አዲስ አበባ፡- የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተፈጥሮ ከነበረው የጸጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ ተላቃ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እየተመለሰች መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የቃል ማቀበል ባለሙያ አቶ ኤልያስ ደለለኝ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ባለፈው ሳምንት ተፈጥሮ የነበረው ሁከት በመወገዱ በአሁኑ ወቅት ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀድሞ ሰላሟ ተመልሳለች ።
ችግሩ የጥምቀት በዓልን አክብረው በሚመለሱ ምዕመናን መካከል መነሳቱን ጠቅሰው፣ ጸቡ ፖለቲካዊ መልክ እየያዘ መምጣቱንና መነሻውና መጨረሻውም ፍጹም የማይገናኝ መሆኑን አስታውቀዋል። አስተዳደሩ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያሳየው ትእግስት ውጤት አለማምጣቱን ጠቅሰው፣ ችግሩም ወደ አጎራባች አካባቢዎች በመዛመቱ የምስራቅ እዝ መከላከያ ሀይል በመሀል ገብቶ አንዲፈታው መደረጉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ሁኔታ የተረጋጋና ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚታይበት መሆኑን አስረድተው፣ ሁሉም ሰው ወደ መደበኛ ሥራው ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሳቸውን አብራርተዋል።
በግጭቱ ስለጠፋው የሰው ህይወትም ሆነ ንብረት ዝርዝር መረጃ የለኝም ያሉት ባለሙያው፤ ሆኖም የከፋ ጉዳት እንዳልደረሰ ገልጸዋል፡፡ ወጣቶቹ መንገድ በመዝጋት ጎማዎችን በማንደድ ነው ተቃውማቸውን ሲገልጹ የነበረው ብለዋል ።
በዚህ ሁከትና ብጥብጥ እጃቸው አለበት የተባሉ አካላትም ለፍርድ የሚቀርቡበት ሁኔታ አለ ያሉት ባለሙያው ፣እስከ አሁንም ጉዳዩን ሲያስተባብሩ ከቦታ ቦታ እንዲዛመት ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው የተባሉ ከ200 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ከበስተጀርባቸው ማነው ያለው የሚለውም እየተጣራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011
እፀገነት አክሊሉ