ዋልያዎቹ በአዲስ አሰልጣኝ የቻን ማጣሪያን ይጀምራሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ከሳምንት በፊት በ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ጋር ያደረጉትን ሁለት ጨዋታ በሽንፈት ከደመደሙ በኋላ ፊታቸውን ወደ ሌላ አህጉራዊ ተሳትፎ መልሰዋል። በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ (ቻን) የማጣሪያ ውድድሮች በቅርቡ ሲከናወኑ ዋልያዎቹ በአዲስ አሰልጣኝ እንደሚመሩ የኢትዮጵያ እግር ካስ ፌዴሬሽን አሳውቋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ገደማ ዋልያዎቹን ሲመሩ የቆዩት አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ተሰናብተው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ብሔራዊ ቡድኑን በጊዜያዊነት እንዲመሩ መወሰኑን ፌዴሬሽኑ ከትናንት በስቲያ አረጋግጧል።

ፌዴሬሽኑና አሠልጣኝ ገብረመድህን ያላቸው የአንድ ዓመት የኮንትራት ስምምነት የሚጠናቀቀው ከቀናት በኋላ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ቢሆንም የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሠባ ላይ ከአሠልጣኙ ጋር መለያየቱ ታውቋል። በዚህም በምክትል አሠልጣኝነት ሲያገለግል የነበረውን አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ በዋና አሠልጣኝነት ጊዜያዊ ሆኖ ዋልያዎቹን እንዲመራ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።

ፌዴሬሽኑ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የቻን የማጣሪያ ውድድር ላይ በዋናው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ከነበሩት ከሱራፌል ዳኛቸውና ከአቤል ማሞ በስተቀር ሁሉም ተጫዋቾች በቻን ውድድር ላይ የሚሳተፉ በመሆኑ ብሔራዊ ቡድኑ በምክትል አሠልጣኙ መመራት ይችላል በማለት ነው። ይህም የፌዴሬሽኑ ውሳኔ በቀጣይ ሌሎች አሠልጣኞችን ተረጋግቶ ለማየት ዕድል ይሰጣል ተብሎ ታምኖበታል።

በፌዴሬሽኑ አዲስ ኃላፊነት የተሠጠው አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ የአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ረዳት በመሆን ላለፉት 12 ወራት ያገለገለ ሲሆን በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኤርትራ ጋር የሚደረገውን ጨዋታ ጨምሮ በሌሎች ማጣሪያዎችም ዋልያዎቹን ይመራል። ይህንንም ተከትሎ ለቻን ማጣሪያ ዝግጅት ከትናንት ጀምሮ እንዲሰባሰቡ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርቧል። የተጫዋቾቹ ጥሪ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን ባማከለ መልኩ የተከናወነ በመሆኑም ሊጉ የማይቋረጥ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን የመጀመሪያ ዙር የደርሶ መልስ ቅድመ ማጣሪያ ከኤርትራ ጋር መደልደሉ የሚታወስ ሲሆን ጨዋታው ጥቅምት 21 እና 24 በደቡብ ሱዳን ጁባ ብሔራዊ ስቴዲየም ይካሄዳል።

በዚህ የማጣሪያ ውድድር በመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ (ሴካፋ) ዞን አስራ አንድ ሀገራት በቻን ተሳታፊ ለመሆን ይፋለማሉ። የኢትዮጵያና የኤርትራ የደርሶ መልስ ጨዋታ ድምር ውጤት አሸናፊም ከሱዳንና ታንዛኒያ አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል። በሌላኛው ምድብ ቡሩንዲና ሶማሊያ የተደለደሉ ሲሆን ሁለቱን የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሀገር የተሻለ የእግር ካስ ደረጃ በመያዝ በቀጥታ በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ የምትሳተፈው ዩጋንዳን ይገጥማል። ደቡብ ሱዳንና ኬንያ በሚገኙበት ምድብ አሸናፊ የሆነው ሀገር ደግሞ የጅቡቲና ርዋንዳ አሸናፊን ይገጥማል።

የ2027 የአፍሪካ ዋንጫን በጣምራ የሚያዘጋጁት ኬንያ፣ ዩጋንዳና ታንዛኒያ የ2025 የቻን ዋንጫን በተመሳሳይ በጣምራ ያስተናግዳሉ። በዋናው የአፍሪካ ዋንጫ በሌሎች ዓለማት ታላላቅ ሊጎች በሚጫወቱ ኮከቦች የተሸፈኑና በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን እድል ለመስጠት እኤአ ከ2009 ጀምሮ እየተካሄደ በሚካሄደው የቻን ዋንጫ ከሴካፋ ዞን አራት ሀገራት ተሳታፊ ይሆናሉ። በሌሎች ዞኖች የሚገኙት ግን ሦስት ሦስት ሀገራትን ብቻ የሚያሳትፉ ይሆናል። ይህም ካፍ ዝቅተኛ የእግር ኳስ ደረጃ ያለውን የሴካፋ ዞን ለማበረታታት የሚያደርገው ነው።

በሴካፋ ዞን ከሚገኙ ሀገራት ዩጋንዳ ከሰባት የቻን ውድድሮች በስድስቱ በመሳተፍ ቀዳሚ ስትሆን ርዋንዳ አራት ጊዜ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ደግሞ ሦስት ጊዜ የመሳተፍ ታሪክ አላቸው።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም

Recommended For You