በድሮ ጊዜ ነው አሉ ….. በመስኮብ ሀገር ሶስት ሴቶች ልጆች ያሉት አንድ ሽማግሌ ነበር። ከሶስቱ አንዲቷ በመልኳና በጥበቧ እጅግ ስመ ጥሩ ናት። አንድ ቀን ወደ ገበያ ሲወጣ፣ ልጆቼ ሆይ ከገበያ ምን ገዝቼላችሁ ልምጣ አላቸው። ሁለቱ ልጆች ጌጥ ገዝተህልን ና አሉት። አንዲቱ ግን እኔ ምንም አልፈልግም፣ ነገር ግን የምመክርህን ምክር ስማኝ አለችው። ለግዜው ነገሩ ከበደው ነገር ግን ልጁ እጅግ ብልህ መሆኗን ያውቃልና ይሁን ንገሪኝ አላት። ወይንማውን በሬ ወደ ገበያ አውጥተህ ስትሸጥ፣ ዋጋ ንገር ያሉህ እንደሆነ የንጉሱን ግራ አይኑን አምጡና ውሰዱ በላቸው አለችው። እርሱም በገበያ ተቀመጠና የበሬውን ዋጋ ንገር ሲሉት፣ ልጁ እንደመከረችው፣ የንጉሱን ግራ አይኑን አምጡና ውሰዱ ይል ጀመረ።
ይህንም ወሬ ንጉሡ ሰምቶ እጁን ይዛችሁ አምጡልኝ ብሎ አዘዘ። ሽማግሌውም በቀረበ ጊዜ፣ ንጉስ ሆይ እንደዚህ ያደረገችኝ ልጄ ናትና ማረኝ እያለ ይለምን ጀመረ። ንጉሱም ይህን በሰማ ጊዜ ሔደህ ልጅህን አምጣትና እምርሃለው አለው። ሽማግሌውም እያዘነና እየተንቀጠጠ፣ ሄዶ ልጁን ይዞ ወደ ንጉስ ቀረበ። ንጉሱም ልጅቱን ባያት ጊዜ ለበሬው ዋጋ የንጉሱን ግራ አይን አምጡና ውሰዱ በላቸው ብለሽ ለአባትሽ የመከርሽው ስለምን ነው አላት።
ንጉስ ሆይ አልቀጣሽም ብለህ ማልልኝና እነግርሀለው አለችው። አልቀጣሽም ብሎ ማለላት። ንጉስ ሆይ፣ ድሃና ጌታ ተጣልተው ወዳንተ የመጡ እንደሆነ በቀኝ የቆመውን ጌታውን ብቻ ታያለህ እንጂ፣ በግራ የቆመውን ድሃውን አታይም ስለዚህ መቼም ግራ አይንህ ሥራ ካልያዘልህ ብዬ ነው አለችው።
ንጉሱም የልጅቱን ንግግር ሰምቶ እጅግ አድንቆ ወዲያውም ወንድ ልጁን ጠርቶ፣ ልጄ ሆይ፣ በመልክና በእውቀት ከእርሷ የምትሻል ሴት የለችምና እርሷን አግብተህ መንግስቴን ይዘህ ኑር አለው። ልጁም እርሷን አግብቶ ንጉስ ሲሆን እርሷ ደግሞ ንግስት ተብለው ኖሩ።
ልጆቼ ሆይ መልካም ንግግርና ጥበብ፣ ሰውን ታከብራለችና ንግግራችሁ ሁሉ በመልካምነትና በጥበብ ይሁን። ልጆች በማስተዋልና በጥበብ መራመድ ሩቅ እንደሚያደርሳችሁ አውቃችሁ አስተውሉ። ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ።
ምንጭ፦ የልጆች ማሳደጊያ
በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2013