ዳንኤል ዘነበ
ማንኛውም ሰው ሲያገባ የመጀመሪያው ትኩረት ፍቅር እና ስምምነት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ አስፈላጊ የሆኑ ምርምሮች በተለይም የኤች.አይ.ቪ ምርመራ አስፈላጊነት ግዴታ ነው፡፡ የደም ወገን (ምድብ) ምርመራ አድርጎ የሚያገባ ሰው የለም፤ አይመከርምም፡፡ ይሁን እንጂ አጋጣሚ ሆኖ አልፎ አልፎ ባል ደሙ አር.ኤች ፖዘቲቭ (Rh+ve) ሆኖ የሚስት ደግሞ አር.ኤች ኔጌቲቭ (Rh-ve) በሚሆንበት ጊዜ በሆድ ውስጥ በሚገኝ ህፃን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርሳል፡፡ ይህም በአማርኛ አጠራሩ ሾተላይ ይባላል፡፡
ሾተላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ የሚችልና ህፃኑን በማህፀን ውስጥ እስከ መሞት (still birth) ሊያደርስ ይችላል፡፡ ይህንን ችግር እንዴት እንደሚያመጣ ከማየታችን በፊት አስቀድመን የደማችንን አይነት ማለትም አር.ኤች ኔጌቲቭ (Rh-ve) ወይም አር.ኤች ፖዘቲቭ (Rh+ve) ማለት ምን እንደሆነ እንመልከት፡፡
አር-ኤች በቀይ ደም ህዋሳት ላይ የሚገኝ ፕሮቲን ነው። በቀይ የደም ህዋሳቸው ላይ ይህ ፕሮቲን ያላቸው ሰዎች አር.ኤች ፖዘቲቭ (ያለው) ሲባሉ የሌላቸው ደግሞ አር.ኤች ነጋቲቭ (አልባ) ይባላሉ። አር.ኤች አልባ (Rh negative ) ወይም አር.ኤች ያለው (Rh positive) የደም አይነት መኖሩ በጤና ላይ የሚያስከትለው ችግር የለም።
ችግር የሚሆነው አር.ኤች አልባ የደም አይነት ያላት እርጉዝ ሴት አር.ኤች ያለው የደም አይነት ያለው ልጅ የፀነሰች ጊዜ ነው። ከዚህ ጋር የተያያዙ አብዛኛዎቹ ችግሮች መከላከል የሚችል መድሃኒት አላቸው። ይህ መድሃኒት አንቲዲ ኢሙኖግሎብሊን (ሮጋም) ይባላል። የሚሰጠውም በመርፌ ብቻ ነው። አር.ኤች ያለው የደም አይነት ያላቸው ሴቶች የዚህ ችግር ተጠያቂዎቹ አይሆኑም። ነፍሰጡር እናት የደም አይነቷ ምን እንደሆነ እንዴት ማወቅ ትችላለች?
በመጀመርያው የቅድመ ወሊድ ክትትል ምርመራ ጊዜ የደም ምርመራ ይደረጋል። ይህ ምርመራ የደም አይነት ምርመራንም ያጠቃልላል። የደም አይነቷ አር.ኤች አልባ በመሆኑ ምን ችግር ሊገጥማት ይችላል?
አብዛኛውን ጊዜ የእናትና የጽንሱ ደም አይቀላቀልም። አልፎ አልፎ ግን ከልጅ ወደ እናት ትንሽ ደም ሊቀላቀል ይችላል። ይህ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥመው በወሊድ ጊዜ ነው። የጽንሱ ደም አር.ኤች ካለው፣ የእናቷ ግን አር.ኤች ከሌለው እና ጥቂት አር.ኤች ያለው የጽንሱ ቀይ የደም ህዋሳት ከእናትየዋ ደም ጋር ከተቀላቀሉ፣ የእናትየዋ ሰውነት አንቲቦዲ የተባለ በደሟ ውስጥ የሚዘዋወር የፕሮቲን ይዘት ያለው ንጥረ ነገር ያዘጋጃል። እኝህ አንቲቦዲ የተባሉ የፕሮቲን ንጥረ ነገሮች ሴትየዋ ድጋሚ በምታረግዝብት ጊዜ አር.ኤች ባለው ጽንስ ቀይ የደም ህዋሳትን እንደ ጠላት ስለሚቆጥሯቸውና ስለሚያጠቋቸው በጽንሱ ጤንነት ችግር ሊፈጠር ይችላል። እኝህ አንቲቦዲዎች የጽንሱ አር ኤች ያዘሉ ቀይ የደም ህዋሳትን በማጥቃት ያጠፏቸዋል። በዚህ ጊዜ ጽንሱ የደም ማነስና ሌሎች የጤና ችግሮች ይደርሱበታል። አልፎ አልፎም በማህፀን ውስጥ እያለ ሊሞትም ይችላል። ይህ ሁኔታ በተለምዶ ሾተላይ በመባል ይታወቃል።
የጽንሱ የደም አይነትስ እንዴት ማወቅ ይቻላል?
የጽንሱ የደም አይነት ማወቅ ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁንና አር.ኤች አልባ የሆነች ነፍሰጡር ሴት የባሏ ደም አር.ኤች ያለው ከሆነ የጽንሱም ደም አር.ኤች ያለው ሊሆን ይችላል። ነግር ግን ባልና ሚስት ሁለቱም አር.ኤች አልባ ከሆኑ የጽንሱም የደም አይነት አር.ኤች አልባ ስለሚሆን ይህ ችግር አያሳስባቸውም። አንዲት ነፍሰጡር ሴት የደም አይነቷ አር ኤች የሌላት ሆና ከተገኘች (ጽንሱ አር ኤች የሌለው የመሆን ዕድል ቢኖረውም) አር ኤች ያለው ጽንስ እንዳረገዘች ታስቦ አስፈላጊው ምርመራና ክትትል እንድታደርግ ይደረጋል። እንዲህ በማድረግ ብዙ ችግሮች ማቃለል ይቻላል።
የአር ኤች አልባ ነፍሰጡር ሴት ቀጣይ ምርመራና ህክምናው
አር.ኤች የሌለው የደም አይነት ያላት እርጉዝ ሴት ሰውነቷ አንቲቦዲ አለማዘጋጀቱ በላቦራቶሪ (indirect coomb’s test) መረጋገጥ አለበት። የመጀመሪያው በደሟ ውስጥ አንቲቦዲ እንደሌለ በላቦራቶሪ ከተረጋገጠ መድሃኒት እንድትወስድ ይደረጋል። መድሃኒቱ ሰውነቷ አንቲቦዲ እንዳያዘጋጅ ይከላከላል:: መድሃኒቱ በሰባተኛው የእርግዝና ወር ላይ በመርፌ ይሰጣታል። ከወሊድ በኋላም የልጁ የደም አይንት ታይቶ አር ኤች ካለው በወለደች በ72 ሰዓት ውስጥ መርፌው በድጋሚ እንድትወስድ ይደረጋል። የልጁ የደም አይነት አር ኤች ከሌለው ግን ተጨማሪ መርፌ አያስፈልጋትም።
ይህ ሁኔታ በመጀመሪያ የእርግዝና ወቅት በህፃኑ ላይ ችግር ባያመጣም መድሃኒቱ ካልተወሰደ ግን ቀጣይ በሚወለዱት ህፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያመጣ ስለሚችል ሰውንቷ አንቲቦዲ እስካላዘጋጀ ድረስ ወደፊት በሚፈጠሩ እርግዝናዎች ሁሉ መርፌው መወጋት ያስፈልጋል።
ሌላው በደሟ ውስጥ አንቲቦዲ ከተገኘ መርፌው መወጋቱ ምንም ጥቅም አይኖረውም። ጽንሱም የችግሩ (የሾተላይ) ተጠቂ ሊሆን ስለሚችል ጥብቅ የሆነ ምርመራና ክትትል አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ህፃኑ እንደተወለደ በአፋጣኝ ወደ ጨቅላ ህፃናት ህክምና ክፍል ተወስዶ አስፈላጊ ምርመራና ህክምና ይደረጋል።
ምንጭ – ጆይ የማህፀን እና የጽንስ ልዩ ክሊኒክ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2013