
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ አበባ፦ የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት መብት አዋጅ ቁጥር 568/2000 ጠንካራና አስገዳጅ በሆነ መልኩ ባለመዘጋጀቱ ተፈፃሚነቱ ላይ ክፍተት በመፍጠሩ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሚኒስቴሩ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አመዲን ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት መብት አዋጅ ቁጥር 568/2000 ተፈፃሚነቱ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ሊደረግ ይገባል።
እንደ አቶ አሳልፈው ገለጻ፤ አዋጁን ጠንካራና አስገዳጅ በሆነ መልኩ ስላልተዘጋጀ በተፈፃሚነቱ ላይ ክፍተት ፈጥሯል። በመሆኑም የአዋጁ የማስገደድ አቅሙን ጠንካራ አድርጎ ማዘጋጀት ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። ለምሳሌ፣ በአንቀጽ 6(4) ማንኛውም አሰሪ ለአካል ጉዳተኞች የስራና የስልጠና አካባቢ የማመቻቸትና ተስማሚ የሆነ የስራ ወይም የስልጠና መሳሪያዎች የማሟላት ኃላፊነት እንዳለበትም ይደነግጋል።
ይሁን እንጂ አንድም የመንግስትም ሆነ የግል ተቋም ሲጠየቅ አይሰማም። ይህ ደግሞ ችግሩ ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን፤ በአዋጁ የተካተቱ የህግ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ባለመደረጋቸው ምክንያት ነው። ተጠያቂነት የሌለበትና የማያስገድድ ህግ ሁሉ ተፈፃሚነት ላይ ደካማ ይሆናል።
ከአዋጁ አወጣጥ ጋር ተያይዞም ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ አሳልፈው፤ የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት መብት አዋጅ ቁጥር 568/2000 ሲወጣ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዳልነበረ አስታውሰዋል። በመሆኑም በአዋጁ አዋጣጥ ላይ የጉዳዩ ባለቤቶች ተሳትፎ አለመኖር አዋጁ ማካተት የሚገባቸው ብዙ ነጥቦችን ሳያካትት እንዲቀር ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል። አዋጁ ከወጣ በኋላ እሱን የሚያስፈጽም ደንብ ያልወጣለት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህ ደግሞ አዋጅ ሲወጣ ከሱ የሚቀዳ ደንብ መኖር ያለበት ቢሆንም፤ አዋጅ ቁ. 568/2000 ግን ደንብ ሳይዘጋጅለት መመሪያ የተዘጋጀለት መሆኑን አስታውሰዋል። በዚህ ረገድ የራሱ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ አዋጁ መሻሻል፤ አዋጁን ማስፈፀሚያ ደንብና መመሪያዎች ማውጣት እንዲሁም፤ አዋጁን የሚያስፈፅም ጠንካራ የሆነ አስፈፃሚ አካል መፍጠር ይገባል። ለዚህም በተቋሙ በኩል ከአዋጁ ጋር ተያይዞ የተጠቀሱትን ክፍተቶች መሰረት በማድረግ በአዋጁ አፈፃፀም ሁኔታን ላይ ዳሰሳ ተሰርቶ ለመንግስት የማሻሻያ ሃሳብ የሚያቀርቡ መሆኑን ነው አቶ አሳልፈው የገለጹት።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2013