አስናቀ ፀጋዬ
ሰዎች በተሰጣቸው ፀጋ፤ አልያም ከህይወት ልምዳቸው ተነስተው ወይ ደግሞ ተምረው በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ ለመሆን የየራሳቸውን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ አንዳንድ የሥራ መስኮች መማርንም እውቀትንም የሚጠይቁ ቢሆኑም ብዙ ሰዎች ግን ጥቂት እውቀት በልምድና በመሞከር ቀስመው በሞያው ውጤታማ ሲሆኑ ይታያሉ፡፡
አንዳንዴም ከተማረው ሰው የበለጠ ሥራ ሠርተው ይገኛሉ፡፡ ይህ ሲባል ግን እንዳው ሥራውን ስለሰሩ ብቻ በቅተዋል ማለት አይደለም፡፡ ሥራ ሁሌም የተሻለና ጥራት ያለው እንዲሆን ከተፈለገ የቀለም ትምህርት ሁሌም አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ ሰዎች ባለቻቸው ትንሽ እውቀት ተጠቅመው ውጤታማ ለመሆን የሚያደርጉት ጥረት አበረታች በመሆኑ ሊደነቅ ይገባል:: የዛሬው የሲራራ እንግዳችንም የዚሁ እውነታ ማሳያ ናቸው፡፡
በቀን ሠራተኝነት፣ በግንበኝነት፣ በለሳኝነትና በሌሎች ከግንባታ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ሥራዎች ሁሉ ሳይንቁና ሳይሰለቹ፣ ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ነገን በማሰብ ሰርተዋል፡፡
የትምህርት ደረጃቸው እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ የዘለቀ ቢሆንም ቀስበቀስ ራሳቸውን በማስተማርና የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን በመውሰድ ሙያቸውን አሻሽለዋል።እውቀታቸውን በልምድና በስልጠና አዳብረውም በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉ የህንፃ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ይህ ሁሉ ጥረታቸውም ዛሬ ላይ ፍሬ አፍርቶ የራሳቸውን ጠቅላላ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ ለማቋቋም በቅተዋል- የሲሳይ ገሰሰ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ገሰሰ::
አቶ ሲሳይ የተወለዱት ቢሾፍቱ ቢሆንም እድገታቸው ግን በቀድሞ የወሎ ክፍለ ሀገር ሳይንት አይባር በሚባል አካባቢ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ በተለምዶ ደምበል ኦሎምፒያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው አብዮት እርምጃ በተባለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን ከወሰዱ በኋላ ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቻውን ብዙም ሳይገፉበት አቋርጠዋል፡፡
በ2004 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተግባረዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በመንገድ ንጣፍ ሥራ ሞያ ሰልጥነው ሰርተፊኬት አግኝተዋል:: በስትራክቸራል ሥራም ስልጠና ወስደው በየካ አባዶ የጋራ መኖሪያ ቤት ሥራዎች ላይ በአንዱ ተፈትነው የኮንስትራክሽን ሞያ ቀስመዋል፡፡ በሰለጠኑበት ጥቂት የሞያ ትምህርቶችም ቀስ በቀስ የኮንስትራክሽን እውቀታቸውን እያሳደጉ መጥተዋል፡፡ በዘርፉ ያላቸውን እውቀት በየጊዜው ለማሳደግ ካላቸው ፍላጎት በመነሳትም ቀን ቀን እየሰሩ በማታው ክፍለ ጊዜ የተለያዩ ሞያ ነክ ኮርሶችን ወስደዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ሥራን ‹‹ሀ›› ብለው ከቀን ሥራ የጀመሩት አቶ ሲሳይ፤ በሂደት ቤቶችን የመለሰን፣ የመገንባት፣ የሴራሚክ ንጣፍ፣ የአናፂነት ፍሬም ዎርክና ሌሎችም ከኮንስትራክሽን ጋር የተያያዙ ሥራዎችን መሥራት ቀጠሉ:: አንዳንድ የሰሩባቸው ድርጅቶች የሥራ ልምድ ሲፅፉላቸውም የሥራ ልምዳቸውን በማስያዝ ከፍ ያሉ ስራዎችንም መስራት ቻሉ፡፡ ይህም ለኮንስትራክሽን ሥራ ያላቸው ፍቅር ይበልጥ እንዲያድግ ምክንያት ሆኗቸዋል። በሂደትም ስራቸውን በማጠናከር የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ እየለወጡ ለመምጣት ችለዋል፡፡
አቶ ሲሳይ ቀደም ሲል በማህበር ከሌሎች ሰዎች ጋር ተደራጅተው የግንባታ ስራዎችን ሲያከናውኑ የነበረ ሲሆን እርሳቸው በነበሩበት ማህበር ውስጥ ያለመግባባት በመፈጠሩና ማህበሩ የመፍረስ አደጋ ስላጋጠመው በግላቸው መስራት ጀመሩ፡፡ በግላቸው መስራት እንደጀመሩም ነገሮች እየተቀየሩ መጡ:: ዘመናዊ የኮንስትራክሽን ሥራ ደግሞ የንግድ ፍቃድ ማውጣት የግድ እንደሚስፈልግም ተረዱ፡፡
ሙሉ ሆነው ለመስራት፣ የሥራ ዕድል በስራቸው ለመፍጠርና ለሀገራቸውም በኮንስትራክሽን ዘርፉ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት በማሳብ የራሳቸውን የኮንስትራክሽን ንግድ ፍቃድ ለማውጣት ተነሳሱ፡፡ በ2011 ዓ.ም የራሳቸውን ንግድ ፍቃድ በማውጣትም የኮንስትራክሽኑን ዘርፉ ተቀላቀሉ፡
የንግድ ፍቃዳቸውን ካወጡ በኋላም ጨረታዎችን በመከታተል በልዩ ልዩ የግንባታ ስራዎች ላይ መሳተፍ ጀመሩ፡፡ ላፍቶ አካባቢ የሚገኝ አንድ የግል መኖሪያ ቤት በመስራትም እጃቸውን አሟሹ፡፡ ልደታ አካባቢም ተመሳሳይ አንድ የግል መኖሪያ ቤት ሰሩ፡፡ በአብዛኛው የሚያከናውኗቸው ስራዎች ሙሉ የግንባታ ስራዎችን ሲሆን የግልና የመንግሥት ስራዎችን ያጠቃልላል:: ለአብነትም መገናኛ አካባቢ በአንድ ትልቅ የሪል እስቴት ግንባታ ሥራ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ደምበል ጀርባ የማርካን ሪዞርት ባለቤትን መኖሪያ ቤትና ድርጅት ሰርተዋል፡፡
በተመሳሳይ ደምብል አካባቢ የሚገኘውን የአሳይ ትምህርት ቤት ተገጣጣሚ ህንፃንም ገንብተው ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡ የረር በር የሚገኘውን የጃክሮስ ኮንስትራክሽን ቤቶች ከመጀመሪያ ጀምሮ ተሳትፈዋል፡፡ ሰንሻይን ማሪዮት ሆቴል ላይም አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ስራዎች እንደአሸን እየፈሉ በመጡበት በዚህ ጊዜ ውድድሩም የዛኑ ያህል እያደገ በመምጣቱ እርሳቸውም ዘርፉ የሚጠይቀውን ሁሉ በማሟላት የደምበኞችን ፍላጎት ለማርካት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ ከእለት እለት ተፈላጊነታቸው እየጨመረ በመምጣቱ ሞራላቸው እየተገነባ ለበለጠ ሥራ መነሳሳታቸውን ይጠቁማሉ፡፡
የንግድ ፍቃድ አውጥተው የኮንስትራክሽን ስራውን ሲጀምሩ የነበራቸው መነሻ ካፒታል አንድ ሚሊዮን ብርና ስልሳ ጊዜያዊ ሠራተኛ ብቻ እንደነበር ያስታውሳሉ። በአሁኑ ወቅት የድርጅታቸው መነሻ ካፒታል እያደገ መጥቶ ስድስት ሚሊዮን ብር መጠጋቱንና አጠቃላይ ድርጅቱም እስከ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ:: ይህም በሂደት የድርጅቱን ካፒታል ይበልጥ እንደሚያሳድገው ይገልፃሉ፡፡
ድርጅታቸው እስከ ሰማንያ የሚሆኑ ሰዎችን ቀጥሮ የማሰራት አቅም እንዳለው የሚጠቅሱት አቶ ሲሳይ፤ የድርጅቱ አቅም ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር ከዚህም በላይ ቀጥሮ የማሰራት አቅም እንደሚኖረው ያምናሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ድርጅቱ በዋናነት ከእንግሊዝ ኤምባሲ አለፍ ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ ለአንድ ሸማች ማህበር ባለ ስድስት ፎቅ ቅይጥ ህንፃ በአንድ መቶ ሚሊዮን ብር እየገነባ እንደሚገኝ ይገልፃሉ፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ላይም ሌሎች ህንፃዎችን በመገንባት የማጠቃለያ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና ለግንባታ የተረከባቸው ሳይቶች እንዳሉም ይጠቅሳሉ፡፡
በቀጣይ የድርጅቱን ሁለንተናዊ አቅም ለማሳደግ ብርቱ ፍላጎት አላቸው። በተለይ፤ ለግንባታ አስፈለጊ የሆኑና እንደ ስካቫተር፣ ሚክሰር፣ ገልባጭ መኪናና የመሳሰሉ ወሳኝ የግንባታ ማሽነሪዎችን በሟሟላት የድርጅታቸውን አቅም በማሳደግ ጥራት ያላቸው የግንባታ ስራዎችን ለማከናወን ሰፊ እቅድ ሰንቀዋል:: የግንባታው ዘርፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ከመሆኑ አኳያም መንግሥት በተለይ ለግንባታ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ የሚገባበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባው ሳይጠቁሙ አላለፉም።
‹‹በአሁኑ ወቅት የኮንስትራክሽን ዘርፍ እጅግ እያደገ መጥቷል›› የሚሉት አቶ ሲሳይ፤ ስራው አስደሳች ከመሆኑ አንፃር ገንዘብ ላይ ብቻ ሳያተኩሩ ጠንክረው እየሰሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ዘርፉ በርካታ የሰው ሃይል የሚይዝ ከመሆኑ አኳያ እና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውም አስተዋፅኦ ትልቅ በመሆኑ በሞያ ሊደገፍ እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ የሞያ ዘርፉ የተሰማሩ ሰዎችም በየጊዜው እውቀታቸውን ማሻሻል እንደሚኖርባቸው ያሳስባሉ፡፡ መንግስትም በዘርፉ የተማረ የሰው ሃይል ከመፍጠር አንፃር ብዙ ሊሰራ እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
ዘርፉ አሁንም ድረስ ሰፊ የገበያ እድል ያለው በመሆኑም ብዙዎች በዚህ ዘርፍ በመሳተፍ ቢሰሩ ራሳቸውን ከመጥቀም በዘለለ በተዘዋዋሪ ሌሎችንም የመርዳት እድል እንዳለም አቶ ሲሳይ ይገልፃሉ፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ታዲያ ዘርፉ እንደው በዘፈቀደ ብቻ ተገብቶበት የሚሰራ እንዳልሆነና ከዚህ ይልቅ ዘመኑ የሚጠይቀውን የኮንስትራክሽን ልምድና ችሎታ ይዞ መገኘትና ጥረት ማድረግ እንደሚስፈልግም ያምናሉ፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚታየው አንዱ ችግር የገንዘብ መሆኑንም አቶ ሲሳይ ጠቅሰው በርካታ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች የመስራት አቅም እያላቸው በገንዘብ እጥረት ምክንያት የጀመሯቸውን ስራዎች ለማጠናቀቅ ሲቸገሩ የሚታዩ በመሆናቸው በዚህ ረገድ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ በብድር ማቅረብ እንዳለበት ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም በፍጥነት እያደገ የመጣውን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ይበልጥ ሊያሳድገው እንደሚችል ይጠቅሳሉ፡፡
የግብአት እጥረት በተለይ የሲሚንቶ መጥፋትም ሌላኛው የኮንስትራክሽን ፈተና መሆኑንም የሚናገሩት አቶ ሲሳይ፤ በግብዓት በኩል ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድም መንግስት የራሱን ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ የሲሚንቶ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመምጣቱ መንግስት የሲሚንቶ ዋጋ ንረትን ማረጋጋት እንደሚኖርበት ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርተው ያሉ ድርጅቶች ከሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ጋር ትስስር ፈጥረው የሚሰሩበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለብት ያመለክታሉ፡፡
በተማሩባቸው አነስተኛ የኮንስትራክሽን ሙያዎች በመጠቀም በኮንስትራክሽን ዘርፍ ተቀላቅለው አነሰም በዛም ህይወታቸውን መለወጥ መቻላቸውን የሚናገሩት አቶ ሲሳይ፤ሌሎችም በተመሳሳይ በዘርፉ ገብተው መስራት ለሚፈልጉ ሁሉ ህጋዊ የንግድ ፍቃድ አውጥተው በርትተው መስራት እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘርፉ የሚጠይቀውን ሁሉ እውቀትና ልምድ ማሟላት እንደሚገባቸው ያሳስባሉ፡፡
በዚህም ለሌሎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ራሳቸውንና ሀገራቸውን መለወጥ እንዲሁም ዘርፉን ከማሳደግ አኳያም የድርሻቸውን መወጣት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡ ዘርፉ ገና ብዙ ያለተሰራበት ከመሆኑ አንፃርም ተስፋ ሳይቆርጡ ብዙ ሰርተው ብዙ ሊያተርፉበት እንደሚችሉም ጠቅሰዋል፡፡
ጠንካራ ሠራተኛ፤ ታታሪና ነገን አላሚ ናቸው።በቀለም ትምህርት ብዙ ባይገፉም ለኮንስትራክሽን ሥራ የተሰጡ ስለመሆናቸው ሁሉ ነገራቸው ይመሰክራል። ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉና ሥራን ሳይመርጡ ከቀን ሠራተኝነት ተነስተው ሁሉንም የኮንስትራክሽን ስራዎች ሞካክረዋል። ሞያቸውን በልምድና በስልጠና አሳድገው የራሳቸውን የኮንስትራክሽን ድርጅት ለማቋቋም በቅተዋል። በግል ጥረታቸውም ገቢያቸውን በማሳደግ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰባቸውን፣ ቀጥረው የሚያሠሯቸውን ሠራተኞቻቸውንና ሀገራቸውን በሞያቸው ማገልገል ችለዋል፡፡
እኛም አቶ ሲሳይ ገሰሰ በግል ጥረታቸው ራሳቸውን ለመለወጥ እያደረጉ ያሉትን ጥረት እያደነቅን በተመሳሳይ ሌሎችም አልተማርኩም በሚል በውስጣቸው ያለውን የሥራ ፍላጎት አምቀው ከመያዝ በማውጣትና የእርሳቸውን አርአያነት በመከተል ታታሪ ሠራተኛ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ሌሎችንም መጥቀም ይችላሉ የዕለቱ መልክታችን ነው፡፡ ሰላም!
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 03 /2013