ምዕራባውያን በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ሩሲያ ከዓለም የኢኮኖሚ ሰንሰለት እንድትነጠል ለማድረግ ሌት ተቀን እየሠሩ ይገኛል። ማዕቀቦችን በመጣል የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብትን ከዓለም አቀፉ ገበያ ጋር ያለውን ትስስር እንዲቋረጥ ለማድረግ ሞክረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በጦር ወንጀል ክሶች የእስር ማዘዣ በሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ አውጥቶባቸዋል። የምዕራቡ ዓለም ጫና እና ግፊት እየሠራ ይሆን? ጊዜ የሚፈታው ይሆናል። ጫናውን መቋቋም እንደሚችሉ የሚናገሩት ፑቲን ከሰሞኑ የብሪክስ ጉባኤን በሀገራቸው አስተናግደዋል። ከጥቅምት 12 -14 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ አባል ሀገራቱ በሩሲያዋ ካዛን ከተማ ተሰብስበዋል።
የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ፣ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና የኢራን ፕሬዚዳንት ማስዑድ ፔዜሽኪያን እና በፈጣን ዕድገት የሚገኙ ከ20 በላይ ሀገራት መሪዎች በዚህ ጉባኤ ላይ ይታደማሉ። ክሬምሊን በሩሲያ ከተደረጉ “ታላላቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ክስተቶች አንዱ” ሲል ነው ጉባኤውን የጠራው። በዚህ ጉባኤ “ማስተላለፍ የተፈለገው ግልጹ መልዕክት ሩሲያን ለማግለል የተደረገው ሙከራ አልተሳካም የሚል ነው” ይላሉ በጂኦ ፖለቲካ እና ፖሊሲ ላይ የሚያተኩረው ማክሮ አድቫይዘሪ የተሰኘው ድርጅት መሥራች ክሪስ ዌፈር።
“ሩሲያ ማዕቀቦችን ተቋቁማ አይበገሬነትዋን እያሳየች እንደሆነ ከክሬምሊን የተላከ ትልቅ መልዕክት ነው። ከውጭ እንደሚታየው ሳይሆን በሀገሪቷ ውስጥ ከባድ ስንጥቆች እንዳሉ እናውቃለን። ነገር ግን በጂኦፖለቲካዊ ዕይታ ሩሲያ ወዳጆች እንዳሏት ማሳያ ነው። እነዚህም የሩሲያ አጋሮች ይሆናሉ” ይላሉ።
ብሪክስ የሚለው የእንግሊዝኛ ምኅጻረ ቃል አባል ሀገራቱን ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ደቡብ አፍሪካን የሚያመለክት ነው። የምዕራቡን ዓለም መሪነትን በመጻረር እንዲሁም ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ እንዲኖር በማለት የተመሠረተ እንደሆነ የሚነገርለት ብሪክስ፤ አድማሱን በማስፋት ግብፅን፣ ኢትዮጵያን፣ ኢራንን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን በአዳዲስ አባልነት ተቀብሏል። ሳዑዲ አረቢያም የሀገራቱን ጥምረት እንድትቀላቀል ተጋብዛለች።
የብሪክስ አባል ሀገራት የዓለማችን 45 በመቶ ሕዝብ ይኖርባቸዋል። የሀገራቱ ምጣኔ ሀብት ሲደመርም ከ28.5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን፣ ይህም የዓለማችንን 28 በመቶ ምጣኔ ሀብት አካባቢ ነው። የሩሲያ ባለሥልጣናት ሌሎች ተጨማሪ 30 ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ወይም ከድርጅቱ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መመሥረት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። አንዳንዶቹም እነዚህ ሀገራት በጉባዔው ላይ ተሳታፊ ናቸው።
በሩሲያ ካዛን በተካሄደው ጉባኤ ከተንጸባረቁ ጉዳዮች አንዱ ብሪክስ ምን ያህል “አብዛኛውን የዓለም ሕዝብ” እንደሚያቅፍ ይጠቀሳል። ጉባኤው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጂኦ ፖለቲካዊ መድረክ ያላቸውን ስፍራ ከማሳየት ውጪ ምን ፋይዳ ሊኖረው ይችላል? የምዕራባውያንን ጫና ለመቀልበስ የሚፈልጉት ፑቲን ለዓለም አቀፍ መገበያያዎች ከዶላር ሌላ አማራጭ ገንዘብ እንዲኖር የብሪክስ አባል ሀገራትን ለማሳመን ተስፋ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ሆኖም ተቺዎች በብሪክስ አባል ሀገራት ውስጥ ያለውን ልዩነት በመንቀስ “ፍጹም ተመሳሳይ አቋም” የያዙ አይደሉም ይላሉ።“በአንዳንድ መንገዶች ቻይና እና ሕንድ በማንኛውም ነገር መስማማት አለመቻላቸው ለምዕራቡ ዓለም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ሁለቱ ሀገራት ቢስማሙ ብሪክስ በዓለማችን ላይ ታላቅ ተጽእኖ ማሳደር ይችል ነበር” ሲሉ የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ባንክ እና የፋይናንስ አገልግሎት የሆነው ጎልድማን ሳክስ የቀድሞ ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጂም ኦኔል ይገልጻሉ።
“ቻይና እና ሕንድ አብዛኛውን ጊዜ እርስ በርስ ለመጠላለፍ የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀነስ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። እነዚህን ሀገራት በምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ ትብብር እንዲፈጥሩ ማድረግ የከበደ ፈተና ነው” ሲሉ ጂም ኦኔል ያስረዳሉ። ጂም ኦኔል ብሪክ የሚለውን ምኅጻረ ቃለ ለአራት በፈጣን ዕድገት ላይ ላሉ ሀገራት ሲያልሙት የነበሩ ሲሆን፣ ሀገራቱ ወደ ዓለም አቀፉ የፖሊሲ ውሳኔ እንደሚመጡም ያምኑ ነበር።
“የሩሲያ የምጣኔ ሀብት እያጋጠመው ያሉ ችግሮች የወጭ ንግድ እና ክፍያ ጋር የተገናኙ ናቸው። አብዛኛው ደግሞ ከአሜሪካ ዶላር ጋር ቁርኝት አለው” ይላሉ ዌፈር። “የአሜሪካው ግምጃ ቤት በዓለም ንግድ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አለው፤ ምክንያቱም ዋነኛ መገበያያ ገንዘቡ የአሜሪካ ዶላር ስለሆነ ነው። የሩሲያ ዋነኛ ፍላጎት የአሜሪካን የዶላር የበላይነት መስበር ነው።
“ለዚህም የብሪክስ ሀገራት አማራጭ የንግድ ዘዴ እንዲዘረጉ እና ዶላር፣ ዩሮን ወይም የትኛውንም የቡድን 7 ሀገራት ገንዘቦችን ያላከተተ የወጭ ንግድ እና የመገበያያ ሥርዓት እንዲኖር ትፈልጋለች። በዚያውም ማዕቀቡንም ጥርስ አልባ ማድረግ ነው” ሲሉ ማስረዳታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም