ሆሳዕና-በስኬት ጎዳና

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ከተማዋ እያደገች ስለመምጣቷ ጎላ ጎላ ብለው የሚታዩ ሕንፃዎቿ አንደኛው ምስክሮች ናቸው። ውስጥ ለውስጥ እየተከናወነ ያለው የመንገድ ፕሮጀክትም እድገቷ እየተፋጠነ ስለመሆኑ የሚናገር ነው። በተለይ ደግሞ በዚህ ዓመት በተመረጡ ከተሞች ላይ እየተተገበረ ያለው የኮሪዶር ልማት ሥራው የከተማውን ገጽታ በውበት ከፍ እያደረገው በመሆኑም ሲጠናቀቅ ምን ያህል ውብና ጽዱ ከተማ ልትሆን እንደምትችል ማሳየት ጀምሯል። የሃድያ ዞን ዋና ከተማ ሆሳዕናን።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሆሳዕና ከተማ ተገኝቶ በሥፍራው እየተካሔደ የሚገኘውን የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ቃኝቷል። የኮሪዶር ልማት ሥራውንም ተመልክቷል። በወቅቱም ይህንኑ የልማት ሥራውንና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን አስመልክቶ ከሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት ከአቶ ደሳለኝ ደፋር ጋር ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አቅርቧል።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በሆሳዕና ከተማ እየተከናወነ ያለው የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ደሳለኝ፡- ማዘጋጃ ቤቱ ያሉት ስድስት ቀበሌዎች ናቸው። በመሆኑም ስድስት ዘርፎች ስላሉት የሚመራውም በስድስት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ነው። እንደ አጠቃላይ ግን 13 ተሿሚዎች ያሉት ሲሆን፣ ይህም የሚመራው በ12 ዘርፎች ነው። በእነዚህ ቀበሌዎች ላይ ሰፊ ሥራዎች ይሠራሉ። ከእነዚህ ሥራዎች አንዱ ከማስፈጸም ጋር ተያይዞ ያለ ሥራ ነው። በተለይም መሠረተ ልማትን በተመለከተ አጠቃላይ ሂደቱ የሚሠራ በሁሉም ዘርፍ ነው። ከዚህ የተነሳ በከተማችን ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ታቅደው እየተሠሩ ይገኛሉ።

ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የኮሪደር ልማቱ ነው። ይህ የኮሪዶር ልማት ሥራ ከተማውን ውብ እና ፅዱ ከማድረግ ባለፈ ለነዋሪዎች ምቹ እንቅስቃሴን እየፈጠረ ይገኛል። ልማቱ፣ ለከተማ ነዋሪው መልካም ነገር ይዞ መጥቷል። ገና ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቅ እንኳን ነዋሪው በተወሰነ መልኩም እየተገለገለበት ይገኛል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ከያዝነው የኮሪዶር ልማት ሥራው ውስጥ እስካሁን ሁለት ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር መተግበር ችለናል። በዚህ ተግባር ብቻ እንኳን ልማቱ የከተማውን ገጽታ መለወጥ ጀምሯል።

እንደ ከተማ አስተዳደራችን ለኮሪደር ልማት የተያዘው እቅድ 35 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ሁለት ነጥብ ስድስቱ የመጨረሻው ማጠናቀቂያ ደረጃ ላይ ደርሷል። በመሆኑም የመብራት ሥራዎች እየተገጠሙለት ይገኛል። ከዚህ ጋር ተያይዞ እስከ ሰኔ የሚጠቃለለው የ24 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ሥራው ደግሞ በጥሩ ሂደት ላይ የሚገኝ ነው። ይህ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆነው የ24 ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር የኮሪዶር ልማት ሥራ በአሁኑ ሰዓት ከ40 በመቶ በላይ ደርሷል።

ልማቱ፣ ብዙዎች እንደሚጠብቁት ከዚህ በፊት በአካባቢው የነበረ የትራፊክ መጨናነቅን ያስወግዳል። በአሁኑ ጊዜም ችግሩ እየቀረ ይገኛል። የከተማው ነዋሪም የእግር ጉዞን ያለሥጋት ስለሚያደርግ እግረ መንገዱንም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ ለጤናው ጥቅም እያገኘበት ያለ ልማት ሆኗል። ሰዎች ቀድሞ እንደነበረው ከተሽከርካሪ ጋር መጋፋትን በማስወገድ በእግረኛ መንገድ እንዲሄዱ እያደረገ የሚገኝ ተግባርም እየሆነ ነው።

እንደ ከተማ አስተዳደራችን እየተተገበረ ያለው የኮሪዶር ልማት ሥራ ብቻ ሳይሆን ሌሎች እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶችም አሉን። ከጎፈር ሜዳ ፓርክ ጋር አብሮ የሚለማ በተለይ የወጣቶች ስብዕና ማዕከል ሰፊ ፕሮግራሞችን ይዞ እየተሠራበት የሚገኝ ነው። ከእነዚህም አንዱ የስብዕና ማዕከል ትልቅ ቤተ መጻሕፍት አለው። የዚህ ቤተ መጻሕፍት አዳራሹ ተጠናቅቆ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ወደ ማሟላት እየተሸጋገርን ነው።

በተመሳሳይ የወጣቶች መዝናኛ ሙሉ ፓኬጅ የያዘ እንደ መሆኑ ካፌ እንዲሁም ወጣቱ ራሱን የሚያዝናናበት ጌም ዞኖችም አሉት። አነስተኛ አዳራሾችን ያካተተ ሲሆን፣ ካፌው እና ሌሎች ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ። ጎፈር ሜዳ ላይም የተጀማመሩ ሥራዎች አሉ። ቀጣይነት ያለው ሥራ ለመሥራት 96 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዟል። የመጀመሪያውን ምዕራፍ ጨርሰን ጨረታውም ተጠናቅቆ ወደ ሥራ በመግባት ላይ እንገኛለን።

ሌላው የሃድያ ሕዝብ የራሱ የሆነ የዘመን መለወጫ ያለው እንደመሆኑ ይህን የዘመን መለወጫ የ‹‹ያሆዴ›› በዓል የሚያከብርበት ቦታ ‹‹ሃድይ ነፈራ›› በመባል የሚታወቅ ነው። ይህ ማለት የሃድያ አጠቃላይ ሕዝብ ዓመቱን ሙሉ በሥራ ሲያሳልፍ ቆይቶ ያንን ጊዜ በሥራ እና ብትጋት ካጠናቀቀ በኋላ ልክ የዘመን መለወጫው ሲደርስ በዕለቱ ወደ አደባባይ ወጥቶ እግዚአብሔር አምላኩን የሚያመሰግንበት እና ደስታውን የሚገልጽበት እንዲሁም ከሌሎቹ ወገኖቹ ጋር ሕብረትን የሚፈጥርበት ቦታ አለው። ሃድያ እራሱ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም ጋር በጋራ በመሆን በዓሉን በድምቀት የሚያከብርበት ቦታ በአሁኑ ጊዜ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን። በተለይ ከድሬንጅ እና ከአስፓልት ሥራ ጋር ተያይዞ ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው። በፌዴራል የሚሠራም የአስፓልት መንገድ ከተማ ውስጥ አለ። እንደ ከተማ አስተዳደሩ አቅም ደግሞ ወደ 20 ኪሎ ሜትር በመሠራት ላይ ያለ መንገድም አለ። በአሁኑ ጊዜ አስር ነጥብ አራቱ ተጠናቅቆ ለትራፊክ ክፍት ሆኗል። ይህ 20 ኪሎ ሜትሩ መንገድ፣ ያለ አንዳች ድጋፍ በኅብረተሰቡ ድጋፍ እና በከተማችን አቅም እየተገነባ ያለ ነው።

በቀጣይ ይህን ልምድ አስቀጥለን የምናስኬደው ይሆናል። መሠረተ ልማት ዘርፉ ላይም እየተሠራ ስለሆነ በከተማችን ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴዎች በመካሔድ ላይ ይገኛሉ። በተለይ ደግሞ ከማኅበራዊ ተቋም አኳያ በምንሄድበት ጊዜ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ጣቢያዎች እና ኅብረተሰቡን አንድ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮች በአግባቡ እየተሠሩ ይገኛሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ የከተማ ልማታዊ ሴፍትነት ፕሮግራም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ነው። በተለይ ሶስት የአረንጓዴ ልማት ቦታዎች ለምተው ክፍት እየተደረጉ ይገኛል። የትምህርት ቤት ጥገናው እና የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች በተቀናጀ መልኩ በመሠራት ላይ ናቸው።

እንደ ከተማ አስተዳደሩ፣ ከጽዱ ከተማ ጋር ተያይዞ የገላ መታጠቢያ ‘ሻወር’ ያካተተ በከተማችን ሶስት መጸዳጃ ቤቶችን ሠርተን አጥናቅቀናል። በቀጣይ አገልግሎት እንዲሰጡ ለኅብረተሰብ ክፍት እየተደረጉ ይገኛል። እነዚህም የገላ መታጠቢያ ያላቸው መጸዳጃ ቤቶች በራሳቸው ገቢ ማስገኘት የሚችሉ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የከተማን ቆሻሻ በተለይ ከመጸዳጃ ቤት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ችግር የሚቀርፉ ናቸው ተብለው የተሠሩም ጭምር ናቸው።

ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ በተለይ እንደ ከተማችን እየተገበርን ያለው ሥራ በጣም ሰፊ ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም በሆሳዕና ከተማ ከስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ውጪ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ። ከዚህም አንጻር ከተማዋ ፈጣን እድገት ላይ ትገኛለች ብሎ መውሰድ የሚቻል ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ሆሳዕና ከተማ በማደግ ላይ ትገኛለች፤ የነዋሪውም ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ እንደመሆኑ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴ ካሉ ቢገልጹልን?

አቶ ደሳለኝ፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግሥት ለዜጎች እያመቻቸላቸው ከመጣው ተግባር ውስጥ አንዱ የቤት ግንባታ ነው፤ ይህን ግንባታ በከተማችን በሰፊው እየሠራንበት ያለ ተግባር ነው። በተለይ ከማህበራት መሬት ጋር ተያይዞ እንቅስቃሴያችን ሰፊ ነው ማለት ይቻላል። ግንባታዎቻቸውም በሚታዩ ጊዜ በጣም ዘመናዊ እና ለኑሮም አመቺ የሆኑ ሥራዎችን እያከናወንን ነው። ከዚህም አንጻር በተለይ የከተማችንን ነዋሪዎች የቤት ችግር ለመቅረፍ በዚህ መርሃ ግብር ላይ በትጋት እየሠራን ነው። በየቀበሌዎቹ ውስጥ ዘልቀን ብንገባ እነዚህን ሥራዎች ማየት እንችላለን። በመሆኑም በሰፊው የተሠራ ሥራ በመሆኑ በተግባር የሚታይ ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከማዘመን ጋር ምን ምን ሥራ ተሠርቷል?

አቶ ደሳለኝ፡- ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የተሠሩ ሥራዎች አሉ። በተለይ እነዚህ ሥራዎች በአራት ዘርፍ የሚታዩ ናቸው። ዘርፎቹ፣ ከንክኪ ነፃ በሆነ መልኩ አገልግሎት የምንሰጥባቸው ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የመሬት ልማት ሥራዎቻችን ሲሆኑ፣ ሁለተኛው ደግሞ የኮንስትራክሽን ሥራዎቻችን ናቸው። ሶስተኛው እንዲሁ የገቢ አሰባሰብ ሥራዎቻችን ሲሆኑ፣ አራተኛው እና የመጨረሻው የመሬት ይዞታው ካዳስተር በሚባል በሚታወቀው ዘርፍ ላይ ከንክኪ ነፃ የሆነ አገልግሎት እየሰጠን ነው።

ይህን ዓይነት አገልግሎት በእነዚህ በአራቱ ዘርፍ ላይ ብቻ ወስነን የምናቆመው ሳይሆን በሌሎችም ዘርፎች ላይ አስፍቶ የመሄድ እቅድ አለን። ከዚህ አንጻር አገልግሎት ፈላጊዎች በየቤታቸው ሆነው በተለይ በቴክስት ሲስተም እና አካውንት ኖሯቸው በአካውንት ደረጃ ማግኘት የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ዝግጅታችንን አጠናቅቀናል። ይህ በመሆኑም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሠርተናል። አገልግሎት ፈልገው ለሚመጡ አስፈላጊውን የግንዛቤ ትምህርት አስጨብጠናል።

በአሁኑ ጊዜ ግን ወደ ትግበራ ለመግባት እየተንደረደርን እንገኛለን። በተለይ አገልግሎት ፈላጊዎች በአካል ወደቢሯችን መምጣት ሳያስፈልጋቸው በቤታቸው አሊያም በየሥራ ቦታቸው ሆነው የተለያዩ ጥያቄዎቻቸውን ወይም የሚፈልጉትን አገልግሎት ሲጠይቁ የእነርሱ መገኘት የግድ ነው ሳንል ለማስተናገድ በትጋት ላይ እንገኛለን። በተለይ ግብራቸውን የመክፈል ሥርዓት ማከናወን የሚችሉበት፣ የቤት ሽያጭ የስም ዝውውር ማንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታን በማመቻቸት ላይ እንገኛለን። ሌላው ቀርቶ አገልግሎታችንን ፈላጊ የሆነ አንድ የከተማችን ነዋሪ አጋጣሚ ሆኖ በሀገር ውስጥ ባይኖር እንኳ ባለበት ሀገር ሆኖ ንብረቱን ያለ ሥጋት

መቆጣጠር የሚችልበትን ሥርዓት እየዘረጋን ነው። ከዚህ አንጻር እንደ ከተማችን፤ እንደ ማዘጋጃ ቤት የራሱ የሆነ ድህረ ገጽ አለ። የትኛውም ሰው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ሲፈልግ ያንን ድህረ ገጽ ተጠቅሞ መረጃ ማግኘት ይችላል።

ሁለተኛው ደግሞ ሥራዎቻችንን ስንሠራ የምናከናውነው በካሜራ በተደገፈ ስልት ነው። ለምሳሌ በሁሉም ጣቢያዎች ላይ የደኅንነት ካሜራዎች አሉ። እነዚህም የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ ካሜራዎች ናቸው። በተለይ ተጠያቂነትን የማስፈን አገልግሎታችን ጋር ተያይዞ ያሉ ሥራዎቻችንን በካሜራው ታግዘን በመሥራት ላይ እንገኛለን። ይህ ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ከኢትዮ – ቴሌኮም ጋር በመሆን ስማርት ሲቲን ቦታዎችን አስጠንተናል። በከተማችን እየተከናወነ ከሚገኘው የኮሪዶር ልማት ጋርም ተሳልጦ እንዲሔድ ቦታዎች ተለይተዋል። ከዚህ አኳያ መግባባት ላይ ተደርሷል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ሥራ የማስጀመር ሂደት ውስጥ እንገኛለን።

ሆሳዕና በጣም ሰፊ ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚስተዋልባት ነች። ከዚህ አንጻር እየሠራን ያለነው ሥራም በጣም ሰፊ ሥራ ነው። በተለይ ቀደም ሲል በከተማዋ ነዋሪዎች ሲያነሱ የነበሩ ቅሬታዎች ነበሩ፤ ከእነዚህ መካከል እንደ ቆሻሻ አወጋገድ እና ፍሳሽ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ይህንን የኅብረተሰቡን ጥያቄና እና ቅሬታ ለመመለስ እና ለመፍታት በአግባቡ እየተሠራ ነው።

 

ከመሠረተ ልማትም አንጻር ሥራዎች በአግባቡ እየተሠሩ ነው፤ በተለይ ሥራዎቹን በየፈርጃቸው ለይተን እየሠራን ነው። አንዱ የለየነው ፈርጅ ቢኖር ጠጠር መንገድ የሚያስፈልገው አካባቢ ያንን የጠጠር መንገድ በአግባቡ በመሥራት ሂደት ውስጥ እንገኛለን። ሌላው ፈርጅ ደግሞ መንገዶችን ወደ አስፓልት ከፍ የማድረግ ሥራ ሲሆን፣ ይህ እያከናወንን ካለነው ሥራዎቻችን ውስጥ ተጠቃሽ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጌጠኛ ድንጋይ መንገድን በተመለከተ ብዙ የሄድንበት ባይሆንም እሱንም እያየን እንገኛለን። በርግጥ በሆሳዕና ከተማ ከዚህ ቀደም የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ በሰፊው የተሠራ መሆኑ የሚታወስ ነው። ነገር ግን ደግሞ ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ መሠራትና ማሳደግ ስለሚጠበቅ ያንን የማድረግ ሂደት ላይ እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡- ለከተማዋ ነዋሪዎች ከንጹህ የመጠጥ ውሃ ጋር ተያይዞ ምን የተከናወነ ሥራ አለ?

አቶ ደሳለኝ፡- ከንጹህ የመጠጥ ውሃ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በተለይ ሁለት የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በዙሪያ ካሉ ወረዳዎች በተለይም ጃዊ ከሚባል ቦታ በጣም ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል አምጥተን አንደኛው አገልግሎት ጀምሯል። አንደኛው ደግሞ አገልግሎት በመጀመር ሂደት ላይ ይገኛል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የውስጥ አቅምን በመጠቀም ደግሞ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሆን የአስፓልት መንገድ ገባ ባሉ አካባቢዎች ላይ የከርሰ ምድር ውሃ መጠቀም ችለናል። ይህ በመሆኑም በከተማዋ ይስተዋል የነበረውን የውሃ ችግር በዚህ መልኩ በመቅረፍ ላይ እንገኛለን ማለት ነው።

በቀጣይ በተለይ ከመዝናኛ ቦታዎች ጋር ተያይዞ 24 ነጥብ አምስት ወይም በሰፊው ማለትም 35 ኪሎ ሜትር በምናለማው የኮሪዶር ልማት ላይ በተለይ የተለያዩ የኩነት ቦታዎችን፣ አረንጓዴ ቦታዎችን፣ የብስክሌት መንገዶችን እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች የሚጓጓዙበት ቦታዎችን አስበን እየሠራን እንገኛለን። እንደሚታወቀው በከተማችን በርከት ያሉ ትልልቅ ሕንፃዎች አሉ። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የሚከናወኑ ሰፊ የልማት ሥራዎች አሉ።

ሌላው እንደ ዘርፍ የሚነሳው የከተሞች የፕላን ዘርፍ ነው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከተማው የአስር ዓመት መዋቅራዊ ፕላን አውጥቶ ነበር። ይህ መዋቅራዊ ፕላን ሙሉ ለሙሉ አዲስ በሚያስብል ደረጃ እያስጠናን ነው። ማስጠናት ብቻም ሳይሆን ያንን ሂደት ጨርሶ እና ጸድቆ ወደ አገልግሎት ገብቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ መዋቅራዊ ፕላኑ በከተማዋ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ብዙ ነገሮችን ያካተተ ነው። ይህ የከተማው መዋቅራዊ ፕላን ካካተታቸው መካከል እንደ የኢንቨስትመንት ቦታዎች፣ የኢንዱስትሪ መንደሮች ሰፊ የሆነ ማሕቀፎችን የያዘ ነው። ይህ መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅቱን ጨርሶ ከሚመለከታቸውም ጋር ውይይት ተካሂዶበት በአሁን ጊዜ ወደ ትግበራ እየተንደረደረ ነው ማለት ይቻላል። አዲሱ መዋቅራዊ ፕላን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታ ከመሆኑም ባሻገር የልማት ፍላጎት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ እንደሚሆን ይታመናል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሰፈር ፕላን ልማት ከዚሁ ጋር አያይዘን እየሠራን ነው። ይህ ከተማ ከዚህ በፊት የከተማ ፕላን አልነበረውም። ከሰፈር ልማት በኋላ ቀጥታ ወደ ትግበራ ነበር የሚገባው፤ ነገር ግን አሁን የከተማ ዲዛይን የሚያስፈልግ በመሆኑ የከተማ ዲዛይን ሥራ እየተሠራ ነው። ከኮንስትራክሽን ዘርፉ ጋር ተያይዞ ሰፊ የሚባሉ ሥራዎችን እየሠራን ነው። ሰፋፊ የመንግሥት ፕሮጀክቶች አሉ። እነዚህ ፕሮጀክቶች በአግባቡ እየተሠሩ ይገኛሉ። ከዚህ አንጻር ማዘጋጃ ቤቱ የመንግሥትን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት በቁርጠኝነት እና በትጋት እየሠራ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከመኖሪያ ቤት እና ከማኅበረሰብ ተኮር እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የተሠሩ ይህ ነው የሚባል ሥራ ካለ ቢጠቅሱልን?

አቶ ደሳለኝ፡- በአጠቃላይ ከመኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ ያለው በአምናው የበጀት ዓመት ብቻ በአንድ ዓመት ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ የተደራጁ ማኅበራትን ማስተናገድ ችለናል። ይህ ማለት በአንድ ማኅበር ውስጥ አስራ ስድስት ሰው ያለ ሲሆን፣ ይህም በጥቅሉ ሲታይ ከሰው አኳያ ከፍተኛ ቁጥር የያዘ ነው ማለት ይቻላል። ከዚያ በፊት የነበሩ ሰፋፊ ሥራዎች አሉ።

ከትምህርት ቤት ጋር ተያይዞ አዲስ የትምህርት ቤት ግንባታዎችም አሉን። ሌላው ደግሞ በከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር ያስጠገነው አንድ ትምህርት ቤት ነው። ነገር ግን በየዓመቱ ማኅበረሰብ ተኮር አገልግሎቶች ላይ እንሠራለን። በተለይ ከተማችን በየጊዜው እየሰፋ የሚሄድ እንደመሆኑ ከመሠረተ ልማቱ ጋር ተያይዞ የሚያስፈልገው ሰፊ ነገር ነው። ከዚህ አንጻር ማህበራዊ ተቋማት ወሳኝ እና አስፈላጊ ናቸው። ከዚህ አንጻር በሚያስፈልጉ አካባቢዎች የነዋሪውን ፍላጎት ለማርካት እና ተደራሽነቱ ላይ እንሠራለን። ምክንያቱም የከተማው ነዋሪዎች ባሉበት ሥፍራ ሆነው ብዙ ባልራቀ ሁኔታ የሚፈልጉትን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጋን እንገኛለን ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- የሃድያ በርከት ያሉ ተወላጆች በውጭ ሀገር በተለይም ደቡብ አፍሪካ እንደሚኖሩ ይነገራል፤ እነዚህ ተወላጆች በሆሳዕና ከተማ ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት እንዴት ይገለጻል? ኢንቨስት ማድረግ እንዲችሉ ምንስ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል?

አቶ ደሳለኝ፡- በርግጥ እኛ ሰፊ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አሉን። እንደ ከተማችን በአጠቃላይ ወደ ሁለት መቶ ሃያ አራት (224) አካባቢ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አሉን። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ተጨማሪ ጥናት እያደረግን ነው። እኛ እየሠራን ያለነው ከተማችን የመጀመሪያ አማራጭ እንድትሆን ሲሆን፣ በተለይም ከተማችን ለኢንቨስትመንት እና ለቱሪዝም ምቹ እንድትሆን አድርገን በመሥራት ላይ እንገኛለን። ይህ በመሆኑም ሰፊ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች አሉ። በተመሳሳይ ደግሞ ሰፊ ምላሽም በመስጠት ላይ እንገኛለን። ወደ እኛ የሚመጡ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት የሚፈልጉ ናቸው። ለምሳሌ ከማኅበራዊ ተቋማት ጋር የሚያያዙ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች አሉ። እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ጋር የሚያያዙም አሉ።

ለምሳሌ የቅርቡን ብንመለከት የልብስ ፋብሪካዎች እና የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች በተመለከተ ተጠይቀናል። ጥያቄውን በመቀበልም ምላሽ እየሰጠን እንገኛለን። ጥናቱን ከማዘጋጃ ቤቱ ጨርሰን ወደ ከተማ አስተዳደሩ ወስደነዋል። ከተማ አስተዳደሩ ደግሞ ወደ ዞን ያስተላለፈበት ሁኔታ አለ። እንደዚሁ የተለያዩ ለምሳሌ እንደ እነ ቄራ ዓይነት አገልግሎቶችን ከእኛ ውጭ ‘አውት ሶርስ’ በማድረግ ሰዎች አገልግሎት እንዲሰጡም እየተደረገ ነው። አንድ ዘመናዊ የቄራ እርድ አገልግሎት ለመስጠት በቅርቡ መሬት የተረከቡ አሉ። ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

ከከተማው እድገት አንጻር ለሰዎች አገልግሎቱን በጥሩ ሁኔታ ማቅረብ አለብን ብለን በማሰባችን አገልግሎቱን ፈላጊዎች ምቾታቸው ሳይጓደል አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ የተቻለንን በማድረግ ላይ እንገኛለን። እነዚህን አገልግሎቶች ለማሳለጥ ለእኛ አንዱ አማራጫችን ኢንቨስትመንት ነው። ከዚህ አንጻር እነዚህን አማራጮች በመጠቀም ላይ እንገኛለን።

በተለይ የሆቴሎች እና የሪል ስቴት ክፍሉ ላይ በአግባቡ እየሄድንበት ነው። አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ለዜጎች የመኖሪያ ቤቶች የምናቀርብበት አማራጭም ብዙ ነው። አንዱ የሊዝ ጨረታ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሪል ስቴት ሲሆን፣ ሶስተኛው በማኅበራት በመደራጀት የሚሠሩት ነው። በዚህ መልኩ ነዋሪዎች በፈለጉት ውስጥ በመካተት የራሳቸውን አማራጭ ማስፋት እንዲችሉ የተለያዩ አማራጮች አሉና እንደ የአቅማቸው ሁኔታ መምረጥ እና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ።

ነገር ግን እየተሠራ ባለው ሥራ በመኖሪያ ቤት ዙሪያ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ማለት አንችልም፤ እየተሠራባቸው ያሉ ተግባራት አሉ። ይሁንና ገና ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉብን መረዳት ያስፈልጋል። ካለው የሕዝብ ብዛት አንጻር እና የሕዝቡ የከተሜነት ሁኔታ የጨመረ በመሆኑ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን እንረዳለን። ያንንም ለማድረግ የበኩላችንን ለመወጣት በመትጋት ላይ እንገኛለን። እንዲያም ሆኖ በተለይ ከዲያስፖራው ጋር ተያይዞ በአሁኑ ጊዜ በአግባቡ እየሠራን እንገኛለን ማለት ይቻላል። በተለይ ከአፓርታማ ጋር ተያይዞ በአግባቡ ተዘጋጅተን እየሠራንበት እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ ደሳለኝ፡- እኔም እድሉ ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

 

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You