ለወገን የተከፈለ መስዋዕትነት

ጥሩ ትስስር እና መረዳዳት ባለበት የማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ነው ያደገችው። በዚህም ስለሌሎች ይመለከተኛል የሚለውን ሃሳብ በውስጧ ይዛ ኖራለች። ከሰባት ዓመት በላይ በጋዜጠኝነት ሙያ አገልግላለች። ለዓመታት ኑሮዋን ከኢትዮጵያ ውጭ አድርጋ ቆይታለች። ከቆየችበት የውጭ ሀገር ስትመለስ ኢትዮጵያ ያላትን ባሕል እና ወግ ሥነምግባር ያለውን ዋጋ ለብዙዎች ለማሳየት የራሷን ፕሮግራም ጀመረች። ይህ የጋዜጠኝነት ሙያ አሁን ወዳለችበት ሕይወት መርቷት ለብዙዎች መፍትሄ እና ደጋፊ መሆንን ችላ በሀገሯ ውስጥ መኖርንን እንድትመርጥ አድርጓታል። ነኢማ ሙዘይን የይመለከተኛል የሱስ እና የአዕምሮ ህሙማን ማገገሚያ የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራች ናት። በዛሬው እትማችንም የነኢማን ሕይወት ጉዞ እና ስኬት ለመቃኘት ወደድን፤ መልካም ንባብ።

ልጅነትን በህብረት

ነኢማ ሙዘይን ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ ዘነበወርቅ አካባቢ ነው። አባቷ የጤና ባለሙያ ሲሆኑ እናቷ ደግሞ ጉሊት ሽጠው ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ጠንካራ እናት ናቸው። ነኢማ ባደገችበት ቤት ውስጥ እሷን ጨምሮ ዘጠኝ ልጆች እህትና ወንድሞች አብረዋት አድገዋል። በዚህ ጊቢ ውስጥ ቤተሰባዊነት፣ እርስ በእርስ መረዳዳት ጎልቶ የሚታይበት የልጅነት ጊዜ መሆኑን ነኢማ ታስታውሳለች።

በልጅነት ጊዜዋ በትምህርቷ እምብዛም አልነበርኩም የምትለው ነኢማ በአባቷ እገዛ ትምህርቷ ላይ የነበራት ትኩረት መመለሱን አንስታለች። ዛሬ ላለችበት ደረጃ እና የሕይወት አስተሳሰብ ወላጆቿን ታመሰግናለች። አሁንም ድረስ በሃሳቧ እና በሕይወት ጉዞዋ የሚደግፏት እናቷን የምንጊዜም የሕይወት ጀግናዬ በማለት በምትጋበዝባቸው መድረኮች ላይ ሁሉ ታነሳቸዋለች።

የነኢማ ወላጅ እናት በአካባቢያቸው በነበራቸው እንቅስቃሴ እና ተሳትፎ የነኢማ ወደ ጋዜጠኝነት መሳብ እና ወደ ሙያው መግባት አጋጣሚም የእሳቸው መሆኑን ትጠቅሳለች። ‹‹ያኔ ልጅ ነበርኩ ከዚያ እናቴ በቀበሌ ውስጥ ይሰጥ የነበረ የጋዜጠኝነት ስልጠና እንድወስድ አደረገችኝ። እኔ ግን ስልጠናውን ከወሰድኩ በኋላ ብዙም ትኩረቴ አልነበረም። ›› በተማረችው የአጭር ጊዜ ስልጠና ነኢማ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ መሳተፍ እና ዝግጅቶችን ማቅረብ የመሳሰሉ ክህሎቶችን አዳብራ ነበር።

ጉዞ ወደ አረብ ሀገር

ነኢማ ምንም ልጅ ብትሆንም በወቅቱ አቻዋ የሆነች እና አብራት የተማረች ጓደኛዋ ወደ አረብ ሀገር አቀናች። በምትኖርበት የአረብ ሀገርም ነኢማ ልትጓጓባቸው የምትችላቸውን ሁኔታዎች በፎቶግራፍ እያደረገች ትልክላት ጀመር። ነኢማ በፎቶ የምታየው የጓደኛዋ ሕይወት፤ ያለችበት ሁኔታ ይበልጥ አጓጓት። በዚህም ምክንያት ልክ እንደ ጓደኛዋ የሚያጓጓትን ሕይወት በአካል ማየት፤ መኖር እና ሰርታ መለወጥን ተመኘች። ተመኝታም አልቀረችም ወሰነች። ጉዞዋን ወደ አረብ ሀገር አደረገች፤ የተመኘችው በፎቶ የተመለከተችው ሕይወትና ነኢማ የገጠማት ግን በፍጹም የተለያየ ነበር። በየመን የቆየችበት ጊዜ መራር እና ፈታኝ ነበር። ነገር ግን ዛሬ ላይ ለደረሰችበት ብዙ የሕይወት ልምድን የወሰደችበት የተማረችበት ነበር።

ነኢማ ጓግታ የሄደችበት አስቸጋሪ የየመን ቆይታ ከሶስት ዓመታት በኋላ ትታ ወደ ሀገሯ ስትመለስ እናቷን ማሳረፍ እና መርዳት ፈለገች። በዚህም የጋዜጠኝነት ሙያዋን ወደ ተማረችበት ቀበሌ አመራች። በዚያም ንቁ ተሳትፎ የምታደርግ ወጣት ነበረች።

በድጋሚ ከሀገር መውጣት

ነኢማ በሀገሯ ውስጥ ሕይወትን ለማሸነፍ ስትጥር ቆይታለች። በኋላ ላይ በትዳር አማካኝነት ወደ አውስትራሊያ የሄደች እህት ነበረቻት። ይህች እህቷ የልጅ እናት ስትሆን ቤተሰቦቿ እንዲጎበኟት የሚያደርግ ግብዣ ላከችላቸው። በዚህ አጋጣሚ ነበር ነኢማ እንደገና ሌላኛውን የሰለጠነ ተብሎ የሚጠራውን ብዙዎች ሊሄዱ የሚመኙትን ሀገር ለማየት የቻለችው። በዚያ የተመለከተችው የባሕል ልዩነት እጅጉን አስፈራት። እሷ ከኖረችበት እና ከለመደችው ባሕል ጋር በፍጹም የተለያየ ሆነባት። በዚህ ወቅት ነኢማ በእምነቷ እየጠነከረች ወደ እምነቷ እየቀረበች መጣች። የሃይማኖት አባቶችን ትምህርትም መከታተል ጀመረች።

እናትነት እና ኃላፊነት

ነኢማ የአንድ ልጅ እናት ናት። ታዲያ ልጅ በልጅነቱ ሲያዩት የሚያሳሳ፤ እድገቱ የሚጓጓ ነው። እያደገ እና የአፍላዎቹ እድሜ ላይ ሲደርስ ደግሞ አጉል ቦታ ላይ እንዳይወድቅ፤ በመጥፎ ምግባር ላይ እንዳይገኝ የሚያስጨንቅም ጭምር ነው። ልጇን በኢትዮጵያ ጥላ ወደ አውስትራሊያ የሄደችው ነኢማ የአንድ ልጇ ናፍቆት ስላላስቻላት ወደ እሷ እንዲመጣ አደረገችው። የልጇ ከእሷ ጋር መሆን መልካም ቢሆንም ሁኔታዎች ግን ለነኢማ ምቹ አልነበሩም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ እና በዚያ ሀገር ያለው የባሕል ልዩነት ልጇ ወዳልተፈለገ መንገድ እንዳያመራ አብዝታ ማብሰልሰል ጀመረች። ወጥቶ እስከሚገባ ድረስ መጨነቅ ሥራዋ ሆነ።

ነኢማ ለዚህም መፍትሔ ያደረገችው ልጇ እስኪያድግ እና ልብ እስከሚገዛ ድረስ በኢትዮጵያዊ ባሕል ታንጾ እንዲያድግ የሀገሩን ባሕል እንዲረዳ በመፈለግ ልጇን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች። ነገር ግን የልጇን ሕይወት ማስተካከል የተሻለ ማድረግ የማትደራደርበት ኃላፊነቷ ነበር። ልጇን በኢትዮጵያ አዳሪ ትምህርት ቤት አስገብታ በድጋሚ ወደ አውስትራሊያ ተመለሰች።

ነኢማ በአውስትራሊያ ቆይታለች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይም ሰርታለች። በቆየችበት የሥራ ዘርፍ ላይ በኢትዮጵያ እያለች የተማረችውን የጋዜጠኝነት ሙያ በአውስትራሊያ ቆይታዋ ልትሰራበት ችላለች። በዚያ የሚገኝ የኢስላሚክ የራዲዮ ጣቢያ ላይ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ትሰራ ነበር።

በድጋሚ ወደ ሀገር መመለስ

በአውስትራሊያ በምትገኝበት ወቅት የኮቪድ 19 ወረርሽን ይፋ መሆን ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎችን ገደቡ። ይህ የእንቅስቃሴ ገደብ ቦታ እና ሁኔታ ያልለየው በመሆኑ እሷ በአውስትራሊያ መንሳቀስ በማትችልበት ሁኔታ፣ ልጇ ደግሞ ትምህርቱን አቋርጦ በቤት ውስጥ ለመቀመጥ ተገደዱ። በቤት ውስጥ ተቀምጦ መዋል ምቾት ያልሰጠው የነኢማ ልጅም እናቱ እንድትመጣ፣ አልያም እሱ እርሷ ወዳለችበት ለመሄድ እንደሚፈልግ ለእናቱ ደጋግሞ መናገሩን ቀጠለ። ነኢማም የልጇ ነገር አላስቻላትም እና በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ያሏትን ግንኙነቶች ተጠቅማ ከኮቪድ ወረርሽን ይፋ መደረግ ከስምንት ወር በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ መጣች።

አዲስ መንገድ – በሀገር ቤት

ታዲያ የኮቪድ 19 ወረርሽን ይፋ በተደረገበት ሰዓት ልጇን ለማየት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ስትመጣ ጊዜዋን እንዲሁ ማባከን አልፈለገችም። በአውስትራሊያ ቆይታዋ ትሰራው የነበረውን የጋዜጠኝነት ሥራ በኢትዮጵያም ማስቀጠል ፈለገች። የእስልምና እምነት ተከታዮች በብዛት የሚከታተሏቸውን የቴሌቭዥን ጣቢያዎች፤ የምታውቃቸውን ሰዎች በመጠቀም የራሷን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመጀመር ወሰነች። የፕሮግራሙ ዋና አላማም በኖረችበት የሰለጠነ ዓለም ሰዎች የሚጓጉለትን ‹‹ሰለጠነ›› የሚባለው ሕይወት ያለበትን ጉድለት ለማስተማር ፈለገች። ይህንኑ ለማስተማር የሚያስችላትን ቶክሾው ለማዘጋጀት ወሰነች። ‹‹ ጄሉል ቲቪ ›› የተሰኘ ጣቢያ ላይ ‹‹ ሹባክ ሾው›› የቴሌቭዥን ፕሮግራምን ጀመረች ። በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ የእምነት አባቶችን በመጋበዝ ሀገራዊ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ፕሮግራሙን ለሰዎች ጠቃሚ መልዕክት እንዲያስተላልፍ ማድረጓን ቀጠለች ።

የአላህ መንገድ

ነኢማ የቴሌቪዥን ፕሮግራሟ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ የቴሌቭዥን ፕሮግራሟን ከሚከታተሉ ሰዎች አንድ ልትሰራው የሚገባ ጥቆማ ደረሳት። ይህ አጋጣሚ

የነኢማን ሕይወት ሙሉ ለሙሉ ቀየረው።

‹‹በከፍተኛ የትምህርት ተቋም በማዕረግ የተመረቁ ሁለት ወንድማማቾች አንድ ደግሞ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ እና በዚህ ሥራው ደግሞ ወንድሞቹን የሚያስተምር ወንድማቸው በአጠቃላይ ሶስት ወንድማማቾች በአዕምሮ ህመም ተጠቅተው የሱስ እስረኛ ሆነው የሚረዳቸው እንደሌለ እና ወጣቶቹ ለአስር ዓመት ያክል በሰንሰለት ታስረው ያለ አስታማሚ በቤት ውስጥ መኖራቸውን ሰማሁ። ›› የምትለው ነኢማ እነዚህ ሶስት ወንድማማቾች ሀድራ ሰኢድ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማዕረግ ተመራቂ፣ አብዱልቃድር ሰኢድ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማዕረግ ተመራቂ በመሆን ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ናቸው። ሚፍታህ ሰኢድ ደግሞ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የቆየ ነው። ወንድማማቾቹ እናት እና አባታቸውን በሞት ተነጥቀዋል።

ነኢማ ይህ ከባድ ጉዳይ በፕሮግራሟ ለመሥራት ወጣቶቹ ወደሚገኙበት ገጠራማ ስፍራ በደቡብ ክልል ጉራጌ ውስጥ የምትገኝ ቸሀ ወረዳ አቀናች። ነኢማ ሁኔታውን እንዲህ ታስታውሰዋለች። ‹‹ለአስር ዓመት በነበረባቸው የአዕምሮ ህመም ማህበረሰቡ አግልሏቸው ቆይተው በቤት ውስጥ ታስረው ነው ያገኘኋቸው። ሆስፒታል ከመውሰድ ይልቅ ግን ሰዎች እንደ ጫትና ሲጋራ ያሉ ሱሶችን እየሰጡ የባሰ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አድርገዋቸዋል። ›› ወጣቶቹ በሰንሰለት ታስረው የቆዩ ማህበረሰቡ አግልሏቸው እና ፈርቷቸው ያለ ቢሆንም ነኢማ ግን በሰላማዊ መንገድ ልታናነጋግራቸው ደፈረች።

ነኢማ የእነዚህን ወጣቶች ታሪክ ሰርታ ተመለሰች። ፕሮግራሙም በቴሌቪዥን መስኮት ተላልፎ ብዙዎች እንዲያዩት ተደረገ። እሷ ግን ከፕሮግራሙ መተላለፍ በኋላ እንዲሁ ዝም ብላ መቀመጥ አልቻለችም፤ ስሜቷ ሁሉ ስለእነዚህ ወንድማማቾች መጨነቅ ጀመረ። የውስጥቷን ፈተና ለመመለስ ወንድማቾቹ የሚያገግሙበትን ሁኔታ የጤና ተቋም፤ የማገገሚያ ማዕከል መፈለጓን ቀጠለች።

በዚህ አጋጣሚም ይረዱኛል ያለቻቸው ሆስፒታሎች ጋር በመሄድ እና የልጆቹን ሕይወት በተቀረጸው የተንቀሳቃሳሽ ምስል በማሳየት የበርካቶቹን በር ማንኳኳት ጀመረች። የወንድማማቾቹን ታሪክ የተመለከቱ ሁለት የጤና ባለሙያዎች፤ ኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል እና ስጦታ ሆስፒታል ዶክተር ዮናስ ወጣቶቹን ለማከም እና የሚያርፉበትን ቦታ ለማመቻቸት ለነኢማ ቃል ገቡላት። ተገቢውን ህክምና እና ክትትል ካገኙም በቶሎ መዳን እንደሚችሉ አረጋገጡላት። ይህ ለነኢማ ትልቅ እረፍት ነበር።

ወንድማማቾቹ ወደሚገኙበት የቸሀ ወረዳ ተመልሳ ሄደች። ለአስር ዓመታት በሰንሰለት ታስረው የቆዩ ናቸውና እንዳያስቸግሯት በመፍራት ከወረዳው አስተዳዳሪ ጋር በመነጋገር የጸጥታ አካላት እንዲዘጋጁላት አደረገች። ነኢማ ግን እንደምትናገረው ‹‹ፈጣሪ የነገራቸው ይመስለኛል፤ ምንም ሳያስቸግሩኝ በሰንሰለትም ሳይታሰሩ ወደ አዲስ አበባ መጡ›› ስትል ጊዜውን ወደኋላ መለስ ብላ ታስታውሳለች።

ነኢማ የነበረችበትን አውስትራሊያ ጥላ ስትመጣ ልጇን ለማየት እና ከልጇ ጋር የተወሰነ ጊዜ ለመቆየት ነበር። ምክንያቱም የልጇ የሥነ ምግባር መሠረት በኢትዮጵያዊ ማንነት የታነጸ እንዲሆን ፈልጋለች እና። ታዲያ በድንገት ሳታስበው የገባችበት ሥራ ወደ አንድ ትልቅ የሕይወት ጥሪ አድርሷታል። የወንድማማቾቹን ታሪክ የተመለከቱ፤ ህክምና ካገኙ በኋላ ያላቸውን ለውጥ በሂደት ያዩ በርካታ እናቶች ተመሳሳይ የሆነ ችግርን ይዘው በቤታቸው የተቀመጡ ወላጆች ወደ ነኢማ ስልክ በተደጋጋሚ መደወል ጀመሩ። ነኢማ የምታስተናግዳቸው ስልኮች፤ የምትሰማቸው ታሪኮች ለአዕምሮዋ እጅግ ውጥረትን ፈጠሩባት። በዚህም የእናቶችን እንባና እረፍት ማጣት ሊቀንስ የሚችል መፍትሔም መፈለግም ቀጠለች። በተለያዩ የአዕምሮ ህመም የተጠቁ እና በተለያዩ ሱሶች ምክንያት ሥራቸውን መሥራት፤ የእለት ተዕለት ተግባራቸውን ማከናወን ያቃታቸውን ወጣቶች ለመርዳት ተነሳሳች። ብዙዎቹ በሱስ የተጠቁት ወጣቶች መሆናቸው፤ በይበልጥ ደግሞ በትምህርታቸውን በትልቅ ውጤት የተመረቁ ፤ ትልቅ ደረጃ ላይ ይደርሳሉ የተባሉ መሆናቸቸው የነኢማን ልብ ይበልጥ አስጨነቀው።

ታዲያ የምትሰራውን ሥራ መልካምነት በልጅነት አዕምሮው የተረዳው የነኢማ ልጅ እናቱ የጀመረችው ሥራ በሱ ምክንያት እንዳይሰናከል በማሰብ ወደ አውስትራሊያ ለመሄድ ወሰነ። እናቱም አደራውን ለአምላኳ ሰጥታ ልጇን ሸኘችው። እሷም የሀገሬ ጉዳይ ኃላፊነት አለብኝ ብላ እዚሁ ኢትዮጵያ ቀረች።

‹‹በጣም ብዙ እናቶች የተማሩ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ የደረሱ ልጆቻቸውን በዚህ ሱስ ምክንያት የአዕምሮ ህመም ተጠቂ ሆነው በቤት ውስጥ እንደታሰሩ፤ ወላጆች ወልደው የወላድ መካን እንደሆኑ እየደወሉ ይነግሩኛል። ›› የምትለው ነኢማ ከተለያዩ ቦታዎች የምትሰማውን የእናቶች ለቅሶ በፍጹም መቋቋም አልቻለችም። በሱስ ተጠቅተው የሚኖሩ ሰዎች ለህመማቸው መፍትሔ ያጡት በአብዛኛው በግንዛቤ እጥረት መሆኑን ተገነዘበች። ብዙዎች በህክምና መፍትሔ ከማግኘት ይልቅ ከሃይማኖታዊ ነገሮች ጋር በማገናኘት ጊዜያቸውን እንደሚፈጁ ተረዳች።

ታዲያ በእነዚህ ሶስት ወንድማማቾች ታሪክ ይመለከተኛል ያለችው ነኢማ መሰል ተመሳሳይ ታሪኮችን በብዛት በማስተናገዷ ተቋማዊ ለማድረግ ወሰነች።

ነገር ግን በሥራዋ የሚደግፏት እና የሚበረታቷት እንዳሉ ሁሉ ለምን አይቀርብሽም የሚሏት ብዙዎች ነበሩ። በምትኖርበት ሀገር ያላትን የሞቀ ሕይወት ትታ በመምጣቷ የሚቆጩ ሰዎችም በርካቶች ናቸው። በእነዚህ አስተያየቶች ልቧ ያልተበገረው ነኢማ የሀገሬ ጉዳይ የኔ ጉዳይ ነው በሚል ስያሜውን ‹‹ ይመለከተኛል የበጎ አድራጎት ድርጅት›› በሚል አዲስ ተቋም ለመመሥረት ቻለች።

አዲስ ጉዞ

ነኢማ ኑሮዋን በአውስትራሊያ በአደረገችበት ወቅት ልትሰራቸው ያሰበቻቸው የራሷ ሃሳብ እና ህልም ነበራት። ነገር ግን በሀገሯ የተመለከተችውን ችግር እንቅልፍ የሚነሳ በመሆኑ ሃሳቦቿን ሁሉ እርግፍ አድርጋ ከፉውንም ደጉንም ከወገኗ ጋር ለመጋፈጥ ወሰነች። በሀገሯ ያየችውን ችግር ችላ ብላ ማለፍ፤ አይመለከተኝም ማለት አልቻለችም።

የበኩሏን አድርጋ ያየቻችውን ችግሮች ለመቅረፍ በምትነሳበት ወቅት ብዙዎች ምን አገባሽ ፣ ለምን አትተይውም የሚል ጥያቄን ያቀርቡላት ነበር። ይህ ሃሳብ ያልተዋጠላት ነኢማ እኔ ይመለከተኛል፣ የአዕምሮ ህመም እናንተንም ይመለከታችኋል የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ላቋቋመችው ድርጅት ‹‹ይመለከተኛል ›› የሚል ስያሜ ሰጠችው።

ይህንን ሥራ ስትጀምር ሰዎችን የምታሳርፍበት ቦታ እጅግ አስፈላጊ ነበር። ነገር ግን ለዚህ ጉዳይ ብሎ የሚያከራይ ፍቃደኛ የሚሆን ሰው አጣች። ከዚያም ለሶስት ዓመት ያክል በኖረችበት ቤት ውስጥ እናቷን ወደ ሌላ መኖሪያ ቤት ቀይራ በራሷ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሥራዋን ጀመረች።

የአእምሮ ህመምን በተመለከተ ሰዎች ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ የአዕምሮ ህመምን፣ ሱስን በቀላሉ መታከም የሚችሉ ህመሞች ቢሆኑም እጅግ ተባብሰው ሰዎች ራሳቸውን እስከ ማጥፋት ድረስ እንደሚደርሱ ነኢማ መገንዘብ ችላለች። በመሆኑም ሳይንሳዊ የሆነውን የህክምና ዘዴ ከመንፈሳዊ ህክምና ጋር በማጣመር ታካሚዎች ካለባቸው ችግር እንዲያገግሙ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ጠንካራ እንዲሆኑ ለሚያምኑበት እምነት ቅርብ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራን በዋናነት ትሰራለች።

ከባድ ፈተናዎች

የአልኮሆል ሱስ ያለባቸው ተጠቂዎች ተጠቃሚ በነበሩት ጊዜ በቀን አንድ ጊዜ በልተው ሌላው ሰዓት ተጠቂ የሆኑበትን ሱስ በመጠቀም ይቆያሉ። ታዲያ ወደሱስ ማገገሚያ ማዕከል ከገቡ በኋላ ሙሉ በሙሉ ሱሳቸውን እንዲያቋርጡ ስለሚደረግ ወደማዕከሉ ከመጡ በኋላ ከባድ የሆነ ሳምንትን ያሳልፋሉ። ራሳቸውን እስከ ማጥፋት የሚያደርስ ሙከራንም ያደርጋሉ። ነኢማም ይህንን ሊከላከል የሚችል ክፍል ማቋቋም ነበረባት። ወጣቶቹ ሱሳቸውን በማቆማቸው ምክንያት በቀን ውስጥ የሚኖራቸው የምግብ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ በየእለቱ መመገብ እንዲሁ ሌላው ተግባር ነው። ሆኖም ነኢማ ለዚህ ሁሉ ዝግጁ ባትሆንም በፈጣሪ እገዛ ችግሮቹን ተጋፍጣ ብዙዎችን እየረዳች ነው።

ነኢማ በሱስ ማገገሚያ ውስጥ ያሉ እነዚህ ወጣቶች እያገገሙ በሚሄዱበት ጊዜ እንዲያነቡ፣ ስፖርት እንዲሰሩ ታደርጋለች። በማዕከሉ ውስጥም ከተለያዩ ቦታዎች መንፈሳዊ እና ሌሎች መጽሐፎችን በመሰብሰብ በማዕከሉ ውስጥ ቤተ መጻሕፍት ገንብታለች። ነገር ግን በጫት ሱስ ውስጥ ወድቀው የቆዩ በመሆናቸው ያገኙትን መጽሐፍ ከማንበብ ይልቅ ቀዳደው የሚጥሉበት ጊዜ ብዙ ነው።

ነኢማ ይመለከተኛል የበጎ አድራጎት ድርጅት የአዕምሮ ህሙማን እና የሱስ ማገገሚያ ማዕከል ስትመሰርት በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ነኢማ መምጣት ጀመሩ። ሆኖም የድርጅቱ አቅም እና የሰው ፍላጎት የሚመጣጠን አይደለም። ‹‹ማዕከሉ ገቢ የሚያገኝበት ወይም ድጋፍ የሚያደርግለት የለም። ›› የምትለው ነኢማ ችግሩን ለመፍታት በሁለት መንገድ ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ታካሚዎችን ታስተናግዳለች። አንደኛው አቅም ያላቸው ጥሩ የሆነ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው ሲመጡ በማዕከሉ ያሉ ሌሎች ታካሚዎችን እንዲደግፉ ይደረጋል። አቅም የሌላቸው ወላጆች ሲመጡ ደግሞ ተመዝግበው በወረፋቸው ይስተናገዳሉ።

ነኢማ በማዕከሉ ውስጥ ያሉ ታካሚዎችን ልጆቼ ብላ ትጠራቸዋለች። ከሳምንት እስከ ሳምንት ይህ ነው የምትለው ፕሮግራም ወይንም ጉዳይ የላትም። አብዛኛውን ጊዜዋን ከእነርሱ ጋር በማውራት፣ እነርሱን ቀርቦ በማነጋገር ጊዜዋን ታሳልፋለች።

ይመለከተኛል ዛሬ እና ነገ

ነኢማ ባቋቋመችው በይመለከተኛል የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ከሚመጡ ታካሚዎች ውስጥ ቀላል በሆነ የድባቴ፣ በተለያዩ ሱሶች ውስጥ የእለት ተዕለት ተግባራቸውን ማከናወን ተስኗቸው፣ በቅርባቸው ሰዎች ርዳታ ማግኘት አቅቷቸው ወደ ሱስ ውስጥ የገቡ ወጣቶች በርካታ መሆናቸውን ትጠቅሳለች። በዚህም ርዳታ አግኝተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ሥራቸውን እንዲሰሩ ተደርጓል። ከተመሰረተ ሁለት ዓመት የሆነው የይመለከተኛል የበጎ አድራጎት ድርጅት የአዕምሮ ህመም እና የሱስ ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ ከ140 በላይ የሚሆኑ ታካሚዎች ይገኛሉ። እስከ አሁን በተሰራው ሥራም ከ500 በላይ የሚሆኑ ታካሚዎች ህክምናቸውን ጨርሰው እና አገግመው ከማዕከሉ ወጥተው ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል የራሳቸውን ሕይወት መስርተዋል። በማዕከሉ የተሞሸሩም አሉ።

ሱስ እና የአዕምሮ ህመም ሰዎች ያላቸውን መደበኛ ሕይወት እንዳይመሩ ከማድረጉም ባሻገር ለወደቁለት ሱስ ተገዢ የሚያደርግ ነው። ታዲያ በማዕከሉ ውስጥ ካለባቸው ሱስ እና የአዕምሮ ህመም ለማገገም የገቡ ሰዎች /ታካሚዎች በየጊዜው የሚከታተሏቸው ሐኪሞች፣ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች፣ የአካል ብቃት የሚሰሩ አሰልጣኞች የመንፈሳዊ ትምህርት አስተማሪዎች ይገኙበታል። የእነዚህ ሁሉ ውጤት የተሻለ ሰው እንደሚደርጋቸው ነኢማ ታምናለች።

ማዕከሉ በሙያዊ መንገድም ሆነ በገንዘብ የተለያየ እገዛ የሚያስፈልገው መሆኑን ጠቅሳ ብዙ ሰዎች ማዕከሉ ለማገዝ ቃል ቢገቡም የአዕምሮ ህመም እና ሱስ በመሆኑ ፈርተው የሚቀሩ እና የማይቀጥሉበት ሰዎች ይበዛሉ ስትል አሁንም ከአዕምሮ ህመም ጋር በተያያዘ ያለውን የግንዛቤ እጥረት ታነሳለች።

በአሁን ሰዓት የማዕከሉን ርዳታ ፈልገው ተመዝግበው ወረፋ የሚጠብቁ በርካታ ሰዎች ይገኛሉ። ታዲያ ነኢማ ይህንን ተቋም ማገዝ የሚችል እና ከማዕከሉ አገግመው ወጥተው ነገር ግን ሥራ በማጣታቸው ምክንያት ተመልሰው ወደ ሱስ ውስጥ የገቡ ወጣቶችን ለማገዝ የሚያስችል ወርክሾፕ በማቋቋም ላይ ትገኛለች። ‹‹ ተቋሙ በዋናነት የተመሰረተው ለድሆች አቅም ለሌላቸው ነው። ስለዚህ አገግመው ሲወጡ በዚህ ማዕከል ውስጥ የእንጨት ሥራ፣ ቴክኒሻን፣ የጸጉር ሥራ እና ሌሎች ሙያዎችን ተምረው ተቀጥረው የሚሰሩበትን እና ገቢ በማምጣት ተቋሙ ራሱን የሚደግፍበትን መንገድ እንፈጥራለን። ›› ስትል የማዕከሉን የነገ መንገድ ተልማለች።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You