ለምለም መንግሥቱ
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ህዳር 29 ቀን በየአመቱ ሲከበር እነሆ 15ኛ አመቱን ይዟል። የዘንድሮው እንደአለፉት የበዓል አከባበሮች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እየተቀባበሉ እንደየአካባቢያቸው ባህልና ወግ ባህላዊ ምግባቸውን፣ መጠጦቻቸውን እየጋበዙ፣ በአልባሳቶቻቸው እያጌጡና እያስተዋወቁ አክብረውታል።
የዘንድሮው ለየት የሚያደርገው ግን በውስን የሰው ቁጥር ሁሉም በየአካባቢው በተለያየ ዝግጅት ማክበሩ ነው። ብዛት ያላቸው ሰዎች አደባባይ ወጥተው ያላከበሩበት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት ሆኖ የቀጠለው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ መሆኑ ይታወቃል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከተዘጋጀው በራሪ ጽሁፍ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የመሰናዶው ዋነኛ ዓላማው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድነት ታሳቢ ያደረገ ነው። በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 25 ላይ እንደተደነገገው ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው።
በመካከላቸው ማንኛውም አይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል። በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በቀለም በጾታ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በሀብት ወይንም በሌላ አቋም ምክንያት ፍትህ ሳይጓደልባቸው እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው።
በሕገ መንግሥቱ እንደተመለከተው የሕዝቦች ህብረ ብሔራዊ አንድነት ማለት የተገነባ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ማለት ነው። የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በመጠቀም በነፃ ፍላጎት፣በሕግ የበላይነት፣እና በራስ ፍላጎት የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጦ የተነሳ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እውን የሚሆንበት አቅጣጫ የሚመለከትበት ነው።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ይህን ታሳቢ ባደረገ በየዓመቱ ቢከበርም፣በውስጡ የያዛቸው ሰፊ የባህል እሴቶች ግን አይዘነጉም። ቋንቋው፣ባህላዊ ዘፈኑና ጭፈራው፣ የለቅሶና የሰርግ ሥርዓቱ፣ የባህል አልባሳቱ፣ ምግብና መጠጡ ወዘተ አንዱ ከሌላው የተለየ በመሆኑ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት አለው። ሁሌም የሚታይና የማይሰለች የሚሆነውም በልዩነት ውስጥ ውበት በመኖሩ ነው። እኛም ባህላዊ እሴቱ ላይ ትኩረት አድርገን ከዚህ እንደሚከተለው ቃኝተናል።
በአዲስ አበባ ከተማ ሳርቤት አካባቢ በዓሉን ሲከበር ጠበብ ባለና በተመጠነ የሰው ቁጥር ቢሆንም ታዳሚው በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በሚለበሱ የባህል አልባሳት በዓሉን ደመቅ አድርገውት ነበር። የአንድ ክልል አልባሳትን ብቻ ለመመልከት ብንሞክር የተለያዩ አልባሳት መኖራቸውን እንታዘባለን። የልብስ ስፌቱ፣ የቀለም አገባብ፣ የጨርቁ አይነት ከነጌጣጌጡ ይለያያል። ወንዱም ሴቱም በአካባቢው አልባስ ደምቆ ነበር። ሁሉም የየራሱ ውበት ስላለው አንዱን ከሌላው ለማበላለጥ ያስቸግራል።
እንደ አጋጣሚ ግን ነጭ በአረንጓዴ ጥለት በሀር ባህል ልብስ የተዋቡትን ወይዘሮ ከዚና አባዱላን አግኝተን ቃለ መጠይቅ አደረግንላቸው። በኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ከዚና በጅማ የባህል አለባበስ ነበር በበዓሉ ላይ የታደሙት።በግንባራቸው ላይም ከጨሌ የተሰራ ጌጥ አድርገዋል።
ወይዘሮ ከዚና ስለለበሱት የባህል ልብስ እንዳጫወቱን በኃይማኖትና በተለያዩ ክብረ በዓላት ወቅትና በሰርግ እንዲሁም እንደዛሬው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል እና የተከበረ እንግዳ ፊት ሲቀርቡ ይዋቡበታል። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ላይ መለበሱ ማንነትን ማስተዋወቂያ ስለሆነ ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል።
ልብሱ በአረንጓዴና በቀይ ጥለት ከፈትል ነው የሚዘጋጀው። የጥለቱ ቀለም እንደ ፍላጎት ቢሆንም በእናቶች የሚዘወተረው ግን አረንጓዴው ቀለም ነው። ከልብሱ ጋር ተስማሚ የሆነ ከብር የሚሰራ የአንገት፣ የእጅና የግር አልቦ እንዲሁም በአናት ላይ በሚደረግ ጌጥ ይለበሳል። የፀጉር አሰራሩም እንዲሁ ከአዘቦቱ ይለያል።
አንዲት ሴት ከነጌጡ ለባህል አልባሳቱ በአሁኑ ወቅታዊ ገበያ እስከ 10ሺ ብር ወጭ ታደርጋለች። አቅምን የሚፈትን ቢሆንም አስፈላጊ ሲሆን ግድ ነው ይላሉ ወይዘሮ ከዚና። ቀደም ሲል ከሶስት መቶ እስከ ስድስት መቶ ብር እንደነበር ያስታውሳሉ።
እርሳቸው የለበሱት የሀገር ባህል ልብሱ ፈትል ቢሆንም ጌጣጌጡ ግን የጅማን ባህል የሚያንጸባርቅ አይደለም። ለማመሳሰል ነው የሞከሩት። ወጭውም ቀለል ያለ ነው። በአሁኑ ጊዜ በማመሳሰል እየተዘጋጀ በመሆኑ ተጠቃሚው ወደሚቀለው እያደላ መሆኑን ይናገራሉ። የመግዛት አቅምን ባገናዘበ ቢቀርብ ግን ቱባውን ባህል ለማስቀጠል ይረዳል ይላሉ።ችግሩ አሁንም ድረስ በኦሮሚያ የጉጂ የቦረና አካባቢ እናቶች ያልተበረዘው የባህል አልባሳት እየተጠቀሙ ስለሆነ እንዳይበረዝ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ይላሉ። ተመሳስሎ የሚዘጋጀው አልባሳት ቱባውን ባህል እንዲበረዝ ከማድረጉ በተጨማሪ በሽመና ላይ የቆዩ ባለሙያዎችን ከሙያው ውጭ እንዳያደርጋቸው ይሰጋሉ።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እና እኩልነታቸው የተረጋገጠላቸው ቀን ብቻ ሳይሆን፣ አለባበሳቸው ሳይቀር ጎልቶ የሚወጣበት ነው ያሉት ወይዘሮ ከዚና፣ ባለፉት 14 ዓመታት በዓሉ ሲከበር እንደክልላቸው የኦሮሞነት መገለጫ የሆኑ ብዙ እሴቶች ጎልተው የወጡበት እንደሆነ ያምናሉ። ከዚህም በላይ ግን ትክክለኛውን የባህል እሴት ለተተኪው ትውልድ እያስተላለፉ መሄድ ላይ ሥራዎች እንደሚጠበቁ ያምናሉ። በዓሉ ከሌሎች ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋርም የሚያስተሳስር በመሆኑ ከበዓሉ ውጭም እርሳቸውን ጨምሮ እያንዳንዱ የየራሱን በመወጣት ሊያጠናክረው ይገባል ይላሉ።
በአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከፍተኛ የቅርስ ጥናት ባለሙያው መምህር መክብብ ገብረማርያም በሰጡት ሙያዊ ትንተና የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ማንነትን የሚገልጹ የተለያዩ እሴቶች የሚንጸባረቅበት ብቻ ሳይሆን፤ ለቱሪስት መስብህም እንዲሆን በማድረግ ለዓለም ጭምር ማስተዋወቅ ይቻል ነበር። ገቢ በማመንጨትም ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ነው የሚያስረዱት። ያለፉት በዓላት በዚህ መልኩ የተቃኙ እንዳልሆኑ እንደ ባለሙያ ታዝበዋል።
ከዚህ ቀደም ባሉት በዓላት ላይ ትኩረት ሲደረግ የነበረው ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት፣ ጥናታዊ ጽሁፍ ማቅረብና ዕለቱን ለማክበር ብቻ በሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ ነው። ጥናቶቹም ቢሆኑ ሰፊ እይታ ያላቸው ባለመሆናቸው አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅ ከማድረግ ባለፈ እንደተባለው ሀገር ተሻጋሪ እንዲሆንና ገቢ እንዲያመነጭ የፈተሸ አይደለም። በዓሉም የስብስብ መልክ ነው ያለው።
በክብረ በዓሉ ወቅት ከፍተኛ አመራሮች ይገኛሉ። የሆነ ኩነት ይከናወናል። በዓሉ ይጠናቀቃል። ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ተንቀሳቃሽ ያልሆነ የምስል ክምችት እንዲኖረው በማድረግ ማንነታቸውን በሚገልጽ መልኩ ዝግጅት እየተደረገ ነው የሚል እምነት የላቸውም።
የበዓሉ ታዳሚዎችም በሌላ አካል የሚያከብሩት እንጂ የራሳቸው አድርገው ተቀብለውት ነው ለማለት አያስደፍርም የሚሉት ባለሙያው ሌላው ትዝብታቸው በዓሉ ማንነትን የሚያዛባ ማሸብረቅ እንደሚበዛበት ማስተዋላቸው ነው።
እንደ ባለሙያው ገለፃ በሌሎች ሀገሮች የሌለ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚንጸባረቅ አንዱ ከሌላው በኃይማኖት፣ በቋንቋ ልዩነት ሳያደርግ አብሮ ተሳስቦ የሚኖርባት ሀገር ናት። ብሄረሰቡ እርስ በርሱ ከመተሳሰሩ የተነሳ አንዱን ከሌላው ለመለየት እንኳን የማይቻልበት የተጋመደ ነው። በብሄር ብሄረሰቦች በዓል ግን እነዚህ እሴቶች ተለይተው እየወጡ አይደለም። በዓሉን ለማድመቅ የሚፈጠሩት ጥረቶች ቢደገፉም ዓላማውን እንዳይስት ግን ይሰጋሉ።
ባለሙያው እንደሚሉት አንድ ብሔረሰብ ማለትዜግነት ነው። ከቅኔው፣ ከእንቆቅልሹ፣ ከምሳሌያዊ ንግግሮቹ፣ ከተረትና ምሳሌው፣ የአበላል ሥርአቱ፣ ቋንቋው፣ አኗኗሩ፣ ስልጣኔው፣ በአስተዳደር መዋቅሩን ሁሉ ያካተተ በመሆኑ ይሄን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ መሆን አለበት።
አንዱን ብሄረሰብ ብቻ ለይተን ብናይ እንኳን የማያልቅ ቱባ ባህል አለው። በበዓሉ ላይ የሚጋበዘው ዕንግዳ ይሄን ሁሉ እንዲያይና እንዲያደንቅ ነው። ግን ይሄ አላማ ግቡን መትቷል ለማለት እቸገራለሁ ይላሉ።
ባለሙያው ክፍተቶቹን ብቻ አልተቹም መልካም የሆኑ ነገሮች እያስተላለፈ 15 ዓመታት እንደተጓዘ ይገልጻሉ። በእርሳቸው እይታ በዓሉ መስተጋብሮችን ፈጥሯል። እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ እንዲከባበር፣ እንዲዋደዱ አድርጓል። መነቃቃትን ፈጥሯል። በተለይም የባህል እሴቶቹ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር መልካም ነገር ፈጥሯል። ሀገራዊ ትስስርም ፈጥሯል። በጋራ ድምጽ ባህልን ማሳየት ተችሏል። ብሄረሰቦች የቻሉትን ሁሉ በማድረግ ማንነታቸውን ለማሳየት ጥረት አድርገዋል።
መምህሩ በምከረ ሀሳባቸው ይህን መልካም የሆነ ነገር ለማጎልበትም ሆነ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንዲቻል የሁሉም ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የባህል እሴቶች የሚታይበት የባህል ማዕከል አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መገንባት አለበት። ይህ ሲሆን ዓመቱን በሙሉ ቱባው ባህል ይጎበኛል።
የዓለም ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣም መንገድ ይከፍታል። በዚህም ከዓለም ተወዳዳሪ የቱሪዝም ከተማ መፍጠር ይቻላል። አዲስ አበባ ለሁሉም ማዕከል፣ የዓለምአቀፍ ድርጅቶችና ኤምባሲዎችም መቀመጫ በመሆኗ የማዕከሉ መኖር ውጤታማ እንደሚደርግ ያምናሉ።
ለዝግጅት ክፍላችን ሃሳባቸውን እንዳጋሩን እንግዶች ሃሳብ የሚታረሙ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም በዓሉ ብዙ ቱሩፋቶች አስገኝቷል። ተረስተው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጎልተው እንዲወጡ፣ በማንነታቸው አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ፣ አንዱ ከሌላው መልካም ነገር እንዲቀስም መልካም ልምድ አስገኝቷል።
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ‹‹እኩልነትና ህብረብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና›› የሚል መሪ ሃሳብ ያለው ሲሆን ይህም አንድነትና አንድ አይነትነት፣ እኩልነትና እኩል መሆን ምንድን ናቸው? ይህ እኩልነትና አንድነት በምን ሁኔታ ሲተገበር የጋራ ብልጽግናን ያጎናጽፋል? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ ነበር።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2013