በአውሮፓና አፍሪካ መካከል ጥልቅ የኢኮኖሚና ባህል ግንኙነት መኖሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ ግንኙነት ውስጥ ግን የጀርመን የንግድ ግንኙነት ዝቅተኛ ሆኖ መቆየቱን መረጃዎቹ ጠቅሰው፣ በሂደት ግን ገጽታው እየተቀየረ ነው ይላሉ፡፡
የጀርመንና አፍሪካ ታሪካዊ ግንኙነት በአሁኑ ወቅት በሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም እና የንግድ ግንኙነት ሳቢያ እየሰፋ ይገኛል፡፡ በርካታ የጀርመን ኩባንያዎችም አፍሪካን መዳረሻቸው እያረጉ ነው፡፡ በኬንያ እአአ በ2016 የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ስራውን የጀመረው ቮልስ ዋገን ኩባንያ እየተስፋፋ ነው፡፡
መሰረቱ የጀርመን የሆነው ባይር ኩባንያም እንዲሁ ባይር መካከለኛው አፍሪካ በሚል እእአ በ2015 በናይጄሪያ ሌጎስ ቅርንጫፉን ከፍቶ እየሰራ ነው፡፡ ዱቼ ቡንደስ ባንክ የተሰኘው የጀርመን ባንክም እንዲሁ በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፉን ለመክፈት ከደቡብ አፍሪካ ሪዘርቭ ባንክ ጋር ሲያደርግ የቆየውን ውይይት እያጠናቀቀ ሲሆን፤ የጀርመኑ አየር መንገድ ሉፍታንዛም ወደ አህጉሪቱ ይበራል፡፡
ጀርመን ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ ዋናዋ የንግድ ሸሪኳ ስትሆን ይህም ጀርመን በቻይና ካላት የንግድ መጠን ሁለተኛው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንደ የጀርመን የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ያሉ ድርጅቶች አፍሪካን የኢንቨስትመንት መዳረሻቸው አድርገው እየተመለከቷት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በአፍሪካ ኢኮኖሚያቸው እያደገ ከሚገኝ ሀገሮች ጋር አብረው ለመስራት ግንኙነት እያደሱ እና እየመሰረቱ ናቸው፡፡
ጀርመን በአፍሪካ ያላት ንግድ መጠን ብዛት ከቻይናና ህንድ ቀጥሎ በርቀት ትከተላለች፡፡ ጀርመን ከአፍሪካ ጋር የምታደርገው የንግድ ግንኙነት መጠን 60 ቢሊየን ዶላር ሲሆን፤ በአንጻሩ ቻይና 200 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ግንኙነት አላት፡፡
ጀርመን በዓለም ሦስተኛዋ ላኪ ሀገር በመባል ትታወቃለች፡፡ በተለይ ደግሞ በቴክኖሎጂና ፈጠራ ውጤቶች በኢንዱስትሪ የወጪ ንግዷ ትታወቃለች፡፡ አፍሪካ በበኩሏ የዓለም ፈጣን እድገት የሚመዘገብባት ሆናለች፡፡ በተለይ ለኢንቨስትመንትና ለመሰረተ ልማት ሀይል ማመንጫ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ዋና ስፍራ ተብላለች፡፡ ጀርመንና አፍሪካ አአአ በ2017 አትራፊ የሆነ ግንኙነት እንደሚያደርጉም ይጠበቅ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ከምታደርግባቸው ሀገሮች መካከል ጀርመን ትጠቀሳለች፡፡ የጀርመኑ ጂአይዜድ (የቀድሞ ጂቲዜድ) በኢትዮጵያ በሰው ሀብት ልማት ፣በግብርና በመሰረተ ልማት ወዘተ ዘርፎች የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ ጀርመን የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች መዳረሻ ከሚባሉት አንዷ መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ዋናዋ የኢትዮጵያ ቡና ገዥ ናት፡፡ በጀርመንና ኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ መጠን እያደገ እንደሚገኝም ነው በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ መረጃ የሚጠቁመው፡፡
እአአ በ2014 ብቻ ጀርመን ወደ ኢትዮጵያ የላከቻቸው ምርቶች ወደ 38 በመቶ በመጨመር 238 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዩሮ ደርሷል፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ እየተካሂደ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ትልቁን ሚና መጫወቱን ነው መረጃው ያመለከተው፡፡ ኢንቨስትመንቱ በጀርመን በተመረቱ ማሽኖች ጭምር የሚካሄድ መሆኑን በመጥቀስ ፣ይህም በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ላለው እድገት የተጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ጀርመን ከኢትዮጵያ ያስገባቻቸው ምርቶችም እንዲሁ በ14 ነጥብ 4 በመቶ ጨምረው ወደ 185 ሚሊዮን ዩሮ ከፍ ማለቱን መረጃው ያመለክታል፡፡ ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ የምታስገባቸው ምርቶች በአብዛኛው ቡናና ጨርቃ ጨርቅ ናቸው፡፡
ይህን ግንኙነት በጀርመንና በኢትዮጵያ መሪዎች ጉብኝት ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራም ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት እአአ በጥቅምት ወር 2016 የጀርመን ቻንስለር አንጌላ ሜርከል ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡ በወቅቱም ከወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡ ይህም የሁለቱ ሀገሮች አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ መጀመሪያ ተብሏል፡፡
በወቅቱም አቶ ሀይለማርያም ጀርመንና ኢትዮጵያ በተለይ አርሶ አደሮችን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ባደረገ በሰው ሀብት በተለይ በውሃው መስክ፣ በምህንድስናና በትምህርት ላይ እጅግ በጣም ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው፣ የመርከል ጉብኝት የሁለቱን አገር ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚያደርሰው ተናግረዋል፡፡ የጀርመን የንግድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸው ተሳትፎ በአውሮፓና በእስያ ሀገሮች ካላቸው ተሳትፎ አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ በስፋት እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበውም ነበር፡፡
ሜርከል በበኩላቸው እንዳሉት፤ሁለቱ ሀገሮች በሰው ሀብት ልማት ፣ በግብርናና ገጠር ልማት ላይ በርካታ ተግባሮች አከናውናዋል፡፡ ኢትዮጵያ በድህነት ቅነሳ ስራዎች የዜጎቿን ህይወት እያሻሻለች ስትሆን፣ በርካታ ዜጎች ከድህነት ተላቀዋል፡፡ የወጣቶችን ፍላጎት ለማሟላት ግን በትኩረት መስራት እንዳለበት እና ሀገራቸው ከዚህ አንጻር ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል፡፡
በወቅቱ ሀገሪቱ በተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ ነበረች፡፡ ሜርከል ችግሩን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር የማድረግ አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹ህዝቡ የተለያዩ የፓለቲካ አመለካከቶችን እንዲያራምድ መፍቀድ ጥሩ ስለመሆኑ አምናለሁ፤ ከውይይት ጥሩ መፍትሔ እንደሚመጣ የዴሞክራሲ ተሞክሮ ያስገነዝባል›› ሲሉ መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን በለውጥ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ሜርኬል ያኔ ፍላጎታቸው የነበረው የተለያዩ የፓለቲካ አመለካከቶች በኢትዮጵያ የመንጸባረቅ ጉዳይ እውን ሆነዋል፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ኢትዮጵያን እየጎበኙ የሚገኙትም ሀገሪቱ በእዚህ የለውጥ አየር ውስጥ ሆና ነው፡፡
ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅትም እእአ በ2014 ሀገሪቱን ጎብኝተዋል፡፡፡ ‹‹ሀገሪቱን ቀደም ሲል አውቃታለሁ፤የአሁኑ ጉብኝት ግን በተለየ የፓለቲካ ምህዳር ውስጥ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት በዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ እንደገለጹት፤ ጉብኝታቸው የሀገራቸው መንግሥት ኢትዮጵያ እያካሄደች የምትገኘውን ሪፎርም በሚደግፍበት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በጉብኝታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፤ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዲሁም ከሲቪል ሶሳይቲ አመራሮች ጋር እንደሚመክሩ ጠቅሰው በዚህም ሀገሪቱ ተግባራዊ እያደረገች ስለምትገኘው ሪፎርም አጠቃላይ ሁኔታ የሚመለከታቸውን አካላት እንደሚያገኙ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሰረት ትናንት ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ከጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር መክረዋል።
በኢትዮጵያ የመጣውን አዲስ አመራር ተከትሎ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ፈጣን አዎንታዊ ምላሽ የሰጡትም ይህን መነሻ በማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጋር ተያይዞ ለመጣው ለውጥ አድናቆትን መግለጽ ብቻ በቂ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ እንደ አውሮፓዊም እንደ ጀርመናዊም ከዚህ ለውጥ ጋር አብሮ መጓዝ ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለዚህም ነው ጉብኝቴ በትክክለኛ ወቅት ላይ የተደረገ ነው ያልኩት» ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩልም በሃገሪቱ የተደረገውን የዴሞክራሲ ሪፎርም ብቻ ሳይሆን ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት እየተደረገ ያለው ጥረት በጣም የሚደነቅ መሆኑንና ይህ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጥሩ ምሳሌና አርዓያ መሆን እንደሚችል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
አገሪቱ በለውጥ ሂደት ላይ አንደመሆኗና ለውጥ ደግሞ በራሱ ይዟቸው የሚመጡ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች መኖራቸውን በመናገር ይህንን ጊዜያዊ ችግር ለማለፈም ጀርመን ድጋፏን አንደምታደርግ ያረጋገጡበት ጉብኝትም ነበር፡፡
በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የዴሞክራሲያዊ ሰርዓት ግንባታና የሪፎርም ስራዎች አውሮፓውያን ስለ አፍሪካ ያላቸውን የተሳሳተ ምስል ለማረም ማስቻሉን በመናገር እነዚህ ስራዎች በተለይም የጀርመንና የኢትዮጵያን ወዳጅነት እንዲሁም ዘርፈ ብዙ አጋርነት ተጠናክሮ ወደ ሪፎርም አጋርነት መሸጋገር እንደሚገባው ማመናቸወንም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ለውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሰጠው ትኩረት ያስቀመጣቸው ማእቀፎች እንዲሁም እየሰራ ያለው የማሻሻያ ሥራ የጀርመን ካምፓኒዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ አነሳስቷል፤ ይህም የሃገራቱን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያሳድግ ይሆናል ይላሉ፡
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያና የጀርመን ግንኙነት ረጅም ዘመን ያስቆጠረና ታሪካዊ መሆኑን አስታውሰው፤ በተለይም የጀርመኑ ፕሬዚዳንት የሚያደርጉት የአሁኑ ጉብኝት ሀገሪቷ በሪፎርም ሂደት ውስጥ ባለችበት ወቅት በመሆኑ ወቅታዊና ወሳኝ ነው ይላሉ፡፡ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በአዲስ ቅርፅ የሚያስኬድና የበለጠ የሚያሳድገው ነው ሲሉም ይጠቁማሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም ከጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ጋር ባደረጉት ምክክር እንዳሉት ለጀርመን መንግሥት የቆየና ቀጣይነት ላለው የቴክኒክና የሙያ ዘርፍ ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለተመዘገበው ስኬት ዋና ዋና መሰረቶች ግለሰቦች፣ ሀሳቦች እና ተቋማት መሆናቸውን አካፍለዋል።
ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በበኩላቸው የኢትዮ-ጀርመን ግንኙነት ለውጥን ወደ መደገፍ ትብብር ከፍ ማለቱን እና እነዚህን ግንኙነቶችን ለማጠናከር እንደሚሰሩም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠውላቸዋል።
ሁለቱም አገራት የቆየ ወዳጅነታቸውን ማጠናከራቸው ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካለቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረትና በፖለቲካውም መስክ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት እየሄደችበት ያለውን የለውጥ ጉዞ የሚያቀጣጥል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011
ሃይሉ ሣህለድንግል