የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አቋርጠው ነው ገና በ17 ዓመታቸው ወደ ውትድርና የተቀላቀሉት። ውትድርናን ተቀላቅለው ሥልጠናቸውን ሳያጠናቅቁ የሶማሊያ ጦር ኢትዮጵያን በመውረሩ የታጠቅ ጦርን ለማሰልጠን ከሰልጣኝነት ወደ አሰልጣኝነት ተሸጋገሩ ።
ከጦር መሪዎች ጋር በመሆን የሀገርን ጥሪ ተቀብለው የገቡትን አዳዲስ የጦር ምልምሎች በመቶ መሪነት ካሰለጠኑ በኋላ፤ የጠላትን ኃይልን ለማባረር ልጅነት ሳይገድባቸው፣ ጦር ሳያስፈራቸው በተለያዩ ግንባሮች በመዝመት ጠላትን ለማባረር በሚደረገው ውጊያ ለሀገር የራሳቸውን መስዋዕትነት ከፍለዋል።
የዛሬው የሕይወት ገጽ እንግዳችን ውትድርና ከአትሌቲክስ ጋር በማስተሳሰር ለሀገራቸው በጦርም በሩጫም የታገሉት ሻምበል መገርሳ ሁንዴ ናቸው። በምሥራቅ እና በሰሜን ግንባር በተደረገው ውጊያ ተሳትፈው ሀገር ቀና እንድትል የታገሉ ወታደር፤ ከውትድርናው ውጭ የሰላም ማሳያ በሆነው ስፖርትም በዓለም መድረክ ሀገራቸውን ያስጠሩ ብርቱ ሰው ናቸው። ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ አሰልጣኝ በመሆን ከኢትዮጵያ አልፈው፤ እስከ እስራኤል የደረሱ እና ብርቅዬ አትሌቶችን ማፍራት የቻሉ ድንቅ ወታደር፣ አትሌት እና አሰልጣኝ ናቸው።
ከአዲስ አበባ ከተማ በስተምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው ወልመራ ወረዳ መናገሻ ኮሎቦ በምትባል ቀበሌ ነው ተወልደው ያደጉት። አትሌት መገርሳ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ እዛው መናገሻ አካባቢ ወደሚገኘው ኢትዮ ዩጎዝላቪያ ትምህርት ቤት ገብተው እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ከትምህርት ገበታ ተቋደሱ።
በወቅቱ የሚኒስትሪ ፈተና የሚሰጠው ስድስተኛ ክፍል ላይ ስለነበር፤ ፈተናውን ወስደው የማለፊያ ውጤት ለማምጣት በመቻላቸው ሆለታ ገነት መለስተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው የሰባተኛ ክፍል ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ። የሰባተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀው ስምንተኛ ክፍል እየተማሩ ነበር ወደ ውትድርና ለመቀላቀል የበቁት።
ወደ ውትድርና ለመቀላቀል የቻሉበትን ምክንት ሲያስረዱ፤ ‹‹በወቅቱ ኢአሕፓ ምክንያት ረብሻ ነበር፣ በዚህ ረብሻ በርካታ ጥፋቶች ነበሩ። መኪና መስበር እና ሌሎች ስለነበሩ በዛ ረብሻ ለመሳተፍ ስላልፈለኩ ነበር በለጋ ዕድሜዩ በ1969 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ወደ ውትድርና የተቀላቀልኩት›› በማለት ወደ ውትድርና ሕይወት የገቡበትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ።
ጠባሴ አካባቢ በሚገኘው ልዩ ኃይል ትምህርት ቤት ገብተው እየሰለጠኑ እያለ፤ በምሥራቅ ጦር ግንባር የሶማሊያ ጦር ወረራ አደረገ። እሳቸውም ባላቸው የትምህርት ደረጃ እና ቀድመው ወደ ውትድርና የተቀላቀሉ በመሆናቸው ለአሰልጣኝነት ተመለመሉ። ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም መጥተው በታጠቅ ጦር ሰፈር የሀገርን ጥሪ ተቀብለው የተቀላቀሉ አዲስ የጦር ምልምሎች ለማሰልጠን ታጩ። በዚህም ወደ ታጠቅ ጦር ሰፈር በመሄድ ከአዛዦቻቸው ጋር በመቶ መሪነት አሰልጥነዋል።
ሥልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ በ1969 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ ወደ ግንባር መዝመታቸውን የሚያነሱት አትሌት መገርሳ፤” የደረሰን ግንባር ድሬዳዋ ግንባር ሲሆን፣ የዛን ጊዜ የሶማሊያ ጦር ድሬዳዋ ላይ ዘምቶ ነበር። እኛ ከመዝመታችን በፊት ወደ ጦር ግንባሩ ቀድመው የሄዱ የጦር ሠራዊት አባላትም ነበሩ።” ሲሉ ይናገራል።
እሳቸው የነበሩበት ክፍለ ጦር 75ኛ ሚሊሻ ብርጌድ ክፍለ ጦር ሲሆን፣ ክፍለ ጦሩ እንዲዘምት የደረሰው የጦር ግንባር በጀሌሳ ግንባር ስለነበር፤ እሳቸውም በክፍለ ጦራቸው ምድብ መሠረት የዘመቱት በጀሌሳ ግንባር ነው። በጀሌሳ ግንባር የሶማሊያ ጦር ስለነበር ወደ ሀሜርካ ግንባር ተዛውረው ምሽግ ሰርተው ለተወሰነ ጊዚያት ተቀመጡ።
በሀሜርካ ግንባር ዳናኬል ወረዳ ላይ እንደነበሩ 1970 ዓ.ም ኅዳር 12 ከሶማሊያ ጦር ጋር ከፍተኛ ውጊያ ተደረገ። ውጊያው በሶማሊያ በኩል ዝግጅት የተደረገበት እና በኢትዮጵያ ሠራዊት በኩል ያልታቀደ በመሆኑ ትልቅ ጉዳት መድረሱን ይናገራሉ።
“ሀሜርካ ግንባር ላይ ሽንፈት ደርሶብን ወደ መከላከያ ወረዳችን ተመለስን። ከዛን በኋላ ነው በሁለተኛው ዙር ወደ ማጥቃት ደረጃ ተሻግረን በጀሌሳ ግንባር፣ ግሪኮቸር፣ ፉኛቢራ፣ ዲራሞ እና ሀናኖሚጤ ቦታዎች ላይ አንድ ወር የፈጀ ውጊያ አድርገን አስለቀቅን። ” ሲሉ ይናገራሉ።
ካራ ማራን ካስለቀቁ የሠራዊቱ ግንባር ውስጥ ከነበሩ ወታደሮች አንዱ እሳቸው መሆናቸውን በመግለጽ፤ “የካቲት 26 ካራማራን አስለቅቀን ጅግጅጋን ተቆጣጠርን። የምሥራቁ ጦርነት ቀላል የሚመስል የነበረ ቢሆንም፤ የሶማሊያ ጦር በከፍተኛ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ስለነበርና የእኛ ሠራዊት በቁጥር ትንሽ ስለነበር መጀመሪያ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነበር። ሚሊሻ ሠራዊቱ ነው ደርሶ ሊያድነን የቻለው።” ይላሉ።
ጅግጅጋን ከተቆጣጠሩ በኋላ፤ እሳቸው ያሉበት ክፍለ ጦር “ሄርት ሼክ” በምትባል ቦታ ላይ ማረፊያውን አድርጎ እዛው ጅግጅጋ ላይ ቆየ። የአትሌቱ የስፖርት ጉዞ የተጀመረው ከዚህ በኋላ ነበር።
ነገር ግን አትሌቱ የስፖርት ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነት እድሜያቸው ነበር። ምንም እንኳን በዓለም መድረክ ሀገራቸውን ወክለው የመወዳደር ሃሳብ በአዕምሯቸው ታስቦ ባያውቅም፣ ትምህርት ቤት እያሉ በእግር ኳስ እና በሌሎች ስፖርቶች ትምህርት ቤታቸውን ወክለው ይጫወቱ እንደነበር ያነሳሉ።
“የስፖርት ፍላጎቴ የመጣው ከትምህርት ቤት ጀምሮ ነው። ትምህርት ቤት እያለሁ እግር ኳስ ጨምሮ ሌሎች የስፖርት ዓይነቶችን በደንብ እጫወት ስለነበር በትምህርት ቤት ደረጃ በሚደረጉ ጨዋታዎች ትምህርት ቤቴን ወክዬ እጫወት ነበር። ይላሉ።”
“እንደውም አንድ ጊዜ ኢትዮ ዩጎዝላቪያ ትምህርት ቤትን ወክለን አለልቱ ላይ ተጫውተን አሸንፈናል። “የሚሉት አትሌት መገርሳ፣ ለስፖርት ካላቸው ፍቅር የተነሳ ትምህርት ቤት ይቀሩ ነበር። ወደ ወታደር ቤት ከገቡ በኋላም ሰላማዊ ወቅቶች ላይ ብዙ ጊዜ ስፖርት ስለሚዘወተር በዛ ዝንባሌ ነበር በዓለም አቀፍ መድረኮች እስከ መወዳደር የደረሱት።
“ሁልጊዜ ሠራዊት ሰላም ሲገኝ ወደ ልማት እና ስፖርት ያዘነብላል። የእኛም ብርጌድ ጅግጅጋ ሲቆይ ወደ ስፖርት ክንውኖች ስለገባ፤ በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስ፣ በመረብ ኳስ፣ በእጅ ኳስ እና በሌሎች የስፖርት ዓይነቶች በፈለግነው የስፖርት ዓይነት ገብተን የምንጫወትበት እድል አገኘን።” ሲሉ ይናገራሉ።
አትሌት መገርሳ በብርጌዱ ውስጥ በእግር ኳስ፣ በመረብ ኳስ የስፖርት ዓይነቶች ገብተው ቢጫወቱም ዝንባሌያቸው ግን ሩጫ ነበር። በዚህም የተነሳ ትኩረታቸውን በአትሌትክስ ላይ አደረጉ። በ1973 ዓ.ም ጦር ኃይሎች በተዘጋጀ ውድድር ምሥራቅ እዝን በመወከል ለመወዳደር ከስፖርት ወዳጆቻቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ መጡ።
“በወቅቱ ልጅም ስለነበርኩ አቅሙም ነበረኝ፤ በዛ ላይ ደግሞ ውትድርና ትልቅ ነገር ነው። ራስን ለማብቃት የሚያስችሉ ብዙ ዲስፕሊኖች የሚያስተምር ቦታ ሲሆን፣ የአዕምሮ ጥንካሬ እና የአካል ጥንካሬ የምናገኝበት መድረክ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ትግሉ ለሀገር ስለሆነ ጥንካሬ ይሰጣል። ይላሉ።”
አትሌቱ የሚወዳደሩባቸው የሩጫ ርቀቶች ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ብዙ መሥራት በሚጠበቅባት የመካከለኛ ርቀት ውድድር ነው። በጦር ኃይሎች በተደረገው ውድድር በአራት መቶ ሜትር አንደኛ እና በስምንት መቶ ሜትር ሶስተኛ ደረጃ ይዘው ማሸነፋቸው አድናቆትን ከማስገኘት ባለፈ፤ ለብሔራዊ ቡድን የመመረጥ እድል ይዞላቸው መጣ።
አትሌቱ በውድድሩ አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ ገና በጦር ኃይሎች የተደረገው ውድድር ሳይጠናቀቅ ነበር ሀገራቸውን ወክለው ለውድድር ወደ አውሮፓ ሀገራት ለመሄድ የታጩት። በዚህም በአራት ሀገራት በእንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ቼኮስሎቫኪያ እና ኖሮዌይ በተደረጉ ውድድሮች በመካከለኛ ርቀት እና በዱላ ቅብብል ውድድሮች በመሳተፍ 52 ቀናት ቆይተው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
የመጀመሪያው ውድድር የተደረገው በእንግሊዝ ሀገር ነው። በእንግሊዝ ወድድሩ ተደርጎ ድል ያልቀናቸው ተወዳዳሪዎች ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ፤ እሳቸው ስላሸነፉ ወደ ቼኮስሎቫኪያ አመሩ። እዛም ድል ተከትሏቸው ነበርና ለማሸነፍ ስለበቁ በዛው ወደ ጣሊያን ተጉዘው፤ በአራት መቶ ሜትር ዱላ ቅብብል አራተኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀቁ። ከዛን በኋላ የመጨረሻ ውድድራቸውን ኖርዌይ ላይ ነበር የተደረገው።
በኖርዌው ውድድር እድል ፊቷን አሳይታ የመለሰችባቸው ይመስላል። ውድድሩን አንደኛ ሆነው ቢያጠናቅቁም እየተወዳደሩ በነበረበት ወቅት ከመስመር ስለወጡ ያመጡት ውጤት ውድቅ ተደረገባቸው። አትሌቱ ቀኝ መስመር ይዘው ሲሮጡ፤ በግራ መስመር ካለው ኩባዊ አትሌት ጋር ተገፋፍተው ነበር ከመስመር የወጡት።
ይህንን ጉዳይ አትሌት መገርሳ ሁንዴ “በወቅቱ ስለ አትሌቲክስ ሕግ በቂ ልምድ እንዳልነበራቸው በማንሳት፤ በቀኝ በኩል የሚሮጥ ተወዳዳሪ በግራ በኩል ያለውን ከገፋ ውጤቱ ይሰረዛል። ነገር ግን በግራ በኩል ያለው ቢገፋም ብዙ ችግር አይኖረውም። ምክንያቱም የራሱ መስመር ስለሆነ። ካዛ በኋላ ስለሕጉ እያወኩ እና እየተስተካከልኩ መጣሁ።” ሲሉ ይናገራሉ።
ከአውሮፓው ውድድር ከተመለሱ በኋላ ወደ ምሥራቅ እዝ ተመልሶ መሄዱ ቀረና፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ተቀላቀሉ። ከዛ በኋላ የሀገር ውስጥ ውድድሮች ሲደረጉ መከላከያን ወክለው፣ በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ውድድሮች ደግሞ ኢትዮጵያን ወክለው መወዳደር ጀመሩ።
አትሌቱ እነዚህን ሁሉ የድል ታሪኮች ሊያሳኩ የቻሉት አስራዎቹን የእድሜ ክልል ሳይሻገሩ ነው። በ19 ዓመታቸው ነበር ብሔራዊ ቡድንን የተቀላቀሉ፤ ከዛ በኋላ ከብሔራዊ ቡድን ሳይቀነሱ በ1 ሺህ 500፣ ስምንት መቶ፣ አራት መቶ እና ሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል በመወዳደር ከብሔራዊ ቡድን ለ18 ዓመታት ሳይቀነሱ ቆይተዋል።
የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ውድድራቸውን አውሮፓ ሀገራት ላይ ተወዳድረው ከመጡ በኋላ፤ በ1989 በእግር ህመም ከአትሌቲክስ ውድድር እስከሚወጡ ድረስ
ኢትዮጵያን ወክለው 24 ሀገራት ላይ ተወዳድረዋል። ሶቬየት ህብረት፣ ሀንጋሪ፣ ቤልጂየም በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ደግሞ፣ ኬንያ፣ ግብጽ፣ አልጄሪያ፣ ናይጄሪያ እና ሌሎች ሀገራት ኢትዮጵያ ወክለው ለመወዳደር ከሄዱባቸው ሀገራት ጥቂቶቹ ናቸው።
ለሁለተኛ ጊዜ በወጣቶች ሻምፒዮና ወደ ጣሊያን ሄደው በስምንት መቶ ሜትር በመወዳደር ሁለተኛ ወጥተው ለማሸነፍ ችለዋል። ከዛ በኋላም ቼኮስሎቫኪያ ላይ በተመሳሳይ ርቀት ተመሳሳይ ውጤት በማምጣት ድል ተቀዳጅተዋል።
አትሌት መገርሳ ኢትዮጵያ ብዙም በማትታወቅበት የአጭር ርቀት ስሟን ለማስጠራት የበቁ አትሌት ናቸው። በወቅቱ ደግሞ አውሮፓዊያን በርቀቱ በጣም ውጤታማ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ውድድሩ ከፍተኛ ትንቅንቅ የሞላበት ነው። በአጭር ርቀት አሁን ላይ የተሻለ ነገር ቢኖርም፤ ሀገርን በማስጠራት ረገድ አሁንም ቢሆን ቀሪ የቤት ሥራዎች መኖራቸውን የሚደረጉ ውድድሮች ይጠቁማሉ ሲሉ ይናገራሉ።
ከሶማሊያ ጋር ስለተደረገው ጦርነት እና ስለጦር ግንባሩ የቅርብ ጓደኛቸው እና አለቃ መጽሐፍ በጻፉበት ወቅት፤ ‹‹ከጦርሜዳ እስከ ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድር›› በሚል የአትሌት መገርሳ ሁንዴ ታሪክና ያሳኩት ድል በመጻፉ ሊካተት ችሏል።
ለ18 ዓመታት ከሮጡ በኋላ በ1989 ዓ.ም እግራቸው ላይ ህመም ስላጋጠማቸው እና የውድድር ጊዜያቸውም እየተገባደደ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ የሚያስመዘግቡት ውጤት እየወረደ ስለመጣም ከውድድር ዓለም ለመውጣት ተገደዱ። ከውድድር መድረክ ከራቁ በኋላ የመንግሥት ለውጥም ስለተደረገ፤ ተመልሰው ወደ ምሥራቅ እዝ ጅግጅጋ እንዲሄዱ ተደረገ።
አትሌቱ ወደ ጅግጅጋ ከተመለሱ በኋላ ሠራዊቱን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወደ ማሰልጠን ነበር የገቡት። የቀድሞ ሠራዊት መበተኑን በማንሳት፤” የደርግ ሠራዊት ስለነበርን ብዙ ጫና ነበር የሚያጋጥመን። እኛም በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ስለነበርን ነው ቀጥታ ወደ ማሰልጠን የገባነው እንጂ ያን ያህል ተወዳጅነት ኖሮን አይደለም።” ሲሉ ጫናውን ያስረዳሉ።
“እኔ ኢህአዴግ ሲገባ የመጨረሻው የጨርቅ ማዕረግ ነበር የነበረኝ፤ ነገር ግን ይህን ማዕረግ አናውቅም በማለት ከሻለቃ ባሻ፣ ምክትል መቶ አለቃ ለመሆን ተዳርሼ እንደገና ወደ 50 አለቃ ማዕረግ መለሱኝ። ጎበዝ ሠራተኛ እንኳን ሆኖ ከ50 አለቃ ወደ ሻለቃ ለመድረስ 10 ዓመት ነው የሚጠይቀው። ጥያቄም ብንጠይቅ መልስ የሚሰጥ አጣን።” ይላሉ።
ጅግጅጋ ላይ ሠራዊቱን እያሰለጠኑ እያለ እሳቸው ያሉበት አየር መቃወሚያ ብርጌድ ወደ ማዕከል ስለተቀየር ወደ አዲስ አበባ ተዛወሩ። ከመጡ በኋላ በ1990 ዓ.ም ከሻዕቢያ ጋር በነበረው ጦርነት ወደ አፋር ዘመቱ። ወደ ጾረና ግንባር ተሰልፈው ካሸነፉ በኋላ ተመልሰው ወደ ማሰልጠኛቸው ገቡ።
ከጦርነቱ መልስ ክፍለ ጦር ውስጥ ስፖርት እንዲቋቋም ስለተደረገ እሳቸው የአትሌቲክስ አሰልጣኝ በመሆን ተመደቡ። በወታደር ቤት በሚደረጉ ፌስቲባሎች የእሳቸው ቡድን ስላሸነፈ፤ በነባርነታቸው እና ባመጡት ውጤት ወደ መከላከያ ስፖርት ክለብ በአሰልጣኝነት ተዘዋወሩ።
ከዛን በኋላ የመከላከያ ብሔራዊ ቡድን መካከለኛ ርቀት አሰልጣኝ ሆነው እየሠሩ፤ በኋላ ዋና አሠልጣኝ ሆነው ተመደቡ። ነገር ግን በሚያዩት አንዳንድ አግባብ ያልሆኑ ሥራዎች እና ማጭበርበሮች ምክንያት ‹‹አይሆንም›› ብለው ስለሚሟገቱ ከአለቆቻቸው ተጽዕኖ ይደርስባቸው ነበር።
“ለሀገር አቋራጭ ውድድር ማጣሪያ ሲደረግ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በርካታ አትሌቶች በተመሳሳይ የአቅም ሁኔታ ላይ ስለተገኙ ማጣሪያ ማድረግ ግዴታ ነበር። በተደረገው ማጣሪያ በሕጉ መሠረት ከአንድ እስከ ስድስት የወጡት ብቻ አትሌቶች ናቸው የሚሰለፉት ነገር ግን፣ ሶስተኛ የወጣችው ከውድድር ትውጣና ስምንተኛ የወጣችው ትሰለፍ የሚል ሃሳብ ስለመጣ አይሆንም ብዬ ተከራከርኩ።” ይላሉ።
“በሕጉ መሠረት ሶስተኛ የወጣችው ነው መሰለፍ የሚገባት፣ የወቅቱ አቋሟም የተሻለ ነበር። በዚህ ምክንያት ከአዛዤ ጋር ተጣላን። ከዛ በኋላም የነበረው ቆይታዬ ጤናማ አልነበረም። የነበረው ጫናም ከፍተኛ ስለነበር የጡረታ ጊዜ ሳይደርስ ነበር የወጣሁት።” ሲሉ ይናገራሉ።
በአንድ ወቅት ኬንያ ላይ ለሚደረግ ውድድር ስምንት አትሌት ስላስመረጡ አትሌቶቹን ይዘው እንዲሄዱ ተወሰነ፤ ነገር ግን አለቃቸው እሳቸውን ተክተው ለመሄድ ጥያቄ አቀረቡ። አትሌት መገርሳ ሁንዴ የሚሄዱት ለብሔራዊ ቡድን አትሌት ስላስመረጡ ነው። ስለዚህ ሌላ ሰው መሄድ አይችልም ተባሉ።
ከውድድሩ በኋላ የመኮንኖች ግምገማ ነበረና ከፍተኛ ግምገማ ተደርጎ ጭቅጭቅ መነሳቱን በማስታወስ፤ “አንዳንድ ጊዜ በደል ደርሶብኝ ለአለቃዬ አቤቱታ ባቀርብም ካዳመጠኝ በኋላ ግምገማ ላይ መልሶ እኔኑ ነው የሚኮረኩመኝ። እናም እንደዚህ ዓይነት ጫናዎች ሲበዙብኝ ለጡረታ ሶስት ዓመት ሲቀረኝ ለመልቀቅ ተገደድኩኝ። ሻምበል ከነበርኩበት ማዕረግ ወርጄ በመቶ አለቃ እንድወጣ ተደረኩ።” ይላሉ።
“አንድ ወታድር፤ የውትድርና ማዕረጉን ሊነጠቅበት የሚችልባቸው ጉዳዮች እንደ ደንብ በዝርዘር ተቀምጠዋል። ስለዚህ ማንም ተነስቶ የአንድ ወታደርን ማዕረግ መውስድ አይችልም። ነገር ግን የእኔን ማዕረግ የወሰዱብኝ በግል ጥላቻ ምክንያት ነው።” ሲሉ ያስረዳሉ።
አትሌቱ በራሳቸው ፈቃድ ሥራቸውን ከመልቀቃቸው አንድ ዓመት በፊት በ2000 ዓ.ም የተሰጣቸውን ሥልጠና ማጠናቀቃቸውን አስመልክቶ፤ በተሰጣቸው የምስክር ወረቀት ላይ ሻምበል የሚል ማዕረግ ነበር ወረቀቱ የተሰጣቸው። ነገር ግን በ2001 ዓ.ም ሥራቸውን ሲለቁ ማዕረጋቸው መቶ አለቃ ተብለው ነበር ከሥራ የተሰናበቱት።
“በውድድሩ ከተፈጠረው ግጭት በኋላ ነው ከሻምበልነት ወርጄ በመቶ አለቃ እንድወጣ የተደረገው። ልጠይቅ ብልም ማንንስ እጠይቃለሁ፤ ሁሉም አንድ ናቸው። እንደዛም ቢሆን ከመጠየቅ አልቦዘንኩም ነበር። በተደጋጋሚ መልስ ሳላገኝ ሥራዬን ተሰናብቼ ወጣሁ።” ሲሉ ይገልጻሉ።
“ለአንድና ለሁለት ወር ጫማችን ከእግራችን ሳይወጣ እግራችን ቆስሎ ለሀገራችን ታሪክ ሰርተናል። ሆኖም መስዋዕትነት እንደመክፈላችን አስታዋሽ አላገኘንም። በውትድርና ሕይወቴን ጭምር ለሀገሬ ለመገበር ቆርጬ ተነስቼ፤ በአትሌቲክስ መስዋዕት ከፍዬ አሁን በእጄ ምንም ነገር የለም።” ሲሉ በተሰበረ ስሜት የደረሰባቸውን የኑሮ ውጣ ውረድ ይናገራሉ።
አትሌቱ ትምህርታቸውን አቋርጠው ለሀገር ፍቅር ወደ ውትድርና ሕይወት በመቀላቀል፤ በውትድርና ትልቁ ነገር የሀገር ደህንነት እንደመሆኑ የአለቆቻቸውን ትእዛዝ ተቀብለው የተራራው ከፍታ ሳይድክማቸው፤ የጉድጓዱ ዝቅታ ሳያስፈራቸው ወጥተዋል፣ ወርደዋል።በመጨረሻ መስዋትነት የከፈሉላት ሀገር የት ወደቅክ አላለቻቸውም።
አትሌቱ በሰላም እጦት ጊዜ በውትድርና፣ በሰላም ወቅት ደግሞ በስፖርት ለሀገራቸው ከመታገል በዘለለ፤ ለሀገራቸው ድንቅ ድንቅ አትሌቶች አፍርተው የሳቸውን ድል እንዲደግም የታገሉ ናቸው። በብሔራዊ ቡድን ሶስት ዓመት፣ በመከላከያ ስድስት ዓመት፣ በ20ኛ መካናይዝድ፣ በኦሮሚያ ማረሚያ ክለብ እና በተለያዩ ክለቦች አትሌቶችን አፍርተዋል።
ወደ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት እንዴት እንደገቡ የሚናገሩት አትሌት መገርሳ፤ “ዱሮ ብሔራዊ ቡድን፤ እንደ ቡድን ተቋቁሞ ከመቶ ሜትር እስከ ማራቶን እና ሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች ይደረግበታል። ስለዚህ አሰልጣኝ የሚመረጠው ባፈራው አትሌት፣ ባመጣው ውጤት እና ብቃቱ ታይቶ ነው። እኔም ልመረጥ የቻልኩት በእነዚህ መስፈርቶች ነበር፤ ነገር ግን ብሔራዊ ቡድኑ ሲፈርስ እኔን ጨምሮ ሌሎች አሰልጣኞች ለቀቅን።” ሲሉ ያስረዳሉ።
አትሌት መገርሳ ሁንዴ በነበራቸው ብቃት በብሔራዊ ቡድን እና መከላከያ ክለብንም በተመሳሳይ ጊዜ የማሰልጠን እድል ነበራቸው። ሌላው ደግሞ የግል ማናጀሮች ሰብስበው የሚያሰለጥኗቸው አትሌቶች ስላሉ በዚህም አንድ ሶስት ቦታዎች ላይ አትሌቶችን አሰልጥነዋል።
አትሌቱ በማሰልጠን ሥራቸው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይገደብ ባሕር ተሻግሮ ወደ እስያ ገብቷል። የእስራኤል ብሔራዊ ቡድን ዝናቸውን ሰምተው ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። እሳቸውም ጥያቄውን ተቀብለው የእስራኤል ብሔራዊ ቡድንን ለአምስት ዓመት አሰልጥነዋል።
የእስራኤል ብሔራዊ ቡድንን ለማሰልጠን እድሉን ሊያገኙ የቻሉት፤ መጀመሪያ ላይ ከእስራኤል መጥተው እሳቸው በሚያሰለጥኑት የሚሰለጥኑ አትሌቶች ስለነበሩ ብቃታቸውን በመመልከታቸው ነበር። በኋላም ወደ እስራኤል ሲመለሱ የአሰልጣኙን ብቃት በመናገራቸው የእስራኤል የስፖርት ዘርፍ አመራሮች መጥተው አትሌት መገርሳ ሁንዴ አነጋገሯቸውና ማሰልጠን ጀመሩ።
ቡድኑን የሚያሰለጥኑት ወደ እስራኤል እየተመላለሱ ነበር፤ አንዳንዴ ደግሞ አትሌቶቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተውም ያሰለጥኗቸውም ነበር። በዚህም አትሌቶቹ ውጤታማ መሆን ችለዋል።
እሳቸው በሀገር ውሰጥ ካሰለጠኗቸው አትሌቶች መሀል ኢማና መርጋ፣ አሊ አብዱል፣ ፈይሳ ሌሊሳ፣ ደረሰ መኮንን እነዚህን እና ሌሎች አትሌቶችን ማፍራታቸውን በመግለጽ፤ ‹‹እኔ በሠራሁት ሥራ አይቆጨኝም፤ ነገር ግን ብዙ የሠራ ሰው ቢታወስ ለቀጣይ ትውልድ ተነሳሽነትን ይፈጥራል›› ይላሉ።
አትሌቱ ከመከላከያ ከጥቅምት 1 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምረው ነበር የለቀቁት። አሁን ከመከላከያ ከለቀቁ 16 ዓመት አልፏቸዋል። ከዛ ከወጡ በኋላ በግል በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ አትሌቶችን እያሰለጠኑ ቢቆዩም አሁን ላይ ለጊዜው እረፍት ላይ መሆናቸውን እና በእሳቸው መሰልጠን የሚፈልግ አትሌት ካሉ አሁንም ማሰልጠን እንደሚችሉ ይገልጻሉ።
አትሌቱ ለአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ ብለው በትዳር ለመጣመር የወሰኑት ገና በለጋ እድሜያቸው ነው። ለብሔራዊ ቡድን ተመርጠው አዲስ አበባ ከቀሩ በኋላ በ1974 ዓ.ም ነበር ያገቡት። ከትዳራቸው ሰባት ልጆችን እና 12 የልጅ ልጆችን አፍርተዋል።
አሁን ላይ ኑሮዋቸውን የሚደጉሙት በጡረታ በሚያገኙት ገቢ እንደሆነ በመግለጽ፤ “በሻለቃ ማዕረጌ ወጥቼ ቢሆን የሚከፈለኝ የጡረታ ገንዘብ የተሻለ ይሆን ነበር፤ ነገር በመቶ አለቃውም ቢሆን ከሚቀር ብዬ ተቀብዬ ኑሮዬን እየገፋሁ ነው። ከዛ ውጪ በግል አንዳንድ አትሌቶችን እና ቡድኖችን የማሰለጥን ቢሆንም፤ ከአንድ ዓመት በላይ ግን ምንም ሥራ ሳልሰራ ቁጭ ብዬአለሁ። ” ይላሉ።
“አሁንም ቢሆን አቅሙም ሆነ የተቀበልኳቸው የተለያዩ የምስክር ወረቀቶች ስላሉኝ ማሰልጠን እችላለሁ። ነገር ግን ትንሽ አትሌቲክሱ የተቀዛቀዘ ይመስላል። እንደ ቀድሞ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሥርዓት ይዘው ሀገርን ለመወክል የሚያደረግ ጥረት የለም፤ ሁሉም አትሌት በግል መሮጥ ነው የሚፈልገው። ይህ ደግሞ ሀገርን ይጎዳል። “ሲሉ ይገልጻሉ።
‹‹አንድ አትሌት ዲስፕሊን ከሌለው፣ ለሀገር አላማ ከሌለው ትንሽ ያስቸግራል። በግል ውድድሮች ላይ ጥሩ ቢሆኑም፤ በኦሎምፒክ እንደታየው የውጤት መውረድ ሲታይ የማሰልጠን ፍላጎት የመቀዝቀዝ ነገር ሊኖር ይችላል። ሆኖም ሁልጊዜም ቢሆን አንድ አትሌት ለሀገሩ ቅድሚያ ሰጥቶ መሮጥ አለበት›› ይላሉ።
በመጨረሻም አትሌቱ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለቀድሞ አለቆቻቸው፣ ለመቻል ስፖርት ክለብ፣ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ በሀዘንም በደስታ አብራቸው ለነበረችው ባለቤታቸው እና ለልጆቻቸው ምስጋን አቅርበዋል።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም