ልጅ ጠላፊው

ቴዎድሮስ አፈወርቅ ይባላል:: አቶ አፈወርቅ ቸኮል እና ወይዘሮ በለጡ ግርማ በ1978 ዓ.ም ቴዎድሮስን ሲወልዱ፤ በቤታቸው የተፈጠረው ደስታ ልዩ ነበር:: እያደገ ድክ ድክ እያለ ሲሔድ፤ እደግ ብሎ የማይመርቀው፤ አቅፎ የማይስመው አልነበረም:: እንደ ማንኛውም ከእርሱ ጋር በተመሳሳይ ዘመን የተወለደ የአዲስ አበባ ሕጻን፤ ስድስት ዓመት ሲሞላው ቄስ ትምህርት ቤት ገባ:: ፊደል ቆጥሮ ሲጨርስ መድኃኒዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን መከታተሉን ቀጠለ::

ንቁ እና ቀልጣፋ መልከ መልካም የሆነው ቴዎድሮስ የእናት እና የአባት ክትትል ታክሎበት፤ ትምህርቱን በትጋት መገብየት ቻለ:: የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናንም በጥሩ ውጤት አለፈ:: ወደ ግንቦት 20 የሁለተኛ እና ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት እስከ 12ኛ ክፍል ተማረ:: መምህራንም ሆኑ ተማሪዎች የሚወዱት ጨዋው ልጅ ቴዎድሮስ፤ በ1994 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተናን በመውሰድ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባውን ውጤት አገኘ::

በ1995 ዓ.ም ቴዎድሮስ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ሲገባ፤ እናቱ ወይዘሮ በለጡ በሶ አስፈጭታ በእጁ ገንዘብ አስይዛ ላከችው:: አቶ አፈወርቅ ግን አባት ናቸውና፤ ከመላክ ይልቅ ብቻውን አልተወውም ብለው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ድረስ አብረው ሔደው አስገብተውት ወደ ቤታቸው ተመለሱ:: ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ ቴዎድሮስ ተቀየረ:: በትምህርቱ መድከም ጀመረ:: ከተለያዩ ተማሪዎች ጋር በመግጠም ወጣ ገባ ማለት አበዛ:: የሚላክለትን ብርም ለሌላ ዓላማ መጠቀም ጀመረ:: አንዳንዴ መለስተኛ ነጥብ አልፎ አልፎ ደግሞ ዝቅተኛ ነጥብ እያስመዘገበ በአምስት ዓመቱ 2001 ዓ.ም በአካውንቲንግ ዲግሪ ለመያዝ በቃ::

የቴዎድሮስ እናት እና አባት በደስታ ለልጃቸው ምርቃት ደግሰው የአካባቢያቸውን ሰው እና ዘመድ አዝማድ ጠርተው አበሉ:: ውሎ ሲያድር ግን ቴዎድሮስ በዲግሪ ቢመረቅም በቀላሉ ሥራ ማግኘት አልቻለም:: ለሁለት ዓመታት እቤት ተቀመጠ:: ቤት ውስጥ ሲቀመጥ ፀባዩ አስቸጋሪ ሆነ፤ ጭራሽ ድብርት ውስጥ ገብቶ ነበር:: በ2003 ዓ.ም ግን አምባሳደር አካባቢ ሐራምቤ ሆቴል አቅራቢያ ቤንጁር ትሬዲንግ ውስጥ በሂሳብ ሠራተኝነት ተቀጠረ:: የሥራ በሩ ተከፈተለት::

የሂሳብ ሥራውን አጠናክሮ ይሠራ የነበረው ቴዎድሮስ፤ ለሶስት ዓመታት ሲሰራ ከቆየ በኋላ አንድ ሃሳብ መጣለት:: ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ በራሱ ለመንቀሳቀስ አሰበ:: ምን ቢነግድ ቶሎ ማትረፍ እንደሚችል ሲያወጣ እና ሲያወርድ፤ ከጅማ ወደ አዲስ አበባ ቡና እያመጣ ቢነግድ እንደሚያዋጣው አሰበ:: ለቤተሰቦቹ ሃሳቡን ሲያቀርብላቸው፤ አልተቃወሙትም እንደውም አበረታቱት:: ቴዎድሮስ ንግዱን አጠናክሮ አንሠራራ:: ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ሌላ ነገር ተፈጠረ፤ ተቀጥሮ የነበረበት ቤንጁር ትሬዲንግ ሂሳቡ ኦዲት ሲያስደርግ፤ ክፍተት አገኘ:: ክፍተቱን የፈጠረው ለሶስት ዓመታት ሂሳብ ሲሰራ የቆየው ቴዎድሮስ ነው ሲል ቴዎድሮስን ማፈላለግ ጀመረ:: አድራሻውን ሲያገኙ ያጠፋው ገንዘብ አለ በሚል ቴዎድሮስን እምነት በማጉደል ወንጀል ከሰሱት::

ቴዎድሮስ ተምሮ ዲግሪ ቢጭንም፤ መማር ብቻውን ሙሉ አያደርግምና ጎዶሎ ጎኑ ገኖ ታየ:: ፍርድ ቤት ቀርቦ ክርክር ተካሔደ:: ነገር ግን በምስክር ብቻ ሳይሆን በማስረጃም ጥፋተኛ መሆኑ ተረጋገጠ:: እምነት በማጉደል ተጠያቂ ነህ ተብሎ ብይን ተሰጠ:: በመጨረሻም ሰባት ዓመት ተፈረደበት:: ቴዎድሮስ በዝዋይ ማረሚያ ቤት የፍርድ ጊዜውን አጠናቅቆ፤ ከቤተሰቦቹ ጋር ተቀላቀለ::

እንደለመደው ከእስር ቤት ወጥቶ በቀላሉ ሥራ ማግኘት አልቻለም:: እንደልጅነቱ ቤተሰቦቹ ቤት መኖሩን ቀጥለ:: እንዲሁ መኖር ሰለቸው:: ስለዚህ ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለበት ማሰላሰል ጀመረ:: ቴዎድሮስ ምንም እንኳ የእስር ጊዜውን ቢያጠናቅቅም፤ ወንጀል ከመሥራት ወደኋላ አላለም:: በመጀመሪያው ቅጣት የተማረ አይመስልም:: እንደገና ለእስር ሊዳርገው የሚችል ትልቅ ስህተት ፈፀመ::

እገታው

ቴዎድሮስ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ ሕይወት ቀላል አልሆነችለትም:: 37 ዓመት ቢሞላውም እንደ እኩዮቹ ትዳር መስርቶ ልጆች ወልዶ የቤተሰብ ኃላፊ መሆን አልቻለም:: እንደውም የቤተሰቡ ጥገኛ ሆኖ እነሱ እየሰሩ ሲያበሉት ከፋው:: በድጋሚ ወደ ሥራ ለመግባት አሰበ:: ሥራ ለመሥራት መነሻ ብር ፈልጓል:: ነገር ግን ብሩን ማግኘት የሚችልበት አጋጣሚ አጣ:: ምርጥ ብሎ ያሰበውን ዕቅድ ነደፈ:: በአቅራቢያው የሚያቃቸው ሰዎች ገንዘብ እንዲያበድሩት ጠየቀ፤ የሰጠው ሰው ግን አልነበረም:: ግራ ሲገባው ገንዘብ ካላቸው ሰዎች በምን ዓይነት መንገድ ገንዘብ ማግኘት እንደሚችል ሲያወጥነጥን ቆየ፤ በመጨረሻም የአቶ አዲሱ አድማሱን ልጅ ቢያግት ገንዘብ ማግኘት እንደሚችል ገመተ::

ከማንም ጋር ሳይመክር እና ተባባሪ ሳይፈልግ በቀላሉ ልጃቸውን የሚያግትበትን ሁኔታ አውጠነጠነ:: ወትሮም ከቤተሰቡ ጋር አጥብቆ የሚገናኘው ቴዎድሮስ፤ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም በአቶ አዲሱ አድማሴ ቤት ተገኘ:: ለጥቂት ደቂቃዎች ከቆየ በኋላ፤ ሕፃን ህልውና አዲስን ኬክ ልግዛላት ብሎ ከእናቷ ላይ ተቀብሎ ሄደ:: እናት የልጇን መምጣት ብትጠባበቅም ልጇና ቴዎድሮስ ኬክ ቤት ደርሰው ቶሎ አልመጡም:: ጭራሽ ዘገዩ፤ ደቂቃዎች አልፈው ሰዓታት መቆጠር ጀመሩ:: እናት በጣም ተጨነቀች::

ቴዎድሮስ ቀድሞም አስቦበት ስለነበር ህልውናን ይዟት ተሰወረ:: ቴዎድሮስ ከሰዓታት በኋላ ለህልውና እናት በመደወል በሂሳብ ቁጥሩ ውስጥ 15 ሺህ ብር ካላስገቡለት ልጅቷን እንደማይለቅ ገለጸ:: ልጃቸው የታገተችባቸው እናት እና አባት ተጨነቁ:: ብሩን ለመስጠት አላመነቱም:: ከአባትየው የሂሳብ ቁጥር በፍጥነት ወደ ቴዎድሮስ የሂሳብ ቁጥር ገንዘብ አዘዋወሩ:: ቴዎድሮስ በበኩሉ ገንዘቡ እንደገባለት ሲያረጋግጥ ቀድሞ ገንዘቡን ከባንክ አወጣ:: ብሩን ከያዘ በኋላ ልጅቷን ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቤተል ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ልብስ የሚሰፋ ሰው ሱቅ ጋር ጥሏት ሔደ::

የህልውና እናት እና አባት ልጃቸው ምንም ሳትሆን መገኘቷን ማመን አልቻሉም:: ምንም ሳትሆን ማግኘታቸው እጅግ ቢያስደስታቸውም፤ የቴዎድሮስ ድርጊት ስላበሳጨቸው ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ክስ መሰረቱ:: ልጃችንን አግቶ ገንዘብ ጠይቆናል በማለት አመለከቱ::

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ ባካሔደው ምርመራ፤ ተጠርጣሪ ቴዎድሮስ ታረቀኝ ለአካለ መጠን ያልደረሰች ልጅን በመጥለፍ እና ገንዘብ ለመቀበል በማሰብ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ በግምት ስድስት ሰዓት አካባቢ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ዘነበወርቅ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ስድስት ዓመት ዕድሜ ያላትን ሕፃን ህልውና አዲስን ኬክ ልግዛላት ብሎ እናቷን እና ሕፃኗን በማታለል፤ ይዟት ከመኖሪያ ቤቷ ወጥቷል::

ህልውናን ከወሰዳት በኋላ ወደ ሕፃኗ ወላጆች በመደወል ሕፃኗ እንድትመለስ የራሱን የሂሳብ ቁጥር በመንገር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቁጥር በመግለፅ 15ሺህ ብር እንዲያስገቡ ጠይቋል:: አባትም በዕለቱ የተጠየቀውን ገንዘብ በፍጥነት ካስገባ በኋላ፤ ቴዎድሮስ መንገድ ዳር ልጅቷን ትቶ በመሔዱ አባት አቶ አዲስ ልጁን ምንም ሳትሆን አግኝቷታል:: በዚህ ምክንያት ተጠርጣሪ ቴዎድሮስ አፈወርቅ በፈፀመው ከባድ ለአካለ መጠን ያልደረሰች ልጅን የመጥለፍ ወንጀል ሊከሰስ ይገባል ሲል ለአቃቤ ሕግ መረጃውን እና ማስረጃውን አቅርቧል::

የዓቃቤ ሕግ ክስ

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ፤ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ነዋሪ የሆነችው ሕፃን ህልውና አዲስ መታገቷን አረጋግጦ ለፍርድ ቤቱ አምስት ምስክሮችን እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ1850/22 በመጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም የተጻፈ ደብዳቤ ገንዘቡ ገቢ የተደረገበት ሂሳብ የራሱ መሆኑን አረጋግጧል በሚል አሳይቷል:: በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አየር ጤና ቅርንጫፍ በቁጥር 00152/23 በጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በተሰጠ ደብዳቤ ተበዳይ አባት ለተከሳሽ ገንዘብ ማስገባቱን የሚያሳይ ሰነድ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል::

በሌላ በኩል ተከሳሹ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ላይ በግልፅ እንደሰፈረው ቴዎድሮስ ምንም እንኳ ፖሊስ ምርመራውን አካሂዶ፤ ማስረጃ ማግኘት ቢችልም እርሱ ግን ድርጊቱን አልፈፀምኩም ሲል ተከራክሯል:: ቴዎድሮስ ምንም እንኳ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ብሎ ቢክድም ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ነህ ሲል ብይን ሰጥቷል::

                                                                                                                 ውሳኔ

ተከሳሽ ቴዎድሮስ አፈወርቅ በተከሰሰበት የሕፃን መጥለፍ ክስ የልደታ አንደኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ሲታይ ቆይቶ በሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ክስ እና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሹን ያርማል፤ ሌሎችንም ያስተምራል ብሎ ባመነበት በስድስት ዓመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You