አስናቀ ፀጋዬ
በኢትዮጵያ 22 ነጥብ 6 ሚሊዮን አባላት ያሏቸው 92 ሺ የህብረት ሥራ ማህበራት እንዳሉና የማህበራቱ አጠቃላይ ካፒታልም 28 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መድረሱን ከፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። በእነዚሁ ህብረት ስራ ማህበራት ስር 1 ሺ 60 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙ ሲሆን ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሥራ እድል ተፈጥሯል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የገበሬ ህብረት ሥራ ማህበር ዩኒየኖች ለተመሳሳይ ዓላማ የተቋቋሙ ቢሆንም አንዳንዶቹ ግን አርሶ አደሩ ላመረታቸው ምርቶች ገበያ በማፈላለግና ምርቶቹ ሸማቹ ዘንድ እንዲደርሱ በማስቻል ረገድ የግል ጥረታቸውን ተጠቅመው ውጤታማ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡
አምራቹንና ሸማቹን በገበያ እኩል ተጠቃሚ በማድረግ ረገድም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ከነዚህ ውስጥም በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ የሚገኘው ጊዮን ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ዩኒየን አንዱ ነው፡፡
የጊዮን ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር ዩኒየን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢያዝን መኮንን እንደሚሉት ጊዮን ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር ዩኒየን በሰባ መሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራትና በ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ካፒታል በመጋቢት ወር 2002 ዓ.ም ተመስርቷል፡፡ዩኒየኑ ሥራውን ሲጀምርም አቅም የሌላቸው ሦስት ዩኒየኖችን በማዋሃድ ነበር፡፡
የዩኒየኑ ምስረታ መነሻ ምክንያትም ሦስቱ ዩኒየኖች በተናጥል የዩኒየኑን ተልእኮ ማሳካት አለመቻላቸውና በጋራ ቢዋሃዱ ይበልጥ የገንዘብ አቅምና የሰው ሃይል በመፍጠር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ይሆናል ብሎ በማሰብ ነው፡፡
በዚሁ መነሻም ለዩኒየኑ የተሰጡ ሰባት ያህል ተግባራትን በማከናወንና ዩኒየኖቹን በማዋሃድ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ዩኒየኑ የተቋቋመበት ዋነኛ አላማ በተለይ አባል ማህበራት አርሶ አደሮች ያለባቸውን ኢኮኖሚያዊ ችግር በመፍታት በተሻለ መልኩ ፍላጎታቸውን ለማርካት ሲሆን ይህም ለአባላት የግብርና ግብዓቶችን ማቅረብ፣ የሰብል ግዢና ሽያጭ ማከናወን፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ማቅረብ፣ የዘር ብዜት ስራዎችን እና የሜካናይዜሽን ስራዎችን መስራት፣ እንዲሁም ለአባላት ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን እና የደረቅ ትራንስፖርት አገልግሎት ለአባላት መስጠትን ያጠቃልላል፡፡
እነዚህኑ አገልግሎቶች በምስራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች ላይ ማለትም በአነደድ፣ አባባል፣ ደጀን፣ ደበይት ላትጊን፣ ሸበል በረንታ፣ነመይና እናርግ እናውጋ በተሰኙ ወረዳዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በአሁኑ ወቅት የዩኒየኑ የአባላቱ ቁጥር ከ165 ሺ በላይ የደረሰ ሲሆን አጠቃላይ ካፒታሉም ያልተመረመረውን ካፒታል ሳይጨምር ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ከምስረታው ጀምሮ ሲያከናውናቸው የቆዩ ስራዎች እንዳሉ ሆነው በአሁኑ ግዜ ለአርሶ አደሩና ለአባል ማህበራት የግብርና ግብዓቶችን በተለይም ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን እያቀረበም ይገኛል፡፡
በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ከአርሶ አደሩ ሰብል ገዝቶ የተሻለ ገበያ በማፈላለግ እንዲሸጥ በማድረግ መሠረታዊ ህብረት ስራ ማህበራትንና አባል አርሶ አደር ተጠቃሚ ለማድረግም ይሰራል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ከፋብሪካዎች ለአባል አርሶ አደሩ ያቀርባል፡፡ዘር በማባዛትም ለአርሶ አደሩ ምርጥ ዘር ያቀርባል፡፡በዚህም መሠረታዊ ማህበራቱና ዩኒየኑ ተጨማሪ ገቢ ያገኛሉ፡፡
እንዲሁም በሜካናይዜሽን የትራክተር እርሻ አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል፡፡ለአባላትም ስልጠና እየተሰጠና ሌሎችንም ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡
ጊዮን ሁለገብ የገበሬ ህብረት ስራ ዩኒየን እንደሌሎች ዩኒየኖች በብዙ መልኩ የሚመሳሰል ቢሆንም አብዛኛዎቹ ዩኒየኖች በማይሳተፉበት የዘር ብዜት ስራ ላይ መሳተፉ ከሌሎቹ ልዩ እንደሚያደርገው ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ፡፡
ዩኒየኑ ጤፍ በብዛት በሚመረትባቸው ቢቸናና ደጀን አካባቢዎች ላይ ምርቱን ሰብስቦ በአብዛኛው ሽያጩን የሚያከናውነው ለሸማች ዩኒየኖች፣ ለሸማች መሠረታዊ ማህበራትና ለዩኒቨርሲቲዎች በመሆኑ ከነጋዴዎች ጋር አይገናኝም። ይህም ዩኒየኑን ከሌሎች ተመሳሳይ ዩኒየኖች ልዩ እንደሚያደርገው ይጠቅሳሉ፡፡
ለሌሎች ዩኒየኖች በትልቅ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል ተሞክሮ ባይኖረውም ጊዮን ሁለገብ የገበሬ ህብረት ስራ ዩኒየን ከመሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት ምርት ተቀብሎ በመሸጥና የውስጥ ካፒታል አቅሙን በእነዚሁ ህብረት ሥራ ማህበራትና በራሱ አቅም ለማጠናከር እየሰራ ይገኛል፡፡
ይህ አልሟላ ሲልም ልክ ሌሎች ዩኒየኖች እንደሚያደርጉት ሁሉ የባንክ ብድሮችን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከዓባይ ባንክና ከገንዘብ ብድርና ቁጠባ ዩኒየኖች ወስዶ ይጠቀማል፡፡ካፒታሉን በማሳደግና አባላትንም ተጠቃሚ በማድረግ በተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኝ ዩኒየን ለመሆንም በቅቷል፡፡
ዩኒየኑ በራሱ አቅም ኢንዱስትሪ በዋናነት ፋብሪካ ለማቋቋም ካለፈው ዓመት ጀምሮ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ የነበረ ቢሆንም በሀገሪቱ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሊያሳካው አልቻለም። ሆኖም በዚህ ዓመት ሁኔታዎች የሚመቻቹ ከሆነ የአዋጭነት ጥናት በማጥናትና በጀት በመያዝ ስራውን ለማከናወን ተዘጋጅቷል፡፡
በዚሁ መሠረት በጎጃም ቢቸና አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ የሚመረተውን የጤፍ ምርት ወደ ዱቄት በመቀየርና እሴት በመጨመር ለተጠቃሚው ለማቅረብ አስቧል፡፡ምርቱ በዚሁ መንገድ ለተጠቃሚው የሚቀርብ ከሆነም ለዩኒየኑ ተጨማሪ ገቢ ስለሚያስገኝ በአካባቢ ላይ የዱቄት ፋብሪካ ለማቋቋም አቅዷል፡፡
በምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ከማቅረብ አኳያ ዩኒየኑ በተለይ ለእንጂባራ ዩኒቨርሲቲ ጤፍ በዱቄት መልክ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡በአዲስ አበባ በተዘጋጁ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች ላይም ጤፍን አበጥሮ፣ ፈጭቶና አሽጎ በተለያዩ መጠኖች ለገበያ እንዲደርስ የማስተዋወቅ ስራ ሰርቷል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ ወደ ሀገሪቱ ከገባ በኋላ ከ30 ሺ ኩንታል በላይ የሚሆን ጤፍ ለሸማች ማህበራት በመሸጥ ሸማች ማህበራቱ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ በማድረግ ረገድ ዩኒየኑ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡በዋናነትም ለአዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ደቡብና ሰሜን ወሎ፣ጎንደርና ምዕራብ ጎጃም ላሉ ሸማች ማህበራት የጤፍ ሽያጭ አከናውኗል፡፡79 ኩንታል የሚሆን ስንዴም በኮቪድ ምክንያት ድጋፍ ላጡ የደጀንና ምስራቅ ጎጃም ዞን ነዋሪዎች አቅርቧል፡፡
በዚህም በተለይ የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠርና ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በማድረግና ምርቱ ለሸማቹ እንዲደርስ በማስቻል የአምራቹንም ሆነ የተጠቃሚው ጥቅም እንዲከበር ሰርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከምርት አቅርቦት አኳያ ተመሳሳይ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በተለይ ወቅቱ ሰብል የሚሰበሰብበት በመሆኑ ከቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት በኋላ የሰብል ግዢውን ለማከናወን አቅዷል፡፡
ዩኒየኑ አሁን ካለበት ደረጃ በበለጠ የመስራት ፍላጎት ያለው ቢሆንም አሁን ያለው የካፒታል መጠን ግን ለመስራት ያቀዳቸውን ስራ ለማከናወን በቂ አይደለም ። የውስጥ ካፒታሉን ለማሳደግና ከተለያዩ ባንኮች ብድር ወስዶ ለመስራትም ችግር ገጥሞታል። ለዚህም የውስጥ ካፒታል አቅሙን ለማሳደግ የአባላቶቹን ቁጥር ማሳደግ ላይ አጠናክሮ ይሰራል፡፡ከውጪም ብድሮችን እያፈላለገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በሌላ በኩል ከመሠረተ ልማት ጋር በተያያዘም በተለይ የማዳበሪያ ስራ ሲሰራ የመጋዘን ግንባታ ወሳኝ ቢሆንም ዩኒየኑ ግን በቂ የሚባል መጋዘን የለውም፡፡ 50 ሺ ኩንታል የመያዝ አቅም ያለው መጋዘን ደጀን አካባቢ ለማሰራት ፈልጎ የነበረ ቢሆንም የፋይናነስ እጥረት አጋጥሞታል፡፡
በመሆኑም ዋጋን መጋራትና መደገፍ የሚችል መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ቢገኝ በረጅም ጊዜ ብድር መጋዘኑን እንዲገነባ በማድረግ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል፡፡ይህም አማራጭ የማይሳካ ከሆነ ዩኒየኑ ግዜ ወስዶም ቢሆን በራሱ አቅም መጋዘኑን ለመገንባት ይጥራል፡፡
በአቅም ግንባታ በኩልም ዩኒየኑ ክፍተቶች ያሉበት ሲሆን እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት የሚሰሩ ድርጅቶች ካሉ አቅምና ክህሎትን የማሳደግ ስራዎችን ሰርተው ችግሩን መፍታት ይችላሉ፡፡ዩኒየኑ የካፒታል አቅሙን ለመገንባት ከሌሎች ዩኒየኖች ጋር የልምድ ለውውጥ እያደረገ ይገኛል፡፡
በቀጣይም ዩኒየኑ በአካባቢው የሚመረቱ ቦሎቄና ሰሊጥን የመሰሉ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጪ ሀገር በመላክ በውጪ ገበያ በስፋት የመግባት እቅዶች አሉት፡፡ የተጀመሩ የሜካናይዜሽን ስራዎችንም በስፋት አጠናክሮ የመስራት ውጥን ይዟል፡፡ ነባር የሰብል ግዢና ሽያጭ ስራዎችን፣ የግብዓት አቅርቦትና ስርጭትን፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን የማቅረብ እና የዘር ብዜት ስራዎችንም አጠናክሮ የማስቀጠል እቅድ ይዟል፡፡
‹‹እስካሁን ባለው ሂደት ጊዮን ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ውጤታማ ነው›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ በተለይ ታቅደው የነበሩ ስራዎች ሙሉ በሙሉ መፈፀማቸውና አንዳንዶቹም ከታቀደው እቅድ በላይ መሰራታቸው የውጤቱ አንዱ ማሳያ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡በቀጣይም ከዚህ በተሻለ መልኩ እንሰራለን ብለው ስለሚያስቡ እስካሁን ባለው ግምገማ ዩኒየኑ ውጤታማ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡
ከፍላጎት በመነሳት በሰባት ወረዳዎች ላይ የግብርና ግብአቶችን ሙሉ በሙሉ ማቅረብ መቻሉም የዚሁ ውጤት ማሳያ መሆኑንም የሚጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው ላይ የሚመረተውን ምርት የተሻለ ገበያ አፈላልጎ በመሸጥ በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየቱም የውጤቱ ሌላኛው ማሳያ ነው ይላሉ፡፡
በተለይ ዩኒየኑ እስከ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ሰብል ሲያቀርብ የነበረ በመሆኑ ውጤታማነቱን የሚያስመሰክር ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡በተመሳሳይ በዘር ብዜት ላይ በአካባቢው የተለመደውን ምርጥ ዘር እዛው በማባዛትና ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት ጥሩ ስራዎችን መስራቱንም ይጠቁማሉ፡፡
በተመሳሳይ ሌሎች የገበሬ ህብረት ስራ ዩኒየኖችም የአባል መሰረታዊ ማህበራትን ፍላጎት በእቅዳቸው ውስጥ ማካተት ለውጤታማነታቸው ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለውና ይህን ፍላጎት አካተው ሊሰሩ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡በተለይ ደግሞ አባል አርሶ አደሩና አባል መሠረታዊ ማህበሩ ላይ ምን አይነት ችግሮች እንዳሉ በመለየትና ፍላጎታቸውን በመረዳት ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ ሊሰሩ እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡
የጊዮን ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ዩኒየን በተለይ የአርሶ አደሩን ፍላጎት በመለየትና በእቅድ ውስጥ በማካተት ብሎም የግብርና ግብአቶች ሳይጓደሉ በማቅረብና ምርት ካመረተም በኋላ ከምርቱ የተሻለ ገበያ እንዲያገኙ ገበያ በማፈላለግ ረገድ እያከናወነ ያለው ስራ ለሌሎች መሰል ህብረት ስራ ዩኒየኖች ጥሩ ተሞክሮ ሊሆን ስለሚችል ወደራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ወስደው ቢሰሩበት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ እንላለን፡፡ሰላም!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10/2013