የትግራይ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው። ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በመኖርና የሰላም ተምሳሌት በመሆን በአርዓያነት ሲጠቀስ የኖረ ነው። የትግራይ ሕዝብ የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር የሚችል ትልቅ ሕዝብ ነው። የትግራይ ሕዝብ ለሀገሩ ዳር ድንበር የሚዋደቅ፤ ከራሱ በፊት ሀገሩን የሚያስቀድም፤ ቅኝ ገዢዎችንና ሌሎች ወራሪ ኃይላትን አሳፍሮ የሚመልስ ጀግና ሕዝብ ነው።
ሆኖም ይህ ሕዝብ ለዘመናት በጦርነት ሲጎዳ ቆይቷል። የትግራይ ሕዝብ ላለፉት 100 ዓመታት ባልተገቡ ጦርነቶች ውስጥ እንዲያልፍ ተፈርዶበት ቆይቷል። በረባ ባልረባው በሚነሱ ጦርነቶች የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖር እና ኑሮውንም እንዳያሻሽል ችግር ገጥሞት ቆይቷል። በተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ ተጎጂ ሆኖ የኖረው የትግራይ ሕዝብ ነው።
ከሁለት ዓመታት በፊትም በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች በፈጠሩት የተሳሳተ ስሌት የትግራይ ሕዝብ ወደአልተገባ ጦርነት ገብቶ በርካታ ወጣቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ አካለጎዶሎ ሆነዋል፤ በርካቶች ተፈናቅለዋል፤ ሀብት ንብረታቸውን አጥተዋል። ሆኖም ለሁለት ዓመታት ያህል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በፕሪቶርያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን እና ብሔራዊ ጥቅምን ባከበረ መልኩ እልባት አግኝቷል። ይህም ስምምነት ከትግራይ አልፎም ለመላው ኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋትን አስፍኗል።
የፕሪቶርያው ስምምነት ሲፈረም በተዋዋዮች በኩልም “በዘላቂነት የጦር መሣሪያ ድምፅ እንዳይሰማ ለማድረግ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የዘለቀው ግጭት እንዲቆም ተስማምተናል” ሲሉ የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት መስማማታቸው የሚታወስ ነው።
በወቅቱም ሕወሓት እና መንግሥት በአንድ ድምፅ ግጭቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራዎችን አስከትሏል ካሉ በኋላ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ከግምት በማስገባት የግጭቱን ምዕራፍ ከኋላችን ትተን “በሰላም እና በመቻቻል ለመኖር” ተስማምተናል ማለታቸው የሚታወስ ነው። ይህንኑ መነሻ በማድረግም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም በማድረግ የትግራይ ሕዝብ ከጦርነት ስጋት ተላቆ ወደ ሰላማዊ ሕይወቱ እንዲመለስ ጥረት ተደርጓል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት እንዲያዞር ተደርጓል። የትግራይ ሕዝብም ፊቱን ወደ ልማት ማዞር ችሏል። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰዋል፤ የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰፍረዋል። አርሶ አደሩም ፊቱን ወደ ግብርና ሥራ መልሷል። በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረው ሕይወቱ መመለስ ጀምሯል።
ሆኖም በትግራይ ውስጥ የሚገኙ በፖለቲካ ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አካላት ይህንን አንጻራዊ ሰላም ለመረበሽና ዳግም በክልሉ አለመረጋጋት እንዲፈጠር እና የፕሪቶርያው ስምምነት እንዳይተገበር እንቅፋት ሲሆኑ ታይተዋል።
እነዚህ ቡድኖች ሰብዓዊነት እና ፖለቲካን በመቀላቀል የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዳይመሰሉ ተግዳሮት ሲፈጥሩ ተስተውለዋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም በጦርነቱ የተሳተፉ ወጣቶች በመልሶ ማቋቋም ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የሚደረገውንም ጥረት ሲያስተጓጉሉ ታይተዋል።
ከሁሉ በከፋ መልኩ ክልሉ ያለውን በጀት ለልማት እንዳያውለው ከ200ሺ በላይ ሠራዊት በማከማቸት እና በመቀለብ በወር እስከ 8 ቢሊዮን ብር በመገፍገፍ ትግራይ በድህነት አረንቋ ውስጥ እንድትቆይ የተደረገበት መንገድ ከተስዋሉ ችግሮች ውስጥ አንዱ ነው።
በአጠቃላይም በትግራይ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ጉራማይሌ ገጽታ ነበረው ነው። በአንድ በኩል ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ ትግራይ አንጻራዊ ሰላም አግኝታ የጥይት ድምፅ የማይሰማባት ክልል ሆና ቆይታለች። በዚህም ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ የመግባት እና ቢያንስ የሰላም አየር የመተንፈስ ዕድል አግኝቶ ቆይቷል።
ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ የተካሄዱ የሰላም ውይይቶች በሂደት መተማመንን እየፈጠሩ መጥተዋል። ጥላቻና ቁርሾን ማለዘብ ችለዋል። ለዜጎች ሰብዓዊና ቁሳዊ አገልግሎቶችን በስፋት ለማቅረብ አስችለዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በጦርነት የሚያልቁ ወገኖችን ሕይወት መታደግ ተችሏል፤ እንደሀገርም ሰላምን ማስፈን አስችሏል።
ከዚህ በተቃራኒ የፕሪቶርያው ስምምነት በአግባቡ እንዳይተገበር እንቅፋት የሆኑ በርካታ ጉዳዮች አጋጥመዋል። ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው አለመመለስ እና አልፍ ሲልም የተፈናቃዮችን ጉዳይ ከወሰን አከላለል ጋር በማያያዝ ፖለቲካዊ መልክ መስጠት፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታጣቂ ማከማቸት እና ከመንግሥት በጀት ላይ እያነሱ መቀለብ፤ ሉዓላዊነትን የሚጋፉ ተግባራት ውስጥ መግባት እና የመሳሰሉት ችግሮች አጋጥመዋል።
እነዚህን ሁኔታዎች ደግሞ አንዳንድ የውጭ ኃይላት እንደምቹ አጋጣሚ ለመጠቀም አኮብኩበው ቆይተዋል። በተለይም በፕሪቶርያው ስምምነት መፈረም ያልተደሰቱ ሀገራት በትግራይ ሁከት እና ብጥብጥ በመፍጠር ከክልሉ አልፎ ሀገሪቱንም ችግር ውስጥ ለመክተት ተስፋ አድርገው ቆይተዋል።
እነዚህ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሁልጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ እድገት ያማቸዋል፤ እንቅልፍ ይነሳቸዋል። ሰላሟ ያስከፋቸዋል፤ ልማቷ ያንገሸግሻቸዋል። እነዚህ የጎረቤት ምቀኞች የሁልጊዜ ምኞታቸው የኢትዮጵያ ውድቀት ነው። ኢትዮጵያ ሁልጊዜ በጦርነት እና በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድትማቅቅ እና ለልመና እጇን እንድትዘረጋ አጥብቀው ይመኛሉ፤ የቻሉትን ሴራ ሁሉ ይዘረጋሉ። ይህንን እኩይ ተግባራቸውንም በትግራይ የተፈጠረውን ክፍተት ለመጠቀም በብዙ ሞክረዋል፤ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች እና ጠንካራ እና ታታሪ የሰው ኃይል ያላት ሀገር ብትሆንም በውስጥ እና በውጭ በሚታቀዱ የጥፋት ውጥኖች ሀገሪቱ በግጭት እና በጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትኖር ተፈርዶባት ቆይታለች። በተለይም ለኢትዮጵያ የማይተኙ እና እድገቷን ማየት በማይሹ የቅርብ እና የሩቅ ሀገራት በሚጠነስሱት ሴራዎች ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀጭጩ እኩይ ሴራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ከልማት ይልቅ በጦርነት እና በግጭት እንድትወጠር እና ልማት እንዳታረጋግጥ ተደርጋ ቆይታለች። ይህም አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የዘለቀ ሐቅ ነው። በትግራይም መፈጸም የፈለጉት ላለፉት ዓመታት ሲያደርጉት የቆዩትን ሴራ እና መከፋፈልን ነው።
ሆኖም ሰላም ወዳዱ የትግራይ ሕዝብ፤ የፌዴራል መንግሥት እና አንዳንድ የትግራይ ፖለቲከኞች ይህንን ሴራ አክሽፈውታል። በትግራይም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በማድረግ በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት ያልተተገበሩ ተግባራት እንዲፈጸሙ እና ትግራይም ወደ ተሟላ ሰላም እንድትገባ መደላድል ተፈጥሯል።
ከአንድ ቀን በፊትም የቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ለአዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ኃላፊነታቸውን አስረክበዋል። በርክክቡ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአቶ ጌታቸው ረዳ ምክትል ሆነው ሲያገለግሉ በመቆየታቸው የነበሩ ድካሞችንና ጥንካሬዎችን በግልጽ እንደሚገነዘቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት አሁን ትግራይ ውስጥ ያለውን ክፍተት ሞልተው ወደ ፊት ሊወስዱ ይችላሉ የሚል እምነት በብዙ አካላት የታመነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ሕዝብ የጠማውን ሰላምና ልማት እንደ ሌሎች ወንድሞቹ ወጥቶ የመግባት መሻት በማሳካት ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም እጅግ ጠቃሚ ነገር ሠርቶ ለማለፍ ታሪክ የሰጣቸውን ዕድል እንደሚጠቀሙበት ተስፋቸውን ገልጸዋል። የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ኃላፊነቶች ለመወጣት በሙሉ ኃይሉ እና በትጋት እንደሚሠራ በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ተመላክቷል።
እነዚህም የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሂደት፣ በጅምር ያለው እንዲጠናቀቅ እና በቀሪ አካባቢዎችም በፍጥነት እንዲተገበር ማድረግ፤ በፕሪቶርያ ስምምነት መሠረት ትጥቅ የመፍታት እና የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ተግባር በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ፤ በክልሉ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፤ ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለሰላም እና ለፀጥታ ጠንቅ የሆኑ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ፤ ለዚህም ተገቢውን የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት።
መደበኛ የልማት ሥራዎች፣ መንግሥታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችና የመንግሥት ግንባታ ሥራዎች እንዲሳለጡ፤ ከሕገ መንግሥታዊ እና ከሕጋዊ ሥርዓት፣ ከሀገር ሉዓላዊነት እና ከፕሪቶርያ ስምምነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ፤ ክልሉ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁ እንዲሆን፤ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ የሆኑበት፣ የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ዓውድ እንዲፈጠር መሥራት። የክልሉ ሕዝብ፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ተዋንያን በሀገራዊ የምክክር ሂደት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤ የክልሉ መንግሥታዊ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ሕዝቦች ትስስር እና መልካም ግንኙነት የሚያጠናከሩ፣ ሕግ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ናቸው። እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ ኃላፊነቶች አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ በትጋት እና በታማኝነት ለመወጣት ቃል ገብተዋል፤ ፊርማቸውንም አኑረዋል።
ስለዚህም ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ እና ካቢኔዎቻቸው ቀሪ የቤት ሥራዎቻቸውን በመጨረስ ትግራይ በዘላቂነት ሰላም የሰፈነባት እና ልማቷ የተረጋገጠባት እንድትሆን አበክረው መሥራት አለባቸው። በዋነኝነት ሊረዱት የሚገባው የጦር መሣሪያ በመሰብሰብ እና ታጣቂ በማከማቸት የሕዝብን ጥቅም ማረጋገጥ አይቻልም። የሕዝብ ጥቅም የሚረጋገጠው ሰላም በማስፈን፤ ልማትን በማረጋገጥ እና ዲሞክራሲን በማጠናከር ነው። ለሕዝብ የሚጠቅመው ትራክተር እንጂ የጦር መሣሪያ አይደለም። ስለዚህም በትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች ከመናቆር እና ከግጭት አዙሪት በመውጣት የትግራይ ሕዝብ የሰላም አየር የሚተነፍስበትን መንገድ መቀየስ ይጠበቅባቸዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም በፖለቲካ ሽፋን ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ የተደረጉ ዜጎችን መመለስ እና ሰላማዊ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ማድረግ በአዲሱ የትግራይ አስተዳደር ሊተገበሩ ከሚገቡ ሥራዎች ቀዳሚው ነው። የተፈናቃዮችን ጉዳይ ከወሰን ማካለል ጋር በማምታት የሚደረጉ ፖለቲካዊ ሴራዎች ከሰብዓዊ ጉዳዮች ተለይተው መታየት ይኖርባቸዋል። አዲሱ አስተዳደር ለሰብዓዊ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ተፈናቃዮች የመመለሱ ተግባርን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
በሌላም በኩል በጦርነት ውስጥ የቆዩ ወጣቶችን በመደገፍ ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የማድረጉም ተግባር ከአዲሱ አስተዳደር የሚጠበቅ ነው። በአሠራር ውስንነቶች እና በፖለቲካ ሸፍጦች ምክንያት በመርሐ ግብሩ መሠረት መፈጸም ያልተቻለውን በጦርነት ውስጥ የነበሩትን ወጣቶች የመመለሱ ተግባር ከአጋዥ አካላት ጋር በመሆን ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው መመለስ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋነኛ ሥራ ሊሆን ይገባል። ከፌዴራል መንግሥት የሚመደብለትን በጀት ለታጣቂዎች ማከፋፈሉን በመተው ለክልሉ ልማት የሚውልበትን ስልት መንደፍ ይጠበቅበታል።
በአጠቃላይ አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለው የአንድ ዓመት የሥልጣን ዘመን ውስጥ ቀደም ሲል የተፈጠሩ ችግሮችን በማረም እና ወቅቱን የዋጀ አሠራር በመተግበር በትግራይ ዘላቂ ሰላም እና ልማት እንደሚጠበቅበት ተገንዝቦ ከወዲሁ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይጠበቅበታል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም