አዲስ አበባ ፡- አምባሳደሮች የዜጎችን መብት በማስከበርና የአገርን ብሔራዊ ጥቅሞች በማረጋገጥ በኩል ሰፊ ሚናቸውን ሊጫወቱ እንደሚገባ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታወቁ።
ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በቅርቡ በተለያዩ አገራት ለተመደቡ አዲስና ነባር አምባሳደሮች የሚሰጠውን ስልጠና ትናንት በሒልተን ሆቴል በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት፤ አምባሳደርነት ትልቅ ኃላፊነትን መሸከም ነው፡፡
በተመደባችሁበት አገር ያሉ ዜጎችን መብት ለማስከበር እንዲሁም የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ መስራት አለባችሁ ሲሉ አምባሳደሮቹን አስገንዝበዋል።
‹‹ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትን ሀገር ወክሎ ለዚህ ሥራ መመደብ መታደል ከመሆኑም በላይ የዜጎችንና የአገርን ሁለንተናዊ ጥቅም የማስከበሩም ኃላፊነት በእጃችሁ ነው››ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፣ አምባሳደሮቹ ይህንን እድል መጠቀምና ታሪካዊ ሥራ ማከናወን እንደሚገ ባቸው አሳስበዋል።
«ሁላችሁም ከተለያየ የሥራ መስክ የመጣችሁ ብትሆኑም ለተቋሙና ለሀገር ሠርታችሁ የእናንተን መደመር ተቋማዊ ቅርፅ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል» ሲሉም አስረድተዋል።
ብዙ ጊዜ አገሮች ድምፃቸው ከፍ ብሎ የሚሰማው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ስለሚሠሩ እንደሆነም ጠቅሰው፣ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት፣ በውጭ ያሉ ዜጎች ለሀገራቸው ግዴታቸውን እንዲወጡ በማስተማር፣ የዜጎችን መብት በማስከበር እና በመከራከር መሥራት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ዕውቀት የቴክኖሎጂ ሽግግር ባለሙያ የገንዘብ አቅምን በመጠቀም ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ዲፕሎማት ለአለቃው ሳይሆን ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም መሥራት እንዳለበት ተናግረው፣ ‹‹ዲፕሎማሲ ከሚሲዮን አጥር ግቢ እየወጣ ነው፣ ሥራችን የውስጥ ጉዳይ፣ የውጭ ጉዳይ ፣ ናይልን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብቶች ሌሎችን በርካታ ነገሮች የሚያካትት ነው ፤ወደ ግጭት የሚያደርሱ ነገሮች ካሉ መከላከል የምንችለው ያለምንም ጦር መሣሪያ በጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ነው ሲሉም ገልፀዋል።
በመድረኩ ሃያ አምባሳደሮችና ሁለት ሚሲዮኖች እየተካፈሉ ሲሆን፣ በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ የአምባሳደሮቹ ባለቤቶችም ይሳተፋሉ። ይህም በሥራው ዙሪያ ግንዛቤ ለመሥጠትና የዲፕሎማሲ አካሄዱን ለማቀላጠፍ የታሰበ አዲስ ጅምር ነው ተብሏል።
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011
ኃይለማርያም ወንድሙ