በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
“እድልዎን ይሞክሩ” ከሎተሪ አዟሪዎች አንደበት የማይጠፋ ቃል ነው። እድሌን ልሞክር ያለው ሎተሪውን ይገዛል። ሎተሪ ገዢው በለስ ቀንቶት የሎተሪው አሸናፊ ቢሆን ደስታው በቀላሉ የሚገለጽ አይሆንም፤ በተለይም ትልቁን ሎተሪ ካሸነፈ። ምክንያትም እጅግ ኢምንት ያህል ገንዘብ አውጥቶ ግዙፍ ገንዘብን ማጋበስ ስለቻለ።
በሎተሪው መግዣ እና አሸናፊ በተሆነበት የሎተሪ የገንዘብ መጠን መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ብዙ ነው። ፈጽሞውኑ አይገናኝም። ምክንያቱም ጉዳዩ ሎተሪ ስለሆነ።
የመዝራትና ማጨድ መርህ ከሎተሪ ጋር ምን ያመሳስላቸዋል? ምንስ ያለያያቸዋል? የሚሉትን ጥያቄዎች እንጠይቅ። ከሚያመሳስላቸው ነገር መካከል አንዱ ነጥብ በሁለቱም አማካኝነት የሚገኘው ውጤት ከተዘራው እጅጉን የበለጠ ሆኖ መገኘቱ ተጠቃሽ ነው።
ለሎተሪ ያወጣነው ገንዘብ ከሎተሪ ካገኘነው ትሩፋት አንጻር ኢምንት እንደሆነው፤ ለዘርነት የምንጠቀመው ጤፍና ዘሩ ፍሬ አፍርቶ ከሚሰበሰበው የጤፍ ምርት አንጻር ዘሩ ኢምንት ነው። ወደ ልዩነት ነጥቡ ስንመጣ ሌላ ወሳኝ ነጥብ እናገኛለን። በሎተሪ እና ዘርቶ በማጨድ መካከል ያለው ልዩነት የተጠባቂነት ልዩነት ነው። ሎተሪ እንደሚወጣልህ እርግጠኛ ሆነህ ከሰው ገንዘብ ትበደራለህ? በፍጹም አታደርገውም።
ምርት ሲመጣልኝ ብለህ አስበህ ግን ልትበደር ትችላለህ። ሎተሪ በተጨባጭ ፍሬውን ይዞ አንተ ጋር ለመድረስ በፍጹም የምትጠብቀው አይደለም፤ እጅግ ሩቅ የሆነ እድል ስለሆነ። ጤፍ ዘርቶ ምርትን ከጎተራ መክተት ግን በተጨባጭ የሚጠበቅ ስለሆነ ከሎተሪው ተመሳሌት በእዚህ ይለያያል። በየትኛውም ነገር ላይ የምትዘራው ዘር ይዞት የሚመጣው ውጤት ከዘሩ አንጻር ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም።
ስለሆነም መዝራትና ማጨድ ትኩረት ይሻል ማለት ነው። የሚታጨደው የተዘራው መሆኑም ሌላው ነጥብ። በምድራችን ላይ ላሉ ችግሮች መፍትሄን ለመስጠት የመዝራትና ማጨድ መርሆች ጠቃሚዎች ናቸው። የተገለጡት ችግሮች ውስጥ የሚወሰደው ትምህርት ራሱ ትርጉሙ ብዙ ነው።
የችግር አፈታት ሥርዓት
ችግርን ነቅሶ ማውጣት ለመፍትሄው የግማሽ መንገድ ያህል ጉዞ እንደሆነ ይታመናል። በእርግጥም ነው። የችግር አፈታት ውስጥ ችግሩን አውቆ መነሳት አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ችግሩ ውስጥ ራሱ የችግሩ መነሻ የሆነውን የተዘራውን የችግሩ ምንጭን የሆነውን ዘሩን መፈለግ ደግሞ ሌላው አስፈላጊ ነገር ነው። ሁሉም ችግር ከችግርነቱ በፊት የተዘራ ዘር አለው። ችግሩ የተዘራው የችግሩ ዘር ማሳያ ውጤት ወይንም ምርት ሲሆን የችግሩ መነሻ ግን ይለያል።
በሕይወት ውስጥ ሥኬትን መጎናጸፍ ማለት ከችግር የተፋታ ኑሮ እንኖራለን ማለት አይደለም። ይልቁንም ችግሩን ለማሸነፍ በምንሄድበት መንገድ ውስጥ በአሸናፊነት እንወጣለን ማለት እንጂ። የዛሬ ችግር ነገም ችግር ሆኖ እንዳይመጣ ከችግሩ ቅርንጫፍ ሆነ ግንድ ይልቅ ዘሩ ላይ መሄዱ የተሻለው መንገድ ነው። ስለሆነም የመዝራትና ማጨድ ህግ ትምህርት አለው። ትምህርቱንም ከዘሩ በፊትና ከዘሩ በኋላ በሚሆነው ተግባራት ውስጥ ይገኛል።
ከዘሩ በፊትና በኋላ
ዘሩ ከመዘራቱ በፊት
በሕይወት ጉዟችን ውስጥ የዘርና ውጤትን ግንኙነት ለመረዳት እንድንችል ዘሩ ከመዘራቱ በፊት የሚያስፈልጉትን ሁለት ነጥቦች እናንሳ። የቤተሰብ አባላት ውስጥ የተለያዩ ተሰጥዖ ያላቸው ልጆች ይኖራሉ። ሁሉም በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ መሆንን ይፈልጋሉ። መንገዱም መዘራት ያለበትን በሚገባ መዝራት ይሆናል። በጥናት ሰዓት በማጥናት እውቀት ይዘራል፣ በስፖርት ውስጥ የሰውነት አቅም ማጎልበት ይዘራል፣ በምግብና በእንቅልፍ ውስጥ ጤንነት ይዘራል፣ ችግሮችን በሰላም መፍታት ደግሞ ሁለንተናዊ ሰላምን ወዘተ መዝራት ያስችላል።
በመደበኛ የጊዜ መርሐግብራችን የምናደርጋቸው ነገሮች ዘር ሲሆኑ ድምር ውጤታቸው ደግሞ ህይወታችንን ባቀድነው መስመር ማሳካት የምንፈልገውን እያሳካን መሄድ ማስቻል ነው። የመዳረሻ ውጤቱ ፍሬው/ምርቱ ሲሆን የሚታጨደው ፍሬ አቅም ደግሞ በዘሩ ውስጥ አለ። ይህ ዘር ከመዘራቱ በፊት ሊኖር የሚገባቸውን አራት ቁልፍ ነጥቦች እናንሳ።
1. ለዘርነት ማብቃት – አርሶ አደሩ ዘሩን ከመዝራቱ በፊት ለዘርነት ያዘጋጀዋል። ችግኝ ጣቢያዎች ነገ ዛፍ የሚሆን ችግኝን ያዘጋጃሉ። በረጅም ዓመታት ውስጥ መጠለያ ዛፍ እንዲሁም የወንበር መስሪያ እንጨት የሚሆነው ዛፍ ከዛፍነቱ በፊት ችግኝ ነበር፤ ከችግኘነቱ በፊት ዘር ነበር፤ ለዘርነትም የተዘጋጀ። ዝግጅቱም ለዘርነት አቅም በማደግ ውስጥ የሚገለጽ። የዘርነት አቅም የሌለውን ብትዘራው የምታስበውን ፍሬ ፈጽሞውኑ ልታፈራ አትችልም።
በብዙ ነገር እደክማለሁ ነገር ግን ውጤታማ ማድረግ አልቻልኩም ለሚሉ ሰዎች ከውጤቱ ይልቅ የዘሩትን ዘር ቢመረምሩ መልካም ይሆናል። የዘሩት ዘር ለዘርነት ያልተዘጋጀ ከሆነ ፍሬን ሊያፈራ ፈጽሞውኑ አይችልም።
ከልቡ በመነሳሳት ውስጥ ሆኖ የማይዘራ ሰው እንዴት ፍሬን ሊያፈራ ይችላል? አንድን ነገር አደርጋለሁ ብሎ የሚነሳ ሰው ትኩረቱን ሆነ አቅሙን አሰባስቦ የሚያደርገው ዘርን መዝራት የሚገኘው በዘርነት ዝግጅት ውስጥ ነው። የሚዘራውን ማዘጋጀት መሠረታዊው ነጥብ ነው። ምን እንደሚዘራብህ ለመወሰን የምትዘራውን መምረጥ፤ የምትዘራውም ለዘርነት ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል።
ዘር በማዘጋጀት ሂደት ውስጥ ምላሽ የሚያሻቸው ሁለት ጥያቄዎች አሉ። እነርሱም፤
ጥያቄ 1. ልዘራ የተገባኝ ምን አይነት ዘር ነው? የምታመርተው የተዘራውን በመሆኑ ምን አይነት ዘር መዝራት እንዳለብህ መወሰን አስፈላጊው እውነት ነው። ቲማቲም ለማጨድ የቲማቲም ዘር ይዘራል እንጂ ማሽላ ሊሆን አይችልም። በህይወትህ ማጨድ የምትፈልገውን በማስቀመጥ መዝራት ያለብህን ዘር መወሰን ትችላለህ።
ጥያቄ 2. ምን ያህል ዘር መዝራት አለብኝ? ውጤት ማስመዝገብ ከሚገባህ ግብ አንጻር የምትዘራው በሰፊውና ያለስስት መሆን አለበት። ጊዜህን የሰጠኸው ነገር ውጤት ለማስመዝገብ የሚረዳህ ነው። ጊዜህን የምትዘራው በሌላ አቅጣጫ ሆኖ ውጤት የምትጠብቀው በተቃራኒው ከሆነ ውጤቱ አልተገናኝቶም ነው። በመሆኑም ከምታስበው ምርት አንጻር የምትዘራውን ማብዛት ወሳኝ ነጥብ ነው።
2. መዝሪያ ቦታ ማዘጋጀት – ዘሩ ከመዘራቱ በፊት የሚዘራበትን ትክክለኛ ቦታ መምረጥም ያስፈልጋል። ትክክለኛውን ዘር መንገድ ላይ ወጥተህ ብትዘራው እግረኛ እረጋግጦት እንዲሁም የመኪና ጎማ አቃጥሎት ያልፋል። ድንጋይ ላይ ብትዘራውም እንደዚያው ነው። በእሾህ መካከል ብትዘራውም ለውጥ የለውም።
በውሃ ላይ ብትዘራውም በውሃ ይወሰዳል። በትክክለኛው ቦታ ላይ በዘራኸው ጊዜ ግን ፍሬው ከጎተራ የሚገባ ይሆናል። በዘርና ምርት መካከል ያለው ግንኙነት ሲታሰብ መዝሪያ ቦታም ግምት ውስጥ መግባት አለበት። እንዲያው ዝም ብሎ መንገድ ላይ የዘራኸውን በቆሎ መንገድ ላይ ለምን አልበቀለም አትልም።
3. መዝሪያ ጊዜ ማዘጋጀት – ጊዜ ታላቁ ሃብታችን ናት። በጊዜ ውስጥ የብዙ ነገሮች ብያኔ አለ። ዘሪው በጊዜ ውስጥ ትርጉም ያለው ክዋኔ አለው። አንድ ሎተሪ ለሽያጭ ክፍት የሚሆንበት ጊዜ አለው። ጊዜ ያለፈን ሎተሪ ብትገዛው ውጤት የለውም። ጊዜ ያለፈን ሎተሪ በእጅህ ይዘህ ከዛሬ ነገ ሎተሪ ቢወጣልኝ ብለህ ብትጠብቅ እንዲሁ ኪሳራ ነው። መፍትሄው የመዝሪያ ጊዜን ማወቅ መቻል ነው።
በህይወትህ ላይ እንዲዘራ የምትፈልገው እውቀት፣ አስተሳሰብ፣ እይታ፣ ባህሪ፣ ተግባቦት፣ ከሰዎች ጋር በሰላም የመኖር አቅም፣ ምርምር፣ ገንዘብ ማግኘት፣ ወዘተ ውጤታማ እንዲሆን የጊዜ ህግ አለ። በጊዜ ህግ ውስጥ መዝሪያ ጊዜህን እወቅ።
አንድን መጽሐፍ ካሉት የ24 ሰዓት ውስጥ በየትኛው ባነበው ጥሩ ነው ብለህ አስበህ የሚስማማውን ጊዜ ስትመርጥለት መዝሪያ ጊዜ አዘጋጀህ ማለት ነው። በሆነ ጉዳይ ላይ እውቀትና ልምድ በማግኘት ወደ ራስህ ሥራ ለማዋል ወሰንህ ከሌሎች ሥር ሆነህ የምትማርበትን ጊዜ ስትወስን መዝሪያ ጊዜ አዘጋጀህ ማለት ነው። በሌሎች ዘርፎችም እንዲሁ ነው።
4. ዘሪውን መምረጥ – ጆሮህን ከፍተህ በጥሞና ሆነህ ዙሪያህን ላዳምጥ ብትል ብዙ ድምጾች እንደከበቡህ ትረዳለህ። በዙሪያችን ያሉት ድምጾች መካከል የምንፈልገውን መስማት እንችላለን። የምንፈልገውን ስንመርጥ ዘሪውን መረጥን ማለት ነው። በአንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ “ዩቲዩብ/YouTube” ገብቼ እማራለሁ ስትል የበዙ ሰዎች የሰሩት ቪዲዮ ይዘረግፍልሃል።
ከእዚያ ውስጥ ግን የምትሰማው የመረጥከውን መሆን አለበት። የመረጥከውም እንድትመርጠው የሚያደርግህ የራስህ መመዘኛ ሊኖርህ ይችላል። በሕይወት ጉዞ ውስጥ የሚመጣውም የሚሄደውም ፈቃዳችንን ከሰጠነው ሊዘራብን ይፈልጋል። በሚዲያ ዘመን ደግሞ ተጋላጭነቱ ሰፊ ነው።
ጊዜያችንን የሚበሉ የበረከቱ ነገሮች አሳስረው አስቀምጠውን ጊዜን መቁጠር የማንችል እንዳንመስል ማሰብ ይኖርብናል። ማሰብ መቻላችንም የሚገለጠው ዘሪውን በመምረጥ በሚሆን ውሳኔ ነው።
ዘርቶ በማጨድ ውስጥ ውጤታማ መሆን ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ከመዘራቱ በፊት አንተ የምትዘራውን ለዘርነት አብቃው፣ ቦታ አዘጋጅለት፣ ትክክለኛ የመዝሪያ ጊዜን ምረጥ እንዲሁም ዘሪ ማን መሆን እንዳለበት ወስን። አንተ ላይ የሚዘራም ሆነ ሌሎች ላይ የምትዘራ ከሆነ እኒህ አራት ነጥቦች ዘሩ ከመዘራቱ በፊት ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው። ስራው ግን አላበቃም። ከተዘራስ በኋላ? ብለህ መጠየቅ አለብህ።
ዘሩ ከተዘራስ በኋላ፣
ተማሪውን ተመልክት፤ ወደ አርሶ አደሩ ቤተሰብም አቅና፤ አትሌቱ ልብ ውስጥ ምን እንዳለ አዳምጥ ሁሉም ስለ ዘራው ዘር ውጤትን ይጠብቃል። ውጤቱ ከመዘራቱ በፊት ባሉት አራት ነጥቦች ውስጥ እንደሚገለጥ አንብበናል። ዘሩ ከተዘራ በኋላ መታሰብ ያለባቸውን አራት ነጥቦች ደግሞ ቀጥሎ እንመልከት፤
1. ጥበቃ ያስፈልገዋል – ሌባ በየትኛውም ቦታ ላይ ተስፋን ሊነጥቅ የሚመጣ ነው። ሌባ ሊሰጥህ አይመጣም፤ ሊነጥቅህ እንጂ። ለዘሩ ጥበቃ የምታደርገው ዘሩ ወደ ፍሬነት ለመቀየር የሚፈጅበት ጊዜ ስላለ ነው። ጥበቃው ከሌባ ብቻም ሳይሆን ከአውሬም ነው። በግብርና ማሳ ውስጥ ሰው የሚመስለን ምስል በእንጨትና በጨርቅ ማቆም የተለመደ ልምድ አለ። ምክንያቱ ደግሞ አውሬ ወደ ማሳው ቢገባ ሰው የቆመ መስሎት እንዲሸሽ ለማድረግ ነው።
አውሬው ከዱር አውሬ እስከ ሰማይ ወፎች አድርገን ልንወስደው እንችላለን። ዘርህን ለማጨናገፍ የሚመጣ ሁሉ መዳረሻው አንድ አይነት ስለሆነ በአውሬነት ብትመድበው አይከፋም። ዘርህ ፍሬ እንዲያፈራ ትፈልጋለህ? ምላሽህ አዎን ከሆነ ከመዝራት በኋላ ጥበቃ አድርገለት፤ ጥበቃ ያስፈልገዋል። በልብ ውስጥ የሚጠበቀውን ደግሞ በይበልጥ ጠብቀው!
2. እንክብካቤ ያስፈልገዋል – ዛሬ ዘርተህ በምርት ወቅት ፍሬውን ለመሰብሰብ ብቻ ብትመለስ ምንኛ ደስ ባለህ። ነገር ግን በተጨባጭ እንዲህ አይነት ምርት የለም። በመዝራትና ማጨድ መካከል የእንክብካቤ የክትትል ስራዎች አሉ። ዘሩ መሬት ይዞ መውጣት ሲጀምር እንክብካቤውን እንደ ወቅቱ ሁኔታና እንደ እድገቱ ሁኔታ ይቃኛል።
በሰውም እንዲሁ ነው። አንድ ልጅ ተጸንሶ፣ ተወልዶ እድገትን ሲጀምር እንክብካቤው በብርቱ ይቀጥላል። ወደ እርሻው ማሳ ገብቶ አረሙን ማረም ሆነ ተገቢውን መድሃኒት መርጨት ወዘተ ለምርታማነት ወሳኝነት አለው።
3. በወቅቱ መሰብሰብ – ዘሩን ሊዘራ በሚገባው የዘርነት አቅም፣ መዝሪያ ጊዜ፣ ቦታ እና ሊዘራው በሚገባ አካል እንዲዘራ ካደረግህ እና ከዘር በኋላም ጥበቃና እንክብካቤ አድርገህ የሚቀርህ ፍሬህን መሰብሰብ ሆኖ ሳለ ከመሰብሰብ ወደ ኋላ ብታፈገፍግ ምን ሊባል ይችላል? እንዲሁ ለመድከም ብቻ የደከመ ከመባል ውጪ። ማንም ሰው እንዲሁ መድከም አይፈልግም። ምርትን በጊዜው መሰብሰብ አለመቻል ምርቱ በሌሎች እንዲሰረቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በአየር ንብረት ለውጥ መጥፋትም እንዲሁ። በወቅቱ መሰብሰብ አስፈላጊነቱ ብዙ ነው።
ዛሬ ትላንት የዘራኸውን የምታጭድበት የጊዜ ስርዓት ነው። ዛሬ ልታጭድ የተገባውን አስደሳች የሆነውን ምርት ለማጨድ ተነሳ። ደስ የማይለውንም ቢሆን የግድ መታጨድ ያለበትን በጸጸት ዛሬን ከማሳለፍ ተቀብለህ ለነገ ትምህርት አድርገህ ውሰደው። ትላንት በዘራው ትዕቢት ዛሬ ውድቀትን ያመረተው ሰው ስለ ትዕቢቱ የመጣበትን ቅጣት ለመቀበል አሻፈረኝ ሲል ለተጨማሪ መጋጋጥ ውስጥ ያልፍና የመለወጫ ዘመኑን ያሳልፋል። የተዘራው መብቀያው ጊዜ ላይ ከደረሰ ቢያስደስትም ሆነ ቢያስከፋ ተቀብሎ በአግባቡ ማስተናገድ ተገቢነት ይኖረዋል። ተቀበለው ግን ቀጥሎ ላለው ዘርቶ የማጨድ ህይወት ትምህርት ይሁንልህ።
4. ትምህርት መውሰድ – በትላንት ውስጥ ባለው ዘርቶ የማጨድ ህይወት ውስጥ የሚገኘው ትምህርት ጥራቱ ላቅ ያለ ነው። የሀገራችን ትምህርት በጥራት በሚታማበት በእዚህ ወቅት በህይወት ተሞክሮ የሚገኘው እውቀት ግን በጥራቱ እንደቀጠለ ነው። ዘርቶ በማጨድ ውስጥ የሚገኘው ትምህርት ለሌሎች ስትናገረውም እንዲሁ አስተማሪ ነው። በጽሁፍ ልታቀርበው ስትሞክርም ትኩረት የሚስብ፤ ህይወትም ለዋጭ ነው። ለነገ ውሳኔዬ ልማርበት ካልክም ጥሩ መምህር ነው።
አርሶ አደሩ በእያንዳንዱ ዓመት የመዝራትና ማጨድ ሂደት ውስጥ የሚወስደው ትምህርት ለሚቀጥለው ዙር ተስፋን መሰነቂያ ይሆነዋል። በእግር ኳስ ሊግ ውስጥ የሚጫወቱ ቡድኖች የሚቀጥለውን ዘመን ከመቀበላቸው በፊት ባሳለፉት የውድድር ዘመን ውስጥ ትምህርት የሆኑላቸውን ነገሮች ተጠቅመው ስለሚቀጥለው ዘመን ይዘጋጃሉ። በመዝራትና ማጨድ ውስጥ ያለውን ትምህርት ፈጽሞውኑ መዘንጋት አይገባም። ከተዘነጋ በህይወት ጉዟችን ውስጥ ከእድገት እየጎደለን ምናልባትም አንድ ቦታ ላይ ተቸንክረን እንድንቀር የሚያደርግ ይሆናል።
አራቱ የመዝራት እና ማጨድ መርሆች
በመዝራትና ማጨድ ውስጥ ፍሬያማ ለመሆን አራቱን የመዝራትና ማጨድ መርሆችን መረዳት ይገባል።
ዛሬ የነገ አባት ነው። ዛሬ የሆነው መሆን ትላንት እናስብ የነበረበት እና እንኖር የነበረበት ኑሮ ውጤት ነው። ዛሬ ላይ በጥበብና በማስተዋል የሚመላለሱ ነገ ላይ ውሳኔን ለመወሰን የሚረዳ ጥበብ ይኖራቸዋል። በሌሎች ነገሮችም እንዲሁ። ከገንዘብ አንጻር ዛሬ ላይ የሚቆጥቡ ነገ ላይ የተትረፈረፈ ነገር የሚኖራቸው ናቸው። ያላቸውን ነገር በሙሉ ዛሬ ላይ የሚያጠፉ ነገ ላይ ምንም አይኖራቸውም። ለዛሬ ብቻ የሚያስብ እና ያለውን ሁሉ በዛሬ ላይ የሚያድፋፋ ነገን አሻግሮ ማየት የማይችል ሰው ነው። በመሆኑም የመዝራትና የማጨድን መርህ በሚገባ መረዳት አስፈላጊ ነው።
መርህ 1. መዝራትና ማጨድ በሁሉም ላይ የሚሰራ ነው፣
አንዳችን ከአንዳችን በእድሜ፣ በጾታ፣ በእምነት፣ በአካባቢ፣ በሙያ፣ በትምህርት ወዘተ ልዩነት ሊኖረን ይችላል። የመዝራትና ማጨድ መርህ ግን በሁሉም ሰው ላይ የሚሰራ ነው። በየትኛውም እድሜ ውስጥ ሁን ዛሬ የምትዘራውን ነው ነገ የምታጭደው። ምንም አይነት እምነት ተከተል ዛሬ የዘራኸው ነገ ላይ የምታጭደው ነው። ይህን በማሰብ በአንደበታችን ሆነ በሌላው መንገድ የምንዘራውን መጠበቅ አለብን። የዘራነውን ከማጨድ ሊመልሰን የሚችል ምንም ምክንያት የለምና።
መርህ 2. የምናጭደው የዘራነውን ነው፣
በተጨባጭ የምንዘራው እርሱን በተጨባጭ እናጭዳለን። ጥላቻን የዘራ ጥላችን ለማጨድ ስንዴ ተዘርቶ ኑግ እንደማይታጨደው እርግጥ ነው። የዘራነውን ያንኑ እንደምናጭድ ስናውቅ የምናጭደውን እንወስናለን። አልኮልን ሆነ አደንዛዥ እጽን ራስህ ላይ ዘርተህ የምታጭደው የእነርሱን ውጤት መሆኑን ማንም ሊጠራጠር አይገባውም። ራሳችንን ፈጽሞውኑ ልናታልል አይገባም፤ የህይወታችንን ያንኑ እናጭዳለን።
መርህ 3. ከዘራነው በላይ እናጭዳለን፣
በሎተሪው መግዣና ሎተሪው በወጣልን ጊዜ በምናገኘው መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ ሁሉ በሚዘራው መጠን እና በምርቱ መጠን መካከል ልዩነቱ ከፍተኛ ነው። የዘራነው ዘር በግማሽ ማዳበሪያ ሆኖ የምናጭደው በብዙ ጆንያ ነው። ትንሽ በምትመሰል እውነተኛና ትክክለኛ ውሳኔ ከፍተኛውን ጥፋት ማስቀረት ይቻላል። ስለሆነም ለዘሩ ትኩረት ይደረግ፤ ምርቱ ከዘሩ እጅጉኑ የበዛ ስለሆነ።
መርህ 4. የምናጭደው ከዘራን በኋላ ነው፣
ሳይዘሩ ማጨድ የለም። የሚታጨደው የተዘራው ነው። የሚታጨደው ወዲያው ሊሆን ይችላል፤ አንዳንዴ ደግሞ ረጅም ጊዜ ሊወስድ ይችላል። የሆነው ሆኖ ቅደም ተከተሉ ግን ሁሌም የሚኖር ነው። ልናጭድ ስለምንፈልገው በማውራት ጊዜን ከማጥፋት በመዝራት ላይ ማተኩር የተሻለ ነው። የምናጭደው ከዘራን በኋላ ስለሆነ ሳንዘራ ማጨድ የለምና በመዝራት እንመን። ራሳችን ላይ እንዝራ በሌሎች ላይም እንዲሁ። ጤናማውን ትምህርት፣ ጤናማውን አስተምህሮ፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ህብረትን፣ ይቅርታ ማድረግን፣ ትጋትን፣ ዋጋ መክፈለን፣ እውቀትን ወዘተ። ውጤቱም የተዘራውን ይሆናል ምክንያቱም
የምናጭደው ከተዘራ በኋላ የተዘራውን ስለሆነ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10/2013