አትሌት ፀጋዬ ሳኚ፤ ለውትድርና የወጡት የሀገርን ጥሪ ተቀብለው የጥቂት ወራት ትዳራቸውን ጥለው ነበር። በቆይታቸውም ሀገር የጠላት ኃይልን ለማባረር ባደረገችው ጥረት ላይ የራሳቸውን ዐሻራ አሳርፈዋል። በትግል ወቅትም ከመረብ፤ በቦምብ ፍንጣሪ ተመትተው እስከ መቁሰል የደረሰ አደጋ አጋጥሟቸዋል።
በውትድርና ለሀገር መስዋዕትነት ከመክፈል ባለፈ፤ በአትሌቲክስ በተለያዩ የአፍሪካ እና የዓለም መድረኮች በመወዳደር የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል። ሁለት ጊዜ የደረሰባቸው አደጋ ከእሩጫ ውድድር አላስቆማቸውም። በዛሬ ገጻችን በውትድርና በአትሌቲክስ ያሳለፉትን የሕይወት ውጣ ውረድ እና ያስመዘገቡትን ድል በተመለከተ አቅርበንላችኋል።
አትሌት ፀጋዬ ትውልድና እድገታቸው አርሲ ክፍለ ሀገር ጭላሎ አውራጃ ኮፈሌ ወረዳ ሽሬ አራጌሴ ቀበሌ ነው። ከአንድ ገበሬ ቤተሰብ በ1948 ዓ.ም ቢወለዱም፤ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ተምረዋል። ቀጥለው ወደ መደበኛ ትምህርት የገቡ ሲሆን፤ በወቅቱ በአካባቢው ትምህርት የሚሰጠው እስከ ስድስተኛ ክፍል ብቻ ስለነበር ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ያለውን የትምህርት ደረጃ አክስታቸው ጋር አርሲ ሄደው እስከ ዘጠነኛ ክፍል ተምረዋል።
አትሌት ፀጋዬ እንደገለፁት፤ በ1968 ዓ.ም የደርግን መንግሥት በመቃወም በተካሔደ አድማ ትምህርት ቤቶች ተዘጉ። በወቅቱ ተማሪው፣ ወጣቱ ይገደል ስለነበር፤ የእርሳቸውም አብሮ አደግ ጓደኛቸው ተገደለባቸው። በዚህ ምክንያት ይበልጥ የተቃውሞው ተሳታፊ ሆኑ። ነገር ግን አባታቸው ‹‹አልፈልግም ልጄን ይገድሉብኛል›› ብለው አትሌት ፀጋዬን ወደ ቤት ወሰዷቸው።
እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በወቅቱ የነበሩ ጓደኞቻቸው ጭምር ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲገቡ ተደረገ። ገጠር ከተመለሱ በኋላ ለጥቂት ጊዜያት አባታቸውን በእርሻ ሥራ እያገዙ ቆይተው፤ የንግድ ሥራ መሥራት ጀመሩ። በወቅቱ የመሬት ባለእርስት የነበሩ ሰዎች የጦር መሣሪያ ስለነበራቸው ትጥቅ እንዲፈቱ ይደረግ ነበር። ስለዚህ ባለርስቶችን ሁሉንም ሰብስበው እስር ቤት ወሰዷቸው። እርሳቸውም ከተማ ቆይተው ሲመለሱ ኢሕአፓ ናቸው፤ ትምህርት ቤት እረብሸው መጥተዋል ተብለው ታሰሩ።
“አንድ ሳምንት ከታሰርኩ በኋላ፤ አባቴ በዛም በዚህም ብሎ አስፈታኝ። የዛኔ እህቴ ልታገባ ነበር። የእርሷ ሠርግ ካበቃ በኋላ እኔንም ማግባት አለብህ አሉኝ። ትዳር አልይዝም ወደ ትምህርት ቤት እመለሳለሁ ብላቸውም፤ የምትመለሰው ለመሞት ነው? አትመለስም የምታገባትን ሴት ምረጥ አሉኝ። ከእኛ ቤት ከፍ ብሎ የአንድ ባለእርስት ልጅ ነበረች፤ እሷን መረጥኩ፤ ሽማግሌ ተላከና ተጋባን።” በማለት ይገልጻሉ።
ከሚስታቸው ጋር የቆዩት ለስድስት ወራት እድሜ ብቻ ነበር። በ1969 ዓ.ም ሶማሊያ ኢትዮጵያን በመውረሯ በኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም በሚዲያ ጥሪ ተደረገ። እርሳቸውም ጥሪውን ተከትለው ዘመቻውን ተቀላቀሉ”።
ስለተመዘገብክ ትዘምታለህ አሉኝ፤ እምቢ ብዬ ብቀር ሌላ ችግር ነው። በዛ ላይ ደግሞ የሀገር ጉዳይ ነው። አባቴም አርበኛ ስለነበር ዝመት ልጄ አለኝ። አባቴ ቀድሞ በጦር ሜዳ ያለውን ነገር ስለሚያውቅ፤ ልጄ በጦር ሜዳ ላይ የሚያጋጥመው ብዙ ነገር ነው ። ስለዚህ መሣሪያ ይዤያለሁ ብለህ ንጹሓንን እንዳትገድል፣ የሰው ንብረት እንዳትነካ፣ ሴት ልጅ እንዳትደፍር ብሎ መከረኝ። “ይላሉ።
ዘመቻውን ከተቀላቀሉ በኋላ የሥልጠና ጊዜያቸውን አጠናቀው፤ ወደ ግንባር ለመሄድ እየተዘጋጁ እያለ የደርግ አባል የሆኑ አንድ ባለሥልጣን ሰልፉን ሲጎበኙ እርሳቸውን ተመለከቱና፣ “አንተ ገበሬ ነህ እንዴ?” ብለው ጠየቋቸው። እርሳቸውም መልሰው ገበሬ እንደሆኑ ገለጹላቸው።
ቀልጣፋነታቸውን ስለተመለከቱ ገበሬ ነኝ በሚለው ምላሽ ውስጣቸው አላመነም ነበር። በኋላም ወደ አንድ ሻለቃ አምጥተው ድጋሚ ሲጠይቋቸው መልሳቸው ተመሳሳይ ሆነ፤ እስከ ስንተኛ ክፍል እንደተማሩ ሲጠይቋቸው እስከ ሦስተኛ ክፍል ብለው መለሱላቸው።
ምክንያቱም ይላሉ አትሌት ፀጋዬ፤” ተማሪ ሆነው፤ ኢሕአፓ ሆነው ሠራዊት ውስጥ ተቀላቅለው ሠራዊቱን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ የሚል ፍራቻ ነበራቸው። አንድ ከኔጌሌ ቦረና የመጣ ጓደኛ ነበረኝ፤ እርሱም ትምህርቱን ያቋረጠው ከ10ኛ ክፍል ነው ። ኬኒያ አካባቢ ስለነበር እንግሊዘኛ ቋንቋ አቀላጥፎ ይናገራል። እሱም እኔም ያቋረጥነው ከሦስተኛ ክፍል ነው ብለን ተናገርን።” ይላሉ።
እርሳቸው እና ጓደኛቸው የሬዲዮ ኦፕሬተር እንዲሆኑ ሥልጠና ተሰጣቸው። ሰኔ 18 ቀን 1969 አዲስ አበባ ከተማ ሰልፍ ካሳዩ በኋላ፤ በማግስቱ በአውሮፕላን ተጭነው ድሬዳዋ ከተማ ሄዱ። ወደ ከተማው ሲደርሱ፤ በከተማው ዙሪያ የተኩስ ድምፅ ስለተሰማ ወደ ሐረር ሄዱ። ከሐረር በመኪና ወደ ጂግጂጋ ገብተው ዙሪያ ጥበቃ አደረጉ።
እነርሱ ሐምሌ ወር ገብተው፤ ነሐሴ 26 ሶማሊያ ጅግጅጋን ለመያዝ ከባድ ውጊያ እንደከፈተች የሚናገሩት አትሌት ፀጋዬ፤ ወቅቱ የነበረውን አሰቃቂ ሁኔታ በአዕምሯቸው ወደ ኋላ ሄደው ሲያስታውሱ፤” ከተማ ወስጥ የነበሩ ነዋሪዎች ከከተማው ሲያፈገፍጉ አንድ ሴት አንድ ልጅ በእጇ ይዛለች፤ አንዱን በጀርባዋ አንዱንም ለመሸከም ትሞክራለች፤ አሮጊቶችም ይሮጣሉ። በዛ መሐል ከባድ መሣሪያ እንደጉድ ይወርዳል።›› በማለት ይገልጻሉ።
“እኛ ውስን እግረኛ ጦር ነበረን፤ በብዛት የነበረን አየር ኃይሉ ስለሆነ፤ ሽፋን የሚያደርግልን እነሱ ናቸው። በጦርነቱ ሬዲዮ ይዤ መልዕክት እየተቀበልኩ ለሠራዊቱ እያስተላለፍኩ ሠራዊቱ ጥሎኝ አፈገፈገ። ከዛን ብቻዬን ተቆርጬ ቀረሁ። ወደ ካራማራ አፈገፈግን፤ መልሶ ማቋቋም ከተደረገ በኋላ አንድ የደርግ ባለሥልጣን መጥተው አበረታቱን። አጋዥ ኃይል ደረሰልን ከሰዓት በኋላ መልሶ ማጥቃት ጀምረን ጅግጅጋን አስለቅቀን ወደ ነበሩበት መለስናቸው።” ይላሉ
ባስለቀቁበት ቦታ ለአንድ ሳምንት በመከላከል ቆዩ። ነገር ግን ከባድ መሣሪያ ስለጠነከረባቸው በመንግሥት ትዕዛዝ ቦታውን ለቀው እንዲወጡ ተደረገ። በሚወጡበት ወቅት መንገድ ላይ ጥይት ጭኖ የሚጓዝ ሦስት የጠላት መኪና አግኝተው በውስጡ ያሉ ወታደሮችን ገድለው መኪናዎቹ ማቃጠላቸውን እንደገጠመኝ ያነሳሉ።
በእዛው መንገድ ላይ እያሉ ሌላ ክስተት እንዳጋጠማቸው የሚያነሱት፤ “ከተማውን በጀርባችን ጥለን ወደ ካራማራ ጥግ ስንሄድ ሁለት የጠላት ታንክ ቀድሞን ነበር። ከዛን ሰማያዊ ባንዲራ አወጣ። ሰማያዊ ባንዲራ ማውጣት እጅ ስጡ ማለት ነው። ቀድመን አንዱን ታንክ ስንመታ፤ ለካስ ከፊት ለፊታችን እግረኛ ጦር ነበር። እነሱን ስንሸሽ ደግሞ ከፊት ለፊታችን ስድስት የጠላት ታንክ እየመጣ ነው። እንደ ዕድል አየር ኃይል መጣልን፤ ሁለቱ ታንኮች ሲቃጠሉ ሌሎች ጥለው ሸሹ። በዚህ ሁኔታ ጠላትን አስለቅቀን ካራማራን በጥሰን ወጣን።” ሲሉ ይናገራሉ።
አትሌት ፀጋዬ እንደሚናገሩት፤ ቆሬ ግንባር ላይ መሽገው በነበረበት ወቅት በቀለብ እጦት ብዙ ተቸግረዋል። በወቅቱ በወንዝ ዙሪያ ስለነበሩ፤ የውሃ ችግር ባያጋጥማቸውም፤ የሐረር ዙሪያ ተከቦ ስለነበር ቀለብ በአውሮፕላን እየመጣላቸው በፓራሹት ይወርድላቸው ነበር። በዚህ ሁኔታ ደግሞ ሁሉንም ሠራዊት በበቂ ሁኔታ ማድረስ አስቸጋሪ ነበር። አውሮፕላኑ ሲወረውር ነፋስ ወስዶ ለጠላት ሰጥቶባቸውም ያውቃል።
እዛው ቆሬ ግንባር እየተዋጉ አለቃቸው በማስተባበር ላይ ሳሉ ደረታቸው ላይ ተመትተው ወደቁ። አትሌት ፀጋዬ ሕይወታቸውን ለማዳን በአዕምሯቸው የመጣላቸውን አማራጭ ተጠቅመው፤ ቀና አደረጓቸውና የተመቱበትን ቦታ በጨርቅ ቢያስሩላቸውም፤ ነፍሳቸውን ማዳን አልተቻለም።
ሬዲዮኑን አንስተው ለአዛዦቻቸው በምስጢራዊ ቃል የአስተባባሪው ሕይወት ማለፉን ገልጸው፤ እርሳቸው ትዕዛዝ እንዲያስተላልፉ እና እንዲያስተባብሩ ተደረገ። መልሶ ማጥቃት ተጀምሮ የሱማሊያን ጦር እንዲያፈገፍግ ካደረጉ በኋላ፤ ግንባር ላይ ባሳዩት ቁርጠኝነት በጦሩ ውስጥ ተወዳጅነትን ማትረፍ ቻሉ።
ድል አድርገው ኦጋዴንን ካስለቀቁ በኋላ አትሌት ፀጋዬ የነበሩበት ሦስተኛ ክፍለ ጦር የቀድሞ መሪ የመንግሥቱ ኃይለማሪያም ክፍል ሆነ። የጦር ሜዳ ታሪካቸው በምሥራቅ ብቻ አላበቃም። ከምሥራቅ ግንባር ከተመለሱ በኋላ በሰሜን ግንባር ተሰልፈው ዘምተዋል።
“የዛኔ 95 በመቶ የሚሆነው የኤርትራ ክፍል በሻቢያ ቁጥጥር ስር ነበር። በሰሜኑ ጦርነት የዘመትኩት በአዲግራት በኩል ሲሆን፤ እኛ በአዲግራት በኩል እያጠቃን እያስለቀቅን አሥመራ ገባን። በምፅዋ በኩል ያለው ጦርም እያጠቃ ወደ አሥመራ ከአሥመራ ወደ ከረን መጣ። ከአምስት ወር ቆይታ በኋላ ናቅፋ ገባን። ከዛ በኋላ አልጌና በሚባልበት አካባቢ ለሰባት ዓመት ኖሬያለሁ።” ይላሉ።
ልጅ እያሉ በትምህርት ቤቶች የእሩጫ ውድድር ላይ ይሳተፉ እንደነበር በመጥቀስ ወደ አትሌቲክሱ እንዴት ሊቀላቀሉ እንደቻሉ ያነሳሉ። አልጌና በነበሩበት ወቅት ቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆነው የስፖርት ወሬዎችን ያዳምጣሉ። እነ ምሩፅ ይፍጠር ተወዳድረው ያሸነፉበትን ዜና ሲሰሙ እንደልጅነታቸው በስፖርት ሊቀጥሉ ባለመቻላቸው ውስጣቸው በቁጭት ይንገበገባል።
በ1973 ዓ.ም የጦር ኃይሎች ውድድር ይካሄዳል ተብሎ የተለያዩ የስፖርት ሜዳዎች ተዘጋጁና ሩጫ የሚችል በሩጫ፣ እግር ኳስ የሚችል በእግር ኳስ፣ ሌሎች የስፖርት አይነቶችን የሚችሉም እንደዛው ልምምድ እንዲያደርግ ተደረገ። እርሳቸውም በሩጫ ለመሳተፍ ሲጠይቁ መቶ መሪ በመሆናቸው የሳቸውን ኃላፊነት የሚወስድ ስለሌለ አይቻልም ተብለው ነበር።
ነገር ግን ሻምበል ድጋፌ የሚባሉ አዛዣቸው በቀለም ትምህርታቸውም ዩኒቨርስቲ ቀመስም ስለነበሩ ተስፋ እንዳይቆርጡ ያበረቷቷቸው ነበር። አትሌት ፀጋዬ የነበሩበት አካባቢ በጣም ሞቃት ስለነበር ልምምድ ሲያደርጉ የሚመለከቷቸው ሰዎች “በዚህ ሙቀት ስትሮጥ ቀልጠህ እንዳትቀር” የሚሏቸው ቢሆንም፤ ወደፊት መሮጥን ብቸኛ አማራጫቸው አድርገው ወሰዱ።
እዛው ጦር ውስጥ በሻለቃ ደረጃ ውድድር ሲደረግ በ5000 እና 10 ሺህ ሜትር አንደኛ ወጥተው አሸነፉ። ቀጥሎም በብርጌድ ደረጃ በተደረገ የሩጫ ውድድር በተመሳሳይ ደረጃ አሸነፉ። በ1974 ዓ.ም በ10ሺህ እና ግማሽ ማራቶን ተወዳድረው በአንደኝነት አጠናቀቁ።
“ከዛ በኋላ አሥመራ ከተማ ለውድድር ለመሄድ እየተዘጋጀን እያለ ቀይ ኮከብ ዘመቻ የሚባል ሲመጣ ወደ ውጊያ ገባሁ። በጦርነቱ በቦንብ ፍንጣሪ እግሬን ተመትቼ ስለቆሰልኩ ሆስፒታል ተኛሁ። ስድስት ወር ታክሜ ድኜ ወጣሁ። ከዛ በፊትም አሥመራ ዙሪያ ተመትቼ የወጣሁት ለአራት ወር ሆስፒታል ተኝቼ ነው።” ሲሉ ይናገራሉ።
የደረሰባቸው አደጋ ከአትሌቲክስ መንደር ሊያጠፋቸው አቅም ያገኘ አይመስልም። ከደረሰባቸው አደጋ ለስድስት ወራት ከልምምድም ሆነ ከውድድር ቢገለሉም፤ መልሰው የስፖርትን በር ከማንኳኳት አልተገደቡም። ከዳኑ በኋላ ተመልሰው ልምምድ ማድረግ ጀመሩ።
በ1976 ዓ.ም በአሥመራ ከተማ የተለያዩ ውድድሮች ሲደረጉ ያሉበትን ዕዝ ወክለው ለመወዳደር ዕድሉን አገኙ። ነገር ያየር ሁኔታው እርሳቸው ከለመዱት ሞቃት አየር ተቃራኒ ስለነበር ድል ሳይቀናቸው ተመለሱ።
“በ1977 ዓ.ም እኔ እና አንድ ልጅ አሥመራ ተጠርተን መጣን። የጠሩን ጄኔራል ‹ጎበዞች እንደሆናችሁ አይቻለሁ እና አሁን የምታደርጉት ውድድር ሦስት ኪሎ ሜትር ትጥቅ ይዞ መሮጥ፣ ስድስት ሜትር መሰናክል መዝለል ነው።› ተባልን። መሰናክሉን ስንዘል ሦስት ሜትር ጉድጓድ አለ፤ ካመለጥን እዛ ጉድጓድ ውስጥ ነው የምንገባው። ይህን ውድድር በጥሩ ሁኔታ ተለማመድኩና አንደኛ ወጣሁ።” ሲሉ ይናገራሉ።
በእዛ ዓመት አዲስ አበባ ላይ ይደረጋል የተባለው ውድድር ለቀጣይ ዓመት ተዛወረ። እርሳቸውም ከነበሩበት የአልጌና ክፍለ ጦር ወደ ምፅዋ ተዘዋወሩ። ወደ ምፅዋ ከተዘዋወሩ በኋላ ወደ ግንባር እንዳይሄዱ ተደረገና ሚሊተሪ ፖሊስ አዛዥ ሆነው መሥራት ጀመሩ። በዚህም የነበራቸው ኃላፊነት ምፅዋ ወደብ አካባቢ ሰርጎ ገብ ጀልባዎችን በመቆጣጠር እና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በተሠራችው ነጯ ቤተመንግሥት ጠዋት ጠዋት በክቡር ዘበኛ ታጅበው ባንዲራ ማሰቀል ነው።
ምፅዋ ላይ እንደዚህ እየሠሩ እያለ በ1978 ዓ.ም ባሬንቱን ጠላት አጠቃ። ተዋግተው ካስለቀቁ በኋላ ተመልሰው ወደ ነበሩበት አልጌና ገቡ። በዛው ዓመት ጥር ላይ በአስቸኳይ ወደ አሥመራ እንዲላኩ ቴሌግራም ተላከ። ሲመጡ በደንብ ተለማመድ ጦር ኃይሎች አዲስ አበባ ውድድር ይካሄዳል ተባሉና ልምምድ ጀመሩ።
ውድድሩን ለመሳተፍ ሚያዚያ ወር ላይ ወደ አዲስ አበባ መጥተው፤ በውድድር ውጤታማ ስለሆኑ አዲስ አበባ ቀርተው ለአንድ ዓመት ልምምድ ካደረጉ በኋላ በኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ለብሔራዊ ቡድን ተመረጡ።
አትሌቱ በማራቶን መወዳደር ጀምረው ስለነበር የመላው አፍሪካ ጨዋታ በኬኒያ ስለሚደረግ፣ በዛ ለመወዳደር የሰዓት ሙከራ ውድድር ማድረግ እንደሚፈልጉ ለአሠልጣኛቸው ተናግረው ተፈቀደላቸው። በውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተወዳደሩ አትሌቶች ከነመሐመድ ከድርና ሌሎች አትሌቶች ጋር ተወዳድረው በአንደኛነት አጠናቀቁ።
በውድድሩ ባልተጠበቀ ሁኔታ በማሸነፋቸው በጣም ተወራላቸው። የታቀደው የኬኒያው ውድድር ቀረና የአበበ ቢቂላ ወድድር በወቅቱ ዓለም አቀፍ ስለነበር በዛ ውድድር ተሳትፈው በሦስተኛነት አሸነፉ።
በውድድሩ አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ ከብሔራዊ ቡድን ደመወዝ ተቆራጭ እየተደረገላቸው መሮጥ ጀመሩ። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው የመወዳደር ዕድል አገኙ። በማራቶን ውድድር አልጀርስ ከተማ ላይ ተሳትፈው አራተኛ ሆነው አጠናቀቁ።
በወቅቱ በአልጀርስ ከተማ የነበረው ሙቀት ከፍተኛ እንደነበር የሚያስታውሱት አትሌቱ፤ ሙቀቱ በጣም ከፍተኛ ስለነበር የሮጡት አመሻሽ ላይ ነበር። ውድድሩ አመሻሽ ላይ ቢደረግም ሁሉም አትሌት በሚባል ደረጃ ሙቀቱን ስላልቻሉ ከእርሳቸው ጋር አራት አትሌቶች ብቻ ውድድሩን አጠናቀቁ። ወድድሩን ሲመሩ ቆይተው በመጨረሻው ደቂቃ በመዘናጋታቸው ከኋላቸው መጥተው ሦስቱም ቀድመዋቸው ገቡ።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1989 በጃፓን ቶኪዮ ከተማ በተደረገ የማራቶን ውድድር ተሳትፈው የዲፕሎማ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። ከዛ ከተመለሱ በኋላ በአበበ ቢቂላ ውድድር ተሳትፈው ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀቁ። ወደ ናይጄሪያ ሄደው በማራቶን እየተወዳደሩ አንድ ክስተት እንደገጠማቸውም አጫወቱን።
“አንድ የናይጄሪያ አትሌት በጣም እየተፎካከረ ስለነበር እርሱን ለማዳከም ወጣ አልኩኝ። በዛ መሐል በሞተር ሳይክል የሚመራን የተሳሳተ አቅጣጫ አሳይቶኝ በተሳሳተው መንገድ እሩጫዬን ተያያዝኩት። እኛን የሚከታተሉ እዛ የሚኖሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ስለነበሩ እነሱ መኪና ይዘው ይከታተሉናል ነበርና “ፀጋዬ፣ ፀጋዬ!” ብለው ሲጠሩኝ፤ ዞር ብዬ ስመለከታቸው መንገዱ በዛ እንዳልሆነና ወደ ግራ እንድዞር ነገሩኝ።” በማለት ይናገራሉ።
ወደ ግራ ሲመለሱ አትሌቶቹ እየሮጡ ተመለከቱ፤ ያላቸውን ኃይል አሟጠው በመሮጥ እየመራ ወዳለው አትሌት ደረሱ። እርሳቸውን ተከትለው ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደረሱ። እርሳቸው አንደኛ ሲወጡ ሁለቱ የኢትዮጵያ አትሌቶች፤ አትሌት ከበደ ባልቻ እና የኃይሌ ገብረሥላሴ ወንድም ተኬ ገብረሥላሴ ሁለተኛና ሦስተኛ ወጥተው ኢትዮጵያ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዛ አሸነፈች።
አትሌቱ መንገድ ስተው ከሄዱ በኋላ ተመልሰው በማሸነፋቸው፤ አበረታች መድኃኒት ወስደዋል በሚል ጥርጣሬ ውድድሩን እንዳሸነፉ፤ ምርመራ ተደርጎላቸው አለመውሰዳቸው ተረጋግጦ ሽልማታቸውን ለመውሰድ ችለዋል። በአጠቃላይ በውድድሩ ኢትዮጵያ ሁለት ወርቅ ስታገኝ አንዱን ያስገኙት እሳቸው ናቸው።
አትሌቱ ኢትዮጵያ ከመወከል አልፈው አፍሪካን ወክለው በአውሮፓ በሚደረግ ውድድር ለመሳተፍ ታጭተው ነበር። ለዛም ውድድር ልምምድ እያደረጉ እያለ፤ ኢትዮጵያ ከእሥራኤል ጋር ዲፕሎማሲያው ግንኙነት በምትመሠርትበት ቀን ኢትዮጵያን ወክለው እንዲሮጡ ከወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጥቆማ ተጠሩ።
አፍሪካን ወክሎ መሮጡ ትልቅ ዝና ያለው ቢሆንም፣ ሀገራቸውን ለማስቀደም በማሰብ በእሥራኤሉ ውድድር ለመሳተፍ ወሰኑ። ወድድሩ በተመሳሳይ ወቅት ስለነበር አፍሪካን ወክሎ መሮጡ ቀርቶ፣ ወደ እሥራኤል አቀኑ። በዛም ወድድር ድል ቀንቷቸው ሦስተኛ ወጥተው አሸነፉ።
የኢጣሊያ መንግሥት አበበ ቢቂላ ያሸነፈበትን ቀን በየዓመቱ በሩጫ ያከበር ስለነበር፤ በሮም አበበ ቢቂላ ያሸነፈበት 30ኛ ዓመት ሲከበር እርሳቸውም በሩጫ ውድድሩ ለመሳተፍ ከሌሎች አትሌቶች እና የክብር እንግዶች ጋር ወደ ሮም አቀኑ። በውድድሩ እርሳቸው ስድስተኛ ቢወጡም፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ይዘው አሸነፉ።
ከአንድ ዓመት በኋላ እሥራኤል ሀገር ለውድድር ተጠርተው በመሄድ በአንደኛነት አሸነፉ። ከውድድሩ ሲመለሱ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ተደረገ። የሚደረግላቸው የደመወዝ ድጎማም ተቋረጠ፤ ይህን ተከትሎ አጠቃላይ የነበረው የአትሌቲክስ ስሜታቸው ተቀዛቀዘ።
የደመወዝ ተቆራጩ ቢቋረጥም አትሌቱ ያለውን ነገር አቻችለው ልምምዳቸውን ቀጥለው ስለነበር ለውድድር ወደ አሜሪካ ሀገር ሄዱ። የሚሮጡበት ቦታ ዳገት ስለነበር ውድድሩን 11ኛ ሆነው አጠናቀቁ።
ከወድድሩ ከተመለሱ በኋላ የደመወዝ ክፍያው ተመልሶ ባለመጀመሩ እራሳቸውን ማስተዳደር ከበዳቸው። ምንም እንኳን ከነበሩበት ዝና ተመልሰው ወደ ቀያቸው ገብተው እርሻ ማረሱ ሲያስቡት ቢከብዳቸውም፤ አማራጭ ስላልነበራቸው ተመልሰው ማረስ ጀመሩ። ለስድስት ወራት እያረሱ ከቆዩ በኋላ፤ ሌሎች አትሌቶች ልምምድ እያደረጉ ነው ተብሎ ተነገራቸው።
ያለደመወዝ እንዴት እሠራለሁ የሚል ጥያቄ ቢፈጠርባቸውም፤ ለአትሌቲክስ ከነበራቸው ፍቅር የተነሳ ጨክነው መቅረት አልቻሉ። ገጠር የነበሯቸውን ከብቶች ሸጠው ተመልሰው መጥተው ዘመድ ቤት በማረፍ፣ በእጃቸው ያለችውን ገንዘብ ቆጥበው እየተጠቀሙ ወደ ልምምድ ገቡ።
“ከዛ ስመለስ ወደ አየር ኃይል ተዛውረሃል፤ ደመወዝ ይከፈልኃል ተባልኩኝ። ተስማምቼ ገባሁ። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ለአንድ ዓመት ሳይከፈለኝ የቆየ ደመወዜ እንዲከፈለኝ ከሌሎች አትሌቶች ጋር ጥያቄ አቀረብን። ጥያቄ ያቀረብንላቸው ባለሥልጣን ለምን እንዳልተከፈለን የሚመለከታቸው አካላት ሲጠይቁ ኢሠፓ ናቸው ብለው ፈረጁን።” ሲሉ ያስረዳሉ
በዚህ ምክንያት ከዛ ቀደም ለአንድ ዓመት የቀረውን ክፍያ ሳይሰጣቸው ቀረ፤ ምንም ማድረግ ስላልቻሉ የቀድሞ ክፍያቸው ቀረ። ተመልሰው ከገቡ በኋላ አየር ኃይልን ወክለው በአበበ ቢቂላ ውድድር መሳተፍ ቻሉ። ውድድሩ ላይ በአንደኝነት ከማሸነፋቸውም በተጨማሪም ውድድሩን በተሻለ ሰዓት አጠናቀቁ። ቀጥለው ወደ ዩጎዝላቪያ ሄደው ተወዳድረው ከመጡ በኋላ፤ በአትላንታ ኦሎምፒክ ለመሳተፍ ልምምድ ላይ እያሉ እግራቸው ላይ ቡጉንጅ ወጣ።
በዚህ ጊዜ ከአትሌቲክስ ተቆራርጠው እንዲቀሩ የሚያደርጋቸው ችግር አጋጠማቸው። እግራቸው ላይ የወጣውን ቡጉንጅ ለመታከም ወደ ፌደሬሽኑ ሐኪም ቤት ሄዱ። መዳንን ፈልገው ቢሄዱም ያልጠበቁት እና እቤት የሚያስቀራቸውን አደጋ አጋጠማቸው። ሐኪሙ መርፌ ሲወጋቸው ነርቫቸውን ስለነካ እራሳቸውን ያወቁት ዘውዲቱ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ነው።
የተለያዩ ሕክምናዎችን ቢወስዱም ከሕመማቸው መዳን ከባድ ሆነ። ያጋጠማቸው ችግር የባሰ ጭንቀት ስላስከተለባቸው የመዳን ተሰፋቸውን አዳጋች አደረገው። ቦርድ እንዲወጡ ከሐኪም ቤት ማስረጃ በማጻፍ ሄደው አመለከቱ። መውጣት እንደማይቻል እና ሐረር ሄደው በውትድርና እንዲሠሩ ነገሯቸው፤ በሕመም ምክንያት አልችልም በማለታቸው፤ ደመወዛቸው እንዲቋረጥ ተደረገ።
ለ21 ዓመታት በውትድርና ያገለገሉ ቢሆንም፤ የጡረታ መብታቸውም ሳይከበር ቀረ። በተለያዩ ስብሰባዎች ለሀገር መታገላቸውን እና የሀገርን ባንዲራ በዓለም ከፍ ማድረጋቸውን አንስተው ‹‹አሁን የተጣልኩበት መንገድ ተገቢ አይደለም።›› ብለው ስሞታ ቢያሰሙም ሰሚ ማግኘት አልቻሉም።
ከውትድርና እና ከአትሌቲክስ ሕይወት በዛ መንገድ ከወጡ በኋላ በሌሎች ሥራዎች ለመቀጠር ቢሞክሩም የደርግ ወታደር ተብለው መገለል እንደደረሰባቸው የሚያነሱት አትሌት ፀጋዬ፤ “አንድ ጊዜ ግብርና ሚኒስቴር በዘበኝነት ተቀጥሬ ለመሥራት ተወዳድሬ ሁሉን ነገር ካጠናቀቁ በኋላ፤ የደርግ ወታደር እንደነበርኩ ሲያውቁ ሌላ ቀን እንጠራሃለን ብለው መለሱኝ፤ ተመልሰውም ሳይጠሩኝ ቀሩ።” ይላሉ።
“ከዛ በኋላ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ መኖሪያ ቤት ሰጥቶኝ ሲኒማ ቤቱ እንድሠራ ወሰደኝ። በአትሌቲክስ የሀገር ባንዲራ በዓለም ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረጌን ተናግሮ ሠራተኞቹ እንዲያከብሩኝ ነገራቸውና መሥራት ጀመርኩ። በዚህም አትሌት ኃይሌ ባለውለታዬ ነው።” ሲሉ ይናገራሉ
“እዛ ለሦስት ዓመት ከሠራሁ በኋላ እዛ ከሚሠሩት ሠራተኞች አንዳንዶች እያጭበረበሩ እንደሆነ በማጋለጤ፤ የኔ መኖር ለስርቆት አመቺ ስላልሆነላቸው ሌላ ቦታ ተዛውሬ እንድሠራ ነገሩኝ። ምንም ባልሠራሁት ጥፋት ሊያዛውሩኝ ስለፈለጉ ተናድጄ ሥራውን ለቅቄ ወጣሁ። ኃይሌ እንድመለስ ሰው ልኮ ቢለምነኝም መመለስ ስላልፈለኩ ቀረሁ። ሰዎቹም አንዳንዶቹ ታሰሩ፤ ሌሎቹ ከሥራ እንዲለቁ ተደረገ። “ይላሉ።
አትሌት ፀጋዬ፤ የሁለት ልጆች አባት ናቸው። እርሳቸው ወደ ጦርነት ሲዘምቱ የመጀመሪያ ሚስታቸው ነፍሰጡር ነበረች። ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው እስከሚያውቁ ድረስ፤ የወንድ ልጅ አባት መሆናቸውን አያውቁም ነበር። ከመጀመሪያ ትዳራቸው ልጅ ቢያፈሩም ትዳራቸው ተመልሶ ሊቆም አልቻለም። ከጊዜ በኋላ ሌላ ሚስት አግብተው አንድ ሴት ልጅ ወልደዋል።
አሁን ላይ አትሌት ፀጋዬ እንደ ዕድል ከቀናቸው ሰዎችን ወክለው ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው ይሠራሉ። ከዛ በተረፈ የመጀመሪያ ልጃቸው፣ አሜሪካ የምትኖር የአክስታቸው ልጅ እና አንዳንድ ጓደኞቻቸው እየረዷቸው በአዲስ አበባ ከተማ ይኖራሉ።
ለሀገራችን እና ለሕዝባችን ሠላም ይስጠን የሚሉት አትሌቱ፣ ሻለቃ ራህማቶ ሸባህ፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ጌጤ ዋሚ፣ ሻምበል መገርሳ በተለያዩ ጊዜያት ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነዋል። በተጨማሪም ለቀድሞ አትሌቶች በሙሉ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም