ዘላለም ግዛው
በደርግ በጊዜ ትልልቅ አውራጃዎችን የመሩ ሰው ናቸው። ለአብነትም በከፋ ክፍለ ሀገር የማጂ አውራጃ የኢሰፓአኮ ተጠሪ፣ ደቡብ ሸዋ የኢሰፓአኮ ተጠሪና በማጂ አንደኛ ጸሐፊ ሆነውም አገልግለዋል። ከዚያ ደግሞ ሾኔ ላይ የኢሰፓ አንደኛ ጸሐፊ ሆነው እስከ 1983ዓ.ም ድረስ በሙያቸው ሰርተዋል።
ከዚያ በኋላም ቢሆን የፖለቲካ ሳይንስና የሕግ ምሩቅ በመሆናቸው በግላቸውም ቢሰሩ ለአገር ማበርከት ያለባቸውን ሲያደርጉ ነው የቆዩት። የዛሬው ‹‹ የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አቶ ግዛው ከበደ። ስለዚህም ከእርሳቸው ጋር ብዙ ወቅታዊ ጉዳዮችንና ሕይወታቸውን ስላነሳን ትማሩበት ዘንድ ጋበዝን።
አዲስ ዘመን፡- እስኪ ከልጅነትዎ ጀምረን እናውራ፤ የት ተወለዱ፣ አስተዳደግዎስ ምን ይመስላል?
አቶ ግዛው፡- ትውልዴ በጨቦና ጉራጌ አውራጃ ወሊሶ /ወንጪ ወረዳ ውስጥ ዋልጋ በሚባል አካባቢ ሰኔ 03 ቀን 1951 ዓ.ም ነው። ትምህርት የጀመርኩት ደግሞ ከጎንደር፣ ከጎጃምና ከተለያዩ አካባቢዎች ቅስና ተምረው ወሊሶ የተገኙትን አባቴ እየቀጠረ አስተምሮኛል። ስለዚህ በቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ቆጠርኩ። ከዚያ በዘመናዊ ትምህርት የመጀመሪያ ደረጃን ራስ ጎበና፣ ሁለተኛ ደረጃን ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ተከታተልኩ። ወደ ሩሲያ ሄጄ እንድማር እድል ባገኝም ባለቤቴ ባለመፍቀዷ የተነሳ የካቲት 66 የፖለቲካ ትምህርት ቤት ገብቼ እንድማር ሆነ። በማዕረግም ተመረቅሁ።
አዲስ ዘመን፡- ፖለቲከኛ ለመሆን ምን አነሳሳዎ?
አቶ ግዛው፡– በአጎራባች ያሉ ገበሬዎች በባላባቶችና በመሬት ከበርቴዎች ብዙ መከራ ሲደርስባቸውና አንዳንዶች ደግሞ በሌሊት ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ሲደረጉ አይቻለሁ። ከዚያም በላይ ገበሬው ካመረተው አስር ኩንታል ውስጥ ሁለት ኩንታል ተኩል ለራሱ አስቀርቶ ሌላውን ለፊውዳሉ ማስረከቡ ያበሳጨኝ ነበር። ከሁሉም የሚብሰው ገበሬው ራሱን፣ ሚስቱንና ልጆቹን ሳይቀር በጉልበታቸው የፊውዳሉ አገልጋዮች እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል።
የመሬት አዋጅ ሲታወጅና የፊውዳል ስርዓት ተገርስሶ ገበሬው ባለመሬት በሚሆንበት ጊዜ እጅግ በጣም ደስተኛ ነበርኩም። ስለዚህም ይህ ነጻነት ፍለጋ ይመስለኛል በትምህርቱ ገፍቼ እንድታገል ያደረገኝ።
ከዚህ በተጨማሪ ለፖለቲካ በነበረኝ ፍቅር የተለያዩ ፖለቲካ ድርጅቶች የሚያወጧቸውን ጽሑፎችና የደርግን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምን እከተል ስለነበረም እንድሳተፍበት አድርጎኛል። ማርክሲዝምና ሌኒኒዝም ፍልስፍና በሚያስተምሩ የጥናት ክበቦች ውስጥም መሳተፌ እንዲሁ። ግን የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል አልነበርኩም።
በደርግ ጊዜ የምርትና የፖለቲካ ካድሬ እንድሆን ተጠይቄም የ11ኛ ክፍል ተማሪ ስለነበርኩ አልፈለኩትም። ግን ወደ አዲስ አበባ ከገባሁ በኋላ ማስመሰሌን ቀጠልኩ። ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዝግጅት ማድረጉ ላይ ትኩረቴን አደረግሁ።
ግን ሁኔታው ሲያጋልጠኝ ተይዤ ታጠቅ ሰልጥኜ በከፋ ክፍለ አገር የማጂ አውራጃ የኢሰፓአኮ ተጠሪ፣ ደቡብ ሸዋ የኢሰፓአኮ ተጠሪና በማጂ አንደኛ ጸሐፊነትና ሾኔ ላይ የኢሰፓ አንደኛ ጸሐፊነት እስከ 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ አገሪቱን እስኪቆጣጠር ድረስ ሰራሁ። ከፖለቲካው ጋርም ተቀላቀልኩ።
አዲስ ዘመን:- እንደ ፖለቲካ ምሁርነትዎ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንዴት ይረዱታል?
አቶ ግዛው:- የኢትዮጵያን ፖለቲካ ዝም ብለህ ውስጣዊ አካሉን ወይንም እንቅስቃሴውን ብቻ አይተህ መገመት የምትችለው አይደለም። የዓለም አቀፍ መለዋወጥም አብሮ ይዞት የሚሄድ ነው። በቀደመው ዘመን ዓለም ለሁለት ተከፍላ ነበር። ምስራቅና ምዕራብ፤ የሶሻሊስትና የካፒታሊስት ጎራ በሚል። እናም ከምስራቅም ከምዕራብም አልሆንም ለሚል የገለልተኛ አገሮች ንቅናቄ ስለነበር ወደዚያ ይገባል። ይህም ነጻ ነው ባይባልም። እናም ይህ እውነታ በየትኛውም ሀገር ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ግንኙነቶች ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም ።
ለምሳሌ አልባኒያ ከማንኛውም አገር ጋር አልሆንም ብላ በሯን ዘግታ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ ከፍታ እየተገለገለች በኢኮኖሚ ራሴን እችላለሁ ብላ ነበር። ግን አገሪቱ ኢኮኖሚዋ እየፈራረሰ መጣ። በአለም ላይ አንዴ ጠቅልለህ በምትጎርሳት እንጀራ ውስጥ ጭምር የአለም ሰራተኞች እጅ አለበት።
ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ተባይ መከላከያ፣ የውጭ ወዛደሮች የተሳተፉበት ማጭድ አምራች፣ ማረሻ አምራቹ ሁሉ እዛ እንጀራ ውስጥ አለ። በመሆኑም ተነጥሎ የሚደረግ ነገር የለም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ፖለቲካም ከዚህ አንጻር ይታያል።
በፊት የሶሻሊስት አገራት ጎራ ውስጥ የነበሩ አገራት ከሶሻሊስት አገራት ድጋፍ ያገኛሉ። በዚህም ነጻ አውጪ ንቅናቄዎች ጫካ ውስጥ ጠንካራ ነበሩ። በቂ መረጃ ይሰጣቸዋል፣ የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ ራሳቸውን ችለው ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ይዋጋሉ። ደርግ ደግሞ ወደ ሶሻሊስት ጎራ ለማስገባት አቅጣጫውን ለመለየት ቢያስቸግርም ቀስ በቀስ በፊደል ካስትሮና በዛን ጊዜ በነበረው የየመኑ መሪ አማካኝነት ከሶቪየት ህብረት ጋር አበሩና ወደ ሶሻሊስት አቅጣጫ እንዲገባ አደረጉት።
የሀገሪቱ ፖለቲካ በ1950 ዎቹ የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ አሻራ ሙሉ ለሙሉ ተጽዕኖ አድርጎበት ነበር፣ አሁንም ያው ተጽዕኖ አልለቀቀውም። የብሔር ፖለቲካ ያንጊዜ የተጀመረና አሁንም ያልለቀቀ አስተሳሰብ ነው። ሌላው ደግሞ በሶሻሊዝም አቅጣጫ መጓዝ አለብን የሚልም አለ። እንዲያውም በእዛን ጊዜ የነበሩ የተማሪዎች ትውልድ ህብረተሰቡን ለመለወጥና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የቆመ ቢሆንም እያደገ ሄዶ ዛሬ የያዘው አቅጣጫ የዚያ ዘመን አሻራ ነው ብዬ አምናለሁ።
አሁን አፍሪካ ውስጥ ስልጣን ከያዝክ ስልጣን፣ ሃብት እና ክብር ታገኝበታለህ። የፈለግከውን መግደል፣ መቁረጥና ምንም ማድረግ ትችላለህ። ከእግዚአብሄር በታች አንተ ሀያል ነህ። በኢኮኖሚም የበላይነት ይኖርሃል። አፍሪካ ውስጥ በሰው እጅ ያለ ገንዘብ እንኳን ያንተ ነው።
ስልጣን መቆናጠጥ ደግሞ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። እንኳንስ ስልጣን ተይዞ። እናም አሁንም የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች አትራፊዎች ናቸው። የመንግስት ግብርም ቀረጥም አይከፍሉም። ግን ሃብት የያዙ ናቸው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው፤ የሰዎች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጣሱትም ከዚህ የተነሳ ነው።
ሕግ እናስከብርም የሚሉት መነሻ ያደረጉት ኃላፊነት ቢሰጣቸው ሌላውን ጨቁነውና ገርፈው ስልጣን ላይ ያለውን ካስወገዱ በኋላ ተወጋጁ ከሚያደርገው በላይ ማድረጋቸው አይቀርም።
ህወሓት ሲያወራ የነበረው ስለዴሞክራሲ፣ ስለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ነበር። ግን በውጊያ ስልጣን የያዙትን የአፍሪካ አገራትን ትተን በአገራችን በተግባር የተሰራውን መመልከት በቂ ነው። አዲስ አበባ ከተማና ክልሎች ከህወሓት ነጻ አልነበሩም። የትኛው የክልል ርዕሰ መስተዳድር ነበር ከህወሓት ነጻ ሆኖ ውሳኔ ይሰጥ የነበረው? የትኛው አካባቢ ነው መሬት ያልተወሰደበት? ማነው በማፈናቀል ተጠቃሚው ማንስ ነው አፈናቃይ? ይህ ሲታይ የትኛውም አገር መጥቀስ አያስፈልግም። የብሄር ፖለቲካ ምንም ፋይዳ የለውም።
ለምሳሌ እያንዳንዱ ሰው ወይም የፖለቲካ መሪ ሃይማኖት አለኝ ይላል። ሃይማኖቱ የሰው ምንጩ አዳምና ሄዋን ነው ቢልም እነርሱ በቀለሙና በብሔሩ ለይተው ከዚህ ነው የሚሉ ናቸው። የሰው ልጅ ሁሉ ወንድማማቾች ናቸው ይላል። እነርሱ ግን አንተ አማራ ነህ፣ ኦሮሞ ነህ፣ሶማሌ ነህ… ይላሉ። እምነት አለኝ ብሎ የሚከተለውና በድርጊት የሚፈጽመው የተለያየ ነገር ነው።
ፖለቲካ ለጥፋት ሳይሆን ለበጎ ነገር፣ የተሻለ ልማት ነው መዋል ነው ያለበት። ልማት የሚመጣው ደግሞ ሰው ገድለህ፣ ቀብረህና አቃጥልህ አይደለም፤ በብስለት ነው። የኔ ሃሳብ ይበልጣል። ስልጣን ባገኝ ይሄንን እሰራለሁ ብለህ ሕዝቡን አሳምነህ ከጎንህ አሰልፈህ፤ ስልጣን ስትይዝም በብቃት ያልከውን ብትተገብር ድጋሚም ትመረጣለህ። ሰው ገለህ ከሆነ ግን ቢከተልህም በፍርሃት እንጂ በማመን አይደለም። ሰውን በማሳመን ነው የራስህ ወገን ማድረግ የሚቻለው። ስለዚህም እንደሌሎች አገሮች በአገራችንም እውነተኛ መሰጠት ያለበት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን:- የአገሪቱ መሰረታዊ ችግሮች ከምን የመነጩ ይመስልዎታል?
አቶ ግዛው:- ብዙ ምንጭ አለው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ዋናው ምንጭ ከብሔርና ከጎሳ ፖለቲካ ጋር ይያያዛል። ለምሳሌ መኢሶን ውስጥ የነበሩ ሰዎች ለመላው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ምስረታ ተጋድሎ አድርገዋል። እነ ሃይሌ ፊዳ ሲከተሉት የነበረው አቋም ይሄ ነው። ቀስ በቀስ ፓርቲው ፈረሰ፤ ሂደቱም ተስተጓጎለ። መጀመሪያ ተይዞ የነበረው ስኬታማ ስላልሆነ በተወሰኑ ጉዳዮች እየተጣበቀ ቀጥሎ ውድድር ውስጥ የብሔር ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ ሰዎች ተሳተፉ። የብሔሮቻቸው ደጋፊዎች አቋማቸውን ሳይረዱም ደገፏቸው። ግን እንዲህ አይነት ነገር በአገር ጉዳይ ላይ አይሰራም።
በተማሪዎች እንቅስቃሴ የዋለልኝ መኮንን ጽሑፍ በመድረክ ከቀረበ በኋላ የብሔር ጉዳይ ጎልቶ እንዲነሳ ተደረገ። በወቅቱ በእንቅስቃሴው እነሌንጮ ለታና ገላሳ ዲልቦ ነበሩበት። እነርሱ የኦሮሞን ፖለቲካ እንደብሔር ጭቆና ይዘው ወጡ። የኢትዮጵያ ተማሪዎች ይህንን ይዘው ሲንቀሳቀሱ ምን ያስከትላል፣ አገሪቱን ወዴት ይወስዳል የሚለውን ግምት አልነበራቸውም ።
ከዚያ ህወሓት ተሳክቶላት ወደ ስልጣን ወጣ። መዋቅር ዘርግቶም 27 ዓመታትን ሲሰራበት ኖረ። እኔ እንጂ አገር የሚል አልነበረም። የሀሰትና በጭራሽ ተመዝግበው የማይታወቁ የተፈበረኩ ታሪኮች ተፈጠሩ። እንደ እነተስፋዬ ገብረአብ አይነቶች በአቶ መለስ አማካኝነት የብሔርን ጉዳይ በሚገባ መሰረት ጣሉበት። በደንብ ተደርገው መጽሐፍቶች ተጻፉ። አካሄዱ የክፍፍል፣ ወደ መንደር የመመለስ፣
የራስን ጎሳ ብቻ የማየትና ሌላውን እንደሰው ያለመቁጠር ነገር ነው። በዚህ የተነሳም ሁሉም ወደማያውቀውና ወዳልተፈጠረበት አዳዲስ ክርታስ ገባ። አሁን ክርታሱ ሲነካ አደጋ ላይ እወድቃለሁ የሚል ስጋት ጋርዶት ሁሉም እንደጠላት መተያየት የጀመረው በዚህ ሥራ ነው።
በሌንጮ ለታ፣ ሌንጮ ባቲ እና ገላሳ ዲልቦ ሲመራ የነበረው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ድርጅት ሲሰራ የነበረው ኦሮሞን የመነጠልና የራሱን መንግስት እንዲያቋቁም ነበር። በጥበት ላይም የተመሰረተ አልነበረም። ግን ኦሮሞ ተጨቆነ ብለው ነበር። በኋላም የግንጠላው መስመር ትክክል አይደለም ብለው ተቀብለው፣ በኢትዮጵያዊነታችን መቀጠል አለብን ብለው ራሳቸው መለሱ። ይህንን አንቀበልም ብለው ቀርተው የገፉበትም አሉ። ስለዚህም የብሔር ፖለቲካ መስመር የያዘውና ህጋዊ ከለላ ያገኘው ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ነው።
የብሄር ፖለቲካ ሲታይ በዋናነት ሁሉንም የብሄሩን ሕዝብ ያካተተ፣ በአንድነት እንዲሰለፍ የሚሞክር ነው። ጠባብ አስተሳሰብ ስላነገበም መሪው የራሱን መንደር፣ ቀበሌ፣ ክልል፣ የወረዳ ሰዎችና የሚቀርባቸውን ይመርጥበታል። ሂደቱ አልፎም ወደ ቤት ይገባና በልጆች መካከል አንተ እናትህን ነው የምትመስለው፣ አንተኛው የእኔ ነህ የሚል የክፍፍል ስሜት ይፈጥራል። መዳረሻውም ቤት ይሆናል።
አዲስ ዘመን:- ለውጥና የለውጡን ሀይል አሰላለፍ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ግዛው:- የለውጥ አሰላለፉ ሁለት ጎራ ይዟል። የጎሳ/ የብሔርን ፖለቲካ እያቀነቀነ የራሱን ጎሳና ብሔር ወደ ስልጣን በማምጣት በአገሪቱ ሃብት ክፍፍል ከፍ በማድረግ ራሱን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚጥር አለ። ሌላው ደግሞ በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ጎሳ መብቱ እንዲጠበቅ፤ እኩልነቱ እንዲከበር ሁሉም በሕዝብነቱ፣ ሰው በሰብአዊ ክብሩ ሳይበላለጥ እንዲኖር የሚንቀሳቀስም ጎራ ነው። እናም አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) የሚመራውም ይህን የሚያደርግ ነው።
በሌላ ጎን ደግሞ አንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች የብሄር ፖለቲካ የመሰረተው ኢህአዴግ አስገድዶን እንጂ አገራዊ ፓርቲ ሰይመን ለመደራጀት ስንጠይቅ በጎሳችሁ ካልተደራጃችሁ በሚል ነው እንዲህ አይነት ስያሜ የሰጠነው ብለው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ዛሬ ደግሞ የጎሳ ፖለቲካ ብቻ ለማራመድ የሚሞክሩ የተፈጠሩበት ወቅትም ነው። ግን በአንድ ጎን የብሄር ፖለቲካና የኢትዮጵያን ህዝብ ያጠቃለለ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር የዴሞክራሲ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እኩልነት መብት እንዲፈጠር ለማድረግ የቆመ ኃይልም የተፈጠረበት ጊዜ መሆኑም አይዘነጋም።
እንደ ብልጽግና፣ እንደ ኢዜማና ሌሎችም ፓርቲዎች በአገር ደረጃ የትኛውንም ጎሳ ሳይለዩ የሚንቀሳቀሱ አሉ። የየራሳቸው የሆነ የፕሮግራምና የአካሄድ ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል። ግን ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የሚፈልጉ ናቸው። የጎሳ ፖለቲካ ደግሞ እርስ በርስ ውድድር ፈጥሮ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት የመግባት ሃሳብ የያዘ ነው።
ስለሆነም አሁን ያለው በዶክተር አብይ የሚመራው ኃይል ይህንንና መሰል ሥራዎችን ማስቆም ይኖርበታል። ትኩረቱንም የበለጠ የሕዝብ የበላይነት የሚያመጣበት አገራዊ ስዕል መሳል ላይ ፣የሁሉም ሕዝብ መብትና እኩልነት፣ የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ጥቅም ማስከበር ላይ ማድረግ አለበት። አሁን እየሆነ ባለው ነገር እንደሚያደርገውም እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን:- ሀገርን እንደ ሀገር እያጋጠማት ያለውን ችግር እንዴት ይገነዘቡታል?
አቶ ግዛው:- አሁን ለውጡ ተቀልብሷል እየተባለ ይጻፋል፣ ይነገራልም። ግን እኔ እንዳየሁት ለውጡ ለአንድም ቀን ወደኋላ አልታጠፈም፤ ወደፊት እየሄደ ነው። ብዙ ደጋፊዎች አሉት። በየትኛውም መስመር እውነትን ይዞ ስለሄደ ስኬታማ ነው። አሁን በመድረክ ላይ ወይም በየመንደሩ ያሉ ሰዎች ብዙ ተደማጭነት የላቸውም። በጥቂት የለውጡ ተቃዋሚዎች የሚደረግ እንቅስቃሴ አለ። ለውጡ ወደፊት በተራመደ ቁጥር የለውጡ ተቃዋሚዎች አቅማቸው እየደከመ እንደሚመጣ አምናለሁ።
የሕዝብ መፈናቀል ችግሩ ፖለቲካውን እናንቀሳቅሳለን የሚሉ የፖለቲካ መሪዎች አስተሳሰብ ውድቀትንና ደካማነትን የሚያሳይ ነው። የትኛውም የፖለቲካ አካሄድ የሰው ደምን የሚያፈስስ፣ የሰው ንብረት የሚያወድም ከሆነ አንገቱ ላይ ማነቆ ገመድ እያስገባ እንደሆነ ማወቅ አለበት። ሁልጊዜ አንድን ነገር በማጥፋት ውጤት አመጣለሁ ስትል የበለጠ አንተን የሚያጠፋ ቢላዋና ሞረድ ታዘጋጃለህ። አጥፊህንም ታበራክታለህ። ግን ሚዛናዊ ሆነው የተቀመጡ ሰዎችን ወደራስህ ለመሳብ ሃሳብ ብቻ ነው የሚበቃህ።
በለውጥ ሂደቱ ብዙ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ ችግር ውስጥ ገብተዋል፣ ብዙ ሰዎች ሞተዋል፣ ብዙ ንብረትም ወድሟል። ይሄ ደግሞ በአንድ የለውጥ ወቅት ሊከሰት የሚችል ነው። አሁንም ተመልሰው ማንሰራራት ያልቻሉ የአረብ አገራት አሉ። ሊቢያ ለማንሰራራት ገና ብዙ ይቀራታል። ሶሪያ የራሺያ መግባት ነፍስ እንድትዘራ አድርጓታል።
ግብጽም በእዚህ ሂደት አልፋ ነው ነፍስ ለመዝራት የበቃችው። ኢትዮጵያ ግን ወደ እዛ ደረጃ አልወረደችም። ነገር ግን በየሰፈሩና በየመንደሩ ችግሮች አሉ።
በሌላ ጎን የአባይን ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ የውጭ ኃይላት እጃቸውን አስገብተው በገንዘብ እየደገፉ አገሪቱ እንድትታመስ ያደርጋሉ። መንግስት ግንባታውን ትቶ አገር የማረጋጋት ስራ እንዲሰራ ለማድረግ። ስለዚህ ኢትዮጵያ እየታገለች ያለችው የውስጥ ጠላቶችን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለማመስና ኢትዮጵያ እንዳልነበረች ለማድረግ የሚጥሩ ብዙ አገራትን ጭምር ነው።
የአባይ ውሃ ቀላል ነገር አይደለም። እንደነኩዌት፣ ግብጽ፣ ኳታር፣ አረብ ኤምሬትና ሌሎችም የአረብ አገራት ከግብጽ መሬት ተከራይተው በአባይ ውሃ ሕዝባቸውን ይቀልባሉ። እስራኤል ውሃ በቱቦ እየፈሰሰላት ትጠቀማለች። ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት ግድብ ሺ ጊዜ ብትገድብ ውሃ አያጡም። በከርሰ ምድር ያላቸው ውሃ በቂ ነው። ግን ወደፊት ድርቅ ቢከሰት ውሃ ካልተረፋቸው ስጋት አላቸው። ከዚያም ውጪ ኢትዮጵያ ተረጋግታ የግድቡን ግንባታ ብታጠናቅቅ ብዙ ጥቅም ሊቀር ይችላል የሚል ስጋት አለባቸው።
ሌላው ደግሞ የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታም አለ። በአባይ ግድብ የተነሳ ኢትዮጵያ የምትለው ነው የሚሆነው። የግብጽ ተስሚነት ያን ያህል ነው። ስለዚህ ግድቡ ዝም ብሎ ውሃ ብቻ አይደለምና እነዚህ ኃይሎች እጃቸውን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አልከተቱም ማለት በጣም የዋህነት ነው። በመሆኑም በገንዘብ የማይደገፍ የፖለቲካ ድርጅት አለ ለማለት ያስቸግራል። ወይ በቀጥታ አልያም የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ተወክሎ በእዛ ፖለቲካ ፓርቲ አማካኝነት እየተደገፉ አገር እንዲፈርስ ይሰራሉ።
ይሄንን ለመቀልበስ ደግሞ ከላይ ያለው አመራሩ ቁርጠኛ ሲሆን ከታች ያለው አመራር ግን ችግር አለበት። ምክንያቱም 27 ዓመታት የነበረውን ልምድ ቆፍሮ አላወጣውም። ወደ ስልጣን እንደሚመለሱ፣ ነጻ እንደሚያወጧቸውም የሚያስቡ ስልጣን የያዙ ወገኖች በታችኛው መዋቅር ውስጥ አሉ።
እነዚህን አካላት የለውጥ አመራር ሕዝባዊ ኮሚቴ አቋቁሞ ሕዝብ እንዲተቸው፣ የስራ አቅጣጫ እንዲከተል፣ ቢሮ ውስጥ ስራውን በአግባቡ እንዲሰራ ማድረግና ባለስልጣኑን መፈተሽ ይኖርበታል። በምርጫ የሚቋቋም መንግስት ስልጣን እስኪረከብ ድረስ ታችኛውን አመራር ሊቆጣጠር የሚችል ሕዝባዊ ኮሚቴ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን:- አሁን ትልቁ ችግር የብሄር ፖለቲካ ነው ይባላል። በደርግ ስርዓትስ እንዲህ አይነት ችግሮች አልነበሩም?
አቶ ግዛው:– በደርግ ጊዜ አንድ ፓርቲ ማለትም ኢሰፓ ነበር። ሌሎች እንደ ኦነግ፣ ኤርትራ ነጻ አውጪና የመሳሰሉት ናቸው። ኤርትራን ሳይጨምር እነዚህ የጎሳ ፖለቲካ መርህ የሚከተሉ ናቸው። ኤርትራን ነጻ ለማውጣት በኤርትራ ያሉት ዘጠኝ ጎሳዎች እንደአገር ይሰሩ ነበር። በፖሊሲ ደረጃ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለውጥ አላመጡም። ስለዚህም የደርግ ስርዓት የዘረኝነት፣ የጎሳ መርህ የሚከተል አልነበረም። ደርግ በሚገርም ሁኔታ ያቀነቅን የነበረው በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ነበር።
የስራ ብቃት ያለው የትኛውም ቦታ ላይ ይቀመጥ ነበር። ለምሳሌ ከሻቢያና ከህወሓት የከዱ ሰዎችን ብቃታቸው ታይቶ የሚመጥኑት ቦታ ላይ ይቀመጡ ነበር። ግን ቁልፍ ቦታ ላይ ተቀምጠው እየሰለሉ መረጃ ያቀብሉ ነበር። ይህንን ያደርግ የነበረው ሁሉንም ብሄረሰብ በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ያይ ስለነበር ነው። በብሄር ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ አልነበረውም።
የትኛውም በሕዝብ ጥያቄ የሚነሳ የፖለቲካ ፓርቲ የለም። የሕዝቡን ፍላጎት አጥንተው የፖለቲካ ምሁራን ናቸው የሚመሰርቱት። የሕዝብ ነው በማለት ሕዝብ የሚፈልገውን አጀንዳ በማንሳት ሕዝቡ ከጎናቸው እንዲሆን ያደርጋሉ እንጂ ሕዝብ ተሰብስቦ እንዲህ አይነት ፓርቲ መስርቱልን አይልም። የብሔር ፖለቲካው የሕዝብ ጥያቄ አይደለም፤ የምሁራን አጀንዳ ነው።
የትግራይ ሕዝብ ሕወሃትን በከፍተኛ ደረጃ እየተዋጋ ነበር። ሽፍታ ስልጣን ይዞ አያውቅም፤ ሕዝባችንን አታዋጉ እያለ ሲቃወም ነበር። እንደውም ከየትኛውም ሕዝብ የትግራይና የኤርትራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ነው። ግን ህወሓትን የሚቃወሙ የትግራይ ሕዝብን ስልጣን ላይ የነበሩት በስልጣናቸው መከታ አድርገው አስጨፍጭፈው የህወሓት የበላይነት እንዲኖር አደረጉ። እናም እንደ ደርግ ሲነሳ ባለስልጣናቱ ዛሬ ለህወሃት እዚህ መድረስ አስተዋጽኦ ያደረጉ መሆናቸው አንዱ ችግር ነው።
አዲስ ዘመን:- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን እንደመጡ በሙስናና ብልሹ አሰራር ሊጠየቁ የሚገባቸው አንዳንድ አመራሮችን ማሰር ነበረባቸው የሚሉ አሉ። እርስዎ ይህንን እንዴት ያዩታል?
አቶ ግዛው:- ዶክተር አብይ ሁሉንም ጥፋተኞች ሰብስቦ ባለማሰር የወሰደው ርምጃ ትክክል ነው። አሁን እኛ ለአገሪቱ መፍትሄ የምንላቸውና የምናስባቸው ነገሮች አሉ። አንደኛ ውስጡ አይደለንም ከመረጃው የራቅን ነን። ስለዚህ የሚመስለንን ሃሳብ እናመነጫለን። የፖለቲካ ብስለታችን አገር ከመምራት አንጻር ስታየው እዛ ካሉ ሰዎች ጋር ራሳችንን ለማወዳደር እንሞክራለን እንጂ ውስጥ ያለውን ውስብስብ ጉዳይ የሚያውቁት ውስጡ ያሉ ሰዎች ናቸው። ዶክተር አብይ ያንን ያላደረጉት የራሳቸው ምክንያት አላቸው።
ሌላው ደግሞ ህወሓት ራሱ ለውጡን በመቀበል ወደ ብልጽግና ፓርቲ ለመምጣት አዝማሚያ ሲያሳይ ነበረ። ሐዋሳ ላይ በተደረገ ስብሰባ ዶክተር ደብረጽዮን ሲናገሩም ለውጡን እንደሚቀበሉ የሚያሳይ ነበር። ታዲያ እንዴት አሁን አንተ ያልከውን ሊያደርጉ ይችላሉ? እነርሱን ከማሰር ይልቅ አማራጭ ሰጥቷቸዋል።
ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር አለብን አላቸው። አንድ ላይ የሆኑ በማስመሰልና ስብሰባም እየተሳተፉ ከቆዩ በኋላ ግን ብዙ ነገር ስላልተመቻቸው ተውት። በመሆኑም ዶክተር አብይ አሁን የራሳቸውን የፖለቲካ ድባብ ባላስተካከሉበት አጋጣሚ እነርሱ ላይ አንድ ውሳኔ አስተላልፈው ቢሆን ኖሮ አስቸጋሪ እንደሚሆን እገምታለሁ።
እነዚህ ሰዎች ከተለያየ ሕዝብ የተወከሉ፣ በዘረፋ የተሳተፉ፣ በቡድን የተሳሰሩ፣ ንብረት ያፈሩ፣ የብዙዎችን ነፍስ ሲያጠፉና ሕገ ወጥ ስራ ሲሰሩ የቆዩ ናቸው። ይህ ያላቸው ደግሞ ከወንጀለኛው ቡድን ጋር እንጂ ከአብይ ጎን አይሰለፉም። ይታሰሩ ቢባል ኖሮ ያን ጊዜ አገሪቱ ወደአልተፈለገ ትርምስ ውስጥ ትገባ ነበር።
ይሄ የፖለቲካ ብልጠት ነው። እነዚህ ሰዎች እርምጃ ባይወሰድባቸውም ራሳቸውን በራሳቸው እየገደሉ ናቸው። ምንም አይነት አቅም የላቸውም። በብዙሃን መገናኛ የሚነዙት ፕሮፖጋንዳም ዋጋ ቢስ ነው። ጥይቱንም ተኩሰው ተኩሰው ይጨርሱታል።
የትግራይ ሕዝብም ከማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ በቡድኑ መከራና ስቃይ እያየ ነው። ሌላው ሕዝብ ወያኔን እየተቃወመ ኢኮኖሚውን ገንብተዋል። እነዚህ ሰዎች ግን የራሳቸውን ኩባንያዎች ገነቡ እንጂ ለትግራይ ሕዝብ ያደረጉለት ነገር የለም። የራሳቸውን ጀሌዎች አደራጅተው ነው የጠቀሙት።
ሕዝቡ ግን ምንም አላገኘም። ትግራይ ያለው የተበደለ ሕዝብ ነው። ቡድኑ የዛን ጊዜ ርምጃ ቢወሰድበት ኖሮ አሁን የያዘውን አቅጣጫ ይዞ ላይቀጥል ይችል ነበር። ርምጃ ሳይወስድ ሲቀር ደካማ ነው፣ ተለማማጭ ነው፣ ቄስ ነው፣ የነፍስ አባት ነው፣ የክርስትና አባት ነው እየተባለ ይተቻል። ግን እርሱ ብዙ ነገሮችን እየወሰደ ይገኛል። ብዙዎችም የጠራ አመለካከት እየያዙ ናቸው ትናንትና ዛሬ አንድ አይደለም።
አዲስ ዘመን:- ዶክተር አብይ በወቅቱ ርምጃ ባለመውሰዳቸው ምክንያት ለውጡ ተቀልብሷል የሚሉ ሰዎች ነበሩ። ይህስ እንዴት ይታያል?
አቶ ግዛው:– ህወሓት ስልጣን ከለቀቀ በኋላ ከዜሮ ተነስቶ ነው መልሶ አገሪቱ እንድታንሰራራ ያደረገው። በአንድ ሌሊት ደግሞ ውጤት አይገኝም። ለውጡ ተቀልብሷል የሚሉት ሰዎች የብሔር ፖለቲከኞች ናቸው። ዶክተር አብይ ኦሮሞ ሆኖ ስልጣን ከያዘ በኋላ ልክ እነዚያ የወንጀለኛ ቡድኖች ይሰሩበት በነበረው ስልት ንግዱን በመያዝ፣ ኢኮኖሚውን በመዝረፍ፣ መሬት በመቀራመትና የመሳሰሉትን ሕገ ወጥ ስራዎች በመስራት ጭምር ለምን አንሰራም? የሚሉም ናቸው ይህንን እያሉ ያሉት። ይህ ደግሞ የፖለቲካ ስራውን ለማዳከም ሲባል የሚደረግ ሲሆን፤ ለውጡ ግን ወደ ፊት እየገሰገሰ እንጂ ወደኋላ አልተመለሰም።
አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ!
አቶ ግዛው:- እኔም ለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2013