አንተነህ ቸሬ
‹‹የገበሬው እውቀት ትኩረት ይሰጠው፤ የገበሬን ሙያ በሳይንስ ማገዝ እንጂ በሳይንስ መተካት እንዳይሞከር›› እያሉ በአደባባይ ይናገራሉ። በርካታ የኢትዮጵያ የግብርና ኮሌጆችና የምርምር ተቋማት የእርሳቸውን ትጋት ይመሰክራሉ። የኢትዮጵያን የብዝሐ ሕይወት ሀብትን የሚያከማችና የሚጠብቅ ተቋም የማደራጀት ተግባራቸው ጎልቶ ይጠቀሳል። ይህ ተግባራቸውም ለከፍተኛ ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸናፊነትና ለሎሬትነት አብቅቷቸዋል። የአንጋፋውን ምሁር የሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደን የሕይወት ጉዞና አበርክቶን በአጭሩ እንቃኛለን።
መላኩ ወረደ የተወለደው ሚያዝያ 16 ቀን 1928 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ወቅቱ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የወረረችበት ስለነበር ሕፃኑ መላኩ ወደ ወላጆቹ ዘመዶች የትውልድ ስፍራ፣ ወደ ቡልጋ፣ ተወሰደ። የፋሺስት ኃይል ተሸንፎ ከአገር ሲባረር መላኩ ወደተወለደባት አዲስ አበባ ተመልሶ ትምህርት ጀመረ። በቅድሚያ በወቅቱ የተለመደውን የቄስ ትምህርት ተማረ።
በመቀጠልም ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገብቶ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን በአዲስ አበባ ተከታተለ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአምቦ እርሻ ኮሌጅ ካጠናቀቀ በኋላ በመጀመሪያ ወደ ጅማ፣ በመቀጠል ወደ ሐረማያ ሄዶ በመማር በግብርና ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ።
የዘረ መል እና የእፅዋት ማሻሻል/ማዳቀል (Genetics and Plant Breeding)ን ያቀፈ የትምህርት ዘርፍ ማጥናት በመፈለጉ ወደ አሜሪካ ተሻግሮ በዚሁ የትምህርት መስክ ሁለተኛ ዲግሪውን ተቀበለ። ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በጅማ ግብርና ኮሌጅ መምህር ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ከጅማ በመቀጠል ወደ አስመራ ሄዶ ለአራት ዓመታት ያህል በመምህርነት አገለገለ።
ለተሻለ የዘረ መል ትምህርት ወደ ስዊድን ሄዶ እውቀቱን ካሳደገ በኋላ ከፍ ያለ የብቃት ማረጋገጫ እውቅና ተሰጥቶት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። ይህ የሥዊድን ቆይታው ለዘረ መልና እፅዋት ማዳቀል ጥናት ትልቅ መሰረት ሆኖታል። መላኩ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ በተመራማሪነት ተቀጥሮ በሚሠራበት ወቅት ‹‹አረማሞ›› በመባል ለሚታወቀውና ምርት ያስተጓጉል ለነበረ በሽታ ዓይነተኛ መፍትሔ ማግኘት ችሏል።
ከዚያም በመምህርነትና በተመራማሪነት ሲያገለግል ቆይቶ ለዶክትሬት ዲግሪ ትምህርቱ ወደ አሜሪካ ተመለሰ። የዶክትሬት ዲግሪውን መቀጠል የፈለገውም በጀመረው የዘረ መል እና የእፅዋት ማሻሻል/ማዳቀል የጥናት መስክ ነበር። የዶክትሬት ዲግሪ የመመረቂያ ጽሑፉ ስለ ስንዴ ዝርያዎች አስደናቂ ውጤት ያመላከተ የምርምር ስራ ነው።
የመላኩ የዶክትሬት ጥናት በስንዴ ዝርያዎች የፕሮቲን ይዘት ላይ ያተኮረ ነበር። በአሜሪካ የዘረ መል ባንክ ውስጥ በተሰባሰቡ የስንዴ ዝርያዎች ላይ ጥናት ለማካሄድ ሲታሰብ እጩ ዶክተር መላኩ የጥናቱ ተሳታፊ እንዲሆን ተመርጦ ስራውን ጀመረ። በአራት ሺ የሥንዴ ዝርያዎች ላይ ጥልቅ ጥናት ካደረገ በኋላ አራቱ ዝርያዎች ከፍ ያለ የፕሮቲን ይዘት እንዳላቸው አረጋገጠ። ከአራቱ ዝርያዎች መካከል ሦስቱ የኢትዮጵያ፤ አንዱ ደግሞ የፖርቱጋል መሆናቸው ታወቀ።
ፖርቱጋሎች ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውንና ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ናሙና መውሰድ የተለመደ ነገር መሆኑን ሲያውቅ አራተኛዋም ዝርያ የኢትዮጵያ እንደሆነች መላኩ ጠረጠረ። ሌሎች ጠቋሚ ነገሮችንና ማረጋገጫዎችንም ፈልጎ አገኘ። በዚህ ጥልቅ ጥናቱ ከአራት ሺ የስንዴ ዝርያዎች መካከል ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያላቸው የኢትዮጵያ መሆናቸውን አረጋገጠ። መላኩ በአራት ሺ የሥንዴ ዝርያዎች ላይ ያካሄደው የጥናትና ምርምር ስራ እጅግ አስደናቂ ውጤት አስገኝቶ የዶክትሬት ዲግሪ ባለቤት አደረገው።
ዶክተር መላኩ በአስደናቂ የምርምር ስራቸው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው በማስተማርና በምርምር ስራቸው ቀጠሉ። በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ለአጭር ጊዜ ሰርተዋል። በመቀጠልም የሐዋሳ ግብርና ኮሌጅን በማደራጀትና የመጀመሪያው ዲን በመሆን ለሦስት ዓመታት ያህል አገልግለዋል። በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለመከታተል ዝግጅት የሚያደርጉ ተማሪዎች የሐዋሳ ግብርና ኮሌጅን እንዲቀላቀሉ ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር። ኮሌጁ አድማሱን አስፍቶና አደረጃጀቱን ቀይሮ፣ ሐዋሳ የኒቨርሲቲ ሆኖ፣ ዛሬ አንቱ የተባሉ ምሁራንንና ተመራማሪዎችን ማፍራት የሚችል ግዙፍ ተቋም ሆኗል።
ዶክተር መላኩ በይበልጥ የሚታወቁበት ስራቸው የብዝሐ ሕይወት ሀብትን የሚያከማችና የሚጠብቅ ተቋም የማደራጀት ተግባራቸው ነው። የእፅዋት ዘረመል ሐብት ማዕከል (Plant Genetic Resources Centre)ን አቋቁመው የአገሪቱ የእፅዋት ብዝሐ ሕይወት እንዲጠበቅ በዋጋ የማይተመን ላቅ ያለ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ይህ ማዕከል በአሁኑ ወቅት ‹‹የኢትዮጵያ ብዝሐ ሕይወት ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biodiversity Institute – EBI)›› በመባል የሚታወቀው ተቋም ነው። ዶክተር መላኩ ተቋሙን ለ16 ዓመታት መርተውታል። ማዕከሉ ሲቋቋም ስለነበረው ሁኔታና ከዓመታት በኋላ ስላለው አቅም ሲናገሩ።-
‹‹ … ሥራውን ስንጀምር የብዝሐ ሕይወት ሀብታችን ዋስትና እንዲኖረው የማድረግ ዓላማ ይዘን ነው የተነሳነው። ማዕከሉ ከመቋቋሙ ቀደም ብሎ የዘረ መል ሐብቶችን ለማሰባሰብ ሙከራ ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ ሐብቶቹን ለማሰባሰብ የሚያስችል የተመቻቸ ማስቀመጫና በቂ የሰው ኃይል አልነበረም። ማዕከሉ እ.ኤ.አ በ1976 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት ከጀርመን መንግሥት ጋር ስምምነት ተፈራርሞ ነው በጀርመኖች ድጋፍ የተቋቋመው።
በወቅቱ የማቋቋም ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰው በተለያየ ምክንያት ሥራው በቅጡ ሳይጀመር ለቀቁ። ከዚያም እኔ ተተክቼ ሥራውን ጀመርኩ። ብዙዎቻችን አብረን የተማርንና የሰራን መሆናችን ጠቀመንና ስራውን ጀመርን። ስራው የተጀመረው የተወሰኑ ዘሮችን በከረጢት በማሰባሰብ ነው።
ተሰብስቦ በከረጢት ተቀምጦ የነበረው የእህል ዘር አቀማመጡም ሳይንሳዊ የማንበር (Conservation) ሂደትን የተከተለ ስላልነበር ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን የተባለ የታወቀ ሳይንቲስት በአንድ ጊዜ አምስት ሺ ናሙናዎችን አምጥቶ ሰጠኝ። ከዚያም የማስፋት ስራውን አጠናክረን ቀጠልንበት።
አሁን ያለው ሕንፃ እየገነባ ስለነበር እኔ እንደመጣሁ ሕንፃውን ለማጠናቀቅ ተረባርበን ጨርሰን አስፈላጊ ቁሳቁሶች ተሟልተው ወደ ሕንፃው እንዲገቡ ተደረገ። ጀርመኖቹ ለዚህ ድጋፍ ወደ 12 ሚሊዮን ማርክ አውጥተዋል። በወቅቱ በሥራው ላይ ጀርመኖች ቢኖሩም በዋናነት ኢትዮጵያውያን ነበርን የምንሰራው። ብዙ ጊዜ የዚሁ ዓይነት ሥራ በሀገሩ ዜጋ ካልተሰራ ለተለያዩ አደጋዎች ሊጋለጥ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል የኛም ፍላጐት ይኸው ነበር ተሳክቶልናል ማለት ይቻላል።
ኘሮፌሰር እንደሻው በቀለ፣ ዶክተር ረጋሳ ፈይሳ፣ ዶክተር አበበ ደምሴ፣ ዶክተር መሐሪ ዘውዴና ሌሎች ተመራማሪዎች ማዕከሉን በማቋቋምና በማጠናከር ሂደት ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው። ማዕከሉ በአፍሪካም ቀዳሚ የሆነ ማዕከል ነው። አሁን በአፍሪካ ብቻም ሳይሆን በዓለም ላይም በብቸኝነት የሚጠቀስበት ነገር አለው። ቤተ ሙከራው እጅግ የዳበረና የታወቀ ሆኗል። ደረጃውም በውጭ ካሉ ማዕከላት ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ነው። ዓለም አቀፍ ገምጋሚዎች ከአምስት አንጋፋ የዓለም ብዝሐ ሕይወት ማዕከላት መካከል አንዱ እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጥተውታል … ›› ብለዋል።
የዶክተር መላኩ ጥረትና በተግባር የተመሰከረ ስኬት ኢትዮጵያ በብዝሐ ሕይወት ጥበቃ ተግባሯ ለበርካታ የአፍሪካ አገራት ተምሳሌት እንድትሆን አስችሏታል። በበርካታ የአፍሪካ አገራት የተከናወኑ የብዝሐ ሕይወት ጥበቃና ልማት ስራዎች መነሻና አርዓያ ያደረጉት የዶክተር መላኩ ጥረት ውጤት የሆኑትን የኢትዮጵያን መልካም ተሞክሮዎችን ነው። የዶክተር መላኩ የጥናት ውጤቶች በታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎችና በዓለም አቀፍ የጥናትና ምርምር መጽሔቶች ላይ ታትመዋል።
ዶክተር መላኩ በዘረ መል ባንክ (Gene Bank) ልማት ላይ የተሰማሩ ወጣት ተመራማሪዎችን በማሰልጠንና ብዝሐ ሕይወትን በመጠበቅ የላቀ አስተዋፅኦ ከማበርከታቸውም ባሻገር ለአርሶ አደሮች መሰረታዊ እውቀት ትኩረትና ክብር መስጠት እንደሚገባም አጥብቀው ይሟገታሉ። ‹‹ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በብዝሐ ሕይወት ሐብታቸው ከበለፀጉ አገራት መካከል አንዷ ናት። ይህን ሐብት ጠብቆ በማቆየት ረገድ ትልቅ ሚና ያላቸው የተፈጥሮ ኃይልና አርሶ አደሩ ናቸው። ሳይንቲስቶች የአርሶ አደሩን ጥበብ ጥልቀት ሊያውቁ አይችሉም።
ለአርሶ አደሮች እውቀት ቦታና ክብር መስጠት ይገባል፤ እነርሱን ማዳመጥ አለብን። ሳይንቲስቱ የራሱን ግኝት እነርሱ ላይ መጫን ሳይሆን የእነርሱን ባህላዊ አሠራር መሠረት አድርጎና አቀናብሮ መጓዝ ያስፈልጋል›› በማለት በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ብዙ ጊዜ በአደባባይ ሲናገሩት የሚደመጡት ንግግራቸው ከብዙ ሳይንቲስቶች ይለያቸዋል። በዚህም ምክንያት ‹‹የገበሬዎች አለኝታ››፣ ‹‹የአርሶ አደሮች ጠበቃ›› ተብለው ይታወቃሉ።
ዶክተር መላኩ በኢትዮጵያ የሚገኘው ነባር የሰብል ዘር ከመጥፋቱ በፊት ከዘመናዊ ምርምርና የማንበር ዘዴ በተጨማሪ በገበሬው ማሳ ላይ ማንበርና ምርታማነቱን ብሎም ተመራጭነቱን ከፍ የሚያደርግ አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን አድርገዋል። ይህ ዘዴ ከኢትዮጵያ አልፎ በመልማት ላይ ባሉ በርካታ አገሮች በመስፋፋት ላይ ይገኛል።
ዶክተር መላኩ በብዝሐ ሕይወት ጥበቃ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳደረባቸውን አጋጣሚ ሲያስታውሱ እንዲህ ብለዋል።
‹‹ … የአንደኛ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ፕሮፌሰር አንደርሰን የተባሉ ምሁር ከኦክላሆማ ዩኒቨርሲቲ መጥተው በአሜሪካ ስላለው የልማት ሁኔታ ንግግር አደረጉ። ንግግራቸውን ሲጨርሱ ‹ጥያቄ ያለው ሰው ካለ መጠየቅ ይችላል› ብለው እድል ሲሰጡ ብዙ ብርቅዬ ዝርያዎች እንዳላችሁ ነግራችሁናል። ለምን አታካፍሉንም ብዬ ጠየቅኳቸው። እኔ በወቅቱ ስለዘረመል ገና ምንም ዓይነት ግንዛቤ አልነበረኝም። ‹‹ … የእኛን ሀብት ከመመኘት መጀመሪያ በአገርህ ያለውን ሀብት ተጠቀም …›› ብለው ሃሳባቸውን በሚያጠናክር ተረት አስደግፈው መለሱልኝ። መልሳቸው ለጊዜው ቢያደናግረኝና ባያረካኝም በኋላ ግን ሳስበው የሀገሬን ሀብት መመልከትና ማጥናት እንዳለብኝ ወሰንኩ። አሁን ላለሁበት ደረጃ መሰረት የሆነችኝና እዚህ እንድደርስ ያስቻለችኝ ያቺ አጋጣሚ ናት።››
‹‹… እኛ ኢትዮጵያውያን ‹ንብረታቸው ወደሌላ እንዳይሄድ አንቀው የያዙ ሰዎች› ተብለን ብዙ ቅሬታ ቀርቦብናል። ነፍስ አድን ጭምር የሆኑና ለዓለም ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉ ከኢትዮጵያ የተወሰዱብን ብዙ ነገሮች እንዳሉ ተገንዝበናል›› የሚሉት ሎሬት መላኩ ወረደ፤ ለውጭ አገራት በየዓመቱ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን የሚያስገኙ/የሚያድኑ በርካታ የዘረ መል ሐብቶች ከኢትዮጵያ መወሰዳቸውን በተደጋጋሚ ሞግተዋል። ለአብነት ያህል ከዓመታት በፊት በአውሮፓና በአሜሪካ በተከሰተ ቫይረስ ምክንያት የገብስ ዝርያ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ሊጠፋ ተቃርቦ እንደነበርና ከኢትዮጵያ በተወሰደ የገብስ ዘረ መል ችግሩ መፍትሄ አግኝቶ አሜሪካ በዓመት ከ180 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከማውጣት መዳኗን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ። ‹‹አሁንም ገና ያላወቅነው ብዙ ሐብት አለን። ግን ሳናውቀው እየጠፋ እንዳይሄድ ያሰጋል›› በማለት ለብዝሐ ሕይወት እውቀትና ጥበቃ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም አበክረው ያሳስባሉ።
አንጋፋው ምሁርና የአርሶ አደሩ ጠበቃ ዘረ መላቸው የተለወጠ ዘሮች (Genetically Modified Organisms – GMOs) በአገሪቱ የብዝሐ ሕይወት ሐብት ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትሉ በመሆናቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ በጥብቅ ይናገራሉ። ‹‹የዘረመል ምሕንድስና ለምግብ ዋስትና ይሆናል በሚለው አልስማማም፤ እንዲያውም ልመና ውስጥ ነው የሚያስገባን … ጉዳዩ ቴክኖሎጂን መቃወም ሳይሆን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ልማት ጉዳይ ነው …›› የሚል ጽኑ አቋም አላቸው።
በብዝሐ ሕይወት የዓለም አቀፍ መድረክም ንቁ ተሳታፊ የሆኑት ሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ፤ የአፍሪካ የእጽዋትና የዘረ መል ሐብት ኮሚቴ (African Committee for Plant and Genetic Resources) የመጀመሪያው ሊቀ መንበር ሆነው ሰርተዋል። የኮሚቴው ሊቀ መንበር ሆነው የተመረጡትም በወቅቱ ኢትዮጵያ እርሳቸው በሰሩት ስራ የዘረ መል ባንክ ባለቤት ስለነበረች ነው። የአፍሪካ ብዝሐ ሕይወት መረብ (African Biodiversity Network)ን በመመስረትም ግንባር ቀደም ሚና ነበራቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ተቋም የእጽዋት ዘረ መል ሐብት ኮሚሽን (UN Food and Agriculture Organization’s Commission on Plant Genetic Resources) ሊቀ መንበርም ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የእጽዋት ዘረ መል ሐብቶች ተቋም (International Plant Genetic Resources Institute – IPGRI) እና የዓለም አቀፍ የገጠር ልማት ፋውንዴሽን (Rural Advancement Foundation International – RAFI) የቦርድ አባል ሆነው አገልግለዋል።
በብዝሐ ሕይወት ልማትና ጥበቃ ዙሪያ በርካታ ጽሑፎችን አዘጋጅተዋል። በኔፓል፣ በሕንድ፣ በምሥራቅ ቲሞር፣ በባንግላዴሽና በሌሎች አገራት የብዝሐ ሕይወት ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን ሰጥተዋል። በአሜሪካም ለስድስት ዓመታት ያህል የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን አስተምረዋል።
ሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ ለብዝሐ ሕይወት ጥበቃና ልማት እንዲሁም ለምርታማነት ማደግ ለሰሯቸው አስደናቂ ስራዎች በርካታ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከዓለማችን ምርጥ የዘር ጥበቃ ማዕከላት መካከል አንዱን አቋቁመው የኢትዮጵያን የዘረ መል ሐብት በመጠበቅ ላከናወኑት ታላቅ ተግባርና ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ፤ በ1982 ዓ.ም ‹‹ተለዋጭ ኖቤል (Alternative Nobel Prize)›› በመባል የሚታወቀውንና አስቸኳይ ምላሽ ለሚሹ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች/ችግሮች ተግባራዊና ተምሳሌታዊ የሆኑ መፍትሄዎችን ላፈለቁ አካላት የሚሰጠውን የ‹‹ራይት ላይቭሊሁድ ሽልማት (The Right Livelihood Award)›› ዓለም አቀፍ ሽልማትን አሸንፈዋል።
በ1982 ዓ.ም የተከናወነው የ‹‹የራይት ላይቭሊሁድ ሽልማት›› ለኢትዮጵያ ልዩ ነበር። በወቅቱ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ እና ፕሮፌሰር ለገሰ ወልደዮሐንስ ከእንዶድ ተክል በመላው ዓለም የሚገኙ ከ200 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን እያሰቃየ ለነበረው ለቢልሐርዚያ በሽታ መድኃኒት በማግኘት ለሰሩት ስራ ሌሎች የ‹‹የራይት ላይቭሊሁድ ሽልማት›› ተሸላሚዎች ነበሩ።
ከዚህ በተጨማሪም የምርጥ ዓለም አቀፍ አስተዋፅዖ (Outstanding International Contribution Award) እንዲሁም የብሔራዊ አረንጓዴ (National Green Award) ሽልማቶችን አሸንፈዋል። በ2008 ዓ.ም ደግሞ በግብርና ምርምር ስራዎቻቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ በሳይንስ ዘርፍ ‹‹የበጎ ሰው›› ሽልማትን ተቀብለዋል። የኢትዮጵያ ብዝሐ ሕይወት ኢንስቲትዩት በ2008 ዓ.ም 4ዐኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር የኢንስቲትዩቱን አንድ ሕንፃ በሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ ስም በመሰየም ለመስራቹ እውቅና ሰጥቷል። የሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ የምርምር ስራዎች ‹‹Seeds of Freedom›› በተሰኘውና በኦስካር ሽልማት አሸናፊው እንግሊዛዊ ተዋናይ ጀርሚ አይረንስ በተተረከው የ30 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም ላይ ታይተዋል።
በአሁኑ ወቅት የ85 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ የሆኑት አንጋፋው ምሁር ሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ፤ የሶስት ልጆች አባት ናቸው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2013