ሙሉቀን ታደገ
ትምህርት የአንድ ሀገር ዋልታ እና ማገር ነው ። ምክንያቱም የአንድ አገር ሁለተናዊ እድገቶች የሚወሰኑት በእውቀት ነው ። የእውቀት መፍለቂያ ምንጩ ደግሞ ትምህርት ነው። ትምህርትን ለማከናወን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቢኖሩም መምህር ግን ዋነኛው ቁልፍ አካል ነው ። መምህሩ ጠንካራ፣ ታታሪ ፣ በስነምግባር የታነጸ ከሆነ ተማሪዎችም እንደ መምህሩ ታታሪ ፣ ጠንካራ እና በስነ ምግባር የታነጹ ሆናል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የተሻሉ ዜጎችን ለመፍጠር የሚችሉ መምህራንን አወዳድሮ ለመቅጠር ፈተና ፈተነ። በፈተናውም ለመምህርነት ከተፈተኑት ውስጥ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል መምህራን የወሰዱትን ፈተና ከ50 ፐርሰንት በታች አመጡ።
ይህንን የተመለከቱ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የተማሪ ወላጆች እና አንዳንድ ጉዳዩ ይመለከተናል ያሉ አካላት እንዴት የተወዳደሩበትን ፈተና ከ 50 ፐርሰንት በላይ ያላመጡ መምህራን ተማሪዎችን በስነምግባር አንፀው ጥሩ ውጤት ተማሪዎች እንዲያመጡ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ሃሳብ ይዘው ወደ አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው አካል እንድናደርስ ጠይቁልኝ ሲሉ ጠይቀውናል ።
በዚህ መሰረት የአዲስ ዘመን ጋዜጣም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ጠይቆ ይህን ምላሽ ይዞ ቀርቧል። አሁን የተካሄደው የመምህራን ቅጥር ሲፈፀም እንደ ከተማ አስተዳደር የከተማው የትምህርት ቢሮ ብቻ ሳይሆን የወሰነው የከተማዋ የፐብሊክ ሰርቪስም ጭምር ነው ። ስለዚህ የከተማዋ የፐብሊክ ሰርቪስ የሰው ኃይል መመሪያ መሰረት ነው ቅጥሩ የተካሄደው ።
በዚህ መሰረት ቅጥሩ አሁን ከተማዋ ባላት ስታንዳርድ መሰረት ከ0 ዓመት እስከ 5 ዓመት አገልግሎት ያላቸውን መምህራን ነው ለመቅጠር የፈለገው ። ያወዳደርነውም ይህንን መስፈርት የሚያሟሉ መምህራንን ብቻ ነው ። መምህራንን ከአምስት ዓመት በታች ለመቅጠር የተገደድነው የከተማ አስተዳደሩ ካለበት የበጀት እጥረት የተነሳ ነው ። ስለዚህ የፐብሊክ ሰርቪስ ይህን መመሪያ አውጥቶ ቅጥር ሲፈጸም ምን ማሟላት እንዳለብን መመሪያ ተቀርፆለት ነው።
ስለሆነም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በመስከረም ወር ማስታወቂያ ካወጣን በኋላ በአስሩ ክፍለ ከተማ ምዝገባ ተካሂዷል ። በዚህም ወደ 28 ሺ የሚጠጉ መምህራንን ምዝገባ አካሂደናል።
ነገር ግን ለቅጥር ይፈለግ የነበረው 1 ሺ 6 መቶ መምህራን ብቻ ነው ። የተለያዩ ከተሞች የተለያየ የአመላመል ፖሊሲ ይጠቀማሉ ። አዲስ አበባ ከተማ የሰው ኃይል ፖሊሲ እነዚህን 1 ሺ 6 መቶ መምህራንን ለመመልመል የተጠቀምንበት መንገድ ወቅቱን እና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ነው ። አሁን የተመዘገበውን 28 ሺ መምህር ለፈተና ማቅረብ አይቻልም ። ምክንያቱም ለመፈተኛ ከሚኖረው የቦታ ጥበት ጋር ተያይዞ ወቅቱ ደግሞ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስጋት ያለበት በመሆኑ ነው ።
28 ሺ መምህር ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ሲመጣ ያስመረቃቸው ዩኒቨርሲቲ መምህራኑን ብቁ ናቸው ብሎ አስመርቋቸዋል ። ስለዚህ ይህ መምህር ብቁ ነው። አሁን ላይ ካለው የስራ አጥነት ካልሆነ በቀር ሁሉም መምህር ብቁ ስለሆነ ውድድር ውስጥ የምታስገባው አይደለም ። ምክንያቱም ውድድሩ መምህራን ስለበዙ እንጂ መጀመሪያ ላይ እኮ መምህሩ ብቁ ነህ ተብሎ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቋል።
ከኮቪድ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመንን የመምህር እጥረት ለመቅረፍ ይህን ማስታወቂያ ስናወጣ ከበሽታውም ጋር ተያይዞ 28 ሺ ሰው ለፈተና ማስቀመጥ ስለማይቻል መጀመሪያው የመመልመያ መስፈርት መምህራኑ ዩኒቨርሲቲ ላይ ባመጡት የመመረቂያ ውጤትን መሰረት አድርጎ የተከናወነ ምልመላ ነው ።
ለፈተና የተመለመሉበት ደግሞ ሌላ አሰራርን የተከተለ ነው ። ለምሳሌ ሒሳብ ትምህርት ላይ ስንሄድ በሒሳብ ዲፕሎማ 50 ሰው ከሆነ ፍላጎታችን የእነዚህን 50 ሰዎች ሶስት እጥፍ ለፈተና እንዲቀመጡ ነው ያደረግነው ። ስለዚህ ከእነዚህ ከመቶ ሃምሳ መምህራን መካከል የተሻሉ 50 መምህራንን እንመርጣልን ማለት ነው። ለሴቶች ደግሞ ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጄንሲ ዜሮ ነጥብ ሁለት ወደታች ዝቅ በማድረግ ሴቶችን መምረጥ እንዳለብን ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት ሴቶች የተለየ መብት ተሰጥው ተመርጠዋል ። በዚህ ስሌት እነዚህ መምህራን ወደ ፈተና እንዲቀመጡ ተደርጓል።
ነገር ግን አሁን የተመረጡት መምህራን በየሁለት ዓመቱ ስራ ማሻሻያ እና የሙያ ማሻሻያ እየወሰዱ፤ የብቃት ፈተና እየተፈተኑ ሙያቸውን በየጊዜው ያድሳሉ። ነገር ግን አሁን ላይ ያጋጠመን የመምህራን እጥረት ስለሆነ ያደረግነው መምህራን ቅጥር እንጂ የመምህራን ምደባ ስላልሆነ ክራይቴሪያን ስነ ዘዴ ተጠቅመን ፈተና ፈትነናል።
እንደሚታወቀው ብዙ አይነት ፈተና አይነቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንደኛው አንድ ሰው ከክፍል ወደ ክፍል ሲሸጋገር የሚሰጥ ፈተና ነው። በዚህም ከክፍል ወደ ክፍል ለማለፍ አንድ ተማሪ 50 ፐርሰንት እና ከዚያ በላይ ማምጣት አለበት የሚል አንዱ መስፈርት ነው።
ነገር ግን አሁን የመምህራን ቅጥር ስናከናውን ዩኒቨርሲቲ ብቁ ናችሁ ብሎ ያስመረቃቸውን መምህራን እኛ ብቁ አይደላችሁም ብሎ የማስቀረት ስለማንችል መጀመሪያ ዩኒቨርሲቲ ባመጡት ውጤት ካወዳደርን በኋላ መልምለናን ።
ከዚያም አሁን መምህራኑ የተፈተኑት ፈተና ለመለያያት እንጂ ከዚህ በላይ ካላመጣችሁ አታልፉም ብለን ለመጣል ወይም ለማሳለፍ አይደለም ።
በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መምህራንን የቀጠረበት አግባብ ግልፅ እና የተሻለች የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር አልሞ የተከናወነ ነው ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2/2013