ለአንድ አገር የኢኮኖሚ እድገት የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ መኖር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲኖር የሚፈለገው የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እውን እንዲሆን በዛ አገር ያለው የዋጋ ግሽበት ላይ ያለው መረጋጋት፣ የሥራ አጥነት ቁጥር መቀነስ፣ በቂ የውጭ ምንዛሬ መኖርና መሰል ጉዳዮች ማክሮ ኢኮኖሚው የተረጋጋ ለመሆን ወይም አለመሆኑ ማሳያዎች መሆናቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር አሰፋ አድማሴ ይናገራሉ፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያና የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱም ይሄንኑ ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በአንድ አገር የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ አለ ከሚያስብሉ በርካታ መለኪያዎች መካከል የመንግስት የበጀት ጉድለት መጠን ማነስ፣ የታክስ አሰባሰብና ሌሎች ነገሮችም የሚነሱ ቢሆንም፤ በዋናነት የሚጠቀሱት የዋጋ ግሽበትና የገንዘብ ምንዛሬ ወይም የመግዛት አቅም ናቸው፡፡ አንዳንድ ዓለማቀፍ ኢኮኖሚስቶች የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ በተለይ በፍጥነት በማደግ ያሉ አገሮች የዋጋ ግሽበት ለአጭር ጊዜ ሁለት አሃዝ ውስጥ ቢገባ በዘጠኝና አስር በመቶ የሚያድግ ኢኮኖሚ ካላቸው ብዙ አያሳስብም ይላሉ፡፡ ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከሁለት አሃዝ በታች መሆን አለበት ይላሉ፡፡
በዚህ ረገድ ታዲያ የተለያየ የኢኮኖሚ አረዳድ ቢኖርም፤ በንድፈ ሃሳባዊም ሆነ በተግባር ካለው ተጨባጭ ሁኔታ መረዳት የሚቻለው እንደ ኢትዮጵያ አይነት በፍጥነት እያደጉ ያሉ አገሮች የዋጋ ግሽበቱ ሁለት አሃዝ ውስጥ ገብቶ እንዳይቆይና የኢኮኖሚ እድገቱን ፍጥነት እንዳይገታ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ መለኪያ የውጭ ምንዛሬ ወይም የገንዘብ የመግዛት አቅም ሲሆን፤ በአንድ አገር የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ መኖር ለባለሃብቶች መተማመንን ይሰጣል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የበጀት ጉድለት፣ የወጪና ገቢ ልዩነትና ሌሎችም ጉዳዮች በማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋትና በባለሃብቱም መተማመን ላይ የራሳቸውን ተጽዕኖ ያሳርፋሉ፡፡
እንደ አቶ ዘመዴነህ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት አስርና አስራ ሁለት አመታት የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት የሚያወጡት መረጃ መሰረት እንኳን በአፍሪካ ውስጥ ፈጣን የሚባለው ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን የዋጋ ግሽበት ሂደቱ ከታየ ለአጭር ጊዜ ከሁለት አሃዝ በታች ወደ ሰባትና ስድስት ይወርድ እና መልሶ ሁለት አሃዝ ውስጥ ይገባል፡፡ ወደ አስራ ሁለትና አስራ ሶስት ይደርሳል፤ ባለፉት ጥቂት ወራት እንደታየውም እስከ 15 ደርሶ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ ደግሞ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሲኖር ዝቅተኛ ገቢ በተለይ መንቀሳቀስና መጨመር የማይችል ቋሚ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ተጽዕኖ ስለሚያመጣ ነው መጠንቀቅ የሚያስፈ ልገው፡፡
በኢትዮጵያ ደግሞ በዋናነት የዋጋ ግሽበት መነሻ የሚሆነው ነዳጅ ነው፤ ቀደም ሲል ነዳጅ እስከ 150 ዶላር በደረሰበት ወቅት የዋጋ ግሽበቱ ቢታይ አያስገርም ይሆናል፤ አሁን ግን ከ50 እስከ 60 ዶላር ባለው ውስጥ ሆኖ ይሄን ያክል መሄድ የለበትም፡፡ በሁለት አሃዝ የሚገለጽ የዋጋ ግሽበት የሚታይባቸው አገራት ጥቂት ናቸው፡፡ እነርሱም የሚያድጉ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ግን በፈጣን እድገት ውስጥ እንደመሆኗ የእድገቷን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የዋጋ ግሽበት ጉዳዮቿን በቋሚነት መፍታት አለባት፡፡
አቶ ዘመዴነህ እንደሚሉት፤ የገንዘብ የመግዛት አቅምን በተመለከተ የኢትዮጵያን ብር ከዶላር ጋር ያለው ሂደት ሲታይ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ተመን በብሔራዊ ባንክ አማካኝነት ነው የሚወሰነው፡፡ በብዙ አገሮች ግን የውጭ ምንዛሬ ዋጋን ገበያው ራሱ ነው የሚወስነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ገበያው ሳይሆን ብሔራዊ ባንክ ወስኖ በዛ መሰረት ባንኮች በነጻነት የመግዣና መሸጫ ዋጋቸውን ይቆርጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ባለሃብቶች መተማመን የሚፈጥሩበት አንዱ መስክ ይህ እንደመሆኑ አሁንም ቢሆን የውጭ ምንዛሬ ተመን/ዋጋ የተረጋጋ መሆን ይኖርበታል፡፡
ዶክተር አሰፋም ይሄን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ ሆኖም እርሳቸው እንደሚሉት፤ አሁን ባለንበት ሁኔታ ምንም የተረጋጋ ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም የዋጋ ግሽበቱ ከወር ወርና ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው፤ የሥራ አጥ ቁጥሩ በጣም ከፍተኛ ነው፤ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለ፤ የወጪ ንግዱ እያደገ አይደለም፤ አገሪቱም ከፍተኛ የሆነ የውጪ የብድር ጫናም አለባት፡፡ እናም እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ላለመኖሩ አመልካቾች በመሆናቸው የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ በአገሪቱ አለ ብሎ ለመደምደም ያስቸግራል፡፡
እንደ ዶክተር አሰፋ ገለጻ፤ በአንድ አገር ሰላምና መረጋጋት ከሌለ የኢኮኖሚ እድገትም ሆነ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ሊታሰብ አይችልም፡፡ አሁን አገሪቱ ውስጥ በተለይ በፖለቲካው መስክ ከፍተኛ አለመረጋጋትና አለመተማመን ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ባለፈም በበርካታ ቦታዎች ግጭቶች አሉ፡፡ እነዚህ ግጭቶች ደግሞ በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ሳይሻሻሉ ማክሮ ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ ማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰላም ሲጠፋ ኢኮኖሚው አይረጋጋም፤ እናም የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ሲኖር፣ እቃዎች ከቦታ ቦታ በበቂ ሁኔታ መዘዋወር ሳይችሉ ሲቀሩ፣ ሰዎች ባለው ስርዓት ላይ መተማመን ሲያንሳቸው፣ የእቃዎችና የሸቀጦች ዋጋ የመጨመር አዝማሚያው ይቀጥላል፡፡ ኢንቨስተሮችም ባለው ሁኔታ ተጠቅመው ፋብሪካ መክፈት ካልቻሉ የሥራ እድል መፍጠር ስለማይቻል የስራ አጥነት ቁጥር ይጨምራል፡፡ እነዚህ ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚው የተረጋጋ እንዳይሆን ጉልህ ድርሻ ያበረክታሉ፡፡
በመሆኑም የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ወደተረጋጋ ሁኔታ እንዲመጣ ከተፈለገ፤ የመጀመሪያው ነገር የፖለቲካ መረጋጋት እንዲኖር ማድረግና ሰላምን መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ኢኮኖሚው በምን አቅጣጫ መመራት አለበት፣ ምን አይነት የፖሊሲ ግብዓት ያስፈልገዋል፣ ምን አይነት የማትጊያና የማንቂያ ግብዓቶች ያስፈልጋሉ፣ ምን መካሄድ አለበት በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ በጥናት ታግዞ ውይይት ማድረግና መስራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት ሁሉንም ነገር ይሰራል ተብሎ መተው የለበትም፡፡ ከመንግስት የሚጠበቀው አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ሲሆን፤ ይሄን ተጠቅሞ ምላሽ መስጠት የግል ዘርፉና የሌሎች አካላት ድርሻ ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ በአገሪቱ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር ከማድረግ አኳያ ሚና ያለው እንደመሆኑም፤ መንግስት አቅጣጫ ሲያሳይ ህብረተሰቡ፣ ባለሃብቱና ሌሎችም አካላት የሚጠበቅባቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
አቶ ዘመዴነህ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የዋጋ ግሽበት መውጣትና መውረድ ወደ አንድ አሃዝ ማውረድ ብቻ ሳይሆን የአንድ አሃዝ ቆይታውንም ቀጣይ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣኑ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗ መልካም ቢሆንም በፍጥነት ላይ ያለ ኢኮኖሚ በእንደዚህ አይነት የዋጋ ግሽበት መዋዠቅና በሁለት አሃዝ ውስጥ መቆየት የለበትም፡፡ በተመሳሳይ አሁን ላይ የውጭ ባለሃብቶች በብዛት ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው፡፡ ኢንቨስት የሚያደርጉት ደግሞ በዶላር እንደመሆኑም የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ወደፊት ምን ይመስላል ብለው ያሰላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለኢንቨስትመንት ስራቸው ከግምት ከሚያስገቧቸው ነገሮች አንዱ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ መሆኑን አመላካች እንደመሆኑ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ተመን ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ይሁን እንጂ ቻይናን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ተወዳዳሪ ለመሆን ሲሉ የገንዘብ ምንዛሬያቸውን እንደ ስትራቴጂ የሚጠቀሙበት ጊዜ አለ፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ የገንዘብ ምንዛሬዋን እንዴት በስትራቴጂ መጠቀም ይገባታል የሚለው በትኩረት መታየት እንዳለበት ያመላክታል፡፡
ለምሳሌ ባለፈው ዓመት የ15 በመቶ የምንዛሬ ማሻሻያ ሲደረግ ዓላማው የነበረው ገቢ ምርትን ለመቀነስና ወጪ ምርትን ለማበረታታት ነው፡፡ ይሄን ብዙ አገሮች ይጠቀሙበታል፡፡ ነገር ግን በደንብ እንዲሰራና ዓላማውን እንዲያሳካ ብዙ መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ፡፡ ምክንያቱም ከውጭ የሚገባውን ምርት መቀነስ ካስፈለገ ያንን የሚተካ ምርት ለማግኘት አገር ውስጥ ምርታማነትን ማስፋፋት ያስፈልጋል፤ ካልሆነ እጥረት ይከሰታል፡፡ የምርት እጥረት ሲከሰት ደግሞ የዋጋ ግሽበት ይከተላል፡፡
በተመሳሳይ ወጪ ምርትን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን እሴት የተጨመረበትን ምርት ለገበያ ማቅረብን ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ጥሬ እቃ የሚላክ ከሆነ ለኢትዮጵያ ብዙም የውጭ ምንዛሬ አያመጣም፤ ለምሳሌ፣ የቡና ዋጋ በኒዎርክ ገበያ ስለሚወሰን ኢትዮጵያ ምንም ማድረግ አትችልም፡፡ እናም እሴት የተጨመረበት ምርት መላክ ላይ አተኩሮ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ የገንዘብ ዋጋ ሲከለስ ጥቅምና ጉዳቱ ታይቶ ነው መከናወን የሚኖርበት፡፡
በመሆኑም የዋጋ ግሽበቱን እንዳይዋዥቅና በቋሚነት የተረጋጋ ማድረግ ይገባል፤ የገንዘብ ተመኑንም ጥቅምና ጉዳቱን ባገናዘበ መልኩ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከፖሊሲ ለውጦች ጀምሮ አስፈላጊ የሆኑ ስራዎች መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ሲሆን ነው ባለሃብቱም እምነት የሚኖረው፤ ማክሮ ኢኮኖሚውም አስተማማኝ መረጋጋት የሚያሳየው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት ብቻ ሳይሆን ባለሃብቱም ምርታማነቱን ማሳደግ ኖርበታል፤ ሁሉም ባለድርሻ የሚጠበቅበትን መወጣት አለበት፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን አሁንም ለዋጋ ግሽበት ትልቅ ድርሻ ያለው የጅምላ አከፋፋይነትና የቸርቻሪነት ሞኖፖሊን መፈተሽ ያስፈልጋል፤ ዘመናዊነትን ማላበስም ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 20/2011
ወንድወሰን ሽመልስ