ኃይለማርያም ወንድሙ
በልጅነታችን ከአቻዎቻችን ጋር ሌባና ፖሊስ እንጫወት ነበር፡፡ ኩኩሉ አልነጋም የሚባል ጨዋታም እንደነበር አልዘነጋውም፡፡ የሁለቱም ጨዋታዎች በመደበቅ ተጀምሮ በመያዝ የሚያከትም ነው፡፡ አሁን አሁን ተመሳሳይ ጨዋታ የሚመስሉ ነገሮች በትልልቅ ሰዎች ሲተገበሩ በዋና ዋና ከተሞች ይታያሉ፡፡
በእርግጥ እየተዝናኑ መሥራት ለስኬት ያበቃል ከድካም ያርቃል ሲባል እሰማለሁ፡፡ ፈፃሚው ማን ነው አስፈፃሚውስ? ብላችሁ እንዳትጠይቁኝ ብቻ፡፡ ጨዋታም የሚመስሉ ሥራም የሚመስሉት ስመለከት አንዳንዴ እነዚህ ጎልማሶች ምን እያረጉ ስል ራሴን እጠይቃለሁ። ይህ ሁኔታ በደንብ አስከባሪዎች በእጅጉ ይተገበራል፡፡
ደንብ አስከባሪዎች እየተንጎማለሉ የጎዳና ንግዱ ሲጧጧፍ ደንብ አስከባሪዎቹና የጎዳና ነጋዴዎቹ ድብብቆሽና አባሮሽ እየተጫወቱ ነው እንዴ? እላለሁ ለራሴ፡፡
የአደባባዮቹን ዙሪያና የመንገዶቹን ዳርቻ የመንገድ ላይ ነጋዴዎች ተቆጣጥረውታል፡፡ ለስንት ዓመት ይዩዙታል? ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ ሰዎቹን ከኢንቬስተር ተርታ መደባችሁልኝ ማለት ነው፡፡ ለዓመታት ሳይሆን ለሽርፍራፊ ሰዓት ነው የሚይዙት፡፡ ታሪክ ተቀይሮ ያሳየን እንጂ በህገ ወጥ ንግዱ የተሰማሩት ወገኖች ሠርቼ ልግባ የሚል ዓላማ ያላቸው ነጭ ድሆች ናቸው፡፡
አንዳንዴ የመንገድ ዳር ነጋዴ ምን ግዴ? ከሚሉት ወገን ብሆንም፤ የተወሰነ ሰዓት ሊነግዱ የሚችሉበት ሁኔታ ለእግረኛም ማለፊያ መንገድ የሚሰጡበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም ይመስለኛል፡፡ እነዚህ የመደበኛው ንግድ እርሾዎች ተደርገው መወሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ እዚህ ተለማምደው ወደ መደበኛው ንግድ ሊገቡ ይችላሉ፤ የሆነውን ያህል በመንግስት ዘንድ ግንዛቤው ያለም ይመስለኛል፡፡
የመንገድ ዳር ነጋዴዎች ዋና ዋና የአደባባይ ቦታዎችን ይመርጣሉ፣ ደንብ አስከባሪዎች ደግሞ ይመጣሉ፡፡ እናንተ በቀን ሦስቴ ስትበሉ እነሱ እናቴ በቀን ስድስቴ ሊበሉ ይችላሉ፤ ደንቦቹ፡፡
እነሱ ባላቸው የሥራ ሰዓት በ’ታታሪነት’ በቀን ሁለት ሥራ ይሠራሉ፡፡ ለተቀጠሩበት ደንብ አስከባሪነት እየሠሩ እግረ መንገዳቸውን በደንብ
ሰባሪነትም ያሰራሉ ተብለው ይጠረጠራሉ በነጋዴዎችና በሸማቾች ማለቴ ነው ተረዱልኝ፡፡ ቢጠረጠሩ ምን ክፋት አለው? ዋናው በፖሊስ አለመጠርጠራቸው ነው ልበል፡፡
ስለ መንገድ ዳር ነጋዴዎች ስናወራ ነጋዴዎቹ እግረኞች ብቻ አለመሆናቸውን ማሳሰብ እፈልጋለሁ። ስማቸው ስለማይገልፀው እንጂ ተሽከርካሪያቸውን መንገድ ዳር አቁመው አልባሳት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ልዩ ልዩ ቁሳቁስ የሚሸጡም ነጋዴዎች አሉ፡፡ደንብ አስከባሪዎች ግን እነዚህን ለማንሳት ባይችሉም ለማስነሳት ሲሞክሩ ግን አላየሁም፤ ለአለቆቻቸው ሪፖርት አቅርበዋል ሲባልም አልሰማሁም፡፡
የበዓል ሰሞን ኢንቨስተር ሠፈር የተመደቡት ነጋዴዎች በጭነት መኪናቸው ዕቃቸውን ይዘው በደራ የገበያ ሥፍራ ከች ይላሉ፡፡ ኢንቬስተሮችም የመንገድ ዳር ነጋዴዎች የሚሆኑበት ክፉ አጋጣሚ አለ፤ ቀን ሲጥል አይታወቅም ነው የሚሉት? ዶሮ፣ ዕንቁላል፣ ወተትና የወተት ተዋፅዖዎች በመኪናቸው ጭነው ሲሸጡ ያያሉ፤ በአንድ በኩል ኑሮ ውድነቱ ናላውን ላናረው ዜጋ አንድ እፎይታ ነው፡፡ ዋጋው ተወደደብኝ ብሎ አይሳቀቅም፡፡
ደንብ አስከባሪዎች ከመንገድ ዳር ነጋዴዎች ማባረር የሚችሉትን ያባርራሉ፤ መያዝ የሚችሉትን ደግሞ ይይዛሉ፡፡ የሚይዙት የሚሸጠውን ቁስና ልብስ ሊሆን ይችላል፤ ባየኋዋቸው አካባቢዎች ያስተዋልኩት ማባረርና ቁሱንም ሆነ ልብሱን ይዞ መሄድ ብቻ ነው ስራቸው፡፡ ለወሰዱት ዕቃ ደረሰኝ ሲሠጡ አላየሁም፤ ስማቸው ደንብ አስከባሪ ቢሆንም፣ እዚያው ቆማችሁ ደንብ በማስከበር ስም ደንብ ሲሰብሩ ልታዩ ከቻላችሁ እንዳትገረሙና እንዳትራገሙ አደራ እላችኋለሁ፡፡
የመንገድ ዳር ነጋዴዎች በብዛት የሚታዩት ግን በመርካቶ፣ በአራዳ፣ በሜክሲኮ እና በመገናኛ አካባቢዎች ነው፡፡ እሁድ ደግሞ በመርካቶ አካባቢዎች የሰንበት ገበያ ተብሎ በሙሉ መንገዱ ተለቆ ሲሠሩ ይታያል፡፡ በዚህ ቀን ህገ ወጥ የመንገድ ዳር ነጋዴ ብሎ መጥራትም ትክክል አይደለም፤ ተፈቅዶላቸው ስለሚሠሩ፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ እያሰብኩ እያለ የመንገድ ዳር ንግድ እንቅስቃሴዎችን ሥርዓት ለማስያዝ እየተሠራ መሆኑን ሰማሁ፡፡ ይህ አይነቱ ንግድ አሁንም ቢሰፋ መልካም ነው፡፡
ለመንገድ ዳር ነጋዴዎች መበራከት ሁነኛ ሚና የሚጫወቱት ህጋዊዎቹ ነጋዴዎች ናቸው ይባላል። አልሸጥ ያለ በገፍ የመጣ ልብስ እንዲሸጥላቸው ይስማማሉ፤ ነጋዴው ትዕዛዙን ተቀብሎ መንገድ ዳር ቆሞ ልብሱን ቆልሎ “ ካመለጣችሁ አላየሁም አልሰማሁም ትላላችሁ፤ አጋጣሚው እያያችሁ አይለፋችሁ በሚገርም ዋጋ” ብሎ ማሻሻጥ ብቻ ነው። ቅር ያላቸው ቀን ደግሞ ባለሱቆቹ ዞረው ደግሞ እኛ ግብር እየገበርን የማይገብረው ይሸጣል ብለው ቅሬታ ያሰማሉ፡፡
ስለ መንገድ ዳር ንግድ ስናወራ መቼም ነጋዴው ሁሉ እግረኛ ብቻ ነው ብለው የሚገምቱ አይጠፉም፡፡ ከላይ የጠቀስነው ረቂቅ ሕጉ ሲወጣ የሚለው ይኖራል። እኔ ግን የመንገድ ዳር ነጋዴ ስል ተለጣፊውን (ተለጣፊ ሱቅ ያላቸው)፣ ተነጣፊውን (አንጥፈው የሚሸጡትን) በጋሪም የሚገፉትም ሆነ በአሽከርካሪ ጭነው የሚሸጡትን (በዓል ሲሆን ደግሞ ይበዛሉ) ደረቱ ላይ ይዞ የሚሸጠውን እንዲሁም በመርካቶ አጠራር ‘ሱቅ በደረቴውን’ የሚባለውን ማለቴ ነው፤ በእጁ ይዞ በደረቱ ደግፎ የሚነግደውን መሆኑ ይታወቅልኝ ፡፡
ከመንገድ ዳር ንግድ እንቅስቃሴዎች ጋር በተገናኘ፣ የትራፊክ አስተዳደር ፍሰትን ለማጣጣምና የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ያለመ፣ የደረጃ አስተዳደር ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡ የመንገድ ላይ ንግድ ደረጃ አስተዳደር ረቂቅ ሕግ በዋናነት፣ የመንገድ ላይ ንግድና የአስተዳደሩ ሥርዓት ምን መምሰል እንዳለበት የሚያስረዳ ነው። ለመንገድ ላይ ንግድ ቦታዎችና ነጋዴዎቹ ሊተገብሩት ስለሚገባ አሠራር ያካተተ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የደረጃ አስተዳደር ረቂቅ ሕጉ ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የመንገድ ላይ ንግድ በትራፊክ ፍሰትና በእግረኞች ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ችግር እያጋጠመ በመሆኑ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡ የደረጃዎች አስተዳደር ረቂቅ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የተገለፀ ሲሆን የመንገድ ላይ ነጋዴዎችን ሕጋዊ ማድረግ፣ የትራፊክ ፍሰት እንዲሻሻልና ለከተማ ውበት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
በዋናነት የመንገድ ላይ የንግድ እንቅስቃሴ ረቂቅ አስተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ጥያቄ መሠረት ይዘጋጅ እንጂ፣ የደረጃ አስተዳደር ረቂቁ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያገለግል መሆን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የደረጃ አስተዳደር ረቂቁ ነጋዴዎችን፣ የትራንስፖርት ዘርፉን፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች አካላት የሚተገብሩት እንደሆነ ይጠበቃል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የደረጃዎች ዝግጅት ባለሙያ ሰሞኑን የሰጡት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የደረጃ አስተዳደር ረቂቁ በዋናነት የእግረኞችን ደኅንነት ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎችን ሕጋዊ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ ጥቅም አለው ፡፡ የደረጃ አስተዳደር ረቂቁ የመንገድ ንግድ ቦታ አመራረጥ በዋነኝነት የትራፊክ መጨናነቅ ባለበት፣ በመስቀለኛ እንዲሁም በመንገዶች ላይ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳይኖር የሚገድብ ነው፡፡
ካለው ችግር አንጻር ህጉን ቶሎ ወደ ስራ ማስገባት ይገባል፡፡ ህጉ የጎዳና ንግድ እያስከተለ ያለውን ችግር እንደሚፈታ ከተመነበት ትግበራውን በጉጉት እንጠበቃለን፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10/2013