“የተማረ ሰው ይግደለኝ” የሚል አንድ የአገራችን ብሂል አለ፡፡ ይህ ሲባል በተማረ ሰው መሞት ጥሩ ነው ለማለት እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ የዚህ አባባል ዋነኛ ትርጓሜ የተማረ ሰው የማመዛዘን ሃይሉ ስለሚጨምር ያለጥፋቴ አይጨክንብኝም፣ ክፋት አይሰራብኝም ከሚል እምነት የመነጨ ይመስለኛል፡፡
ዛሬ ዛሬ ግን “የተማረ” የምንለው የህብረተሰብ ክፍል አብዛኛውን የአገሬውን ህዝብ አኗኗር ሲያምስ ይታያል፡፡ “የተማረ” የሚለው ሃሳብ ምን ያህል ሁሉንም እንደሚያስማማ እርግጠኛ ባልሆንም ለጊዜው “ፊደል የቆጠረ” በሚለው እንድትረዱልኝ እጠይቃለሁ፡፡ ለዛሬም ሃሳቤን እንዳነሳ ያስገደደኝ በአብዛኛው በዚሁ ፊደል በቆጠረው ማህበረሰብ እየተቀነባበረ የሚሰራጨው መረጃ እያስከተለ ያለው ጉዳት ነው፡፡
በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍጥነት እያደጉ ከመጡ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ ማህበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ የኢንተርኔት መስፋፋትና ሉላዊነት (Globalization) ለችግሩ መባባስ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡
በአገራችንም ትላልቅ የእጅ ስልኮችን በመያዝ ፌስቡክ መላላክ አዲስ ፋሽን እየሆነ ነው፡፡ በመንግስት መስሪያ ቤቶችም ውስጥ ከስራ ሰዓት ውስጥ ምን ያህሉ ለፌስቡክ እንደሚውል ቢሮ ይቁጠረው፡፡ ሁለት ጓደኛሞች አብረው ቢሆኑም በሃሳብ ተለያይተው በየራሳቸው ሃሳብ ውስጥ የሚዋልሉበት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል፡፡ በቤት ውስጥም ቢሆን ተመሳሳይ ባህርያት እየተስፋፉ ይገኛሉ፡፡ ማታ ላይ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በየራሳቸው ስልክ ውስጥ ተደብቀው የሚያመሹበት ሁኔታ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ይህንንም የተለያዩ ሰዎች በምሬት ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ለአንዳንዶቹም የትዳር ፍች መንስኤ እስከመሆን እየደረሰ ይገኛል፡፡
በተለይ የፌስ ቡክ ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ አብዛኛው የወሬ ምንጭም ይኸው ፌስ ቡክ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ያስገድዳል፡፡ በሰዎች ዘንድ እሉታዊ መነጋገሪያነቱ እያደገ የመጣው የአገራችን ፖለቲካ መነሻም የፌስ ቡክ ወሬ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ በርካታ ሰዎች ይህንን የፌስ ቡክ ወሬ በመቃረም “የፖለቲካ ተንታኝ” እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ በተለይ በጫት ቤትና በመጠጥ ቤት ሰዎች ሲገናኙ እነዚህ የፌስ ቡክ አርበኞች ከፖለቲካ ምሁራን የበለጠ ወቅታዊውን የፖለቲካ ሁኔታ የመተንተን ስራቸውን ያቀላጥፉታል፡፡
በዚህም ከፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ሌብነት፣ ከፍርድ ቤት ውሎ እስከ ቀበሌ ሸንጎ ድረስ ሁሉም እንደ ክብደቱ ይተነተናል፡፡ በዚህ ብቻም አያበቃም፤ አሁን አሁን ደግሞ የሃሜትና የሌብነት ምንጭም ጭምር እየሆነ ነው፡፡ በተለያዩ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ቡድኖችን ስም በሚፈልጉት መልኩ የሚያብጠለጥሉበት ተራ የወንጀለኞች መናኸሪያ እየሆነ ነው፡፡
የታዋቂ አርቲስቶች፣ ፖለቲከኞች፣ የባለስልጣናት እና የሌሎችም ግሰለቦች ስም በፌስቡክ እየተነሳ እንዲህ ናቸው፣ እንዲህ ነበሩ፣ ወዘተ በሚል ይብጠለጠላል፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህን የማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎች መነሻ በማድረግ አንዳንድ መደበኛ የብሮድካስት ሚዲዎችም በዚሁ ተግባር ውስጥ መሳተፋቸው ነው፡፡ ይህ የጋዜጠኝነትን ሙያ የሚያረክስ ተግባር በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በተለይ “ሚዛናዊነት” የሚለው የጋዜጠኝነት አንዱ መርህ አሁን አሁን ብዙም ትኩረት የተሰጠው አይመስልም፡፡ አንድ መረጃ ሲገኝ ያንን መረጃ ይዞ ላለመቀደም ወይም ከዚያም በተለየ ፍላጎት ቶሎ ለማድረስ ሲባል ብቻ ለህዝብ ጆሮ ማድረስ ተለምዷል፡፡ ከሚመለከተው አካል ስለጉዳዩ መጠየቅ ቢሆን አንድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ብዙም ሲታሰበብት አይታይም፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ የብሮድካስት ሚዲያውን ዜናዎች ማየት/ማዳመጥ በቂ ነው፡፡ ቢያንስ በየቀኑ አንድ በዚህ አይነት ሁኔታ ሚዛናዊነት የጎደለው ዜና ማግኘታችን አይቀርም፡፡ በተለይ የቀጥታ ስርጭት በሚመስል መልኩ የሚቀርቡት የኦንላይን ሚዲያዎች ሚዛናዊነትን የመጣስ ሁኔታ በስፋት ይስተዋልባቸዋል፡፡
በርግጥ ዛሬ በጋዜጠኝነት ስነምግባር ላይ ለማውራት አይደለም የተነሳሁት፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላ ጊዜ እመለሳለሁ፡፡ ለዛሬ በማህበራዊ ሚዲያው የሚራገቡ ጉዳዮች የመብዛታቸውና ከዚህ ጎን ለጎንም እነዚህን መረጃዎች አምኖ የሚቀበለው ሰው መብዛቱ ላይ የታዘብኩትን በጥቂቱ ላንሳ፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት ከጓደኞቼ ጋር ሻይ ቡና እያልን አንድ ጓደኛችን ለረጅም ሰአት ተጥዶበት ከነበረው ሞባይሉ ተላቆ ይህንን ቪዲዮ ተመልከቱ ብሎ አንድ ዘግናኝ ምስል አሳየን፡፡ ምስሉ ከወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ቢሆንም የተቀነባበረ ነበር፡፡ በምስሉ ላይ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ የተጨፈጨፉ ሰዎች እና በአካባቢውም ቆንጨራ የያዙ ሰዎች ይስተዋላሉ፡፡ ከስር ደግሞ አንድ ብሄር ሌላን ብሄር የሚያጠቃ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በወቅቱ ይህ ጉዳይ ለኛ ዋነኛ የመነጋገሪያ ጉዳይ አልነበረም፡፡ እንደ አንድ ዜጋ ግን ይህ ጉዳይ ዜና በመሆኑ ትኩረት የምንሰጠው ሊሆን ይችላል፡፡
ነገር ግን ከኛ መካከል አጋጣሚ አንድ ሰው የተለጠፈው ምስል ከዚህ ቀደም በምዕራብ አፍሪካ አንድ አካባቢ የተፈፀመ እንደነበርና እንደሚያውቀው በመናገር ይህ የተቀነባበረ ምስል መሆኑን ተናገረ፡፡ ነገር ግን በዚህ አጋጣሚ ይህ ሰው ስለምስሉ መረጃ ስላለው ለጉዳዩ ትኩረት እንዳንሰጥ ቢያደርገንም ስንቶች ግን በዚህ ምስል ተታለው የየራሳቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ እንደሚይዙ መገመት አያዳግትም፡፡ አሁን አሁን በአገራችን እዚህም እዚያም እየተፈጠሩ ለሚገኙ ብሄር ተኮር ግጭቶችም በእንዲህ አይነት ሁኔታ በተቀነባበረ መንገድ በሰው አዕምሮ ውስጥ እንዲሰርፁ የተደረጉ መረጃዎች የሚኖራቸው አስተዋፅኦ የላቀ እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡
ከሁሉ በላይ ግን አሁን አሁን “ሼር” በሚል ሃሳብ አንድን ምስል ወይም መረጃ ለበርካታ ዜጎች የማድረሱ ሂደት ምን ያህል አንድን መረጃ ለበርካታ ዜጎች ተደራሽ እንደሚያደርገውም መገመት አያዳግትም፡፡ ይህ ምስሉን ያሳየን ጓደኛችን መረጃውን ያገኘው ከፌስ ቡክ ነው፡፡ ነገር ግን እሱም ቢሆን ለሌሎች የፌስቡክ ጓደኞቹ ሼር በማድረግ አባዝቶታል፡፡
በወቅቱ መረጃውን ከፌስ ቡክ ማግኘቱን ሲነግረን አንዳንዶቻችን መረጃው የፌስ ቡክ መረጃ ሁሉ ትክክል ነው ብለህ እንዴት ታምናለህ ስንል ተቃውመነው ነበር፡፡ አንዳንዶቻችን የፌስ ቡክ መረጃ ማንም የሚለጥፈው በመሆኑ ሊታመን አይገባም ስንል ከፊሎቹ ደግሞ እውነት ሊሆን ይችላል በሚል መከታተሉ ተገቢ እንደሆነ አስረግጠው ነገሩን፡፡ እንግዲህ አስቡት! በዚያ ቦታ ላይ የነበርነው ከመረጃ ጋር በቅርበት የመገናኘት እድሉ የነበረን እና ለቴክኖሎጂውም ብዙም ያልራቅን ሰዎች ነበርን፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉትና ቴክኖሎጂውን በቀላሉ የሚጠቀሙ ሰዎች በነዚህ መረጃዎች እንዴት እንደሚጠለፉ መገመት አያዳግትም፡፡
ሰሞኑን ደግሞ አንድ መልዕክት በፌስ ቡክ አድራሻዬ ደረሰኝ፡፡ መልዕክቱ በአጭሩ እንዲህ የሚል ነው፡፡ አንድ በከፍተኛ ጤና እክል ምክንያት ለችግር የተዳረገ ሰው ፎቶ ተለጥፏል፤ ሰውየውም በውጭ አገር ህክምና ማግኘት የሚገባው በመሆኑ እርዳታ እንዲደረግለት የሚጠይቅ ልመና ሲሆን ድጋፍ ማድረግ የምትፈልጉም በሚል የባንክ አካውንት ቁጥር ከስሩ ተቀምጧል፡፡ እንግዲህ ይህ መረጃ ምን ያህል ተአማኒነት ይኖረዋል? ምን ያህልስ በዚህ መልኩ መረጃን ማስተላለፍ ይቻላል? የሚለው ለህግ ባለሙዎች የሚተው ሆኖ እንዲህ አይነት መረጃዎች ግን ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡
አሁን አሁን እየቀዘቀዘ ቢመጣም አንድ ሰሞን በፌስ ቡክ አካውንት በሚሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ መጠን እያስቀመጡ እንኳን ደስ ያለህ! እድለኛ ነህ! የሎቶ ሎተሪ ደርሶሃል! በሚል የብዙዎችን ቀልብ የሚስቡ መረጃዎች ሲለጠፉ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ እንዲህ አይነት መረጃዎች በስፋት ውሸት መሆናቸው ሲደረስባቸው ደግሞ በተለያዩ መንገዶች መተላለፍ ጀምረዋል፡፡ በአጠቃላይ ግን እነዚህ የሌብነት መንገዶች በአጭሩ ሊቀጩ ይገባል፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ አሁን አሁን በአገራችን በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ አንዳንድ መረጃዎች የጥላቻ ማስፋፊያዎች እየሆኑ መምጣታቸው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በተለያዩ የፌክ ወይም የውሸት አካውንቶች በመጠቀም እና የተለያዩ የብሄር ስም በመያዝ አገራችንን ለማበጣበጥ ሲጠቀሙበት ማየት እየተለመደ ነው፡፡
ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅን፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን፣ ከመደጋገፍ ይልቅ መገፋፋትን፣ ከይቅርታ ይልቅ በቀልን_ በአጠቃላይ_ ከገንቢ እና እውነተኛ መረጃዎች ይልቅ አፍራሽና ሀሰተኛ መረጃዎችን የማሰራጨት አሳፋሪ እና አንገት የሚያስደፋ ተግባራት በስፋት እያስተዋልን ነው፡፡
ወርቃማ ጊዜያቸውን በማባከን ቀኑን ሙሉ_ የኔ ዘር እንደዚህ የእሱ ዘር እንደዛ_ በማለት ሲባዝኑ የሚውሉ በርካታ ሰዎችም በዚሁ ስራ ተጠምደው ይውላሉ፡፡ ሃይማኖትን የማንቋሸሽ፣ የግለሰቦችን ስም በመጥራትና ምስላቸውን አቀነባብረው በመለጠፍ_ ከህሊናቸው ተነጥለው የሚዳክሩ ግለሰቦችም_ በገሀድ ይታያሉ፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ የሚባክነው ጊዜም ቢተመን ከፍተኛ ኪሳራ እንዳለው መገመት አያዳግትም፡፡
በርግጥ ማህበራዊ ሚዲያ በአግባቡ ከተጠቀሙበት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ከተለያዩ አገራት ተሞክሮ ማየት ይቻላል፡፡ ከዚህ አንጻር አንዳንድ አገራት ከማህበራዊ ሚዲያ የሚያገኙትን መረጃዎች በብቁ ባለሙያዎች በማስተንተንና እውነታውን በማጣራት የተሳሳተውን ጥለው ተአማኒውን_ በመውሰድ_ ስኬታማ ስራዎችን እየሰሩበት ነው፡፡ ሆኖም በአብዛኛው ያልተማረ እና የአዕምሮ ንቃተ ህሊናው በሚገባ ያልዳበረ ማህበረሰብ ውስጥ ሁሉም የማህበራዊ ሚዲያ መረጃ ትክክል ነው ተብሎ ስለሚወሰድ ለከፋ ጉዳት ይዳርጋል፡፡
በተለይ የእልህና የብሽሽቅ ይዘት ያለባቸው መረጃዎችን_ ተደራሽ ለማድረግ የሚንሸራሸሩ ጽሁፎች እና ምስሎች በውሸት የተሞሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ እንዲንሸራሸሩ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ዋነኛው ተጠቃሚው ስለ መረጃዎቹ አሰባሰብና ምንጭ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እንደ አረም በመዛመት ከቁጥጥር ውጪ ሊሆኑ ወደሚችሉበት ደረጃ እየደረሱ ይገኛሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መድሃኒቶችንም በፌስቡክ በማዘዝ እያንዳንዱን ግለሰብ ሊጎዳ የሚችል ተግባርም ይስተዋላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በቅርቡ ያጋጠመኝን ላውጋችሁ፡፡ ከስራ ወጥቼ ወደቤት ስሄድ እቤት ውስጥ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የተለያዩ የአትክልት አይነቶች ተገዝተውና ተደበላልቀው ሲከታተፉ ተመለከትኩ፡፡ ያየሁት ነገር አዲስ በመሆኑ ይህ ምንድነው ብዬ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ የተለያዩ የበሽታ አይነቶችም ተዘርዝረውልኝ ለነዚያ በሽታዎች ፈውስ በመሆኑ አመጋገባችን በዚህ መልኩ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ተነገረኝ፡፡ መረጃውን ከየት አገኛችሁት ብዬ ላቀረብኩት ጥያቄ የቀረበልኝ ምላሽ ደግሞ ፌስቡክ የሚል ነበር፡፡
በርግጥ በእለቱ የተመለከትኩት የምግብ አሰራር ለጉዳት የሚዳርግ አይደለም፡፡ ነገር ግን በእንደዚህ አይነት ሁኔታ እስከአመጋገባችን እና የጤናችን ሁኔታ ድረስ ውስጣችን ዘልቆ ተዓማኒነት ያተረፈው ፌስቡክ ምን ሊያስከትል እንደሚልችም ስጋት ገባኝ፡፡ ዛሬ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የተጀመረው ሰዎችን አሳምኖ ለድርጊት የመገፋፋት ጅምር ነገ ለሌላ አላማ ሊውል የማይችልበት ምክንያት እንደማይኖርም ተገነዘብኩ፡፡ እናም የፌስ ቡክ መረጃን ሙሉ ለሙሉ ማመን የሚያስከትለውን ጉዳት ለቤተሰቤ አባላት ለማስረዳት ሞከርኩ፡፡ ለጊዜው የማውቀውን ያህል ስለማበራዊ ሚዲያ ምንነትና ባህርያት ለማስረዳት ብሞክርም ምን ያህል ተሳክቶልኛል ለሚለው ጥያቄ ግን በቂ ምላሽ የለኝም፡፡ ምክንያቱም ፌስቡክ በአብዛኞቻችን ህይወት ውስጥ ስር ሰዷልና ስለጉዳቱም ሆነ ስለጠቀሜታው በስፋት ማስተማር ይጠይቃል፡፡
በተለይ አሁን አሁን ይህ ለዚህ አይነት በሽታ ፈውስ ነው፤ ይህ ደግሞ ከእንዲህ አይነት ደዌ ይገላግላል፤ ለእድሜ ማራዘሚያ ይህንን ብትወስዱ፣ ወዘተ የሚሉ የፌስቡክ መረጃዎች የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ ነው፡፡ እንዲህ አይነት መረጃዎች ዛሬን ለቴክኖሎጂው ተገዢ እንድንሆንና በዚህ መካከልም ነገን ወደ ስህተት ለመገፋፋት ከወዲሁ መንገድ የሚያመቻቹ በመሆኑ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ እነዚህን የማህበራዊ ሚዲያዎች ስንጠቀምም የመረጃዎቹን ትክክለኛነት አጣርተን ቢሆን ይመረጣል፡፡
ዛሬ ዛሬ ዘርን፣ ሃይማኖትን አካባቢን ወዘተ መነሻ ተደርገው በፌስቡክ የሚለጠፉ መረጃዎችም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ መንግስትም ከማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የራሱ ፖሊሲ አውጥቶ ህብረተሰቡን ከሃሰት መረጃዎች የሚከላከልበትን መንገድ መፍጠር አለበት፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የማህበራዊ ሚዲያው የሁከትና የብጥብጥ እንዲሁም የማህበራዊ ቀውስ ምንጭ እየሆነ መዝለቁ የሚያስከትለው ቀውስ ከባድ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 20/2011
ውቤ ከልደታ
Keep up the amazing work! Can’t wait to see what you have in store for us next.