በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
ውሏችንን “ሀ” ብለን ስንጀምር “እንዲህ አደርጋለሁ፤ ይህን እፈጽማለሁ ወዘተ” ብለን ዕናቅዳለን:: በዕቅዳችን መሰረት ወደ መተግበሩ ስንገባ ሁሉም ዕቅዳችን ከሰው ጋር የተገናኘ እንደሆነ እንረዳለን:: የምንሠራው ለሰው፤ የምንሰራው ከሰው ጋር::
እዚህ ውስጥ አንድ ነገር ይፈጠራል፤ እርሱም ከሰው ጋር የሚኖር ግንኙነት:: በግንኙነቱ ውስጥ ደግሞ ግጭት:: ጠቃሚ የሆነውን ግጭት ወይንም መጋፈጥ መቀበል ከመጋጋጥ እንደሚያድን እንመልከት::
ፊደል ካስትሮ ስለ አብዮት ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ “አብዮት የመኝታ ላይ ጽጌሬዳ አይደለም በትላንት እና በነገ መካከል የሚደረግ መራራ ትግል እንጂ::” በመጽሐፍት አብዮት ሲተረክ፣ በፊልም ሲታይ፣ ትምህርት ሆኖ ሲማሩት ወዘተ አብዮት እንደ ጽጌሬዳ ይመስላል፤ በውስጡ የሚያልፉ ግን መራራውን ጽዋ ይጎናጽፉበታል::
ከተከፈለው ዋጋ ማግስት የሚገኘው ውጤት ወደፊትን ለማረቅ እና ወደፊቱን በመልኩ ለማድረግ ይረዳል:: እሥራኤላውያን ከግብጽ ወጥተው በምድረበዳ ወደ ከነዓን ባደረጉት ጉዞ ውስጥ ከፈርዖን ጋር የተደረገው ግብግብ በትላንት እና በነገ መካከል የተደረገ ትገል አድርገን መውሰድ እንችላለን::
የቃላት ሚና
ከሰዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ውስጥ የምንጠቀማቸው ቃላት ከምናሳየው የፊት ገጽታ፣ ከድምጸታችን እና ሌሎች ተጓዳኝ ነገሮች ጋር በመሆን የምናደርገውን ግንኙነት ይወስነዋል:: “የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም” እንደምንለው ንግግራችን በግንኙነት መካከል ትልቁን ቦታ ይይዛል:: የምናቀርበው ተጠየቅ ጉልበቱ የሚመዘነው በቃሎቻችን ውስጥ ነው::
በቃላት ውስጥ አንድ ሞገደኛ ሌላ ሞገደኛን ይፈጥርና ግብ የለሽ የሆነ ግብግብ በመንገዳችን ሊገጥመን ይችላል:: ከመጋጋጥ የመጋፈጠን አስፈላጊነት በምናብራራበት በእዚህ ጽሁፍ ውስጥ በአላስፈላጊ ቃላት ምክንያት የሚመጣ መጋፈጠን ባህል የምናደርግበትን በር የሚከፍትልን እንዳይሆን በሩን በሚገባ መዝጋታችንን እርግጠኛ መሆን ስላለብን ስለ ቃላት ሚና ያስቀደም ነው::
መኪና እየነዳን ነው ብለን እናስብ:: ከፊታችን ያለው መኪና በመዘግየቱ ምክንያት እኛም እየዘገየን:: ከኋላችን ያለው መኪና እኛ ከፊት ለፊታችን የምናየውን ነገር የማየት ዕድል ስለሌለው ለምን ዘገየህ ብሎ ክላክሱን ያንቧርቅዋል፤ ከቻለም አልፎህ ለመሄድ ጥረትም ያደርጋል:: በእርግጥ ቸኩሎ ይሆናል፤ ግን የስሜቱ መረበሽ አንተን ጥፋተኛ አድርጎ ነው:: የዘገየንበት ምክንያት ከፊት ለፊታችን ያለው መኪና ተበላሽቶ የቆመ ወይንም ሰዎችን እያሳልፍን መሆኑን ሲረዳ የፈጠረው ግርግር አላስፈላጊ መሆኑን ይረዳል ይሆናል::
በእርግጥ በዓይን አይቶ እስኪረዳ ድረስ የመዘግየትህ ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል ብሎ አስቦ የሚታገስም ይኖር ይሆናል፤ ጥቂት የሚሆኑ ቢሆንም:: እኒህን ሁለት ከኋላችን እያሽከረከሩ ያሉ ሰዎችን ችኩል(ሞገደኛ) እና አሳቢ (ልከኛ) ብለን ልንከፍላቸው እንችላለን::ሁለቱም በቃላታቸው ይታወቃሉ::
ሞገደኛው በሞገደኛ ቃላቶቹ ሲገጥመህ ልከኛው ከሀሳብ በወጡ ቃላቶቹ ይግባባሃል:: ከመጋጋጥ መጋፈጥ ውስጥ በልከኝነት ወይንም ከሀሳብ ውስጥ በወጡ ቃላት ውስጥ በሚደረግ የምክንያታዊ ተጠይቅ ውስጥ የሚኖር መጋፈጥ ነው:: የጨበጣ ተጋፈጥ እርሱ ሞገደኝነት ነው:: ልከኛው ደግሞ ሞጋችነት:: ትላትን እና ነገን ለማስታረቅ የሚረዳ፤ ስለ ራዕይ ሲባል የሚሆን መጋፈጥ::
መጋፈጥ ወይንስ መጋጋጥ 1 – ሞገደኛውን?
በመኪና ማሽከርከር ወቅት የሚገጥሙን ሞገደኛ አሽከርካሪዎችን እንዴት ብንይዛቸው ጥሩ ነው የሚለው የውሏችን መንፈስ ይወስነዋል:: አንተ በተጠየቅ ውስጥ ብትሆን፣ አንተ የቱንም ያህል በምክንያታዊነት ውስጥ ብትሆን፣ አንተ የቱንም ያህል በእሳቤ ውስጥ ሆነህ ብትመጣ ግራ የሚሆኑ ይገጥሙሃል::
ከሞገደኛው ጋር ሞገደኛ ልሁን ብለህ ካሰብክ በየፌርማታው ስትጨቃጨቅ እና ስትነታረክ የውሎህን ውጤታማነት በድምሩም የህይወት ዘመንህን የምታበላሽ ትሆናለህ:: ስለሆነም እንዴት የሚለውን ለመመለስ ማሰብ ያስፈልጋል ማለት ነው::ሞገደኛ ሰዎች መንገድ ላይ ብቻ ናቸው ያሉት ብሎ ማሰብ ደግሞ ፈጽሞ ስህተት ይሆናል::
ሞገደኛ ሰዎች በሁሉም ቦታ ሊገኙ ይችላሉ:: በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በገብያ፣ በቤተክርስቲያን በአጭሩ በሁሉም ቦታ:: ጥያቄው በሞገደኝነት የሚገጥሙንን ሰዎችን እንዴት እናስተናግዳቸው ናቸው የሚለው ነው:: እንጋፈጣቸው ወይስ እንለፋቸው?
መጋፈጥ ወይንስ መጋጋጥ 2 – ውጤት አልባውን?
ሌላው ጥያቄ በሥራቸው ውጤት አልባ የሆኑ ሰዎችን እንዴት እንጋፈጥ የሚለውን ነው? የተሰጣቸውን ሥራ በጥራትም ሆነ በሚጠበቀው ደረጃ ውስጥ ሰርቶ የማቅረብ የሰነባበተ ችግር ያለባቸው ሰዎችን በተመለከተ የሚኖርህ አማራጭ መጋፈጥ ወይንም አብሮ በመጓዝ መጋጋጥ ይሆናል:: ሥራውን በአግባቡ መሥራት ባልቻለው ሰው ምክንያት ባለጉዳዮች ሲማረሩ ትመለከት ይሆናል::
እንዲሁም የሥራ ባልደረቦቹ ሲያማርሩ ትሰማለህ:: እንዲህ አይነት ሰዎችን ወደ መስመር ውስጥ ለማስገባት በሚደረገው ሂደት ውስጥ የማንፈልገውን ውሳኔ ለመወሰን እንገደድ ይሆናል:: ይህ ውሳኔ ወደ መጋፈጥ የሚመራን ይሆንና ስሜት የሚረብሹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ::
መፍትሔው – መጋፈጥ!
ከሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ውስጥ መጋፈጥ እና ማለፍን መለየት የምንችልበት አቅም ላይ ልንገኝ ይገባናል:: መጋፈጥ ያለብንን እና ማለፍ ያለብንን መለየት እጅግ አስፈላጊ ነው:: የምንወስደውን እርምጃ ጊዜውን ማጤንም እንዲሁ:: ሞገደኛውን አሽከርካሪ ልንጋፈጠው ብለን እንደ አመጣጡ ካስተናገድነው ውጤቱ ምን እንደሚሆን ማሰብ ጥሩ ነው::በተጨባጭ በሌሎች ስፍራዎች ለምሳሌ በሥራ ቦታ በተመሳሳይ ሁኔታ ማለፍ ውጤታማ የማያደርግበት ሁኔታም ይኖራል::
በቀላሉ ማለፍ የሚለው መልስ የሚሰራበት ቦታም እንዳለ የማይሰራበት ቦታም አለ:: ማለፍ የማይሰራበት ደረጃ ላይ ሲደርስ እንዴት መጋፈጥ እንደሚገባን ማወቅ ይኖርብናል::
ቁጣ ሁልጊዜ አስፈላጊ አይደለም፤ ነገርግን አስፈላጊ የሚሆንባቸው ጊዜዎች አሉ:: ቁጣ ሰፈር መገኘት እንደሌለብን የምናስባቸው ወቅቶች ይኖራሉ፤ የግድ መገኘት ያሉብን ወቅቶችም እንዲሁ:: በቁጣችን ፀሐይ እንዳይገባ ማድረግ እንችላለን፤ ማስወገድ ግን በፍጹም:: መጋጨት የሌለብን ወቅት አለ፤ ደግሞም ያለብን:: ለምን ?
ማንም ሰው ቢሆን ግጭትን አይፈልግም:: ነገር ግን ግጭት በሁሉም ቦታ አለ:: በፍርድ ቤት ችሎት ሆነ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት ይሁን ከጎረቤት ጋር፣ በትዳር መካከል እንዲሁም በወላጅነታችን ውስጥ ከልጆቻችን ጋር፣ የቅርብ ከምንላቸው ጓደኞቻችን ወይንም በአግባቡ አላናገረኝም ብለን ከምናስበው የሆነ ሰው ጋር::
በየትኛውም አካባቢና ሁኔታ ውስጥ ግጭት አለ፤ ሊፈጠርም ይችላል:: ግጭትን ለማስወገድ ነገሮችን ለማለስለስ የምንሄድበት መንገድ ግን ግጭትን በመሸሽ በማድበስበስ ላይ ያተኮረ መሆኑ ችግር ነው:: በእዚህም ምክንያት ማህበረሰባችን ባልተፈቱ ችግሮች ህመም ውስጥ አብሮ መኖሩን እንደቀጠለ ይገኛል::
እጅግ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ግጭት በጤናማ መንገድ በሚፈታበት ቤተሰብ ውስጥ ያድጋሉ:: አብዛኛውን ጊዜ ግን ሁኔታውን አድበስብሶ በመቅበር ወደፊት መራመድ ሆኖ ይታያል::
አለመግባባት የሚፈጥረውን ውጥረት በተጋፈጥክ ጊዜ ምን ታደርጋለህ? አንዳንዶቻችን ምናልባት ከሚከተሉት ነገሮች በአንዱ ወይንም በብዙው ራሳችንን ጥፋተኛ እናደርግ ይሆናል::በሰዎች ፊት የምንናገረው እና ከጀርባ የምናደርገው ተቃራኒ መሆን፣ ልንጠብቀው የማንችለውን ተስፋ መግባት፣ጥፋተኝነትን ወደ ሌላ ሰው ላይ ማዞር፣ ጥቃት መሰንዘር፣ሰዎችን ዝም በማለት ወይንም በማኩረፍ ማለፍ፣ በአሽሙር መናገር፣ ድጋፍ አላገኘም ብሎ ከመስጋት የሚደረግ መስጠት፣የግለሰቡን ሙሉ ስሜት ላለመጉዳት በማሰብ ግማሽ እውነትን መናገር፣ በውስጣችን “አይሆንም” እያልን በአፋችን “አዎ” ማለት፣ ነገሩን ችላ ማለት ከነገሩ መውጣት ወይንም ነገሩን መቁረጥ ወይንስ ንዴታችንን ለማብረድ ንዴታችንን የምንወጣበትን ሌላ ሦስተኛ አካል መፈለግ::
መጋፈጥ አለመግባባትን ይፈጥራል ብለን አስቦ ለነገ ማሳደር በሂደቱ ውስጥ ለውጥ እስከሌለ ድረስ ውጤቱ ከችግር ጋር መኖር ስለሚሆን መፍትሄው መጋፈጥ ይሆናል:: አንዳንዶች መጋፈጥ በማበረታታት ለውጥ እንደሚመጣ ይመክራሉ::
ይህ ጥሩ ነው:: መጋፈጥ የምንለው በሽልማትም ሆነ በሌሎች መንገዶች ለውጥ ሊመጣበት ላልቻለ የረጅም ጊዜ ተጽዕኖው ከፍተኛ ለሆነ አፈፃፀም ወይንም የባህሪ ችግር ነው:: መሸለም ወይንም ማበረታታት አዎንታዊ ስለሆነ በተቀባዩ ዘንድ የሚፈጥር አሉታዊ ግብረ-መልስ ስለማይኖር ቀላሉ ሥራ ነው:: ነገር ግን አሉታዊ የሆነን ባህሪ መጋፈጥ እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነው:: አንዳንዶች የመጠላት ወይንም የመገፋት ዕድል የሚገጥማቸው በመሆኑ ይፈሩታል:: አንዳንዶች የሚላተሙት ሰው የሚፈጥረውን ቁጣ ታሳቢ በማድረግ እጅግ ለመተጋገል ዝግጁ ሳይሆኑ ይቀራሉ::
ነገር ግን የሰውዬው ባህሪ ያልተገባ ከሆነ መጋፈጥን በመፍራት ጉዳዩን መተው አደገኛ የሆነ ውጤት እንደሚኖረው ደጋግመን ማንሳታችንን ልብ ይሏል:: በመጀመሪያው ግለሰቡ ለተቋሙ በሚጠቅም መንገድ እየተንቀሳቀሰ ስላልሆነ ተቋሙ የሚጎዳ ይሆናል::
በሁለተኛ ደረጃ ግለሰቡ ውጤታማ ካለመሆኑ የተነሳ ያንተንም ውጤታማነት የሚቀንስ ይሆናል:: በመጨረሻ ግለሰቡ ባልተገባ መስመር ውስጥ ሆኖ ዛሬ ላይ ካልተነገረው ራሱን በማስተማር መቀየር የሚችልበት ዕድል ኖሮ ሳለ ሰርቀኸዋል ማለት ነው:: አንድ ሰው ከሰዎች ጋር መጋፈጥን ችላ ብሎ ዝም በሚልበት ጊዜ ራሱን ሊጠይቅ የሚገባው ዝምታው ለራሱ ጥቅም ታስቦ ወይንስ ለትልቁ ምስል የሚለውን ነው:: ለራሱ ሲል ያደረገው ከሆነ የሚኖረው በራስ ወዳድነት የህይወት ቅኝት ውስጥ ነው ማለት ነው::
መጋፈጥ ወይንም መታገል ለሁለቱም ጥቅም በሚሆን ስሌት በሚሆንበት ጊዜ እጅግ ጠቃሚ ውጤት ይኖረዋል:: ከእዚህ በተቃራኒው ሁልጊዜ ግጭት አሸናፊ እና ተሸናፊ እንደሚፈጥር እናስብ ይሆናል:: ነገር ግን የግድ ያ ይሆናል ማለት አይደለም:: ለሁለቱም ወገን በሚጠቅም ሁኔታ የሆነ መጋፈጥ እንዲሆን በቅድሚያ ቀና የሆነ አመለካከት ሊኖረን ይገባል::
መጋፈጥን እንደ ዕድል መቁጠር በሂደቱ ሰዎች ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድቁ መርዳት እንደሆነም ማሰብ ይገባል:: ነገር ግን ስልጣንህን ለማሳየት ወይንም እንዲሁም በንዴት ውስጥ ሆነህ አትጋፈጥ:: በአክብሮት እና ሌላኛውን ሰው ጥቅም ማዕከል ባደረገ ሁኔታ አድርገው:: ለመጋፈጥ የሚረዱ አስር መመሪያዎችን ጆን ማዕክስዌል የተባሉ ጸሐፊ እንደሚከተለው ይመክራሉ::
1. መቼ እንጋፈጥ – አሁኑኑ!መጋፈጥን ባዘገየኸው ቁጥር መሥራት ያለበትን ሥራ እንዳይሠራ እየሆነ በመሆኑ የሚጎዱ እየበረከቱ ይሄዳሉ:: አሁኑኑ የመጋፈጥ አስፈላጊነት በኋላ ላይ ሊከሰት ከሚችል የበዛ ጭቅጭቅ ለመራቅ ዕድልን ይሰጣል::
2. የምንጋፈጠውን ግለሰብ እንዴት እንየው? ግለሰቡን ከስህተት ተግባሩ ለይተህ ተመልከት!ሰውዬው የሚያደርገውን ተግባር እንጂ ግለሰቡን አትጋፈጥ:: ግለሰቡን ልታበረታታው ወይንም ልታገዘው ይገባል:: ተግባሩን ግን ልትጋፈጠው ይገባል:: ይህ ማለት ግለሰቡን ከስህተት ተግባሩ ለይቶ መመልከት አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስረዳ ነው::
3. ግለሰቡ ሊቀይረው የሚችለው ነገርን ተጋፈጥአንድ ሰው ሊቀየርው የማይችለውን ነገር ለመቀየር ጥረት ብናደርግ ግለሰቡን ተስፋ እንዲቆርጥ እናደርገው ይሆናል እንጂ ለውጥ አያመጣም:: ስለሆነም ልናጋፈጥ የምንችለው ግለሰቡ ሊቀይረው ወደ ሚችለውን ነገር የሚገፋው መሆን አለበት::
4. ግለሰቡን በአዋንታዊነት ተመልከተውሁልጊዜ የሰዎች ፍላጎት ትክክል እና መልካምን ለማድረግ የሚረዳ እንደሆነ አድርገህ አስብ:: ይህ ከሆነ ነገሮችን በግልጽነት ለማየት እና መስተካከል ያለበትን አቅጣጫ ለመለየት ዕድልን ይሰጣልና ግለሰቡን በአዋንታዊነት ተመለክተው::
5. ነጥብ ተኮር ሁንአንድ ሰው ለውጥን እንዲያደርግ የምንፈልግበትን ነጥብ ለይተን በማውጣት በነጥቡ ላይ በማተኮር መጋፈጥ አስፈላጊ ነው:: በግልጽነት ነጥሮ በወጣ ነጥብ ላይ ማተኮር ካልቻልክ ሃሰተኛ የሆነ ግምትን ልትይዝ ትችላለህ:: ሃሰተኛ ግምት ላይ የተያዘ መጋፈጥ ውጤቱ ዓላማውን የሚያሳካ አይሆንምና ነጥብ ተኮር ሁን::
6. አሽሙርን አስወግድበአሽሙር መናገር የሰዎችን ተግባር ከመጋፈጥ ሰዎቹን በቀጥታ ማጥቃት ስለሚሆን ስህተት ነው:: በምትጋፈጥበት ጊዜ አሽሙርን ወይንም በዘወርዋራ መናገርን ማስቀረት አለብህ:: እውነታውን በቀጥታና በተገቢው ሁኔታ ማቅረብ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል::
7. “ሁልጊዜ” እና “በፍፁም” የመሳሰሉ ቃላትን አስወግድአንድን ሰው በፍጹም ይህን አይነት ባህሪ አታሳይ በምንልበት ጊዜ እየጠየቅነው ያለውን በሆነ ሕግ ቁጥጥር ሥር ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ነው:: ይህን ከማድረግ ጭንቅላቱን ተጠቅሞ መፍትሄን እንዲፈልግ እና ካለበት ሁኔታ እንዲወጣ መሰረታዊ መርሆች ላይ ሆኖ ማበረታታት ጥሩ ይሆናል::
8. ስህተት በተሰራው ነገር ላይ ምን እንደተሰማህ ንገረውየግለሰቡ ሁኔታ ያበሳጨህ ከሆነ ያበሳጨህ መሆኑን ወዲያውኑ መንገሩ መልካም ነው:: ሌላ ጊዜ ወደ እዚያ በመመለስ ስሜትን የሚያቃውስ ክፍተትን ከመፍጠር የተሻለ ነውና::
9. ችግሩን ማስተካከል እንዲችል ለግለሰቡ መንቀሳቀሻ ዕቅድ ስጠውሁልጊዜ የምትጋፈጠው ግለሰብ እንዲሳካለት እንጂ እንዲወድቅ ማሰብ የለብህም:: ችግሩን ለመቅረፍ ዕርዳታ/እግዛ ልታደርግለት ከተቻለህ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት ሁኔታ ይፈጠራል::
10. እንደ ግለሰብና እንደ ጓዳኝ በእውነተኛ ስሜት ቅረብግለሰቡን ለመጋፈጥ ስትነሳ ልክ እንደ ሳንዱች እንደሆነ አስብ:: የመጋፈጫው ነጥብ በሳንዱቹ ውስጥ እንዳለው ሥጋ ነው:: በሁለቱም አቅጣጫ በእውነተኛ ስሜት እና በማበረታቻ የታጀበ መሆን አለበትና በእውነተኛ ስሜት ቅረብ::
መጋፈጥ በምክንያታዊነት እና ከጉዳዩ በላይ የምንጋፈጠውን ሰውን በማስቀደም ሲሆን ውጤቱ ስሜትን ለማርካት ከሚደረግ የቃላት ጋጋት ያለፈ ይሆናል:: እንደ ግለሰብ፣ እንደ ቤተሰብ፣ እንደ ማህበረሰብ እንዲሁም እንደ ሀገር ከመጋጋጥ መጋፈጥ ያለብንን በማወቅ በአግባቡ በትልቁ ምስል ውስጥ ሆኖ መጋፈጥ ወደ ውጤት እንደሚመራን አስባለሁ:: በመጋፈጥ ምክንያት ከሣር ቅጠሉ ጋር ግጭት ውስጥ መግባት እንዳይሆን በጥንቃቄ እንዲሆን በመምከር::
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 03 /2013