በሽታን ቀድሞ መከላከል ዋነኛው የህክምና ክፍል ነው:: አንደኛው የመከላከያ መንገድ ደግሞ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅምን መጨመር ነው:: የትኞቹ ምግቦች ይህንን ሊያደርጉ እንደሚችሉ እናያለን:: በሽታ የመከላከል አቅምን የሚጨምሩ የምግብ አይነቶችን በበቂ ሁኔታ መመገብ ሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅሙ እንደሚጨምር ብዙ ጥናቶች ያሳያሉ:: ይህን በማድረግም በቀላሉ ጉንፋን፣ ኢንፌክሺኖች እንዳያጠቁን ይከላከላሉ:: በጥናት ከተረጋገጡ ምግቦች ጥቂቶቹን ማንሳት አስፈላጊ ነው::
የሲትረስ ፍራፍሬ
ብዙ ሰዎች ጉንፋን ከያዛቸው በኋላ በሽታ የመከላከል አቅምን ለመጨመር በቫይታሚን ሲ የበለፀጉ ምግቦችን ያዘወትራሉ:: ቫይታሚን ሲ ነጭ የደም ሴልን በመጨመር ከኢንፌክሺን ለመዋጋት ይረዳል:: ሁሉም የሲትረስ ፍራፍሬዎች በቫይታሚን ሲ የበለፀጉ ናቸው:: ከእነዚህም ውስጥ፤ የወይን ፍሬ፣ ብርቱካን፣ መንደሪን፣ ሎሚ ይጠቀሳሉ:: ሰውነታችን ቫይታሚን ሲን ስለማያስቀምጥ ዕለት ተዕለት መወሰድ ይኖርበታል::
ቀይ የፈረንጅ ቃሪያ
ከሲትረስ ፍራፍሬዎች ቀይ የፈረንጅ ቃሪያ 3 ጊዜ የበለጠ የቫይታሚን ሲ መጠን ይይዛል:: እንዲሁም በቤታ ካሮቲንም የበለፀገ ነው፤ ይህንንም ሰውነታችን ወደ ቫይታሚን ኤ በመቀየር የዓይን እና የቆዳን ጤንነት ይጠብቃል:: በሽታ የመከላከል አቅምን ከመጨመሩም ባሻገር ቫይታሚን ሲ ጤናማ ቆዳ እንዲኖር ያደርጋል::
አበባ ጎመን
አበባ ጎመን በቫታይሚን (ኤ፣ ሲ፣ ኢ)፣ ሚነራል፣ ፋይበር እና ሌሎች አንታይኢክሲዳንቶች የተሞላ የአትክልት አይነት ነው:: ይህ አትክልት በጣም ጤናማ ከሚባሉት ይመደባል:: የጤና በረከቶቹን ላለማጣት የአበባ ጎመንን ብዙ ማብሰል አይመከርም:: ጥናቶች እንደሚያሳዩት መቀቀልም የተሻለ እንደሆነ ነው::
ነጭ ሽንኩርት
ነጭ ሽኩርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወደድ ነው:: በስልጣኔዎች ውስጥ ነጭ ሽንኩርት በሽታን በመከላከሉ ዘርፍ ግንባር ቀደም ነበር:: ጥናቶች እንደሚያሳዩት ነጭ ሽንኩርት የደም ሥር የመዘጋት ወይም የመጠጠር አቅምን ይቀንሳል::
ዝንጅብል
ዝንጅብል ከታመምን በኋላ የምንዞርበት ሌላው ጠቃሚ የምግብ አይነት ነው:: የሰውነት መቆጣትን በመቀነስ የጉሮሮ መቁሰልን እና ኢንፌክሺንን ለመዋጋት ይረዳል:: እንዲሁም የማቅለሽለሽ ስሜትንም ይቀንሳል:: በተጨማሪም ህመምን የመቀነስ፣ የደም ውስጥ ስብ መጠንን የመቀነስ ባህሪ አለው::
ቆስጣ
ቆስጣ ከቫይታሚን ሲ በተጨማሪ በብዙ አንታይኦክሲዳንቶች እና በቤታ ካሮቲን የበለፀገ ነው:: እነዚህም የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራል:: ቆስጣም በውስጡ ያሉትን ንጥረ ነገሮችን እንዳያጣ ብዙ መብሰል የለበትም::
እርጎ
ማጣፈጫ ያልገባበት እርጎ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ይነገራል:: እርጎ የቫታሚን ዲ ምንጭ ነው:: ቫይታሚን ዲ የሰውነትን በሽታ የመከላከል ሥርዓት በማስተካከል በተፈጥሮአዊ መንገድ በሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራል::
እርድ
ይህ ቅመም የሰውነት መቆጣትን ስለሚቀንስ ለአርትራይትስ በሽታ ለዓመታት ሰዎች ሲጠቀሙት ይታያል፤ ውጤቱም አስደናቂ ነው:: እርድ በውስጡ በከፍተኛ መጠን ኩርኩሚን (Curcumin) የተባለ ንጥረ ነገር ይይዛል፤ ይህም ቀለሙ ቢጫ እንዲሆን እና በእንቅስቃሴ ምክንያት የሚመጣ የጡንቻ ጉዳትን እንደሚቀንስ ይነገራል:: በተጨማሪም ንጥረ ነገሩ በጥናት የተረጋገጠ በሽታ የመከላከል አቅምን የመጨመር እና በቫይረስ የሚመጡ በሽታዎችን ለመቋቋም እንደሚረዳ አሳይተዋል::
አረንጓዴ ሻይ
አረንጓዴ እና ጥቁር ሻይ ፍላቮኖይድ (Flavonoid) በተባለ አንታኦክሲዳንት የተሞላ ነው:: አረንጓዴ ሻይ ከጥቁር ሻይ በተሻለ ተጨማሪ ሌሎች ሃይለኛ አንታኦክሲዳንቶችንም በውስጡ ይይዛል:: ይህም የሰውነትን በሽታ የመከላከል ሥርዓት እንደሚያግዝ ይነገራል:: እንዲሁም አረንጓዴ ሻይ L-theanine የተባለ አሚኖ አሲድ ምንጭ ነው፤ ይህም ጀርምን ለመዋጋት የሚያስፈልግ ውህድን በመጨመር ሰውነትን እንደሚያግዝ ይነገራል::
ፓፓዬ
ፓፓዬ ሌላው በቫይታሚን ሲ የበለፀገ ፍራፍሬ ነው:: በተጨማሪም ፓፓዬ የምግብ መፍጨት ሥርዓትን የሚያሳልጥ እና ሴሎችን መቆጣት የሚቀንስ ውህድ አለው:: ፓፓዬ በውስጡ ፖታሺየም፣ ማግኒዢየም እና ፎሌት ስለሚይዝ ለጤና እጅጉን ጠቃሚ ነው::
ምንጭ -ሔልዝ ኢንሹራንስ ኔትዎርክ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2013