ድህነትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለተንሰራፉባቸው ማኅበረሰቦች፣ የበጎ አድራጎት ተግባራት የማኅበራዊ ፈውስ ሁነኛ መገለጫዎችና መሳሪያዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡ የበጎ አድራጎት ተግባራት ገንዘብን፣ ፍቅርን፣ ጊዜንና ሌሎች ሀብቶችን ከራስ ቀንሶ ለሌሎች በማካፈል የሌሎችን ችግር ለማቃለል፤ ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን ለማጠንከር እንዲሁም መተሳሰብና መከባበር የሰፈነበትን ማኅበረሰብ ለመፍጠር የማይተካ አወንታዊ ሚና አላቸው፡፡
መረዳዳት የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነና የእርስ በእርስ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን አጠንክሮ የኖረ ተግባር ነው፡፡ መረዳዳት ባይኖር ኖሮ አሁናዊ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አሁን ከሚታየው የተለየ ይሆን ነበር፡፡ ይህ መረዳዳትና መተጋገዝ በብዙ መንገዶች ይከወናል፡፡ በተናጠልና በጥቂት ግለሰቦች ስብስብ ከሚከናወኑ የመረዳዳት ተግባራት በተጨማሪ፣ መደበኛና ሕጋዊ አሰራሮችን ተከትሎ የበጎ አድራጎት ተቋማትን የማቋቋምና የመስራት ተግባርም በስፋት የሚታወቅ አሰራር ነው፡፡
ችግሮችን ተቋቁሞ ለማለፍ ብርታት የሚያጥራቸው ሕፃናትና አረጋውያን፣ ለብዙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው፡፡ አካላቸውና አዕምሯቸው ያልጠናው ለጋ ሕፃናት እና ብዙ ደክመው በማምሻ እድሜያቸው ላይ አቅም የከዳቸው አረጋውያን፣ የቤተሰብና የዘመድ እንክብካቤ በሚፈልጉበት የእድሜያቸው ምዕራፍ ላይ ለችግር ተጋላጭ ሲሆኑ ችግሮችን የሚቋቋሙበት ብርታት አያገኙም፡፡ የበጎ አድራጎት ተግባራት እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለማቃለል በዋጋ የማይተመን ሚና አላቸው፡፡ ‹‹ድንበር የለሽ የበጎ አድራጎት ማኅበር›› የተሰኘው ምግባረ ሰናይ ድርጅት የተመሰረተው የሀገር ተረካቢና የሀገር ባለውለታ የሆኑትን እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘላቂነት ለማገዝ ነው፡፡
የማኅበሩ የቁጥጥር ኦዲተር አቶ ምህረት ታከለ ‹‹ድንበር የለሽ›› የበጎ አድራጎት ማኅበር በዋናነት አረጋውያንን፣ ወጣቶችንና ሕፃናትን በመርዳት ተግባር ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ ይገልፃሉ፡፡ ድርጅቱ የተመሰረተው ‹‹በጎ እናስብ/Think Positive›› በሚል መሪ ቃል በ15 በጎ ፈቃደኛ አባላት፣ በኅዳር 2006 ዓ.ም ነው፡፡
የማኅበሩ ዓላማዎች በጎ ፈቃደኝነትን ማስፋፋት፣ ሱሰኝነትን መከላከል፣ ንቁ ዜጎችን ማፍራት፣ ባህልና ወግን ማስጠበቅ፣ ጾታዊ ጥቃትን መከላከል፣ መተሳሰብ፣ መከባበርና መረዳዳትን ማጎልበት እንዲሁም ሰላም ወዳድ ማህበረሰብን ማፍራት ናቸው፡፡ የማኅበሩ ዋና ቢሮ ባህር ዳር ከተማ የሚገኝ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በ10 ከተሞች ቅርንጫፎችን ከፍቶ ዘርፈ ብዙ የበጎ አድራጎት ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከአምስት ሺ በላይ አባላትም (የማህበሩ መታወቂያ ያላቸው) አሉት፡ ፡
‹‹ሁሉም ሰው በጎ ፈቃደኛ እንዲሆን እናስተምራለን፡፡ ኪነጥበብን በመጠቀም ሰዎች ከሱሰኝነት የሚላቀቁበትን መፍትሄ ለማበጀትም እንሰራለን፡፡ ወጣቶች ሳምንቱን ሙሉ መጻሕፍትን እየተዋሱ እንዲያነቡ በማድረግ የአስተሳሰብ አድማሳቸው እንዲሰፋ ለማደረግ እንጥራለን›› ሲሉ ምኅረት ይናገራሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ማኅበሩ ፍላጎት ኖሯቸው ገንዘብ ከፍለው መሰልጠን ለማይችሉ ወጣቶችና ታዳጊዎች ኢትዮጵያዊ ግብረ ገብነትና የትወና ስልጠናዎችን ለ12 ዙሮች በነፃ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ታዳጊዎችና ወጣቶች አለባበሳቸው ጭምር ምክንያታዊና ባህልና ወግን የጠበቀ እንዲሆን ያስተምራል፡፡
ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ በመሆኑ ስለሰላም አስፈላጊነት ይሰብካል፡፡ የበጎ ስራ ተግባራት ከዕለታዊ ድጋፍ ተሻግረው በግለሰቦች ሕይወትና በማኅበረሰብ ኑሮ ላይ ዘላቂ ለውጥ እንዲያስገኙ ኅብረተሰቡ፣ የበጎ አድራት ተቋማት፣ ድጋፍ ፈላጊዎችና መንግሥት የየራሳቸው ኃላፊነቶች እንዳሉባቸው ያስገነዝባል፡፡
ማኅበሩ በዋናነት ትኩረት የሚያደርግባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ህፃናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ምኅረት፣ 100 አረጋውያንን ያለማቋረጥ እየደገፈ እንደሆነና 104 ተማሪዎች በየቤታቸው ሆነው ትምህርት እንዲማሩ እያደረገ እንደሚገኝ ይገልፃሉ፡፡ ወጣቶች ከሱስ ተላቅቀው የልብስ ስፌት፣ የውበት እና የመኪና አሽከርካሪነት ስልጠና በነፃ እንዲያገኙም አድርጓል ሲሉ ጠቅሰው፣ ወጣቶቹ ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ በመንግሥት ተቋማትና በግል ድርጅቶች ስራ አግኝተው እየሰሩ እንደሚገኙም ነው ያስታወቁት፤ ከሱስ ተላቅቀው ስራ ይዘው ማኅበሩን ማገልገላቸው ትልቅ ስኬት እንደሆነም አቶ ምኅረት ይናገራሉ፡፡
አቶ ምኅረት እንዳስታወቁት፤ ማህበሩ በዋናነት በባህር ዳር ከተማ የበጎ ፈቃደኝነት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ በማድረግ በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል፡ ፡ ለአብነት ያህል ንብረታቸው ለተቃጠለባቸው የአጣየ ከተማ ነዋሪዎች 47 ኩንታል ልብስ እንዲሁም ቻግኒ ከተማ ለነበሩ ተፈናቃዮችም አልባሳት ሰጥቷል፡፡ ለራያ ቆቦ ነዋሪዎችም ልዩ ልዩ ድጋፎች ተደርገዋል፡፡ በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች የአልባሳትና የሌሎች ቁሳቁስ ድጋፎች ተሰጥተዋል፡፡
‹‹በዋናነት የምንሰራው ድጋፍ ላይ ነው፡፡ ወደ ማኅበሩ ቢሮ መምጣት ላልቻሉ ሰዎች የቤት ለቤት ድጋፎችን እናደርጋለን›› ሲሉም ጠቅሰው፣ ‹‹ከጥገኝነት ነፃ የሆነ ትውልድ ይፈጠር ዘንድ በሰው አዕምሮ ላይም እንሰራለን፤ በጎ ካሰብንና በጎ ነገሮችን ማድረግ ከቻልን፣ ሰው ከጥገኝነት መላቀቅ እንደሚችል በማመን እንሰራለን›› ይላሉ፡፡
‹‹ድንበር የለሽ›› የበጎ አድራጎት ማኅበር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ፣ ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ባሏቸው ማህበረሰብ ተኮር ተግባራት የበርካታ ሰዎች ሕይወት በበጎ ተለውጧል፡፡ አቶ ምኅረት እንደሚገልጹት፣ ማኅበሩ ስራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከ200ሺ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ይህ አሀዝ ግን ዘላቂ ጥቅም ያስገኙትን ድጋፎች ብቻ እንጂ ጊዜያዊ ድጋፎችን (ለአብነት ያህል በበዓላት ወቅት የሚደረጉ ጊዜያዊ ድጋፎች) የሚያካትት አይደለም፡፡
ማኅበሩ ለበጎ አድራጎት ስራዎቹ መከወኛ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በሦስት መንገዶች እንደሚያገኝ አቶ ምኅረት ያስረዳሉ፡፡ የአባላት መዋጮ አንዱ የገንዘብ ማግኛ መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፣ የማኅበሩ አባላት በየወሩ ከ15 ብር ጀምሮ እስከ አንድ ሺ ብር (የወርቅ ደረጃ አባላት) እንደሚያዋጡም ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚኖሩ ወገኖች ድጋፍ ማግኘት ነው ያሉት አቶ ምኅረት፣ ለተቋማት ደብዳቤ በመፃፍ ድጋፍ የመጠየቅ አሰራርም ማኅበሩ ለበጎ አድራጎት ስራዎቹ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያገኝበት ሌላው መንገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ማኅበሩ መንግሥት መሸፈን ያልቻላቸውን ችግሮችና ክፍተቶችን የሚሞላ በመሆኑ፣ መንግሥት ብዙ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል›› የሚሉት አቶ ምኅረት፣ ‹‹መንግሥት ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የስልጠና እድሎችን ያመቻቻል፡፡ ማኅበሩ ለሚያቀርባቸው የቦታና ሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል፡፡ የማኅበሩ አባላት ደህንታቸው ተጠብቆ የበጎ አድራጎት ስራዎችን እንዲያከናውኑ የትብብር ድብዳቤዎችን በመፃፍ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጣና ክፍለ ከተማ፣ ሽምብጥ ወጣቶች ማዕከል ውስጥ ቢሮ ሰጥቶናል፡፡ ወጣት ማዕከሉ አዳራሽ ስላለው አዳራሹን ለድጋፍ መስጫ ስራዎቻችን እንጠቀማለን›› በማለት መንግሥት ለማኅበሩ ስለሚያደርጋቸው ድጋፎች ያስረዳሉ፡፡
ባህልና ወግን ከማስጠበቅ አንፃር እንዲሁ ማህበሩ ይሰራል፡፡ አቶ ምኅረት ይህንንም አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ፣ በ2013 ዓ.ም 12 የማኅበሩ አባላት ከባህር ዳር ወደ ላሊበላ የ310 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ሲያደርጉ፣ በወቅቱ በአካባቢው ጦርነት ስለነበር ከሰላምና ደህንነት እንዲሁም ከባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤቶች ደብዳቤዎችን አግኝተው ጉዞ ስለማድረጋቸው ያስታውሳሉ፡፡
ድርጅቱ ስራዎቹን ሲያከናውን ስለሚያጋጥሙት ችግሮችም አቶ ምኅረት አመልክተዋል፡፡ ‹‹ማኅበሩ ስራውን በጀመረባቸው ዓመታት ከነበሩ ፈተናዎች መካከል አንዱ የአመለካከት ችግር ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ‹ገንዘቡ ለትክክለኛው ዓላማ አይውልም› ብለው የማሰብ አዝማሚያ ይታይባቸው ነበር፤ ይህ ችግር አሁን የለም›› ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የነበረው የሰዎች አስተሳሰብ ተቀይሮ ማኅበሩ ለግለሰቦችና ለተቋማት የድጋፍ ጥያቄ ሲያቀርብ ሁሉም አቅሙ የፈቀደውን የገንዘብ፣ የአልባሳት፣ የቁሳቁስና የምግብ ድጋፍ ያደርጋል፤ ድርጅቶችም ወደ ማኅበሩ በመምጣት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ በኑሮ ውድነትና በሌሎች ችግሮች ምክንያት አሁን ያለንበት ወቅት ብዙ ሰዎች ድጋፍ የሚፈልጉበት ጊዜ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳ ብዙ ሰዎችን ተደራሽ ማድረግ እየተቻለ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ የቦታ ጥበትም ሌላው ችግር መሆኑን ጠቁመው፣ ችግሩን ለመፍታት ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር መፍትሄ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ በመመስረት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እነዚህ ወገኖች ከችግሮቻቸው ተላቅቀው በማኅበረሰብና ሀገር ግንባታ ሂደት የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ የማድረግ ዓላማን ይዞ የሚንቀሳቀሰው ‹‹ድንበር የለሽ›› የበጎ አድራጎት ማኅበር፣ በዜጎች ሕይወት ላይ ዘላቂ ለውጥ ለመፍጠር እና ማኅበሩ የተደራጀ ተቋማዊ አቅም እንዲኖረው የሚያስችሉ የረጅም ጊዜ እቅዶች እንዳሉትም አቶ ምኅረት ይገልፃሉ፡፡
ዋናው የማኅበሩ እቅድ በግለሰቦችና በተቋማት ከመደገፍ ተላቅቆ ገቢ ማመንጨት የሚያስችል አቅም በመገንባት ለአባላትና ለሌሎች ወገኖች የሥራ እድል መፍጠር እና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሆን ነው፡፡ በሌላ በኩል ለሰዎች እለታዊና ጊዜያዊ ድጋፎችን ከማድረግ ይልቅ ዘላቂ የሆኑና በሰዎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሊፈጥሩ የሚችሉ ድጋፎችን በማድረግ ሰዎችን ከጥገኝነት አስተሳሰብ ማላቀቅ ላይ አተኩሮም ይሰራል፡፡ ሰው ድጋፍ ማድረግና መስጠት ያለበት ስለተረፈው ብቻ ሳይሆን መስጠት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን አቅም በፈቀደ መጠን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት በጥልቀት ማስገንዘብም ሌላው የማኅበሩ እቅድ ነው፡፡
‹‹ድንበር የለሽ›› የበጎ አድራጎት ማኅበር፣ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ፣ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ያሏቸው የበጎ አድራጎት ተግባራትን ሲያከናውን በመቆየቱ ከበርካታ ተቋማት እውቅናዎችን አግኝቷል፡፡ ለድርጅቱ እውቅና ከሰጡ ተቋማት መካከል የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር፣ ዓድዋ የታሪክና ባህል ኅብረት፣ ‹‹ፓወር ቤዝ አምረፍ›› እና ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይጠቀሳሉ፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም