የዲያስፖራ ወገናቸውን ትርጉም ባለውና ዘላቂ በሆነ መንገድ በአግባቡ ማንቀሳቀስ በቻሉ አገሮች ዲያስፖራዎች በትውልድ አገራቸው ልማት ላይ የሚጫወቱት ሚና ቁልፍ ሥፍራ ተሰጥቶት የኖረ ጉዳይ ነው። በዚህ ሁኔታ ዲያስፖራ ወገናቸውን በአግባቡ አንቀሳቅሰው ውጤታማ ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኬንያ፣ ግብፅና ናይጀሪያ የሚጠቀሱ ሲሆን ከእስያ ቻይና፣ ህንድና ደቡብ ኮሪያ ይጠቀሳሉ።
የዲያስፖራ ተሳትፎ ዓይነቶች የተለያዩ ሲሆኑ፣ ለአብነትም የዲያስፖራ ሥራ ፈጣሪዎች የቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በአገር ቤት የካፒታል ገበያዎች ውስጥ የሚደረግ ኢንቨስትመንት፣ የዲያስፖራ ቱሪዝምና ‹‹የአገር ቤት ምርቶች›› ንግድ፣ የዲያስፖራ በጎ አድራጎት፣ የዲያስፖራ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የዲያስፖራ ዲፕሎማሲና ንቅናቄ ናቸው።
የዲያስፖራ ሥራ ፈጠራሁሉም ዓይነት የሥራ ፈጠራዎች ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት በእኩል መጠን አስተዋጽኦ አያበረክቱም። በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ሥራ የገቡ ሥራ ፈጣሪዎች ወይም ሥራ መቀጠር ስላልቻሉ ለራሳቸው ሥራ የፈጠሩ ዜጎች፣ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ነው። ዕድሎችን ተጠቅመው ወደ ሥራ የገቡ ሥራ ፈጣሪዎች፣ በአንፃሩ በኢኮኖሚው ውስጥ በሚፈጠሩ አዳዲስና በማደግ ላይ ያሉ ዘርፎች ውስጥ ገበያ ሊያገኙ ስለሚችሉ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ የመፍጠር ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።
ኢትዮጵያ በእጅጉ የሚያስፈልጋትን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፈጠራ የታከለበትና እሴትን የሚጨምር የሥራ ፈጠራ ወደ ኢኮኖሚዋ ሊያስገባላት ከሚችለው ከዚህ ዓይነቱ የዲያስፖራ ተሳትፎ ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች። መሰል ሥራ ፈጣሪ ኢንቨስተሮች የኢኮኖሚ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽንን ዕውን በማድረግ ረገድ የራሳቸውን ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። እነዚህ ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወይም የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃዎችን በማስተዋወቅ ነባር ኢንዱስትሪዎችን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራሉ። ኢኮኖሚውን በማዘመን ረገድ ሰፊና ትርጉም ያለው ተፅዕኖ የሚፈጥሩ አዳዲስ አገልግሎቶችንና የንግድ ሐሳቦችንም ሊያስተዋውቁ ይችላሉ።
እነዚህ ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወይም የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃዎችን በማስተዋወቅ ነባር ኢንዱስትሪዎችን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራሉ። ኢኮኖሚውን በማዘመን ረገድ ሰፊና ትርጉም ያለው ተፅዕኖ የሚፈጥሩ አዳዲስ አገልግሎቶችንና የንግድ ሐሳቦችንም ሊያስተዋውቁ ይችላሉ።
የዲያስፖራ ኢንቨስትመንት በካፒታል ገበያዎችእስካሁን ድረስ የነበሩት የፖሊሲ ትኩረቶች ስደተኞች ወደ አገር ቤት በሚልኩት ገንዘብ ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ። ስደተኞች ወደ አገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ በፋይናንስ ፍሰት ውስጥ ትልቅና እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ባያጠያይቅም፣ ይህ ገንዘብ ከዲያስፖራው ሊገኙ ከሚችሉት የግል የገንዘብ ፍሰቶች አንዱ ብቻ ነው። ‹ሬሚተንስ› በመባል የሚታወቀው ይህ የገንዘብ ዝውውር የስደተኞችን ገቢ መልሶ ከማከፋፈል ያለፈ ፋይዳ የለውም። የላቀው ፈታኝ ነገር የዲያስፖራን ሀብት ማንቀሳቀስ ነው። በዚህ ረገድ የካፒታል ገበያዎች ቁጠባን በማበረታታት ገንዘቡን ወደ ምርታማ ኢንቨስትመንቶች ፈሰስ የማድረግ የተወሰነ ሥራ ያከናውናሉ።
በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ ታላላቅ የመንግሥት ድርጅቶችንና ተቋማትን ወደግል ንብረትነት ለማዞር አቅጣጫ መቀየሱ፣ እንዲሁም በአገሪቱ እጅግ ሰፊ ነገር ግን መዋቅራዊ ያልሆነና ቁጥጥር የማይደረግበት የአክሲዮን ገበያ በመከናወን ላይ መሆኑ፣ በኢትዮጵያ የተደራጀና ዘመናዊ የአክሲዮን ገበያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቋቋም ልዩ የሆነ ምቹ መደላድል የሚፈጥር ነው።
የአክሲዮን ገበያ ሲቋቋም ደግሞ ኢትዮጵያዊው ዲያስፖራ ባለበት ሆኖ ገንዘቡና ደኅንነቱ በተጠበቀና አትራፊ የአገር ቤት ኢንቨስትመንት ላይ የሚያውልበት ምቹ መድረክ ያገኛል። ዲያስፖራዎች ደረጃውን በጠበቀ የአክሲዮን ገበያ መጠቀማቸው
ኢንቨስትመንታቸው ‹ሊኩዊድ› (በቀላሉ ወደ ጥሬ ገንዘብ ሊለወጥ የሚችል) እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ፣ በጊዜ ሒደትም አግባብነት ያለው የዋጋ ትመናና አድናቆት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል።
ዲያስፖራው እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በውጭ አገሮች ባንኮች ውስጥ በቁጠባ መልክ ቢያስቀምጥም፣ ይህ ነው የሚባል ወለድ እያገኘበት አይደለም። በኢትዮጵያ በሚፈጠር ትርፋማ የኢንቨስትመንት ዕድል ገንዘባቸውን ከባንክ አውጥተው፣ በአገራቸው ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ የዲያስፖራ ኢንቨስተሮችን መሳብ ይቻላል። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አጠቃላይ ዓመታዊ ቁጠባ ከአምስት ቢሊዮን እስከ አሥር ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል።
የዲያስፖራ የጋራ ፈንድየጋራ ፈንዶች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ግለሰብ ኢንቨስተሮች ሊያጋጥማቸው የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ወጪ አውጥተው የግል የኢንቨስትመንት ሥራ አስኪያጅ መቅጠር ሳያስፈልጋቸው፣ ኢንቨስትመንታቸው ሙያዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል። በዚህ መሠረት ኢንቨስተሮች በትውልድ አገራቸው በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ፍላጎቱ ቢኖራቸውም፣ ሥራውን በግላቸው ለማስተዳደር ጊዜውና የሙያ ብቃቱ የሌላቸው የዲያስፖራ ኢንቨስተሮች ጉዳዩን የሚያስተባብረውን የዲያስፖራ ኤጀንሲን ቀርበው ማነጋገር ይችላሉ።
በይፋ የሚሸጡ ያላደጉ አገሮች ኮርፖሬሽኖች/ኩባንያዎች ጥቂት ከመሆናቸው ባሻገር፣ የተመዘገቡትም እምብዛም ዕውቅና የሌላቸው እንደ መሆናቸው፣ በእነዚህ አገሮች የዲያስፖራ ፈንዶች የዋጋ ትመና የማድረግ አገልግሎትም ሊሰጡ ይችላሉ።
የዲያስፖራ ቱሪዝምና ‹‹የአገር ቤት ምርቶች›› ንግድዲያስፖራዎች ለቱሪዝምና በትውልድ አገራቸው ለተመረቱ ወይም ከእናት አገራቸው ጋር ተያያዥነት ላላቸው የተለያዩ የአገር ቤት ምርቶች ገበያ በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የተለያዩ የዲያስፖራ ቱሪዝም ዓይነቶች መካከል የሕክምና ቱሪዝም፣ ከንግድ ጋር ተያያዥነት ያለው ቱሪዝም፣ የባህል (Cultural) ቱሪዝም፣ የትውውቅ ቱሪዝም፣ ትምህርታዊ ቱሪዝምና ‹‹የጀብድ ተሞክሮ›› ቱሪዝም (Adventure Tourism) ይገኙበታል።
አገሮች ያመረቷቸውን ወይም የእነሱ መገለጫ የሆኑ የተለዩ ምርቶችንና ቁሳቁሶችን ለዲያስፖራ ገበያ በማቅረብና በመሸጥ ጠቀም ያለ ገቢ ያገኛሉ። በስደት የሚኖሩ ቤተሰቦች የአገር ቤት ምርቶችንና ቁሳቁሶችን በተለይ ደግሞ ምግብ ነክ ነገሮችን በብዛትና በቋሚነት ይጠቀማሉ። ባህላዊ ዕቃዎችና አልባሳትን የመሳሰሉ የአገር ቤት ምርቶች በአብዛኛው በጉልበት የሚመረቱና ጥበብ የሚንፀባረቅባቸው እንደ መሆናቸው፣ የሚያስገኙት ገቢ በአገር ቤትና በቤተሰብ ደረጃ የሚያስደስት ነው። በአሜሪካ የባህላዊ ዕቃዎችና አልባሳትን የመሳሰሉ የአገር ቤት ምርቶች በዳያስፖራ የንግድ ትስስሮች በሚገባ የተደራጁ ሲሆኑ፣ ከ50 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ዳያስፖራ የአገር ቤት ምርቶችን ነው የሚገዛው።
የዲያስፖራ በጎ አድራጎትበግለሰቦች የሚደረግ የበጎ አድራጎት ሥራ በአገሮች የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው የሚገኘው። ባላደጉ አገሮች አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ውስጥ ከመደበኛው የልማት ድጋፎች ይልቅ የግለሰቦች በጎ አድራጎት ከፍ ያለ ድርሻ የያዘ ነው። የግለሰብ በጎ አድራጎቶች መደበኛ የልማት ተቋማት የያዙትን ያህል የሙያ ክህሎትና ሀብት፣ እንዲሁም የግል የንግድ ተቋማትን ያህል የረዥም ጊዜ የልማት አቅም ላይኖራቸው ቢችልም ሁነኛ የልማት አቀጣጣዮችና የፈጠራ አመንጪዎች ሆነው ያገለግላሉ። አንዳንዴም ጠቀም ያለ ሀብት ያቀርባሉ።
ፈቃደኞችን የመመልመልና የመቅጠር ዓላማን አንግበው የሚተገበሩ ፕሮግራሞች እንደ አጠቃላይ በስድስት ዋና ዋና ምድቦች የሚከፈሉ ሲሆን፣ ትኩረት የሚያደርጉባቸው መስኮችም የንግድ ዕድገትና የቴክኒክ ምክር፣ የኅብረተሰብ ጤና የአቅም ግንባታ፣ የድኅረ ግጭት ዕርዳታና መልሶ ማቋቋም፣ የከፍተኛ ትምህርት የአቅም ግንባታ፣ የፖሊሲ ማማከር አገልግሎቶችና የወጣቶች ፕሮግራሞች ናቸው። ዲያስፖራዎች በአገር ቤት በሚከሰቱ ርዕደ መሬት፣ ድርቅና ግጭቶችን በመሳሰሉ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከሰፊው የዲያስፖራ የሰው ኃይል፣ የፋይናንስና የማኅበራዊ ሀብት በተሟላ ሁኔታ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች፣ ዲያስፖራውን በስፋት በማነቃነቅ በሁሉም የአገሪቱ ብሔራዊ የዕድገትና የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያስችሉና ፈጠራ የታከለባቸው የተቀናጁ ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመንታኅሣሥ 7/2013