ፍሬህይወት አወቀ
የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታመናል። ይህ ዘርፍ ውጤታማ የሚሆነው ታዲያ በጤናማ የንግድ ውድድር ውስጥ ማለፍ ሲችል ነው። ያኔ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትና የዜጎች ገቢ እንዲጨምር ያደርጋል። ነገር ግን በተቃራኒው የግሉ ዘርፍ የሚበረታታ ካልሆነና ምቹ የመወዳደሪያ ሜዳ ካልተፈጠረለት የሀገር ኢኮኖሚ የሚፈለገውን ዕድገት አያስመዘግብም።
ስለሆነም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ድርሻ ያላቸው የግል ባለሀብቶች ሊበረቱና ሊበረታቱ ይገባል። ለዛሬ ሉና ኤክስፖርት ቄራ ድርጅትን በስኬት እንግዳችን ይዘን ቀርበናል።
አቶ ተስፋልደት ሀጎስ የሉና ኤክስፖርት ቄራ መስራችና ባለቤት ናቸው። ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የእንስሳት ሀብት በመረዳት ከዛሬ 18 ዓመት በፊት ዘርፉን ተቀላቅለዋል። እንስሳትን አርዶ እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ሀገሪቷ ያላትን የእንስሳት ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል ያለመው ሉና ኤክስፖርት ቄራ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከሚገኙ ስጋ ላኪ ድርጅቶች መካከል የቀዳሚነት ስፍራ ይዟል።
የዛሬ 18 ዓመት ሥራ የጀመረው ሉና ኤክስፖርት ድርጅት ከሀገር ውስጥ አቅርቦት አልፎ እሴት ተጨምሮበት የሚዘጋጅ ትኩስ ስጋ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል። ድርጅቱ 200 ሰዎችን ቀጥሮ ወደ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ ሥራው እየሰፋ ሲሄድ የሰው ኃይሉንም በመጨመር በአሁኑ ጊዜ ለ850 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይም የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከዚህም በላይ ሀገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመቅረፍ የድርሻውን እየተወጣ ያለ ቀዳሚ ስጋ ላኪ ድርጅት ለመሆን በቅቷል።
ድርጅቱ የተለያዩ ፈተናዎችን አልፎ ለስኬት የበቃ ሲሆን፣ ከጅምሩ ይዞ የተነሳውን ዓላማ ለማሳካትም በጥረት እየሰራ መሆኑን የሚናገሩት የሉና ኤክስፖርት መስራችና ባለቤት አቶ ተስፋልደት ገበያውን በተሻለ ሁኔታ እየመራና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን እያሰፋ ወደ ውጭ የሚላከውን የስጋ መጠን በመጨመር ተወዳዳሪነቱን ከፍ ማድረግ መቻሉን ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንዳሉት ሉና ኤክስፖርት ቄራ ወደ ስራው በገባበት የመጀመሪያ ዓመት ላይ ምርት ወደ ውጭ መላክ አልቻለም ነበር። ለአንድ ዓመት ያህል በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ፍየሎችን እያረደ ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ነው የቆየው። ለአንድ ዓመት በዚህ ሁኔታ ቆይታ ካደረገ በኋላ ነው ምርቱን ወደ ውጭ መላክ የጀመረው። የገበያ መዳረሻዎቹም ሳውዲ ዓረቢያና ዱባይ ነበሩ።
የስጋ ምርት ወደ ውጭ በመላክ በሀገሪቱ ቀዳሚ የሆነው ሉና ኤክስፖርት ቄራ ሲጀምር 200 ፍየሎችን ለማረድ አንድ ቀን ሙሉ ፈጅቶበታል። በሂደት ግን አሰራሩ ተሻሽሎ በየቀኑ እርድ በማከናወን በአሁኑ ጊዜ በቀን እስከ 1ሺህ500 ፍየሎችና በጎች ዕርድ በማከናወን ለገበያ የማቅረብ አቅም ፈጥሯል። በወር ውስጥም በአማካይ 45 ሺህ ፍየሎችና በጎች ዕርድ ይከናወናል።
ሉና ኤክስፖርት ቄራ በየዕለቱ ወደ ውጭ ሀገር ገበያ ከሚልከው የስጋ ምርት በአማካይ በዓመት 20 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኛል። የስጋ ወጪ ንግድ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ በተለይም በሚያስገኙ የውጭ ምንዛሪ ትልቅ ድርሻ ያለው ዘርፍ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ያልተሰራበት ዘርፍ ነው። ለአብነትም ሉና ኤክስፖርት ቄራ በዓመት አሁን ከሚያስገባው 20 ሚሊዮን ዶላር በበለጠ 100 ሚሊዮን ዶላር ማድረስ የሚቻልበት ዕድል አለ። ነገር ግን ከድርጅቱ ቁጥጥር ውጭ በሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች ድርጅቱ የዕቅዱን መቶ በመቶ ማከናወን አልቻለም።
ሞጆ የሚገኘው ሉና ኤክስፖርት ቄራ በ18 ዓመት የስራ እንቅስቃሴው አንድ ጊዜ መዘጋቱን አቶ ተስፋልደት ያስታውሳሉ። እርሳቸው እንዳሉት በወቅቱ ድርጅቱ የነበረበትን ክፍተት አሻሽሎ ሥራውን ዳግም በመጀመር አሁን ድረስ ዘልቋል። በየዓመቱ በሚደረገው የጥራት ቁጥጥር በሥራው እየቀደመ መጥቷል። በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታወቀው ኤፍ ኤፍ ሲ ከተባለ የምግብ ጥራት ደረጃ ተቆጣጣሪ በጥራቱ ዕውቅና ማግኘት ችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም እኤአ በ2020 አሜሪካን ሀገር ላይ በተደረገ ዓለም አቀፍ የምግብ ደህንነት ውድድር ከአፍሪካ የአንደኛ ደረጃነትን አግኝቷል። ውድድሩ የተካሄደው በአሜሪካ ሲያትል ሲሆን አቶ ተስፋልደትም ቦታው ድረስ በመገኘት ሽልማቱን ተቀብለዋል።
ሁሉም ስራ በጥራት መሰራት እንዳለበት የሚያምኑት አቶ ተስፋልደት፤ በተለይም በወጪ ንግድ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ ምርት ማምረት የግድ ነው ይላሉ። እንስሳቱ የሚመገቡትን ምግብ የተሻለ በማድረግ እንዲሁም ጤናቸውን በመጠበቅ ጥራት ያለውን የስጋ ምርት ለማቅረብ የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጋሉ። በዚህም በሀገሪቱ በስጋ ንግድ ተሰማርተው ስጋ ወደ ውጭ ገበያ ከሚልኩ 13 ቄራዎች መካከል ሉና ኤክስፖርት ቄራ ድርጅት ቀዳሚ ነው።
ድርጅቱ ከሀገሪቱ ስጋ ላኪዎች መካከል ቀዳሚ ቢሆንም ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ሀብት ልክ የስጋ ምርት ወደ ውጭ መላክ እንዳልቻለች አቶ ተስፋልደት ያነሳሉ። አሁን በሀገሪቱ ያለውን የእንስሳት እርባታ በማሻሻል ሀገሪቱ ጥራት ያለው የስጋ ምርት በስፋት ወደ ውጭ መላክ እንድትችል በእንስሳት እርባታው ላይ ለመሳተፍ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።
እንስሳቱ ከውልደታቸው ጀምሮ አመጋገባቸውን ጤናማ በማድረግ ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት ከአርብቶ አደሩ ጋር በጋራ ለመስራት የዛሬ ሰባት ዓመት ፕሮጀክት ቀርጸው ለመንግስት ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
ድርጅቱ በአሁን ወቅት እንስሳቱን ሰብስበው ከሚያመጡ ነጋዴዎች ተረክቦ ያርድና ትኩስ ስጋ ወደ ውጭ ገበያ ይልካል። የስጋ ገበያ ፍላጎቱ የሚቀያየር መሆኑን አቶ ተስፋልደት ያነሳሉ። በረመዳን የበዓል ወቅት ስጋ በብዛት የሚፈለግ በመሆኑ ሰፊ ትዕዛዝ ይኖራል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ገበያው የሚቀዛቀዝ በመሆኑ ቄራዎች ከአርብቶ አደሩ ጋር በጋራ መስራት እንዳለባቸው ያምናሉ። ቄራዎች ገበያው በሚጠይቃቸው ጥራትና መጠን ልክ መላክ የሚቻል በመሆኑ ገበያውን በቋሚነት ለመቆጣጠር ጥራት ላይ መስራት እንዳለበት ይናገራሉ።
አቶ ተስፋልደት ከዚህም ስራቸው ጎን ለጎን አትክልት በማልማት ውጤታማ ናቸው። ወደ ቄራ የሚገቡት እንስሳት ከመታረዳቸው በፊት ለተወሰነ ጊዜ በሚቆዩበት ቆቃ አካባቢ አትክልት ያለማሉ። የአካባቢውን አርሶ አደሮችም አደራጅተው በራሳቸው መሬት ላይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ካሮትና ቃሪያ ማምረት እንዲችሉ ያበረታታሉ። ለዚህም የእርሻ መሳሪያ፣ ዘር በመስጠትና የባለሙያ እገዛ እንዲያገኙ በማድረግ አርሶአደሮቹ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
ለምሳሌ ያህል ሲጠቅሱም፤ አርሶ አደሩ በተደረገለት ድጋፍ ሽንኩርትና ቲማቲም አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆኗል። ይሄንን ያዩ ሌሎች አርሶ አደሮችም ተሳታፊ ሆነዋል። በአሁኑ ጊዜ 135 አርሶ አደሮች ተደራጅተው በጋር የሚያመርቱትን አትክልትና ፍራፍሬ የሉና ኤክስፖርት ቄራ እህት ድርጅት ለሆነው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለያየ ቦታ ለሚገኘው ፍሬሽ ኮርነር ሱፐር ማርኬት በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል። ድጋፍና ክትትሉ አርሶ አደሮቹ በራሳቸው የእርሻ ቦታ ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
አርሶ አደሮቹ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። ለዚህ ዋናው ምክንያት በሀገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት የአትክልት ማቀዝቀዣ ቤቶችና በርካታ ማሽኖች በመቃጠላቸው ነው። ይሁን እንጂ በቀጣይ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩን በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያደርጉትን ድጋፍና ጥረት ተስፋ ሳይቆርጡ እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ።
አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ የስጋ ወጪ ንግዱን ማሻሻል ይቻላል ብለው ያምናሉ። በትንሽ ስራ መሰረታዊ ችግር የሆነውን ድህነት ለማጥፋት አርሶና አርብቶ አደሩን መደገፍ የግድ ነው ይላሉ። አርብቶ አደሩ እንስሳቱን ሲያረባ ባለሀብቱ የተለያዩ ድጋፎችን ማለትም ምርጥ ዘር፣ በማዳቀል፣ የእንስሳት መኖ በማቅረብና የእንስሳቱን ጤና በመጠበቅ ጥራት ያለው እንስሳት በአጭር ጊዜ ማግኘት እንዲችል ድጋፍ እንዲያደርግ ተነሳሽነት ወስደውና ፕሮጀክት ቀርጸው ለመንግስት አቅርበዋል።
አቶ ተስፋልደት፤ በተሰማሩበት የስጋ ወጪ ንግድ እና ለሀገር ውስጥ የአትክልት አቅርቦት ስራ ስኬታማ መሆን የቻሉ ባለሀብት ናቸው። የተለያዩ ማሽኖች፣ መኪናዎችና መሰል ንብረቶችን ማፍራት ችለዋል። በቀጣይ ደግሞ ዛሬ በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰነውን የአትክልት ንግድ ወደ ውጪ ኤክስፖርት ለማድረግ ሰፊ ዕቅድ አላቸው።
በሀገር ውስጥ አሁን የሚታየውን የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ንረት በማርገብ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መሰረታዊ የሆኑ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ቃሪያና ካሮት ማግኘት ለማስቻል ነው። እርሻውን በማጠናከር አሁን በከተማ ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ በማቅረብ ላይ የሚገኙትን አስር የገበያ ማዕከሎች ቁጥር እስከ 50 ለማድረስ ቀጣይ እቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ።
አቶ ተስፋልደት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማህበረሰቡ በመስጠት ማህበራዊ ግዴታቸውን የሚወጡ ባለሀብት ናቸው። በዚህም በማህበራዊ አገልግሎት ቆቃ አካባቢ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርበዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኝ በአንድ የመንግስት ትምህርት ቤት ለ135 ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ድጋፍ ያደርጋሉ። ይሄንን ፕሮግራም የጀመሩት የከተማ አስተዳደሩ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ምገባ ከመጀመሩ በፊት ሲሆን፤ አሁንም በጎ ተግባራቸውን ቀጥለዋል።
ሉና ኤክስፖርት ቄራ በየዕለቱ ትኩስ ስጋ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ በሀገሪቱ ካሉት 13 ቄራዎች ቀዳሚ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። የስጋ ወጪ ንግዱን በጥራት ማምራትና የገበያ ተደራሽነቱን ማስፋት የግድ በመሆኑ በዚሁ ዙሪያ ጠንክረው በመስራት ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ተወዳዳሪ መሆን የምትችል እና የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር በመሆኗ በቀጣይም ይህን ሀብት በመጠቀም ከአርብቶ አደሩ ጋር በጋራ በመስራት ዘርፉን ማሻሻልና ኢኮኖሚውን ማሳደግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
በተለይም ሁልጊዜ ቋሚ የሆነ ገበያ እንዲኖር አሁን ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ጥረት እያደረጉ ያሉት አቶ ተስፋልደት፤ መለያቸውን በመፍጠር ቋሚ ገበያ ለማግኘት ይሰራሉ። አሁን ለውጭ ገበያ እየላከ ካለው የስጋ መጠንና ጥራት በበለጠ ዘርፉን ማሳደግ ዓላማው ነው። ለዚህም እንስሳቱ ከሚመገቡት ምግብ አንስቶ የጤና ሁኔታቸውን በመከታተል ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለማቅረብ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት የግሉ ዘርፍ የጎላ ሚና እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ። ዘርፉ ጤናማ የንግድ ስርዓትን ተከትሎ ሲሰራ ደግሞ ሀገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከመቅረፍ ባለፈ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠርና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ክፍተቶችን መቅረፍ ይችላሉ። በመሆኑም እንግዳችን በተሰማሩበት ዘርፍ ሚናቸውን በመወጣትና ወደፊትም የበለጠ ለመሥራት የተነሳሱ በመሆናቸው በአርአያነት የሚጠቀሱ ባለሀብት ለመሆን ችለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2013