ሶሎሞን በየነ
ማንኛውም ሰው የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ሕዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግሥትን፣ የውጭ አገር መንግሥትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ በሰው አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፤ የሰውን ሕይወት ለአደጋ ያጋለጠ፤ ሰውን ያገተ ወይም የጠለፈ፤ በንብረት፣ በተፈጥሮ ሐብት ወይም አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፤ ወይም የሕዝብ ወይም ማህበራዊ አገልግሎት እንዳይሰጥ በከፍተኛ ሁኔታ ያስተጓጎለ እንደሆነ ከአስር ዓመት እስከ አስራ ስምንት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ የተሻሻለው የጸረ ሽብር አዋጅ ይደነግጋል።
የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ተሾመ ወ/ሐዋርያት በበኩላቸው ሽብርተኝነት ዓለም፣ አገር፣ ክልል አቀፍ ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ ሽብርተኝነት አንድ ቡድን ወይም ግለሰብ የራሱን አስተሳሰብ፣ ፍላጎት፣ ዓላማ፣ ዕቅድ በኃይል ወይም በጉልበት ለማስፈጸም መጣር፣ መዘጋጀትና አስገድዶ ማስፈጸም ማለት ነው።
ሽብርተኝነት ከግለሰብ ተበዳይነት ያለፈ በብዙኃን መብትና ጥቅም ላይ ያነጣጠረ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ ሽብርተኝነት በቡድን፣ በብዙኃን፣ በሕዝብና በአገር መብትና ጥቅም እንዲሁም ሉዓላዊነት ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ አንድ ድርጅት ወይም ግለሰብ የራሱን ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ርዕዮተ ዓለም በኃይል ወይም በጉልበት ለማስፈጸም፤ እንዲሁም የኔ እምነት የኔ ዓላማ ተግባራዊ ይሁን ብሎ በሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት፣ በመንግስታዊ መዋቅር፣ በሕገ መንግስት ስርዓት፣ በአገር ሉዓላዊነት፣ ላይ በአገርና በሕዝብ አንድነት ላይ ወንጀል ለመፈጸም መዛት፣ ማሰብና መፈጸም ሽብርተኛ የሚያስብል ሲሆን፤ ይህን መሰል ድርጊት የፈጸሙ ድርጅቶችን ወይም ግለሰቦችን መጀመሪያ ድርጊቱን መፈጸማቸውን ማረጋገጥና ድርጊቱን ፈጽመው ከተገኙ በሕግ መሰረት ሽብርተኛ ብሎ ፈርጆ ማዕቀብ መጣል እንደሚያስፈልግ አቶ ተሾመ ተናግረዋል።
ህ.ወ.ሓ.ት ገና በጥዋት ወደ ስልጣን ሲመጣ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በአሜሪካ የሽብርተኝነት መዝገብ ላይ ስሙ በሽብርተኝነት የሰፈረና እስካሁንም በዝርዝሩ ሰፍሮ የሚገኝ እንደሆነ ገልጸው፤ ህ.ወ.ሓ.ት ወይም ጁንታው ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ሽብርተኛ ተብሎ የሚያስፈርጁ ቁጥር ስፍር የሌላቸው የሽብር ወንጀሎችን መፈጸሙን ይናገራሉ።
ጁንታው በአገሪቱ ከመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ወዲህ እንኳን ከትግራይ ክልል በስተቀር በመላው የኢትዮጵያ ክፍል 113 ግጭቶችን በማቀነባበር በግለሰብና በቡድን መብት፣ በሰዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት፣ በሃይማኖት፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችና የወንጀል ውጤቶችን በአጠቃላይ ከጀርባ ሆኖ ሲያስተባብር ሲመራ ድጋፍ ሲያደርግ በሚዲያዎቹ ሲያስተዋውቅ እንደነበር ተናግረዋል።
የዛሬ ወር ደግሞ የሃገር ሉዓላዊነት መገለጫ፣ የአገሪቱ አንድነት ተምሳሌት ወይም ደግሞ የአገሪቱ የብሔራዊ ጥቅሟ ህልውና ማስከበሪያ ተቋም የሆነውን መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አውስተው፤ በዚህ አረመኔያዊ ተግባሩም ከሰብዓዊነት ባፈነገጠ ሁኔታ በአገር መከላከያ አባላትና ተቋሞቹ ላይ አረመኔያዊ ጥቃት ፈጽሟል። ይህም በአገር አንድነትና ሉዓላዊነት የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ተሾመ ጁንታው ለውጡ ከመጣ በኋላ በመቐለ መሽጎ ለውጡን ከማደናቀፍ ባሻገር የአገሪቱ አንድ ክልል የሆነችውን የትግራይ ክልልን ከፌዴሬሽኑ ለመገንጠል ቀን ከሌሊት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ ይህም የአገሪቱ አንድ ክልል የሆነችውን የትግራይ ክልልን አቅዶበት ሆን ብሎ ከፌዴሬሽኑ ለመገንጠል ሲያደርገው የነበረው እንቅስቃሴ የአገር ክህደት መሆኑን ተናግረዋል።
ጁንታው በአገር መከላከያ ላይ የፈጸመው ጥቃት ትልቅ የአገር ክህደት ወንጀል ነው ያሉት ባለሙያው፤ በአገር መከላከያ ሰራዊቱ ላይ ትልቅ የአገር ክህደት ወንጀል ከመፈጸሙ ባሻገር ታጣቂ ኃይሎችን በማሰማራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ የሚደረግላቸውን መብቶች በመጣስ ሰዎች በማንነታቸውና በብሔራቸው በጅምላ እንዲጨፈጨፉ፣ በዘራቸው ተለይተው እንዲገደሉ እንዲሁም ሰዎች በማንነታቸው ተለይተው አካላቸው እንዲጎልና ንብረታቸው እንዲወድም ማድረጉን ተናግረዋል።
በብሄራዊ ደረጃ የአገር መከላከያ ሰራዊት ሊይዛቸው የሚገቡ የጦር መሳሪያዎችን የመከላከያ ካምፖችን ደፍሮ የሰራዊቱን አባላት ገሎ እራቁቱን ሰዶ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ወንጀል ከመፈጸሙ ባሻገር፤ መሳሪያ በጁ ያልያዘን ሰራዊት በመረሸንና ከበድኑ ላይ በመጨፈር እንዲሁም ሲቪል ሰዎችን አስሮ በማንገላታትና በመረሸን አለም አቀፍ የጦር ወንጀል ፈጽሟል።
አቶ ተሾመ በክልሉ የሚገኙ በፌደራል መንግሥት የሚተዳደሩ ኤርፖርቶችን፣ የኤሌክትሪክ ተቋማት፣ የቴሌኮም ተቋማትን፣ መንገድ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙን ጠቁመው፤ ይህም የሚያሳየው የማፊያው ቡድን ዓላማውን፣ ፍላጎቱንና ስሜቱን ወይም ደግሞ እቅዱን በኃይል ለማሳካት ያደረገውን ጥረት እንደሆነ ገልጸዋል።
ስለዚህ ህ.ወ.ሓ.ት ወይም የጁንታው ቡድን ከምስረታው ጀምሮ ሽብርተኛ ብሎ ለማስፈረጅ የሚያስችል እጅግ ከበቂ በላይ ምክንያቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ድርጅቱ በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ከተደረገ አባላቶቹ በፈጸሙት ወንጀል በዋናው የወንጀል ሕግ ከመጠየቃቸው ባሻገር በአገሪቱ የሽብርተኝነት የወንጀል ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ስለሚያስችል ድርጅቱ እንደ ድርጅት ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ህልውና እንዳይኖረው፣ የድርጅቱን አርማና ፍላጎት አንግቤ እንቀሳቀሳለሁ የሚል ማንኛውም ሰው በሕግ ተጠያቂ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።
የሕግ ባለሙያው ህ.ወ.ሓ.ት ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀን ድርጅት አርማውን ይዞ መገኘት፣ በስሙ መሰብሰብና መደራጀት በዓለም አቀፍ መድረክ የተወገዘ እንደሚሆን ጠቁመው፤ አባላቶቹ በሽብርተኝነት ወንጀል ከመጠየቃቸው ባለፈ በማንኛውም ሁኔታ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀ ድርጅት አባላቱ፣ ተቋማቱ፣ ስሙ አርማው ስራ ላይ ሊውል አይችልም። በየትኛውም የዓለም ክፍል በስራ ላይ ውሎ ቢገኝ በወንጀል እንደሚያስጠይቅ ተናግረዋል።
ስለዚህ በሕጉ መሰረት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉዳዩን አጠናቅሮ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ የጁንታውን ቡድንና መሰሎቹን ሽብርተኛ ተብለው መፈረጅና በዓለም የሽብርተኛ ስም ዝርዝር ውስጥ ማስፈር ይገባል። ተከታትሎ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግና ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ሽብርተኛው ያፈራው ንብረት ለሃገር ብሔራዊ ጥቅም ተወርሶ መዋል እንዳለበት ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2/2013