ሰላማዊት ውቤ
ሥፍራው በቀድሞ አውራጃ ተብሎ በሚጠራው በዛሬው የሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ወረዳ ውስጥ ነው። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ያቀፈችው የገጠሯ ቲቲራ ቀበሌ በወረዳው ውስጥ ትገኛለች። ሲያስተውሏት የነዋሪዎቿ የሳር ክፍክፋት የተጎናፀፉ ጎጆዎች ውበት ደስታ ይፈጥራል። ማልደው አረንጓዴ ምንጣፍ የሚመስል ሣር በተላበሰው ሜዳ ላይ ለግጦሽ የተሰማሩት ከብቶች ቀልብ ይስባሉ። ብዛታቸውም አጃይብ ያሰኛል። መንገድ ላይ አልፎ አልፎ እህል የጫኑ አህያና በቅሎዎች እንዲሁም ሰው የሚያጓጉዙ ጋሪዎች ይስተዋላሉ።
በየማሳው አፍርቶ የተንዠረገገው ቡና መቅላት በመጀመሩ ይማርካል። የብዙዎቹ ነዋሪዎች አውደ ጊቢ እንደ ከተሜው በብረት በር የተቸነከረ ሳይሆን ገላጣ ነው። በመሆኑም አላፊ አግዳሚው ዓይኑን ወርወር እያደረገ ይቃኘዋል። ብዙዎቹ ግቢዎች ጥገቶች ታስረው ይስተዋላሉ።
በአጠቃላይ በዕይታ ውስጥ የሚገባው ገጽታ የክልሉን፣ የወረዳውንና የቀበሌውን አንጡራ ሀብት ይዘረዝራል። ነዋሪው ይሄን በረከት ተጠቅሞ አካባቢውን ለማሳደግ የሕዝቡን አኗኗር ለማዘመን የሚጋብዝ ይመስላል።
የሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ወረዳ ነዋሪና ተወላጁ የሲላ ዳኤ ጉራሮ የስራ ፈጠራ ትጋት ገና ከመነሻው ይሄን አገናዝቧል። መሰረቱን ለምለሚቱ ገጠር ላይ ጥሎ እራሱንና ሕብረተሰቡን እዛው ባለበት ቀዬ ለመጥቀምም አልሟል።
አርሶ አደር ሲላ ዳኤ በተለይ በቡና ሀብቷ ስሟ ጎልቶ በሚጠራው ሲዳማ በተለያዩ ንግድ ሥራዎች በመሰማራት ይህን ህልማቸውን ዕውን በማድረግ ይታወቃሉ። ዕውን ማድረግ የቻሉት በደጃፋቸው ከሚያገኙት ቡና ጀምሮ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች በመሰማራትና በተፈጥሮ የተቸራቸውን የሥራ ፈጠራ ክህሎት በመጠቀም ነው።
ላለፉት ስድስት አሥርት ዓመታት የሀገር ውስጥና የውጪ የቡና ንግድ፣ የከብት ንግድ፣ የቡና መፈልፈያ፣ የቡና ወፍጮ፣ የእህል ወፍጮ፣ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዳስትሪ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ተሰማርተውና የንግድ ፈር ቀዳጅ መሀንዲስ ሆነው የከበደውን የገጠሩን ሕብረተሰብ አኗኗር ዘይቤ ለማቅለል ጥረዋል።
ከአብራካቸው የወጡት 20 ልጆቻቸውም የእሳቸውን ፈር ተከትለው በግብርናውና በኢንዱስትሪው መስክ በመሰማራት ገጠሩን የሀገሪቱን ክፍል እያለሙ ይገኛሉ። ከነዚህ በተለይ በንግዱ መስክ ከተሰማሩት ከዘጠኙ ወንዶች ልጆቻቸው መካከል በስኬታማነት እንደ ሀገር አንቱ ለመባል የበቁት አቶ ሀብታሙ ሲላ ይጠቀሳሉ። ሆኖም የአቶ ሀብታሙ ሲላን ተሞክሮ በይደር አቆይተነው መሰረት የጣሉላቸውን የአባታቸውን የአቶ ሲላ እና የሀያታቸውን የአቶ ዳዬን አርያነት ያለው ተሞክሮ ማስቀደም መርጠናል።
አቶ ሀብታሙ ስለ አባታቸው አርሶ አደር ሲላ ሲያጫውቱን መነሻቸው ከአያታቸው ከአርሶ አደር ዳኤ ጉራሮ ያደርጋሉ። አቶ ሀብታሙ እንደሚሉት አያታቸው ዳኤ ውልደትና እድገታቸው በሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ወረዳ ልዩ ስሙ ቲቲራ በሚባል ገጠር መንደር ውስጥ ሲሆን በቡና፣ በእንሰትና በከብት ርቢ ነበር የሚተዳደሩት።
መተዳደሪያ ሥራቸው የተትረፈረፈ ጥሪት አስቋጥሮ ሀብታም ባያሰኛቸውም ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ አያንስም ነበር። ሦስት ሚስቶቻቸውንም የማስተዳደር አቅም ነበራቸው።
ሦስተኛ ባለቤታቸው ካሮ ቲሮ የአባታቸው የሲላ እናት ናቸው። በአንድ ወይፈን ምክንያት በተነሳ አለመግባባት ከአያታቸው ከአርሶ አደር ዳኤ ጋር ፍቺ ከመፈፀማቸው በፊት አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አፍርተዋል።
አንድ ቀን ወይዘሮ ካሮ ለአያታቸው ቁርስ በማቅረብ ላይ ሳሉ ነበር አለመግባባቱ የተፈጠረው። አያታቸው ካላቸው ከብት መካከል አንዱን ወይፈን ለባለቤታቸው ለወይዘሮ ካሮ እያሳይዋቸው ‹‹ሟች አያቴ በህልሜ እየደጋገመ ወይፈኑ ለማጥቃት ሲደርስ ለአባትህ ስጠውና መርቆህ መቃብሬ ላይ ይሰዋልኝ ብሎኛል›› ሲሉ ይነግሯቸዋል። ባለቤታቸው ካሮ ያሏቸው ነገር አልተዋጠላቸውም። የሁለቱ ጣውንቶቻቸው ጊደር ሳይሰዋ የእርሳቸው ይሰዋል መባሉም ስላላስደሰታቸው በሀሳቡ አልተስማሙም።
ለትዳራቸው መፍረስም ምክንያት ሆኖ ተለያዩ። በሲዳማ ባህል ሴት ልጅ ከባሏ ስትፋታ አብራ ካፈራችው ንብረት መካከል ይዛ የምትሄደው የቆጮ መቁረጫ ቢላዋና ከእንጨት የተሰራ ባህላዊ ትራስ ብቻ ነው። ወይዘሮ ካሮም እነዚህን ቁሶች ብቻ ነበር ይዘው ከቤታቸው የወጡት። ወደ ወላጆቻቸው ቤት ሲመለሱም በሆዳቸው ጽንስ ይዘው ነበር።
ለባለቤታቸው ለመንገር ዕድሉን ሳያገኙ ነው አለመግባባቱ ተፈጥሮ የተለያዩት። አርሶ አደር ሲላ ዳኤ እንዲህ ባለው ሁኔታ ነበር ተጸንሰው የተወለዱት።
በሲዳማ ክልል ያናሴ ጩሜ ልዩ ስሙ ቱሉ በተባለው የገጠር መንደር በ1924 ዓ.ም በወርሃ ሚያዝያ ማገባደጃ የተወለደው ጨቅላ ብስራት ውሎ ሳያድር አባታቸው መኖሪያ ቀዬ ቲቲራ ደረሰ። አርሶ አደር ዳኤ ጊዜ ሳያጠፉ ከባለቤታቸው ጋር ያጣላቸውን ወይፈን በወንድ አያታቸው መቃብር ላይ እንዲሰዋ ያደርጋሉ። በሲዳሚኛ ጨሜሳዎች የሚሰኙት የአካባቢው ሽማግሌዎች እንደ ባህላቸው የታረደውን ከብት ሞራ ያያሉ።
ሽማግሌዎቹ ከሞራው ላይ በጥልቅ አስተውሎ ያነበቡትን ለአርሶ አደር ዳኤ እንዲህ ሲሉ ነገሯቸው ‹‹ካሮ ከአንተ ነው ፀንሳ የሄደችው። ልጁ ያንተ ነው። ወደፊት እጅግ ስመጥርና ሕይወቱ በስኬት የተሞላ አንተንም አካባቢውንም የሚያስጠራ ሀብታም ይሆናል። አምጣውና ህጻኑ አንተ ጋር ይደግ›› ህፃኑ ሲላ ጡት እስኪጥል ጠብቀው አራት ዓመት ሲሞላው ከእናቱ ወስደው አሳደጉት።
የህፃኑ ወደ አባቱ ቤት መምጣት ጥሩ አጋጣሚ ነበር። የዳኤ ሁለተኛ ሚስት ዳኢቴ ልጅ ስላልነበራቸው ፍቅርና እንክብካቤ በመስጠት እንደራሳቸው ልጅ ነበር የያዙት። ህፃኑ ወደ አባቱ ቤት በመጣ በዓመቱ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ወረረ። በወቅቱም በአካባቢው የወንድ ብልት በመስለብ የሚያሰቃዩ የጣሊያን ባንዳዎች መኖራቸው ለእንጀራ እናቱና ለአባቱ ታላቅ ስጋት የፈጠረ ነበር።
አባቱ ዳኤ ወደ እርሻ ሥራ ሲሄዱ ባለቤታቸው ልጃቸው ሲላን አጥብቀው እንዲጠብቁ ማሳሰባቸውን ባለቤታቸው ዳኢቴም ህፃኑ ወደ ውጪ ወጥቶ ለአደጋ እንዳይጋለጥ መከታተላቸውን ተያያዙት።
ዳኤ ለእርሻ ሥራ በሄዱበት በአንዱ ቀን የወንድ ብልት የሚሰልቡት ባንዳዎች እነ ዳኤ ግቢ ይዘልቃሉ። ይሄኔም ወይዘሮ ዳኢቴ ሴቶች ከወገብ በታች በሚለብሱትና ከቆዳ በተሰራ ቱባዋ በተሰኘ ባህላዊ ልብሳቸው ውስጥ ህፃኑን ይደብቁታል።
ከባንዳዎቹ መካከል አንዱ ህፃኑ ሲያጮልቅ አይቶት ስለነበር ከጓደኞቹ ወደ ኋላ ይቀርና በወገቡ ላይ የታጠቀውን የመሥለቢያ ሥለታም ጩቤ እየደባበሰ ወይዘሮዋ ህፃኑን እንዲሰጡት ይጠይቃቸዋል። በሚያሳዝን ድምጽ በመማፀን ‹‹ሜያቴ፣ ሜያቴ›› ይላሉ። ሜያቴ በሲዳሚኛ ‹‹ሴት ናት፣ ሴት ናት›› ማለት ነው። ባንዳውም አምኗቸው ጥሏቸው ይሄዳል። በዚህ መልኩ ነበር ህፃኑ ከመሰለብ የተረፈው።
ልጃቸው አቶ ሀብታሙ እንዳጫወቱን ህፃን ሲላ አድገው ትዳር መሥርተው ዛሬ የ20 ልጆች አባት ሆነዋል። የኑሮ ስኬት ጉዞአቸውም ከልጅነታቸው የጀመረ ሲሆን፣ ከልጆቻቸው መካከልም እርሳቸውን ጨምሮ ዘጠኙ ወንዶች የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል በሲዳማና በደቡብ ክልል በቡና፣ በሰንጋና በተለያየ የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ ለመሆን ችለዋል።
የአካባቢ ፀጋን በመጠቀም አንድ ብለው ወደ ንግድ ሥራ የገቡት አቶ ሲላ ቡናን ከአካባቢው አርሶ አደር ቀርጮ በተሰኘ መስፈሪያና በዘንግ በተንጠለጠለ ኪሎ ገዝቶ ለነጋዴ በማቅረብ ነው።
በተጨማሪም በአካባቢው ይከናወን በነበር የመንገድ ሥራ ላይም በመሳተፍ ገንዘብ ያገኙ ነበር። ከንግዱና ከሥራው ባገኙት ገንዘብም ሁለት በሬዎች በመግዛት ወደ ሰንጋ ንግድ ገቡ። በ1953 ዓ.ም ለአካባቢው የመጀመሪያውን የእህል ወፍጮ ከፍተው ለስድስት ዓመት ሰርተዋል።
የወፍጮውን ሞተር ለእሸት ቡና መፈልፈያ በማዋል የመጀመሪያው ነበሩ። ለኢንደስትሪ ሽግግርም መንገድ የከፈቱ ናቸው። የቤት መኪና በመያዝም ለአካባቢያቸው የመጀመሪያው ሰውም ሆነዋል። መኪናቸው የእርሳቸው ብቻ አልነበረችም። የአካባቢያቸውን ሰዎች በነፃ በማጓጓዝ የሚረዱባትም ነበር።
አርሶአደር ሲላ የትምህርት ቤት ደጃፍን ቢረግጡም ከሶስተኛ ክፍል በላይ አልዘለቁም። ሆኖም ግን ድፍረት፣ ብልህነት፣ ፍጥነት፣ አስተዋይነት፣ ጽናት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ጥንካሬ፣ የሥራ ፈጠራ ክህሎት ያላቸው ሲሆኑ፣ ሁሉንም መሞከርና ፈጥኖም ወደ ተግባር በመለወጥ ይታወቃሉ። ተስፋ የሚቆርጡ ሰውም አይደሉም።
አቶ ሀብታሙ ስለ አባታቸው አርሶ አደር ሲላ ድፍረት እንዳጫወቱኝ፤ አንድ ወቅት የቤተሰብ ትዕዛዝ ተቀብለው ቅቤ ለመግዛት ከሰንጋ ነጋዴዎች ጋር ስድስት ቀን በእግር ሲጓዙ እግረ መንገዳቸውን ዳደሆ፣ ሆፉርሶና ብድሬ በተባሉ በሚያልፉባቸው አካባቢዎች ከብት በርካሽ ዋጋ እንደሚሸጥ ይሰማሉ።
አጋጣሚውን በመጠቀምም በቀን 25 ሳንቲም እየተከፈላቸው የጉልበት ሥራ ሰርተውና ከአካባቢው ነጋዴ ቡና በስፍርና በዘንግ ሚዛን ገዝተው በመሸጥ ባገኙት ገቢ ሁለት በሬዎች ገዝተው ወደ አካባቢያቸው ይመለሳሉ። ከብቶቹን አትርፈው ሸጧቸው። ጥቅሙን ስላዩ ወደ ዳደሆ፣ ሆፉርሶና አካባቢው እየተመላለሱ የከብት ንግዱን ተያያዙት። እስከ ዲላና ይርጋ ጨፌ በመንዳት በወጣትነታቸው ሰንጋ ነጋዴ ለመሆንም በቁ።
በከብት ንግድ ውስጥ በቆዩባቸው ጊዜያቶችም በርካሽ ዋጋ አግኝተው ሊያተርፉባቸው የሚችሉባቸውን አካባቢዎችንም በቀላሉ ስለተረዱ እግረ መንገድም የከብት ሀብት የሚገኝባቸውን ለማወቅ ችለዋል። የአካባቢ ባህልንም አውቀዋል።
በመንገድ ላይ የሚያጋጥሟቸውን ሽፍቶች ለመከላከል ሲሉም ከኦሮሞ ባህል አንዱ የሆነው የዝምድና መፍጠሪያ ጡት በመጥባት ዝምድና ፈጥረው ከሚያጋጥማቸው አደጋ ሊድኑ ችለዋል። ቋንቋቸውንም ለምደው ከማህበረሰቡ ጋር ለመግባባት በቅተዋል።
አርሶ አደር ሲላ ስለመልካምነታቸውም ይነገርላቸዋል። በጥሩ ከሚያነሷቸው መካከልም አቶ ተሾመ ቤላሞ አንዱ ናቸው። አቶ ተሾመ በንግዱ ዓለም በሲዳማ ክልልና በደቡብ ክልል ስኬታማነትን ከተቀዳጁ ነጋዴዎች መካከል አንዱ እንዲሆኑ ካስቻሏቸው ወዳጆቻቸው መካከል በቀዳሚነት ያነሷቸዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ዕድሜያቸው የአባትና ልጅ ያህል ይራራቃል።
እንደ ጓደኛም እንደ አባትም ቀርበው በሀሳብና በሌሎችም ድጋፎች ለውጤት አብቅተዋቸዋል። ‹‹የንግድ አስተማሪዬ›› ሲሉም ይጠሯቸዋል። ስለ ሥራ ትጋት፣ ስለንግድ ዕውቀት፣ ስለ አዳዲስ የንግድ ፈጠራ፣ ስለገንዘብ አያያዝ ከእርሳቸው ተምረዋል።
‹‹ሳይማር በተፈጥሮ ባገኘው ዕውቀት ትክክለኛውን የንግድ ሳይንስ ተግባራዊ የሚያደርግ ፈላስፋ›› ሲሉም ያወድሷቸዋል። አርሶአ አደር ሲላ የንግድ ችሎታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለማጋራት እራሳቸውን የማይገድቡ ለሁሉም ቅርብና ምቹ ሰው እንደሆኑ መሥክረውላቸዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 8/2013