እንዳልተቀረፈ መሸሸግ አይቻልም። ዛሬ ላይ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ጥያቄ ሲነሳም በበርካቶች ዘንድ እንደሚሳካ ስጋት አለ። የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት መነሳታችን ግን ባይሳካ እንኳን ይህን ጥያቄ በዘላቂነት ለመመለስ ይዞት የሚመጣው መልካም አጋጣሚ እንደሚኖር አርቆ ማሰብ ተገቢ ነው።
በታዋቂና በስመ ጥር ግለሰቦች የሀገርን ገጽታ ለሌላው ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሉት አይነት ትርጉም ያለው ነው። የመጀመሪያው የልምድ ልውውጥ ነው። ቀጥሎ የሚመጣው የእግር ኳስ ደረጃችንን ማሳየትና በቀጣይ ለምናደርጋቸው ነገሮች በተጨባጭ ማሳየት ነው። ካፍ በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታም ሁለቱም ግባቸውን መተዋል። አፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ ብርቅ የሆነበት ትውልድ አፍሪካ ዋንጫን ሊያዘጋጅ ጥያቄ አቅርቦ መልስ በመጠባበቅ ላይ መገኘቱ በራሱ ትልቅ ትርጉም አለው።
እንዲህ አይነቱ ሁኔታ የነበሩንን በማስታወስ ቀጣይ ሂደታችንንም የሚያቀላጥፉልን ናቸው። ከዚህ ባለፈ አብሮ የሚነሳው ነገር ገጽታ ግንባታ ነው። አንድ ታዋቂ ሰው ከሀገራችን ወደሀገሩ ሲመለስ ብዙ ነገራችንን ለሌሎች በማጋራትና ዳግመኛ መመለስን በማሰብ ነው። ይሄ መሆኑ ከእግር ኳስ የእርስ በርስ ትስስር ጎን ለጎን እስከ ገጽታ ግንባታና የቱሪዝም ፍሰት ድረስ ባለው ደረጃ ተጠቃሚነታችንን የሚያረጋግጥ ነው። ሀገራች ኢትዮጵያ ያልተሰራባቸው ቢሰራባቸውም ተገቢውን ጥቅም ካላስገኙ ዘርፎች የቱሪስት መስህብ ተጠቃሽ ነው። እንዲህ አይነቱን አካሄድ ከማስተካከልና ትርፍ ከማምጣት አኳያ ሚናቸውም አብሮ የሚነሳ ነው።
የሀገራት የገቢ ምንጭ ኤክስፖርትን ከመሳሰሉ የኢኮኖሚ ዋልታ እኩል በገጽታ ግንባታ ጀምሮ በቱሪዝ ፍሰት የቀጠለ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ እውነታ ነው። ለኳሱ እድል መስጠት ማለት ለብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን መልስ መስጠት ሆኖ ሊታይ የሚገባው ነው። እንደእግር ኳስና አትሌቲክስ ያሉ ብዙሀኑ የሚታደምባቸውና የሚመለከታቸው ጨዋታዎች ብዙ ትርፎች የሚገኙባቸው ላቅ ሲልም ለተሻለ ሀገረ ግንባታ መሰረት የሚጣልባቸውም ናቸው። ስለሆነም ወደኳሱ ማየት፣ ለእግር ኳሳችን ዋጋ መስጠት በዚህ ልክ ሊታይ የሚችል ይመስለኛል።
ከግብጽና ከሱዳን ጋር በመሆን ኳስን ለአፍሪካውያን ያስተዋወቀች፣ ካፍን የመሰረተች፣ የመራች፣ አፍሪካ ነጻነት ተምሳሌት የሆነች፣ የስልጣኔና የብኩርና ምድር ከተሳትፎ ልቃ የአፍሪካ ዋንጫን የምታዘጋጅበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ወደቀደመ የከፍታ ምኩራቧ አዘንብላ የጸሀይ መውጫ ምስራቅነቷ ይቀጥላል። ሰላም መጥቶ፣ ፍቅር በዝቶ፣ እርቅ ወርዶ፣ አብሮነት ጎምርቶ፣ ኢትዮጵያዊነት ለምልሞ፣ ወንድማማችነት አብቦ፣ ሳቅ እና ትቅቅፍ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ፈንጭተው ሁሉም ነገር መልካም የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም