አስመረት ብስራት
አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ ወይም ክፍያ ግለሰቦች ወይም ቤተሰቦች የጤና መታወክ ባጋጠማቸው ጊዜ ካልታሰበ ከፍተኛ የህክምና ወጪ የሚጠበቁበት ስልት የሆነው ጤና መድን ከፅንሰ ሃሳቡ ጀምሮ እስከአሁን የመጣው መንገድ ምን ይመስላል? የሚሉና በጤና መድን ዙሪያ ያሉ የተለያዩ ጉዳዮችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበን አነጋረናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፦ ጤና መድን ማለት ምን ማለት ነው?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ ጤና መድን ማለት አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ አባል ወይም ቤተሰቦች የጤና መታወክ ሲያጋጥማቸው የህክምና ወጪዎችን የሚሸፈንበት መንገድ ነው። ጤና መድን ማለት በአጭሩ የቁም እድር ነው። ስለዚህ የጤና መድን ገቢ በሚገኝ ወቅት አነስተኛ መዋጮ በማዋጣት ወይም በመክፈል ግለሰቦች ከነቤተሰቦቻቸው ሲታመሙ ካልታሰበ ከፍተኛ የህክምና ወጪ የሚድኑበት መንገድ ነው። ጤና መድን ገንዘብ በኪሱ ሳይኖር ህክምና ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት አንድ ሰው በዓመት ሦስት ጊዜ የጤና ተቋማትን መጎብኘትና መጠቀም እንደሚኖርበት ያስቀምጣል። የዓለም ጤና ድርጅት ይህን ቢልም አብዛኛው ህብረተሰብ በገንዘብ እጦት ምክንያት ወደ ህክምና ተቋማት የሚሄድበት ሁኔታው አነሰተኛ ነው። ጤና መድን ግን በቅድመ ክፍያና ስጋትን በመጋራት የጤና ፋይናንስ ስርዓት በገጠርና በከተማ የሚገኙ መደበኛ ባልሆኑ ዘርፎች የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ወደ ድህነት አዝቅት እንዳይገቡ የሚከላከል ነው።
አዲስ ዘመን፦ በሀገራችን የጤና መድን መቼ ተጀመረ?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ እንደ ሀገር እንቅስቃሴ የተጀመረው በ2002 ዓ.ም ነበር። በ2003 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን የሙከራ ትግበራ ተከናወነ በመቀጠል በ2004 ዓ.ም ክልሎቹ ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የሙከራ ትግበራ መመሪያ በማውጣት በ2004 ዓ.ም መጀመሪያ 13 ወረዳዎች የማህበረስብ አቀፍ የጤና መድን ትግበራ ጀመሩ። ትግበራው ላይ የታዩ ችግሮችን በመንቀስ በ2005 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን የሙከራ ትግበራ መመሪያ ተከለሰ፣ 2008 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት የሚያስችል ስትራተጂ እና የማስፋፊያ መመሪያ ወጣ፣ 2012/13 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አዋጅ ዝግጅት ተደርጎ መፅደቁን እየተጠባበቀ ይገኛል። ይህ መመሪያ ሲፀደቅ በትብብርና በዘልማድ የሚሠራውን ሥራ ተጠያቂነትን ባስቀመጠ መልኩ ለመሥራት ያስችላል።
አዲስ ዘመን፦ ጤና መድን ለምን አስፈለገ?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ መንግሥት እንደ መንግሥት የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ማዳረስ ይኖርበታል። ይህንንም ለማከናወን እየሠራ ነው። ነገር ግን ለህክምና መስጫ የሚሆኑ ቤቶች ተሠርተው በውስጣቸው ግን በርከታ የጤና አገልግሎትን በአግባቡ እንዳይዳረስ ያደረጉ ግብአቶች እጥረት አለባቸው። ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ደግሞ የገንዘብ አቅምን ማጎልበት ግድ ሆኖ ተገኝቷል። ሁሉንም የህክምና አገልግሎት በነፃ ማዳረስ ከመንግሥት አቅም በላይ ነው።
ህብረተሰቡም በአቅሙ ልክ ቆጥቦ በህመሙ ልክ የሚታከምበት ስርዓት በመሆኑ መነግሥትና ህዝቡ ተጋግዞ ተገቢው አገልግሎት እንዲገኝ ያደርጋል ማለት ነው። ከዚሀም በተጨማሪ ጤና መድን የድሃ ደሃ የሆኑ የህብረተስብ ከፍሎች በነፃ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ የሚያስችልበት ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል።
በሀገራችን የጤና መድን ለመተግበር ገና በ1986 ዓ.ም በወጣው የጤና ፖሊሲ ላይ ተመላክቷል። በዚህም መሠረት የጤና መድን አንድ ሰው በኪሱ ገንዘብ ሳይኖር የህክምና አገልግሎት ማግኘት ያስችላል፤ የህክምና ወጪ ለመቀነስ ያግዛል በሚል እሳቤ ወደተግበራ ለመግባት ተችሏል። ይህ ተግባርም በህብረተሰቡ ዘንድ መደጋገፍን ያጎለብታል፤ከዕርዳታ ነፃ ለመውጣት ያስችላል፤ ለጤና ሴክተር ከፍተኛ የፋይናንስ ምንጭ ይሆናል።
የአገልግሎት ተጠቃሚነትን ስለሚያሳድግ የጤና ተቋማት ገቢያቸው ስለሚጨምር የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎችን በማሟላት ተጠቃሚነትን ያሳድጋል። በውጭ ድጋፍ ላይ የተንጠለጠለ የጤና አገልግሎት እንዳይሆን ከህበረተሰብ በሚሰበሰብ ገንዘብ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው። እንዳጠቃላይ ሦስት ዓይነት የጤና መድን ዓይነቶች አሉ።
አዲስ ዘመን፦ ሦስት ዓይነት የተባሉት የጤና መድኖች ምን ምን ናቸው?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን፣ ማህበራዊ ጤና መድን እና የግል የጤና መድን ይባላሉ። ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። በተለይ 80 በመቶ የሚሆነው የገጠር ማህበረሰብ ክፍልን ይወክላል።
ማህበራዊ ጤና መድን በአብዛኛው ጊዜ በተለይ በመንግሥት ሠራተኛውና በጡረተኛው ዘንድ የጤና ወጪ በሚጨምርበት ጊዜ በሚነሱ ጥያቄዎች የሚጀመር የጤና መድን ሲሆን፤ 25 በመቶ የሆነውን የማህበረሰብ ክፍል ይሸፍናል። የግል የጤና መድን በግል ደረጃ ግለሰቦች የጤና ኢንሹራንስ ወይም መድን የሚገቡበት ስርዓት ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ ትርፋማ የጤና መድን ነው ይባላል። አሁን ላይ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ስርዓት ላይ እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ምንድነው?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ማለት ቋሚ ወርሐዊ ገቢ ወይም ደመወዝ የሌላቸውን ሰዎች በአንድ ላይ በመሰብሰብ የሚገጥማቸውን የህክምና ወጪ በጋራ መተሳሰብና መደጋገፍ መርህ ለመጋራት የሚያቋቁሙት፣ ለትርፍ ያላለመ፣ የጤና አገልግሎትን እንደ ፍላጎት በመግዛት የህክምና ተጠቃሚነትን የሚያሻሽልና ለጤና እንክብካቤ አገልግሎት የፋይናንስ ስርዓትን የሚያሳድግ ማህበራዊ ተቋም ነው።
በመተግበር በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖረውን አርሶ አደር ጨምሮ መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ክፍል አንድ ላይ በመሰብሰብ በህመም ወቅት ከኪስ የሚከፈለውን የህክምና ወጪ ለማስቀረት የዘመናዊ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚነቱን ማሳደግ የሚችል ነው። በአባላት መካከል በተናጠል የሚያጋጥምን የህመምና ስጋት በጋራ በመተሳሰብና በመተጋገዝ መርህ በመከተል ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ተደራሽ በማድረግ በወረዳው የሚኖረው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከመላው የቤተሰብ አባሉ ጋር ጤናው ተጠብቆ ምን እከፍላለለሁ፤ ገንዘብ የለኝም ብሎ ሳይጨነቅ ውል ወደ ተያዘለት ጤና ጣቢያ ተቋምና የሪፈራል ስርዓቱን በመጠበቅ ሆስፒታል በመሄድ የህክምና አገልግሎት የሚገኝበት በመሆኑ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ ያለው ነው።
በተግባር ወደ እንቀስቃሴ ይገባል የተባለውና በ2015 ዓ.ም ወደተግባር ይገባል የተባለው አሁን መደበኛ ባልሆኑ የሥራ ዘርፎች ላይ የሆኑትን ከማገልገል በተጨማሪ በተግባር በመደበኛ ሥራ ዘርፍ የተሰማሩበትን ሰዎችን ተጠቃሚ የማድረግ ሰርዓት በመዘርጋት ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ባለው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ተጠቃሚው ማነው?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ መንግሥት ዋናው ዓላማው ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ነው። ይህን ስርዓት የዘረጋው። ህብረተሰቡ ሲጠቀም ነው መንግሥት ተጠቃሚ የሚሆነው። አሁን ባለው ስርዓት በጣም ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያለውን ሰው ተጠቃሚ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፦ ጤና መድን ለአባላቱ ምን ዓይነት የህክምና አገልግሎቶችን ያቀርባል?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ የጤና መድን ሰው ቀድሞ ለጤናው የሚያቅድበት ከሆነ ለየትኛው ጤና አገልግሎት ነው የሚታቀደው የሚለውን አባለቱ ማወቅ አለባቸው። በዝቅተኛ ወጪ ከሚገኘው እስከ ከፍተኛው ድረስ የጤና አገልግሎት መደበኛ የሆኑ የጤና አገልግሎቶች በሙሉ ይካተታሉ። የማይካተቱት ውስን የሆኑ ናቸው።
በጣም ትልልቅ ገንዘብ ሊያስከፍሉ የሚችሉ ዓይነት ህክምናዎች ብቻ ካልሆኑ በስተቀር ሌሎቹ በሙሉ ይካተታሉ። በመደጋፍ የሚካሄድ የህክምና ስርዓት ውስጥ አንድ ሰው ብቻ ለረጅም ጊዜ በማከም ገንዘቡ እንዳያልቅ ለረጅም ጊዜ የህክምና ክትትል የሚፈለጉ የህክምና ዓይነቶችን አያካትትም።
በአጠቃላይ ግን የተመላላሽ ሕክምና፤ የተኝቶ ሕክምና፤ የቀዶ ህክምና፤ በሕክምና ባለሙያዎች የታዘዙ የምርመራ አገልግሎቶች፣ ፅንስ ህክምና መድሀኒቶች በአገልግሎቱ በጣም ትልልቅ የሚባሉ ከልብ ቀዶ ህክምና ጀምሮ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገለፁ እስከ አራት መቶ የሚደርሱ የህክምና አገልግሎት ዓይነቶች ይታቀፋሉ።
አዲስ ዘመን፦ በጤና መድን የማይካተቱ የህክምና ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ ለረጅም ጊዜ የሚደረግ የህክምና ክትትል ማለትም እንደ ዲያሊስስ ወይም የኩላሊት እጥበት ዓይነቶች ከሀገር ውጪ የሚኬዲበት የህክምና ዓይነቶችን አያካትትም። እነዚህ የህክምና ዓይነቶች አይካተቱም ማለት ጤና መድን እስከ መጨረሻው ድረስ ይህን ግልጋሎት አይሰጥም ማለት አይደለም። የህብረተሰቡ የመከፈል አቅም እያደገ ሲሄድና የጤና መድን የገንዘብ አቅም ሲጎለበት አሁን አይከተቱም የተባሉት የጤና እክሎችን ሁሉ በጤና መድን ስር የሚታቀፉ ይሆናሉ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሁን በሀገራችን በተጨባጭ በቂ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነብት የጤና መድን አገልግሎት ምን ሊሠራ ይችላል ብለው ያስባሉ?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ የጤና መድን ስርዓት ውሰጥ ዋናው ዓለማው በመደጋገፍ ላይ የተሞረኮዘ አገልግሎት የማግኘት ስርዓት መዘርጋት ነው። ይህ ማለት በተለያየ መልኩ የህክምና አገልግሎትን ለማግኘት የሚያስችሉ አቅሞችን ለማጎልበት ያገዛል ማለት ነው። ሁሉ የህክምና አገልግሎቶች በመንግሥት ኃላፊነት ይሸፈናል ማለት አይደለም። መንግሥት ጤና ተቋማት ወስጥ ያልተገኘን አገልግሎት በግል ማግኘት የሚያስችል አሠራርም ይዘረጋል። የግል ጤና ተቋማትም የተደራጁት ለዓለማ ነው።
መንግሥት የግል ጤና ተቋማትን በማደራጀት የራሳቸውን ሚና በጤና መድን ውስጥ እንዲጫወቱ ይደረጋል። አሁንም ባለንበት ስርዓት ውስጥ በመንግሥት የህክምና መሰጫ የማይኖሩ መድኃኒቶችንም ምርመራንም በግሎቹ በማድረግ የከፈሉት ገንዘብ ተመላሽ እንዲሆንላቸው ይደረጋል።ይህ የአሠራር ስርዓትም በተመረጡ የግል ጤና ተቋማት ለመስጠት ስርዓት የማስያዝ ሥራም የሚሠራበት አግባብም ለመፍጠር ታቀዷል።
አዲስ ዘመን፦ ፕሮግራሙ ተግባራዊነቱ ላይ የተለያዩ እንቅፋቶች ገጥመውት እንደነበረ ይነገራል፤ ይሄንን እንዴት ይገልፁታል?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ የጤና መድን ከተጀመረ ስድስት ዓመታት ሆኖታል። እስከአሁን ባለው አካሄድ ጥሩ ሁኔታ ነው ያለው። እንዲህም ሆነው በርከታ እንቅፋቶች ገጥመውናል። ከእነዚህም ውስጥ በአስተዳደርም በፈፃሚ አካላት ላይ የታዩ ችግሮች ነበሩ። ከነበሩት ችግሮች መካከል ጥቂቶቹን ብጠቅስልሽ፤ የጤና ተቋማት ዝግጁነት አለመኖር፣ የመድሃት አቅርቦት ችግር፣ ላብራቶሪ አገልግሎት ችግር፣ የባለሙያ የስነ ምግባር ችግር መኖር፣ በህክምና አሰጣጥ ፕሮቶኮል መሰረት አለመሥራት፣ ተጠቃሚዎችን ያለአግባብ ወደ ውጭ መላክ፣ የክልልና የፌዴራል ቋት ባለመቋቋሙ ተጠቃሚዎች የሪፈራል ስርዓቱን ተከትለው አገልግሎት ለማግኘት ተጨማሪ ወጪ የሚያወጡ መሆኑ በህክምና መስጫ ተቋማት አካባቢ የታዩ ከፍተቶች ናቸው።
ከአመራር አንፃርም የታዩ ክፈተቶች ይኖራሉ፤ እነዚህም ከሦስተኛ ወገን ጋር ውል በማሰር ተገልጋዮች ሳይጉላሉ አገልግሎት እንዲያገኙ አለማድረግ፣ አመራሩ የሚገባውን ትኩረት ሰጥቶ ያልያዘው መሆን፣ የአባልነት ምጣኔ አነስተኛ መሆን ፤ በወረዳዎች መካከል የአፈጻጸም ልዩነት መኖር፣ የተቋሙ ሠራተኞች በከፍተኛ ሁኔታ መልቀቅና በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ አገልግሎት እስኪጀመር መዝግየት፣ በፎቶግራፍ እና በተለያዩ ምክንያቶች የመታወቂያ ስርጭት በወቅቱ አለማከናወን፣ ተጠቃሚዎች ከኪሳቸው ለሚያወጡት ወጪ የመተካት ወጥ አሠራርና መመሪያ አለመኖር ዋና ዋና ተግዳሮቶች ተብለው ከተለዩ ናቸው። እነዚህ ችግሮች በአግባቡ ከተለዩ በኋላ ለመፍታት እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ችግሮቹን ለመፍታትስ ምን ያህል ርቀት ለመሄድ ተችሏል?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ ከላይ እንደጠቀስነው የግል የጤና ተቋማት በጤና መድን ላይ የራሳቸው ሚና አላቸው። ይህም ሲባል የመድሃኒት እጥረት ሲከሰት መድሀኒት ከግል ተቋማት በመግዛት ወጪው እንዲጣጣ የማደረግ አካሄዶች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያለውን ክፍተት ለማቃለል አስችሏል። የግል ተቋማት የጤና ተደራሽንተን ለማዳረስ ክፍተት ሸፍነው እያገለገሉ ነው። በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ ነው። ሌላው የግበአት እጥረትን ለመቅረፍ ገንዘብ በተገቢው ሁኔታ ለመሰብሰብ ከተቻለ ያሉ ችግሮችን በሂደት ለምፈታተ የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር ተችሏል።
አሁን ደግሞ ጠያቂ ማህበረሰብ ለመፍጠር ተችሏል። ለጤናው አቅዶ የቆጠበው ማህበረሰብ የጎደለውን ሲያመለክት ጤና መድን ለተገልጋዩ በመሞገት ለተሻለ አገልግሎት ይሠራል። ይህንን ጉዳይ የሚከታተለው የተደራጀ አደረጃጀት ተፈጥሮ ክትትል ይደረጋል። በአጠቃላይ ችግሮቹ ቢኖሩም የአገልግሎትን የመሻሻል ሥራ በመሥራተ የጠራ የህክምና አገልግሎት ለሁሉም ዜጋ ለመስጠት የሠራል።
አዲስ ዘመን፦ በመጨረሻ ከአባላት የሚሰበሰበው መዋጮ ምን ያህል እንደሆነ ቢነግሩን?
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦ የአገልግሎት ስርዓቱ በመደጋግፍ ላይ የተሞረኮዘ በመሆኑ የአባላት መዋጮውን መክፈል ለአገልግሎቱ መሳካት ተቀዳሚ ተግባር ነው። በዚህም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ሥራ ላይ ያለው የመዋጮ መጠን፣ ለገጠር ብር 240፣ ለገጠር ከተሞች ብር 350፣ ለትልልቅ ከተሞች ብር 500 ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት የገቢ መጠንን ያገናዘበ የመዋጮ መጠን እንደሚተገበር በመመሪያው በመቀመጡ ነው።
ይህ የመጮ መጠን በ2013 ዓ.ም ተሻሽሎ ለክልሎች የተላለፈው የመዋጮ መጠን፣ ለገጠር ብር 375፣ ለገጠር ከተሞች ብር 500፣ ለትልልቅ ከተሞች ብር 665፣ በአርብቶ አደር አካባቢ 325፣ እንዲሆን ተወስኗል፣ ይህም የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ እየጨመረ የሚሄድበት ሁኔታም ይኖራል።
ህብረተሰቡ መረዳት ያለበት በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን አዲስ ነገር ሲጀመር የራሱ ችግሮች ይዞ መመጣቱን ነው። የጤና መድንም ሰው በፍቃዱ አገልግሎቱን እንዲጠቀም ለማድረግ የማሳመን ሥራው እጅግ ፈታኝ የሆኑ ወቅቶችን ማሳለፉን ነው። የታዩ ችግሮችንም ለማሻሻል ህብረተሰቡ ግንዛቤውን አሳድጎ በብዛት ተጠቃሚ መሆን ሲችል የጠራ አገልግሎት እየተፈጠረ ይሄዳል። ስለዚህም በመተጋገዝና በመደጋገፍ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ሁሉም ዜጋ የጤና መድን አባል መሆን ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ ፍሬህይወት፦እኔም አመሰግናለሁ።