ወርቁ ማሩ
በአሁኑ ጊዜ አገሪቷ ወደዚህ ቀውስ እንድትገባ ያደረገው የህወሓት ጁንታ ቡድን ገና ከበረሃ ጀምሮ ባደራጀው የኢኮኖሚ መዋቅሩ አማካኝነት አብዛኛውን የሃገሪቷን ሃብት በቁጥጥሩ ስር በማድረግ በህገወጥ መንገድ የከበረ ድርጅት ነው። በተለይ ኤፈርት በሚል ከህገመንግስቱ ባፈነገጠ መንገድ በፈጠረው ድርጅት አማካኝነት ሁሉንም የኢኮኖሚ ዘርፎች በቁጥጥሩ ስር በማድረግና ሌሎች መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከገበያ እንዲወጡ በማድረግ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ተቆጣጥሮ እንደቆየ ምሁራን ይገልፃሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሃገሪቷ የተከሰተውን ህዝባዊ ለውጥ ተከትሎ ገና ለገና የለመደው ህገወጥ ዘረፋና ምዝበራ ሊበላሽ ይችላል በሚል ስጋት ለውጡን ለማደናቀፍ ትልቅ ጥረት አድርጓል። በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ጊዜያት ከ113 የሚሆኑ ግጭቶች ጀርባ በመሆን ትርምሱን ሲመራና ሲያስተባብር እንደቆየ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ አሳውቀው እንደነበር ይታወሳል። ቡድኑ ለሚያከናውናቸው የሽብር ተግባራት ደግሞ እነዚህ ለዘመናት በህገወጥ መንገድ ራሳቸውን ያሳበጡ ድርጅቶች ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ እንደነበሩ ይታመናል። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም መንግስት 34 የኤፈርት ድርጅቶችን አግዷል። እኛም ቡድኑ በሃገሪቱ በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ ሲያደርግ የነበረው ህገወጥ እንቅስቃሴና ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስመልክቶ የህግ ባለሙያ አነጋግረናል። እንግዳችን አቶ ውብሸት ሙላቱ ይባላሉ። ጠበቃና የህግ ባለሙያ ሲሆኑ በፐብሊክ አድምንስትሬሽንም የሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። አዲስ ዘመን ላቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡– ጁንታው ከ1977 ዓ.ም የተከሰተው ድርቅ የኢኮኖሚ አቅሙን ለመገንባት ዋናው አጋጣሚ እንደነበር ይነገራል፤ ከዛ ጊዜ ጀምሮ የራሱን ኢኮኖሚ እንደዘረጋ ብዙዎች ይስማማሉ፤ ይህንን እንዴት ያዩታል? ሁኔታው ከህግ አንጻርስ እንዴት ይታያል ?
አቶ ውብሸት፡– የዚህ ቡድን ትልቁ የጭካኔውና የስግብግብነቱ ትልቁ ማሳያ በድርቅ ከተጎዱና በሞት አፋፍ ላይ ከነበሩ ሰዎች ከመንጋጋ ላይ ፈልቅቆ ምግብ መውሰዱ ነው። ይህ ቡድን ቅንጣት ታክል ሰብአዊነት የሌለው ለመሆኑ ትልቁ መገለጫ ይህ ነው። በ1977 ዓ.ም የተከሰተውም ይኸው ነው። ያ ብቻ አይደለም፣ በሴፍቲኔትና በተለያዩ ምክንያቶች ለእርዳታ የሚሰጡትን ሁሉ ያለ ይሉኝታ ነበር የሚወስደው።
በተለያዩ አገራት ፖለቲካውንም ኢኮኖሚውንም ጠቅልለው የያዙ ሃይሎች ተፈጥረው ያውቃሉ። የዚህኛው ግን ለከት የሌለው ነው። ሽፍታም እንዲህ አይነት የዘቀጠ ሞራል የለውም። ሽፍታ ከደሃ አይሰርቅም፣ አይቀማም። አቅመ ደካሞችን አያንገላታም። ማፍያም ትልቅ ሞራል አለው። ከአቅመ ደካሞች እና ድሆች አይቀማም።
“ግርሃም ሃንኩክ ሎርድስ ኦፍ ፖቨርቲ” የሚል አንድ ጽሁፍ ለንባብ አቅርበው ነበር። በዚህ ጽሁፍ የኢኮኖሚ አቅም የገነቡ ተቋማት አሉ፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች። ጌቶቹ ዓለም አቀፍ ተቋማት ናቸው። በኛ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ግን እነዚህ ግን ጌታ የሆኑት ከድሆች እየቀሙና እየዘረፉ ነው። እናም እነዚህ ቡድኖች የኢኮኖሚ ግዛት የመሰረቱት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው።
ከዚያ ስልጣን ላይ ከመጡ በኋላ በፖለቲካውም መስክ አግላይ ብቻ ሳይሆን ሌላውንና ከሱ ውጭ የሆነው የሚያስወግድ፤ በኢኮኖሚውም መስክ በዝባዥ ነው የሆነው። ይህ ደግሞ እየጣማቸው በከፍተኛ ሃይል ቀጠሉበት። እና አሁን ላይ በኢትዮጵያ ትልቁ ኢንቨስተር የህወሓት ጁንታ ነው፤ ከፌደራል መንግስትም በላይ የኢኮኖሚ አቅም ፈጥሯል። የዚህ ቡድን አባላት የማይጠረቃ ሆድ ነው ያላቸው።
አዲስ ዘመን፡– ቡድኑ መንግስት ከሆነ በኋላም በጀመረው መልኩ በመቀጠል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መቆጣጠር የሚያስችል አቅም ገንብቷል፤ በዚህም የሄደበት መንገድ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ አደጋ ውስጥ መክተቱም ይነገራል፤ ይሄን እንደ ዜጋ እንዴት ያዩታል፤ ህግስ እንዴት ያየዋል?
አቶ ውብሸት፡– አንድ ቡድን በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው የበላይ ከሆነ እና በዚያ ላይ ያለው አስተሳሰብ ከላይ እንዳየነው አግላይ ከሆነ አገርን በሙሉ አደጋ ላይ ነው የሚጥለው። ይህ ሲሆን የፈለገው እንዲያደርግ እድል ይሰጠዋል። አገር ማፍረስንም ጨምሮ ማለት ነው። አገርን ማፍረስ ከፈለገ ያፈርሳል፤ መግደልም ከፈለገ ይገድላል። ስለዚህ አደጋውም በጣም የከፋ ይሆናል። የሆነው ይህ ነው። አሁን እየተወሰደ ያለው የህግ ማስከበር እርምጃም ይህንን ለመቀልበስ ነው።
ኪራይ ሰብሳቢነትም የዚህ ቡድን አንዱ መገለጫ ነበር። ወደ ኢኮኖሚውና ወደዘርፉ የሚቀላቀሉ አካላት ሲኖሩ ለሆኑ የነሱ ሰዎች ይነገራቸውና እንዲዘጋጁ ይደረጋል። ከዚያ ዝግጅት ሲጨርሱ ህጉ ይወጣል፤ ለምሳሌ ከውጭ ያለቀረጥ ተሽከርካሪ ማስገባትና የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚሰራ ድርጅት ፈቃድ ለመስጠት ለሰዎቻቸው ሁሉ ይነገርና ህጉ እንዲወጣ ይደረጋል። ከዚያ በኋላ የቀን ገደብ ተቀምጦ ፕሮፖዛል እንዲቀርብ ይደረጋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚሰጠው አጭር ጊዜ ደግሞ የሚፈለገውን ስራ ለመስራት የሚያስችል አይሆንም። በዚህ ጊዜ እነዚያ ሰዎች ቀድመው የሚፈለውን ነገር ከውጭ አዘዋል። እንዲህ አይነት ስራዎች ደግሞ በየዓመቱ ይቀያየራሉ። ለምሳሌ ዘንድሮ በሆቴል ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት ህግ ከወጣ በሚቀጥለው ዓመት ለማኑፋክቸሪንግ ሊሆን ይችላል። እንደዚህ አይነት ማበረታቻዎች ማን እንደሚወስድ ይታወቃል።
ለምሳሌ ከልማት ባንክ ገንዘብ ተበድረው ገንዘቡ ሲያልቅ ሁሉም ባንኮች ለልማት ባንክ 27 ከመቶ ብድር እንዲሰጡ ተደረገ። ለአግሮ ፕሮሰሲንግ፤ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ወዘተ እየተባለ እያንዳንዱ ብድር ባንኮች ከሚያበድሩት ወደልማት ባንክ እንዲዞር ተደረገ። ከልማት ባንክ ገንዘብ ሲያልቅ ከሌሎች ባንኮች እንዲዞር ተደርጎ ተዘረፈ።
ሰዎቹ ባዶ እጃቸውን ወደልማት ባንክ ይሄዳሉ። ከዚያ በሚሊየንና በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ይወስዳሉ። እዚሁ ቁጭ ብለው ገንዘባቸውን ይወስዳሉ። ከዚያ ገንዘቡ ስራ ላይ አይውልም፤ ስራው አይሰራም። አንድም እዚህ ግባ የሚል መሬት ላይ ኢንቨስት የተደረገ ነገር አታገኝም። ይህ እኮ መወዳደር አይደለም፣ መዝረፍ ነው።
በሌላ በኩል የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደግል ሲዞሩም ይህን ነበር የሚያሳየው። በደርግ ጊዜ የተወረሱ፣ ወይም ደርግ በራሱ የገነባቸው ሃብቶች ወደግል ሲዞሩ ተመሳሳይ ሸፍጥ ነው የተሰራው። ሰዎች ባዶ እጃቸውን ይመጡና ከዚያ ይህንን ለሚገዛ ሰው የባንክ ብድር ይመቻቻል ይላል። ከዚያ ባዶ እጃቸውን አይናቸውን በጨው ታጥበው ይሄዳሉ። የጨረታ አሸናፊ ይሆናሉ። ከዚያ የሆነ ባንክ እንዲከፍልላቸው ይደረጋል። ከሆነ ዓመት በኋላ የግላቸው ይሆናል። ከዜሮ የትልቅ ሆቴል እና ፋብሪካ ባለቤት፣ ከዜሮ ሚሊየነር ይሆናሉ ማለት ነው። ይህ ግለሰቦች ጭምር የሚጠቀሙበት ስልት ነው። ይህ ህወሓት እንደ ድርጅት ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን በድርጅት ስም እዚያ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች የሚሰሩት ሸፍጥ ነው።
መስፍን ኢንጂነሪንግ የተመሰረተው ከፓዊ በተዘረፈ ሃብት ነው። ደርግ ፓዌ ላይ የገነባው ትልቅ ፋብሪካ ነበር። ይህ ቡድን ኢትዮጵያን መቆጣጠር ሲጀምር እንዳለ ነቃቅሎ ሁሉንም ወደዚያ አጋዘው። ከዚያ በኋላ ደግሞ መስፍን ኢንጂነሪንግን ለማጠናከር እነማሩ ብረታ ብረት፣ አምቼ የመሳሰሉትንና አቅም የነበራቸውን ድርጅቶች አከሰመ።
ስለዚህ ይህ ውድድርን የመከልከል ብቻ ሳይሆን ሌላውን የማጥፋት፣ የማውደም እና የመዝረፍ አካሄድ ነበር። ከፈለገ ሌላውን ባለማወዳደር ጠቅላላ ያጠፋል፤ ካልሆነ ደግሞ በጉልበት ያጠፋል። በሚገርም ሁኔታ መወዳደር የሚችሉ በርካታ ድርጅቶች ነበሩ። ቻይና ህንድ ወዘተ እየሄዱ የሚነግዱ ግለሰቦችም ነበሩ። ከዚያ የራሳቸውን ሰዎች ኤልሲ አስከፍተው አብረዋቸው እንዲሄዱ ማድረግ ጀመሩ። አካሄዱም ከመነሻው ጀምሮ የአውሮፕላን ቲኬት አብሮ እንዲቆርጡ ያደርጋሉ፤ ነጋዴው የሚሄድበት ቦታ አብሮ እንዲሄድ፤ እሱ የሚያርፍበት ሆቴል እንዲያርፍ፣ እሱ የሚገዛውን እየተከተለ እንዲገዛ ያደርጋሉ። ከዚያ በኋላ እቃው ተጭኖ ሲመጣ ጉምሩክ ላይ የተቀናቃኙ ነጋዴ እንዲቆይ ይደረግና ያኛው እንዲወጣ ይደረጋል። ለዚህ የሚዘጋጁ በርካታ ወጥመዶች አሉ። ይህንን ብዙ ጊዜ ሰርተውበታል። በዚህ የተነሳ በርካታ የቻይና አከፋፋዮች ውል ስትዋዋል ጉምሩክ ላይ የምታውቀው ዘመድ አለህ ወይ እስከማለት ደርሰው ነበር። ከሌለህ ካንተ ጋር ውል ለመዋዋልም ፍላጎት አያሳዩም። ይህ ቡድን በዚህ መንገድና ከዚህም በከፋ ሁኔታ ነው ሲዘርፍ የነበረው። በአጠቃላይ በንግድ ህጉና በሸማቾች የንግድ ውድድር አይተዳደርም።
በሌላም በኩል በከፍተኛ ሁኔታ የንግድ ሰርዓቱ ውስጥ ገብተው ውጤታማ የነበሩትን የስታር ቢዝነስ ግሩፕ እና ሌሎች በርካታ የመከኑ የንግድ ድርጅቶችን ማንሳት ይቻላል። እነ አቢሲኒያ ባንክን ጭምር በርካታ የነሱ አካላት አክሲዮን እንዲገዙ አድርገው በነሱ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርገው ነበር። እዚያ ውስጥ የነበሩ ሰዎችንም የተለያዩ ምክንያት እየፈለጉ ስምንት እና ዘጠኝ ጊዜ አስረዋቸዋል። ሃያት ሪል ስቴትንም ማንሳት ይቻላል። እነዚህ አካላት በሁሉም የቢዝነስ ስራ ውስጥ ነው የተሰማሩት። በኤፈርት ስር ያሉትና የሚታወቁት እንኳ ከ47 የማያንሱ ናቸው። ንግዱን በሁሉም ሴክተር ተቆጣጥረውት ነበር።
አዲስ ዘመን፡– የቡድኑ ህገወጥ ተግባር በተለይም የግሉ ዘርፍ ላይ ያደረሰው ጥፋት ከፍ ያለ እንደሆነ በስፋት ይነገራል፤ ይህንን እውነታ ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል ?
አቶ ውብሸት፡– እንግዲህ የትግራይ ልማት ማህበር አለ። እሱና ኤፈርት የተለያዩ ናቸው። የትግራይ ልማት ማህበር ከላይ የሚታየው ለህዝብ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተቋቋመ ነው። ኤፈርት ግን ሌላ መንግስት ነው። ኤፈርት እኮ በጦርነት ጉዳት ስለደረሰባቸው ያን ለማቋቋም የሚል ነገር የለውም። የንግድ ድርጅት ነው። ይህ በፓርቲ ስም የአምባገነኖች መንግስት ማቋቋም ነው።
በኢትዮጵያ ህግ የፖለቲካ ፓርቲዎች የንግድ ድርጅት ማቋቋም እንደማይችሉ በግልጽ ይደነግጋል። ነገር ግን ህወሓት በጣም በገዘፈ ሁኔታ ተሳታፊ ነበር። ሌሎቹም ነበራቸው። ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደኢህዴንም ነበራቸው። ነገር ግን የነዚህ የሶስቱ ሃብት ተደምሮ የህወሓትን አንድ አስረኛ እንኳ አያክልም ነበር። ያም ሆኖ ግን በአራቱም ድርጅቶች የተቋቋሙበት መንገድ ትክክል አይደለም።
ይህ ቡድን የትግራይ መንግስት የመመስረት እቅድ ነበረው። በዚህ ሂደት ደግሞ የትግራይ ህዝብ ወደሌላ የማየት እድል እንዳይኖረው አድርገዋል። እናም ለህወሓት ህግ አርጩሜ ነው፤ አንዳንዴ ግን ከዚያ አልፎ ጎራዴ ይሆናል።
የህወሓት ጁንታ ህግን ሊያከብር ቀርቶ የሚሰራው ተገላቢጦሽ ነበር። ፓርቲ መነገድ አይችልም ብሎ ራሱ በስፋት የንግድ ግዛት መመስረት የዚህ ማሳያ ነው። የንግድ ውድድር ህግ ካወጣ በኋላ ውድድር እንዳይኖር ይሰራል። አደገኛ ቦዘኔ ብሎ ካወጣ አደገኛ ቦዘኔ ያልሆኑ ስራ ላይ ያሉ መመታት የሚገባቸው ሰዎች አሉ ማለት ነው።
አሰራራቸውን በተመለከተ አንድ ድርጅት ይመሰርቱና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አንድ አክሲዮን እንዲገዛ ያደርጋሉ፤ ከዚያ የንግድ ፈቃዱ በሱ ስም ይሆናል ማለት ነው። እሱ ሲወርድ ለሌላ ያስተላልፋል። የአክሲዮን ማህበር አባላት ደግሞ የተለያዩ ድርጅቶች ይሆናሉ። ይህ አሁን በየትኛው ህግ ነው ትክክለኝነቱን ማረጋገጥ የሚቻለው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የንግድ ስራ ውስጥ ባይገቡ ይመረጣል፤ ከሆነም ግን ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ይህ በሆነበት ሁኔታ ዴሞክራሲ፣ ፍትሃዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድር ፈጽሞ አይታሰብም።
አዲስ ዘመን፡– በወንጀል ውስጥ ካላቸው ቀጥተኛ ያልሆነ ተሳትፎ አንጻር ህግ እንዴት ያያቸዋል ?
አቶ ውብሸት፡– እነዚህ ድርጅቶች እንዲህ መሆን የለባቸውም ሲባል ሰሚ አልነበረም። ለምሳሌ ሱር ኮንስትራክሽን በአማራ ክልል ያልሰራው ወንጀል አልነበረም። ነገር ግን በወቅቱ እነዚህ ድርጅቶች ምን እየሰሩ ነው የሚል ጥያቄ ሲነሳ የትግራይ ድርጅቶች እንዳይሰሩ ነው የሚል ምላሽ ይሰጣል። ነገር ግን ሱር ኮንስትራክሽን ከሰራው መንገድ ይልቅ የሰራው ምሽግ ይበልጣል። በአማራ ክልል ጠለምት አካባቢ። በቅማትና በአማራ ክልል መካከል የተፈጠረው ግጭት በተመለከተ በርካታ ድርጅቶች ነዳጅ የሚያመላሱ መስለው መሳሪያ ሲያመላሱ ነበር የቆዩት። በየቦታው በነዚህ ድርጅቶች ውስጥ የተገኘው የጦር መሳሪያም የዚህ ማሳያ ነው። ስለዚህ የሽብር ድርጊትን ፋይናንስ የሚያደርጉት እነዚህ ድርጅቶች ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይ ክልል የተገኘው መሳሪያ በርካታ እንደነበር ብዙዎቻችን ያየነው ነው። ይህ ሁሉ በምን ይገዛል። ከነዚህ ድርጅቶች በሚገኝ ፋይናንስ ነው።
የጁንታው ቡድን አባላት የእርሻ መካናይዜሽን በሚል ሁመራ አካባቢ እርሻ እንደነበራቸው ይታወቃል። ይህንን ስመለከት እነዚህ ሰዎች በእርሻ ስም አደንዛዥ እጽ ሊያለሙ እንደሚችሉም መገመት ይቻላል። በእርሻ ስም ይህንን ሲሰሩ ላለመሆናቸው ማረጋገጫ የለም። በአጠቃላይ በጦርነት ላይ በቀጥታ ኢንቨትስ ሲያደርጉ ነበር።
በአገራችን የተፈጠሩት በርካታ ግጭቶችን ስንመለከት የፋይናንስ አቅም ይፈልጋሉ። ይህ ገንዘብ ከየት ነው የሚገኘው ካልን ከነዚህ ድርጅቶች ለመሆኑ ግልፅ ነው። ስለዚህ እነዚህ አይነት ድርጅቶች በደምብ መታየት አለባቸው። እስከዛሬ ለፈፀሙትም መጠየቅ አለባቸው። እነዚህ ድርጅቶች ህጋዊ ማንነት ስላላቸው መከሰስ ይችላሉ። ስለዚህ እነዚህ ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ የግድ ነው። ይህንን በማድረግም እነዚህ ድርጅቶች በቀጣይ ግጭትን ስፖንሰር እንዳያደርጉ ማድረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– እነዚህ ድርጅቶች ከሃገርም አልፎ በጎረቤት አገራት ላይ ተጽዕኖ እንዴት ይታያል?
አቶ ውብሸት፡– ከተወሰነ ዓመታት በፊት “ፓናማ ፔፐርስ” በሚል የወጣ አንድ ሰነድ ነበር። በዚህ ሰነድ ላይ የህወሓት ድርጅቶች በአንዳንድ የውቅያኖስ ዳርቻ ላይ ተሳትፈው እንደነበር አትቷል። በግለሰቦች ስም ኢንቨስት የሚያደርጉ አሉ፤ ትልልቆቹ የመሳሪያ ደላላዎችም ከነሱ ጋር ሲሰሩ እንደነበር አውጥቷል። ይህንን ስንመለከት በአገራችን እነዚህ ሰዎች የጦር መሳሪያ ንግድ ላይ ተሰማርተው እንደነበር መገመት ይቻላል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገራችን የጦር ህግጋት ያልወጣው አንድም ለዚህ ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥ የጦር መሳሪያ በገፍ ነበር የሚሸጠው፤ ይህንን ግን ማነው የሚሸጠው፤ እንዴት ነው ወደኢትዮጵያ የሚገባው፤ ካልን አይታወቅም። አንዳንድ ጊዜ እኮ ገበያ ሲጠፋ የጦር መሳሪያ ምዝገባ ይባላል። ከዚያ አርሶ አደሩ ይሰጋና ከተመዘገበ ሊወስዱት ነው ብሎ ሌላ ሁለተኛ መሳሪያ ይገዛል። ከዚያ ከመዘገቡ በኋላ ይወስዱባቸዋል። ከወሰዱ በኋላ ደግሞ እንደገና መልሰው ለሽያጭ ያመጣሉ። ስለዚህ ገበያ ይፈጥራሉ። የሚከለክሉትም፣ የሚፈቅዱትም እነሱው ናቸው። አንዳንዴ እኮ ተሽከርካሪዎች የመከላከያ ኮድ ተሰጥቷቸው ነው መሳሪያ በገሃድ የሚነግዱት። ስለማይፈተሽ ማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ጥይት በገፍ ይሸጣል። መሳሪያም በገፍ ይሸጣል። አይመዘገብም፤ ሻጭ የለም። እንደገና መሳሪያ ትገዛለህ፤ በዚህ ጊዜ ማስመዝገብ ይጠበቅበሃል፤ ግን ከየት አመጣኸው አትባልም። ይህንን ለረጅም ዓመታት በገፍ ሲሰሩበት ነበር።
ይህን ነገር ደግሞ በተመሳሳይ በጎረቤት አገራትም ሰርተውታል። አንዳንድ አገራትም ለዚህ ምቹ ነበሩ። ለዚህ ደግሞ አንዱ በሰላም ማስከበር ስም ሲሰሩበት ነበር። በሌላም በኩል ደቡብ ሱዳን ላይ ሰርተዋል። ለምሳሌ አቶ ስዩም መስፍን ደቡብ ሱዳንን ለማበጣበጥ በገሃድ ሲሰሩ እንደነበር ሲነገር ነበር። ከግጭት ብዙ ማትረፍ ስለሚቻል የኢትዮጵያን ዙሪያ በማበጣበጥ ከዚህ ለማትረፍ ጥረዋል። ቡድኑ በዚህም ከፍተኛ ገንዘብ ያገኝ ነበር። በኢትዮጵያ መርከብ ስም የኢትዮጵያ መርከብ ባልሆኑ መርከቦች መሳሪያ ሲነግዱ ነበር።
ስለዚህ ይህ ቡድን ከሃገሪቷ አልፎ ለቀጠናው መረጋጋትም ካንሰር ነበር። እና ይህንን መዞ ማውጣትና ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድንም በሙሉ ከዚህ ቡድን ማንፃት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– ከህግ አንጻር የወደፊት እጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን ይችላል?
አቶ ውብሸት፡– ይህ ግልፅ ነው። አንድ ድርጅት ህገወጥ ተግባር ውስጥ ተሰማርቶ ከተገኘ ይከሰሳል። እንደሁኔታውም ንብረቱ በመንግስት ሊወረስ ይችላል፤ ካልሆነም በገንዘብ ቅጣት ሊቀጣ ይችላል። እነዚህ ድርጅቶችም የፈፀሙት ወንጀል በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ሊወረሱ ይችላሉ። በሚወረሱበት ጊዜ እዚያ ውስጥ ያሉ ሰራተኞች ይኖራሉ፤ ለዚህ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ይህ ማለት ድርጅቱን መውረስ ማለት ማፍረስ ማለት አይደለም። ስለዚህ አመራሩን በመቀየርና ዓላማውን በማስተካከል ወደጤናማ የንግድ ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ይገባል። ስለዚህ እነዚህ አንዴ ከተለዩና ማስረጃው በአግባቡ እስከተጠናከረ ድረስ ቀጣዩ እርምጃ በህጉ መሰረት ይሆናል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– መንግስት በቀጣይ እንዲህ አይነት ችግሮች እንዳያጋጥሙ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?
አቶ ውብሸት፡– እንግዲህ መንግስት ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ እያንዳንዱን ስራ ህግን መሰረት አድርጎ መስራት አለበት። እንግዲህ አንዱና ዋናው ፍትህ የሚሰፍነው ህግን መሰረት አድርጎ መስራት ሲቻል ነው። ፍትህ ምንድነው ሲባል የተለያዩ ትርጓሜዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ዋናው ህግ ላይ በተቀመጠው መሰረት መተዳደርና ያን ህግ የተላለፈ እንደጥፋቱ ሲቀጣ የተጎዳው ደግሞ ሲካስ ነው። ስለዚህ ህግን መሰረት አድርጎ መስራት የጨዋታው ህግ ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ ህግ ላይ የሙጥኝ ማለት ይገባል።
አንዳንዴ ህግን እየተከተሉ፤ ሌላ ጊዜ ከህግ ውጭ መንቀሳቀስ አደገኛ ዋጋ ያስከፍላል። የንግድ ህጎች አሉ፤ የሸማቾች ጥበቃና የንግድ ውድድር ህግ አለ፤ የትኛው ድርጅት ወይም አካል ንግድ ውስጥ መሰማራት እንዳለበት እና እንደሌለበት ግልፅ ነው። የንግድ ድርጅቶች በአክሲዮን ማህበራትም ሆኑ በሌላ መንገድ የተቋቋሙት በየዓመቱ ማቅረብ ያለባቸው ሪፖርት አለ። እንደገናም ተቆጣጣሪ ተቋማትም አሉ። እነሱ ስራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ ማድረግ ይገባል። ስለዚህ ህግን መሰረት አድርጎ መስራትና በዚህ መሰረት መስራታቸውንም መቆጣጠር ለአንድ ቀንም ቢሆን ልንዘነጋው አይገባም።
በአሁኑ ወቅት ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተስፋፍቷል፤ ሽብርን በገንዘብ መደገፍ ተስፋፍቷል። ስለዚህ ፋይናንሻል ኢንተለጀንስ እንዲህ አይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ መከታተል፤ ሽብርን ፋይናንስ የማድረግ እንቅስቃሴ መኖር አለመኖሩን መከታተል፤ እነዚህ አይነት የንግድ ድርጅቶች ህግን ተከትለው በውድድር መንፈስ እየሰሩ መሆን አለመሆናቸውን መከታተል፤ ይህንንም ሊቆጣጠሩና ሊከታተሉ የሚችሉ ጠንካራ አቅም ያላቸው ተቋማትን መገንባት፣ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠርም እግር በእግር እየተከታተሉ ወደህግ ማምጣት፣ ወዘተ ያስፈልጋል። ይህ አጠቃላይ የንግድ ስርዓቱን ጤናማ እንዲሆን ያደርገዋል።
ብሄራዊ ባንክም በተለይ የፋይናንስ ተቋማትን ማጠናከር አለበት። ባለፉት ዓመታት አንዱ ችግር የነበረው ብሄራዊ ባንክ መስራት ያለበትን ስራ አለመስራቱ ነው። ብሄራዊ ባንክ በሚሰጠው በርካታ ብድርና ገንዘብ ነበር ሲሰራ የነበረው።
አዲስ ዘመን፡– ብሄር እና ሀይማኖትን መሰረት አድርገው የሚቋቋሙ የቢዝነስ ተቋማት ከህግ አንጻር እንዴት ይታያሉ?
አቶ ውብሸት፡– እንግዲህ ከዚህ ጋር ተያይዞ ችግሩ የአንድ ሴክተር ጉዳይ ብቻ አይደለም። ችግሩ ዘርፈብዙ ነው። ገና ከመነሻ ጀምሮ በርካታ ተቋማትና ሃገሪቷ የተመሰረተችበትም ጭምር ችግር ያለበት ነው።
ሃገሪቷ በጠቅላላ የተዋቀረችው ብሄርን መሰረት አድርጋ ነው። በህገ መንግስቱ መሰረት ኢትዮጵያን ስታያት ዝም ብሎ 80 አካባቢ ብሎኬቶች የተደረደሩበት አይነት ነው። እነዚህ ብሎኬቶች ደግሞ እንድትነቃቅላቸው ተደርገው ነው የተሰሩት። ህወሓት ሲሰራቸው የነበሩ ነገሮችም እነዚህ ብሎኬቶች እንዲላቀቁ ነበር። ከዚያ ባሻገር በአብዛኛው ልዩነት ላይ ነበር ሲሰራ የነበረው።
አንዱ ብሎኬት ከስር ገብቶ ሌላው ተጭኖታል፤ አንተ ከዚህ ታንሳለህ፣ ያንተ ቦታ እዚህ አይደለም፣ ወዘተ እያለ ነበር ልዩነቱ ላይ ጠንክሮ የሰራው። እያንዳንዱ ብሎኬትም ራሱን የቻለ እንደሆነ ደንግጓል። እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት ነው የሚል አስቀምጧል።
በአጠቃላይ መዋቅሩ ብሄርን መሰረት ያደረገ ነው። ስለዚህ የንግድ መዋቅሩን ብቻ ለይተን ብናየው ፋይዳ የለውም። ብዙ ነገር ላይ ክለሳ መደረግ አለበት። ለምሳሌ ፓርቲ ብሄርን መሰረት ያደረገ ነው። ክልል ብሄርን መሰረት ያደረገ ነው። የንግድ ተቋማትም ብሄርን መሰረት አድርገው መሆን የለበትም ብንል ብቻውን የሚሆን አይደለም። ስለዚህ መሰረቱ ላይ ነው ችግሩ ያለው። ከዚህ በመነሳት ችግሩን ለመፍታት መሰረቱን ማስተካከል ይጠይቃል።
የንግድ ስም ሲወጣ የብሄር ስም ለንግድ ምልክት መጠቀም ክልክል ነው ይላል። ለምሳሌ ባንክን ብትወስድ በባህሪው አንድ ባንክ በአንድ ብሄር ብቻ ሊሰራ አይችልም። ኢንሹራንስም፣ ሌሎች የቢዝነስ ተቋማትም እንደዚሁ። ነገር ግን ጁንታው ህግን ለሚፈገልገው ነገር እንጂ ህጉን ለማስጠበቅ ስለማይፈልግ እንደፈለገ ነበር የሚሰራው። ሃገሪቱን አንድ የሚያደርጓት፣ የሚያስተሳስር ነገር ማድረግ ሲገባ ሲሰራ የነበረው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነበር። ኢትዮጵያንም እንደ ብሎኬት ጥርቅም ነበር ሲሰራባት የነበረው። ነገር ግን ኢትዮጵያ የብሎኬት ጥርቅም አይደለችም። ከዚያ በላይ ናት። አንድ ብሄር ከሌላው የተለየ ነው ካልክ አንድ የሚያደርጋቸው ላይ እንጂ መስራት ልዩነቱማ ይታወቃል። ስለዚህ አንድነትን ለማጠናከር፣ ኢትዮጵያን እንደአንድ ሃገር ለማስቀጠል ይህ ነገር በአጠቃላይ ከስር መሰረቱ ፍተሻ ማድረግን ይጠይቃል። የንግድ ተቋማት ሁኔታም በዚሁ አግባብ የሚታይ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ውብሸት፡– እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 9/2013