መልካምስራ አፈወርቅ
ቅድመ –ታሪክ
ጥንዶቹ በርካታ ዓመታትን በቆጠሩበት ትዳር ክፉን ከደግ አይተዋል፤ ልጆች ወልደው የልጅ ልጆች አፍርተዋል፤ ንብረት ይዘው ሀብት ገንዘብ ቆጥረዋል:: እነዚህ ዓመታት ለባልና ሚስቱ ቁጥሮች ብቻ አልነበሩም:: ትዳራቸውን ለማፅናት እድሜያቸውን ከጉልበታቸው፣ ጊዚያቸውን ከጤናቸው ገብረዋል:: ቤታቸውን ለማቆምና ልጆችን ከወጉ ለማድረስ የበዛ ዋጋን ከፍለዋል::
ቄስ ወርቁ ዳዲሞስና ወይዘሮ ማሚቴ ወፈራ፣ በትዳር በቆዩባቸው ስልሳ ዓመታት አስራ አንድ ልጆችን አፍርተዋል:: ከእነዚህ ልጆቻቸው የተገኙ ፍሬዎች የደስታ ምንጮች ሆነዋቸው ዓመታትን አሻግረዋቸዋል::
ባልና ሚስቱ ከወለዷቸው አስራ አንድ ልጆች መሐል አንደኛዋ ኑሮዋን ከባህር ማዶ አድርጋለች:: የምትኖርበት አገረ አውስትራሊያም የዜግነት ስጦታ አበርክታላት ህይወቷን በስፍራው ካደረገች ዓመታት ተቆጥረዋል::
ወይዘሮ ሰብለ ኑሮዋ በአውስትራሊያ ቢሆንም ሁሌም አገሯን ታስባለች:: ወደ ትወልድ ስፍረዋም አንድ ቀን መመለስን ትሻለች:: ይህ ይሆን ዘንድም በሰው አገር ከምታገኘው ገንዘብ እየቆጠበች ወደ አገር ቤት ትልካለች:: ሀዋሳ ከተማ የሚገኙ ቤተሰቦቿም ወይዘሮዋ የምትልከውን ገንዘብ እየተቀበሉ ያኖራሉ::
አዲስ ሃሳብ
ከጊዜ በኋላ ወይዘሮ ሰብለ አገሯ መግቢያ የሚሆናትን ጎጆ መቀለስ ፍላጎቷ ሆነ:: ይህን ሀሳቧን ያጋራቻቸው ቤተሰቦቿም የልቧ ይሞላ ዘንድ ከጎኗ ሊሆኑ ቃል ገቡ:: የምትልከውን ብር እየተቀበሉና የምትፈልገውን እያሟሉ ለጎኗ ማረፊያ ያሰበቸውን ቤት ሊገዙ ፍለጋ ጀመሩ::
በዚህም እናትና አባቷ በስማቸው ቤት ለመግዛት ማሰባቸውን ነግረዋታል:: እሷም በሀሳቡ ተስማምታለች:: ከጊዚያት በኋላ በውጣ ውረድ የሚገዙ ቤቶች ታሰሱ:: ተፈለጉ:: ዓይን የወደቀበት ሲገኝ እንከን እየተፈለገ፣ ዋጋ ከፍና ዝቅ ሲደረግ ቆየ:: ፍለጋው ተጠናቆ የታሰበው እንደተገኘ ወይዘሮዋ ካለችበት ወደ አገር ቤት ተመልሳ ቤቱን አየች:: ቤቱ ብዙ ነገር የሚጎድለው ቢሆንም፣ በደንብ ከታደሰና ከተሰራ ግን ማለፊያ ቤት ይሆናል::
ሰብለ የቤቱን ይዘት አስተውላ ብዙ አሰበች:: አዎ! ቤቱን በተሻለ ቁመና ለማየት በርከት ያለ ገንዘብ ያስፈልጋል:: የወደፊቱን መልካምነት የምታልመው ወይዘሮ መልሳ መላልሳ አሰበች:: የሚፈለግባት ወጪ ቀላል አይደለም:: ጥቃቅኖቹን ጨምሮ ጫን ያለ አቅምን ይጠይቃል:: መጠኑ ቢከብዳትም ዓይኗን አላሸችም::
እናት አባት ቤቱን በሃላፊነት ቆመው አሰሩ:: ልጅም እየተመላለሰች የሚያስፈልገውን አሟላች:: ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ አውጥታም የትናንት ህልሟን አሰውባና አሳምራ ፈፀመች::
አሁን የሚቀራት ቢኖር ሙሉ ሰነዱንና ማረጋገጫ ካርታውን መረከብ ይሆናል:: ቤቱን ከነሙሉ ቁመናው ቤት ለማድረግ የሚፈለጉ መረጃዎች ሊሟሉለት ይገባል:: ግንባታውን ህጋዊ ለማድረግም ይህ ይሆን ዘንድ ግድ ይላል::
ጥያቄ አንድ
ወይዘሮ ሰብለ ከውጭ ወደ አገርቤት በነበራት ምልልስ የቤቱን ለውጥና ዕድገት አስተውላለች:: ግንባታው ከነበረበት ተነስቶ አሁን አለበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ተለፍቶበታል:: ወደፊት ቢኖሩበትና ቢሸጡት አዋጭነቱ ታላቅ ነው::
ሰብለ ቤቱንና አስፈላጊ ሰነዶቹን ለመቀበል ከወላጆቿ ጋር ውይይት ይዛለች:: ከዛሬ ነገ በእጄ ይገባል ያለቸው መረጃ መዘግየቱ ቢገባት ወላጆቿ ያስረክቧት ዘንድ ጥያቄዋን ቀጠለች:: የታሰበው አልሆነም:: እንደዋዛ በቆይታ የቀጠለው ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ጊዚያት ተቆጠሩ::
አሁንም ወይዘሮዋ ውትወታዋን ቀጠለች:: ገንዘብ አውጥታ የሰራቸውን ቤት ሙሉ ሰነድ ይሰጧት ዘንድ ተማፀነች:: ጥያቄዋን የሰሙ ወላጆች እሺ እምቢ ሳይሏት ጊዚያት ነጉዱ:: ዝምታቸው ሲበዛባት በሽምግልና ያስጠየቀችው ወይዘሮ በዚህም ሀሳቧ አልሰመረም:: ውሎ አድሮ በልጅና በወላጆች መሀል ቅያሜ ተጫረ:: እልህና ንዴት የበዛበት ንግግር ሰላም አላወረደም::
ክስ…
ለጥያቄዋ ምላሽ ያላገኘችው ልጅ የመጨረሻ ባለችው አማራጭ ለመግፋት መንገድ ጀምራለች:: እናት አባቷን በሕግ ለመጠየቅ ክስ ያሰበችው ሰብለ ‹‹አሉኝ›› የምታላቸውን ማስረጃዎች አሟልታ ‹‹ቤቴና ተያያዥ ሰነዶቹ ይሰጡኝ›› ስትል ሙግት ይዛለች::
በፍርድ ቤት ውሎ እናት አባቷን በሕግ የጠየቀችው ወይዘሮ በደቡብ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርባ አቤቱታዋን አሰማች:: ፍርድ ቤቱ የአቤት ባይዋን ጥያቄ ከሥሩ መርምሮ ወላጆቿን ጠርቶ ጠየቀ:: በወቅቱ ወላጅ እናት ቤቱ የልጃቸው ስለመሆኑ አልካዱም:: አባት ግን የልጃቸውንና የባለቤታቸውን ሀሳብ በጽኑ ተቃውመው ተከራከሩ::
ቄስ ወርቁ ቤቱ ከባለቤታቸው ጋር ለዓመታት የኖሩበትና በጋራ ያፈሩት ንብረታቸው ስለመሆኑ ተናገሩ:: ምንም እንኳን ንብረቱ በባለቤታቸው ስም ቢመዘገብም ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ አውጥተውና አሻሽለው የሰሩት ስለመሆኑና አሁንም አከራይተውት እንደሚገኝ መረጃ ጠቅሰው አስረዱ::
የመጀመሪያ ውሳኔ
ፍርድቤቱ የግራ ቀኙን ሀሳብና ክርክር ካደመጠ በኋላ ለውሳኔው ቀጠሮ ሰጥቶ ቤተሰቡን አሰናበተ:: በተባለው ቀን ተጠሪዎችንና አመልካችን አቅርቦም በሕግ አግባብ ይሆናል ያለውን ውሳኔ አሳለፈ:: በዚህም መሰረት ንብረትነቱ የወይዘሮ ሰብለወንጌል ወርቄ መሆኑንና ይህም ተፈፃሚ ይሆን ዘንድ ተጠሪዎች ግዴታቸውን እንዲከውኑ ሲል አስታወቀ::
በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኙት ወላጅ አባት ሕጉ ተፈፃሚ እንዲሆን አልፈቀዱም:: እንደተባሉትም ቤቱንና ሰነዱን ለልጃቸው ለማስረከብ አልወደዱም:: ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ‹‹ይግባኝ›› አቅርበው ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይላቸው ‹‹አቤት›› አሉ::
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀደምሲል በሥር ፍርድ ቤቶቹ የተላለፈውን ውሳኔ መመርምር ያዘ:: የቤተሰቡንና የቤቱን የይገባኛል ጥያቄ በማጥናት ጉዳዩን ከስሩ ለማወቅ ሞከረ:: ፍርድ ቤቶቹ ቤቱ ለወይዘሮ ሰብለወርቅ ‹‹ይገባል›› ሲሉ መወሰናቸው ስህተት ያለመሆኑንም አረጋገጠ:: ይህ ምላሽ የደረሳቸው አባት አሁንም ውሳኔውን በይሁንታ አልተቀበሉም:: ወደሰበር ሰሚ ችሎት ቀርበው ጉዳዩ ዳግም እንዲታይላቸው አቤት አሉ::
የዚሁ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ተጠሪዋ የውጭ አገር ዜጋ መሆናቸውን በማወቁ ጉዳዩ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚዳኝ ነው በሚል ሳይመለከተው ቀረ::
አመልካች የሰበር አቤቱታውን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቀረቡ:: ሰበር ችሎቱ ቤቱ የተሰራው በልጅቷ አንጡራ ሀብትና ገንዘብ መሆኑን በሥር ፍርድ ቤቶቹ መረጃ አረጋግጫለሁ ሲል ምላሽ ሰጠ::
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በፍትሐብሔር ቁጥር 1195 መሰረት የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ያለው ሰው የቤቱ ባለቤት ሊሆን እንደሚችል ግምት ቢወስድም ግምቱ በማንኛውም ማስረጃ ሊስተባበል እንደሚችል የሚታመንበት በመሆኑ የስር ፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ የሕግ ስህተት እንዳልተፈፀመበት አስታወቀ::
እናም፣ ቄስ ወርቁ ዳዲሞስ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ያቀረቡት የአቤቱታ ክስ ተሰሚነት አላገኘም:: ከባለቤታቸው ጋር ያፈሩት ንብረት በጋራ ሀብትነት ቢመዘገብም ልጃቸው ቤቱን ለመገንባት ሙሉ ለሙሉ ያወጣቸው ገንዘብና ያፈሰሰቸው ሀብት የቤት ባለቤትነት መብትን እንዳማያሳጣት ተነግሯቸዋል::
አባወራው ተስፋ አልቆረጡም:: ራሳቸው፣ ባለቤታቸውና፣ አስራ አንድ ልጆቻቸው በቤቱ መብት አላቸው እያሉ ነው:: ምንም እንኳን እስካሁን የተጓዙበት የሕግ መንገድ ባያዋጣም ‹‹ይብቃኝ›› ሲሉ አልተቀመጡም::
አዲስ ማመልከቻ
ቄስ ወርቄ አሁን የመጨረሻ ባሉት አማራጭ ለመንቀሳቀስ ጉዞ ጀምረዋል:: በዚህ አማራጭ ተገቢ ፍትህና የሕግ ውሳኔ እንደሚያገኙ ወስነውም ማመልከቻ አስገብተዋል:: አባወራው የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት በተጻፈ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄና አቤቱታ ቅሬታቸውን በጽሁፍ አቀረቡ::
ግለሰቡ ለጉባኤው ባቀረቡት ጥያቄ የደቡብ ክልልና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በእሳቸው ያሳለፉት ውሳኔ ተገቢ አለመሆኑን ይገልፃል:: ውሳኔው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 የተረጋገጠላቸውን የንብረት ባለቤትነት መብት ዋጋ የሚያሳጣ በመሆኑም ትርጉም እንዲሰጣቸው ለአጣሪ ጉባኤው አቤቱታቸውን አቀረቡ::
የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የቀረበለት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሁኔታውን ማጣራት ያዘ:: መኖሪያው በቄስ ወርቁ ዳዲሞስ ባለቤት በወይዘሮ ማሚቴ ወፈራ ስም የተመዘገበ እንደመሆኑ ንብረትነቱ የጥንዶቹ የጋራ ንብረት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን አውነታ መመርመር ጀመረ::
በሌላ በኩል ደግሞ የንብረት ስያሜው በባልና ሚስቱ ቢሆንም ቤቱ የተገነባውና የተሻሻለው በልጅቷ በወይዘሮ ሰብለ ወንጌል ገንዘብ በመሆኑ የሀብት ባለቤትነቱ ለአባወራው አይገባም ሲባል የቆየበትን ሀሳብ ሲያጠና ቆየ::
የክልሉ የቤተሰብ ሕግ አዋጅ እንደሚጠቁመው በአንደኛው ተጋቢ ስም ተመዝግቦ የሚገኝ ንብረት የግል ስለመሆኑ በሕጉ አግባብ ካልተመዘገበ በቀር የጋራ ይሆናል የሚል የሕግ ግምት ያስቀመጠበት ምክንያት ሕገ መንግሥታዊ ከለላን ለማጠናከር መሆኑ ታምኖበታል::
የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለውሳኔው መሰረት ያደረገው የወይዘሮ ሰብለ ወንጌል ምስክሮች ቤቱ የተገዛው በእሳቸው ገንዘብ ነው የሚለውን ሀሳብ በመያዝ ነው:: ይሁን እንጂ ምስክሮቹ የህሊና ግምት ማስተባበል ያለማስተባበላቸውን ሳይመረምር ሕግ መተላለፉ አግባብ አለመሆኑን አረጋግጧል::
የፍርድ ቤቶቹን ውሳኔ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 34/3/ ላይ ለቤተሰብ ከሰጠው ከለላና ከአመልካች ሕገ መንግሥታዊ የንብረት መብት አኳያ መመርመር አግባብ ሊሆን እንደሚገባ ታምኖበታል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞም ቤተሰብ የህብረተሰብ የተፈጥሮ መሰረታዊ መነሻ ስለመሆኑ ከግምት ገብቷል::
ይህ አከራካሪ ቤት የተገዛው ወይዘሮዋ ከአውስትራሊያ በላኩት ገንዘብ መሆኑ ይታወቃል:: ይሁን እንጂ ገንዘቡ እንደስጦታ ከመቆጠር የዘለለ የወላጅ እናትንና የትዳር አጋራቸውን የባለቤትነት መብት የሚያሳጣ ሊሆን አይገባም::
ውሳኔው በጋብቻ ውስጥ የተፈራን የጋራ ንብረት ለማሸሸ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑና በሕግ እውቅናና ከለላ የተሰጠውን ቤተሰብ የሚጎዳ ስለሆነ በቤተሰብ ሕጉ ላይ የተቀመጠውን ሕግ የሚጋፋ ይሆናል:: ከዚህም ጋር ተያይዞ የአንደኛው የግል ንብረት የሦስተኛ ወገን የሚሆንበትን አግባብ ሊያመቻች አይገባም፡፡
ውሳኔ
ምክር ቤቱ የአጣሪ ጉባኤውን የውሳኔ ሀሳብ ሲመረምር ቆይቷል፡፡ የሕገ መንግሥቱን ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብም ፈትሿል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቶቹ እስካሁን ያሳለፉት ውሳኔ የግለሰቡን ሕገ መንግሥታዊ የንብረት ማግኘት መብትን የሚጥስ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ በውሳኔውም በተለያዩ ደረጃ ያሉ ፍርድ ቤቶችና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያስተላለፉት ፍርድ ተፈፃሚ ሊሆን አይገባውም ሲል ብይኑን ሰጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 03 /2013