ተገኝ ብሩ
ደራሲ አሌክስ አብርሀም (የብዕር ስም ነው) ከሚፅፋቸው ልዩ ልዩ አጫጭር ልቦለዶች ወጎችና በተጨማሪ በጣት የሚቆጠሩ የግጥም መድብሎች አሉት፡፡ግጥሞቹ በሀሳብ ይዘታቸው ጥልቅ ናቸው፡፡ በራሱ የአፃፃፍ ስልት የአንባቢን ስሜት በመግዛትና እንዲመራመር የሚጋብዙ ሚስጥራዊ አገላለፆች በማቅረብ የስነ ግጥም ልዩ ክህሎት ያለውና በአሁኑ ጊዜ ተጠቃሽ ከሆኑ ጽሁፎች የሚመደብ አድርጎታል ፡፡
በ2009 “አንፈርስም፤አንታደስም” በተሰኘ የግጥም መድበሉ ውስጥ ካካተታቸው 50 የግጥም ስብስቦች ውስጥ በይዘቱ ተለይቶብኝ የመረጥኩትን “መስቀል አደባባይ” የተሰኘ ግጥም በራሴ አተያይ የግጥሙን ይዘት ለመተንተን የሞከርኩበት ፅሁፍ በዚህ መልክ አሰናዳሁት፡፡
ደራሲው በዚህ ግጥሙ የብዙ ሀገራዊ ሁነቶቻችን መድረክ የሃይማኖትና ህዝባዊ በአሎች ማስተናገጃ የሆነው መስቀል አደባባይን በተለየ አይኑ ተመልክቶ እዚያ መድረክ ላይ የተፈጠሩና ሆነው ያለፉ ክስተቶች፣ አደባባዩ ለህዝቡ ምን እንደሆነ ፣ የምን አይነት ሁነቶች ማሳያና ማሳለጫ እንደሆነ ይዘረዝርበታል፡፡
መስቀል አደባባይ ከቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት አንስቶ ያስተናገዳቸውን ታላላቅ አገራዊ ሁነቶች በማንሳት ህዝባዊ ትዕይንቶችን በመጥቀስ ከእኛ ታሪክ ጋር ምን ያህል ትስስር እንዳለው፣ የእኛን ልዩ መልክ መለዋወጥ መቀየርና ሀገራዊ ተጨባጮችን በትዝብት በመንገርም በመገሰፅም ዜማ አላብሶ ቃላትን መርጦና አሰናኝቶ አቅርቦበታል፡፡
ግጥሙ ከስያሜው አንስቶ ገጣሚው ያነሳውን ጉዳይ ግዙፍነት ያመላክታል፡፡መስቀል አደባባይ ለኛ ኢትዮጵያዊያን ልዩ ትርጉም አለው፡፡ለውጥ ፈልገን ድምፃችን ያሰማንበት፣ድል ስንሰማ ወጥተን የቦረቅንበት፣ ተሰባስበን በደስታና በሀዘን ያነባንበት፣ እንደ አገር የገዘፉ ሁነቶች ተዘጋጅቶ ብዙ ያየንበት ታሪክ በተለያየ መልክ የተንፀባረቀበት መድረክ ነው፡፡
በዚህ ግጥም ማህበረሰባዊ አመለካከትና ፍልስፍናችን፣ የተሳሳተና የተስተካከለው ልማዳችን ተተችቶበታል፡፡አደባባዩ እኛን በዚህ መልክ የሚገልፅ ነው ተብሎ እዚያ የሆነውን በማሳያነት በግጥሙ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡
ግጥሙን ገና ሲጀምር “ይሄው” በሚል አንዲት ንጥል ቃል መጀመሩ አፅንዖት ለመስጠት ጠቅሞታል፡፡አንድን ብርቱ ጉዳይ ለማመላከት ትኩረት እንዲሰጡት ለማሳሰብ በሚመስል መልኩ “ይሄው..” በሚል አንዲት አፅንዖት እንዲሰጡ በሚያደርግ ቃል በሩን ይከፍታል፡፡
“ይሄው…
የተሰፈረበት የታሪክ ቁናችን ፤
ደግሞ የሰፈርንበት የዘመን ቋታችን”
ተከተለኝ ቱሪስት ውጣ ደረጃውን፤
የመውጫ መውረጃ መረማመጃውን
እያለ የሚናገረው ታሪክ ለማያውቀው አዲስ “ቱሪስት” ብሎ ለፈጠረው ገጸባህሪ ነው፡፡ገጣሚው ለታሪኩ መንገሪያነት የተጠቀመበት ስልት የተመረጠና የታሰበበት መሆኑን ያመለክታል፡፡ የእኛን ታሪክ መንገሪያ አድርጎ የፈጠረው ገፀ ባህሪ፣ የታሪካዊውን ቦታ ምንነት ያልተረዳ ገና እንዲያውቅ የሚነገረው አዲስ ለአገሩም እንግዳ ቱሪስት ሆኖ የተሳለው ሆን ተብሎ ነው፡፡
“የመውጫ መውረጃውን” ታሪካችን አንዴ ከፍ ብለን ደምቀን የፈካንበት ሌላ ጊዜ ደግሞ ባልተገቡ መንገዶች ወደማይገባን ዝቅታ የተመለስንበትን ሁነት ለመግለፅ ተጠቅሞበታል፡፡የአደባባዩ መወጣጫ ደረጃው እንደ አገር አንዴ ከፍ መለስ ብለን በሌላኛው ታሪካችን ዝቅ ያልበትን ሁነት ሊነግረን ፈልጎ ተጠቅሞበታል፡፡የታሪካዊውን ቦታ ሁነት እንዲህ ሲል ይተርካል።
እዚህ ጋር ነበረ ግራ እጆቻችን ሽቅብ አስወንጭፈን
በፍርሀት ቡጢ ከእግዜር ካባ ገፈን፤
ልበስልን ያልነው ቄሳርን አግዝፈን…
ይህ ስንኝ አደባባዩ ህዝብ ወዶ ፈቅዶ ያነገሰውን በፍቃዱ ስልጣን ስለሰጠው አካል ድጋፍ የገለፀበት፣ አብሮነቱን ያረጋገጠበት መሆኑን ይጠቁማል፡፡ነገር ግን ምላሹ ተቃራኒ የገጠመው ያላሰበው መሆኑን በትዝብትም በትችትም መልክ ይገልፃል፡፡
እዚሁ ጋር ነበር ቄሳር ወንድማችን
ብርድ ላይ ጦርነት አውጆ ያሳወጀን
እዚቹ ላይ ነበር በሰጠነው ካባ
ያገር ሙቀት ታቅፎ በቆፈን ያስፈጀን
በዚያ ዘመን ህዝብ አክብሮ ያነገሰው፣ የሾመውና በፍቃዱ
ክብር የሰጠው ባለስልጣን፤ አገርና ህዝብ የጣለበትን እምነት ዘንግቶ የሰጠውን ሀላፊነት ረስቶ ያጎናፀፈውን ክብርና የሰጠውን እምነት ንዶ በተቃራኒው ሆነ፡፡በትክክል ሀላፊነቱን ባለመወጣቱ በዚህም ህዝብ የደረሰበትን ውጣ ውረድ ያመላክታል፡፡የህዝብ እርዛትንና የባለስልጣናቱን በምቾት መደላቀቅ በንፅፅራዊ ቃል የገለፀው፡፡ሙቀትን የምቾት ጥግ፤ ቆፈንን ደግሞ የችግር መለኪያ በማድረግ አጉልቶታል፡፡ቀጠለ፡-
ተከተለኝ ቱሪስት …
ውጣ ደረጃውን መረማመጃውን…
እዚሁ ጋር ነበር ቀይ ቀለም በጠርሙስ
ሞልተን ይውደም ያልነው
ቀይ ግፍ የፃፍነው…
እዚቹ ጋር ነበር
ያኔ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ህዝብ እዚያው አደባባይ ላይ ሰብስበው በወታደሮቻቸው ታጅበው ያደረጉትን ንግግርና ተግባር ያስታውሳል፡፡እዚያው አደባባይ ላይ የሆነውን ይጠቅሳል፡፡ፕሬዚዳንቱ ሀገር የካዱ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያሉዋቸውን ይውደሙ ብለው በቀይ ቀለም የተሞላ ጠርሙስ ይዘው በመወርወር ያሳዩበትና ደምን የመሰሉበት ሁናቴን ያመላክታል፡፡ብዙም ሳይቆይ እዚያው አደባባይ ላይ በዚያው ጊዜ የተፈፀመ ቀይ ሽብርን ክፉ ገጠመኝንም ያወሳል፡፡እንደ ሀገር የተሰራን ስህተት ያመላክታል፡፡ይተቻል፣ያወግዛል፡፡
ቀጠለ፡- በሬ የሚያካክሉ…እርግቦች አቁመን ሰላም የዘመርነው
እዚህ ጋር ነበረ እነእንትና ቁመው ሽለላ ያሳዩት፤
እዚሁ ጋር ነበር…ለምን ብለው ባሉ… እነእነትና ያለቁ
ስለ ሰላም እንደ ህዝብ በአንድነት ቆመን የዘመርንበት ሁኔታ ብዙም ሳይቆይ እዚያ ቦታ ላይ የእርስ በርስ መጫረስ አንዱ ወገን ሌላኛውን ወገን የፈጀበት ያለ ምክንያት መጠፋፋት የተስተዋለበትን ክፉ ገጠመኝ ያመለክታል፡፡
ተከተለኝ ቱሪስት…
እዚሁ ጋር ነበር ፣ንብ ለብሰን ሰም ጎርሰን፤
የማር ተስፋ ነክሰን..
አውራችን ፊት ለፊት የተሰበሰብነው
እዚችው ጋር ነበር ላባችን ሳትደርቅ
ማር ይቅርብን ያልነው…
ሁለት ጣታችንን ጣምራ ጦር አድርገን
የባለ ማሩን አይን ደፍረን ያነቆርነው
እዚህ…ጋር…እኮ ነው
ከላይ ተከታትለው በተደረደሩት ስንኖች ደግሞ በ1997 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የሆነውን ያስታውሳል፡፡የእኛ የኢትጵያዊያን የአቋምና የሁናቴ ለውጥ የመምሰልና ማስመሰል ጥግ በዚያ ወቅት ገጠመኝ በጉልህ ይገልጣል፤ ያመላክታል፡፡እዚሁ አደባባይ ላይ ነው የኢህአዴግ ደጋፊ ብዛት የታየው፤ በማግስቱ ደግሞ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የጠራው ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ያው ህዝብ ድጋሚ መውጣቱም የታየው ፡፡የኢህአዴግ ደጋፊ የመሰለው የቅንጅት ሆኖ መገኘቱን ያመላከተበትን፤የታየበትንም ገጠመኝ ያስታውሳል፡፡
ተከተለኝ ቱሪስት … ውጣ ደረጃውን መረማመጃውን
እዚህ ጋር ነበረ ይሁዳ የሳመን፤
የመውደዱን ተስፋ አጥብቆ የሰጠን
እዚሁ ጋር ነበር በእርካሽ የሸጠን…
ረጋሚን መርቀን ባራኪ የረገምነው…
ዘራፍ ብለን ወጥተን…አፈር ቆማሪዎች ወዮላችሁ ያልነው፤
“አፈር የነካኩ አፈር በሉ” ሲባል “ሀሌሎያ” ያልነው
ብሎ ገጣሚው ማህበራዊ ሂሱን ቀጠለ፡፡ሰጥቶ መንሳትን፣አምኖ መከዳትን፣ አገር መሸጥን፣በስህተት መፈረጅን፣ያለ ምክንያት መደገፍና መቃወምን በአጠቃላይ ማህበራዊ ህፀፅን ያሳየበት ነው፡፡ልምድና ድርጊታችን ልክ እነዳልነበር በልከኛ ቋንቋ ያመላከተበት፡፡
እንዲህ ብሎም ያሳርጋል፡- እዚህ ጋር እኮ ነው…
እዚሁ ጋር ነበር ደቆ ላይደቅልን ታሪክ ያላመጥነው፤
አምልጠን ላናመልጥ በጅምላ የሮጥነው
እዚሁ ጋር ነበር …..
ተቃውሞና ድጋፋችን ያልታረቀ፤አካሄዳችንም ልክ እንዳልሆነ በመስከን ውስጥ የሚገኝን መፍትሄ አለመገንዘባችንን ያመላክታል፡፡ለውጥ ላናመጣ የደገፍነው ላይለውጠን ነገር የተቃወምነው ሁሉ በእኛነታችን ላይ ጠብ ያለ ነገር አለመፍጠሩ ቆም ብለን ማሰብ እንዳለብን ያመላክታል፡፡አበቃሁ ቸር ይግጠመን፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2013