ውብሸት ሰንደቁ
ደቡብ ክልል ጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ኦቾሎ ላንቴ ቀበሌ ምድሩ አረንጓዴ፣ ምንጮች እዚህም እዚያም እንደልብ የሚታዩበት ሥፍራ ነው፡፡ ይህ አረንጓዴን እንደ ኩታ የተላበሰ ቀበሌ የሚታወቀው በቲማቲምና በሙዝ ምርት ነው፡፡ በዚህ ቀበሌ ዓባያ ሐይቅን ጨምሮ ሌሎች ወንዞች ስላሉ የአካባቢው አርሶ አደር ለመስኖ ልማት እንግዳ አይደሉም፡፡
በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ኦቾሎ ላንቴ ቀበሌ ከወንድ አርሶ አደሮች እኩል ደፋ ቀና ብላ የምትኖር እንስት አለች፡፡ አገሬው እንደ አባወራ ይያት እንጂ ለቤቷ ሁሉንም ነች፤ የአባወራነትን ድርሻ ከባለቤቷ ከአቶ ሲሳይ ጎርፌ ጋር እኩል እንዲያውም በአብዛኛው የአንበሳውን ድርሻ እሷው የምትወጣ ድንቅ እንስት፡፡ እቤት ውስጥ የእማወራነት ተግባርንም ጥንቅቅ አድርጋ የምትከውን ታታሪ ሴት ናት፡፡
ምንም እንኳን ሥራዋ ቀን ከሌሊት የሚያጣድፍ ቢሆን ልጆቿን ጉልበታቸውን ሰስታ ከትምህርት ገበታ አላደናቀፈችም፡፡ እንዲያውም ከማንም እንዳያንሱባት አስጠኝ ቀጥራና ጥሩ ትምህርት ቤት ከሚባል የትምህርት ገበታ እያቋደሰች ትገኛለች፡፡ አንደኛዋ ሴት ልጇ አራተኛ ክፍል ሁለተኛዋ ልጇ ደግሞ ሁለተኛ ክፍል እየተማሩ ናቸው፡፡ ልጆቼ በአካልም በአእምሮም ጤናማ እንዲሆኑ በቻልኩት መጠን የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙና በጥሩ ሁኔታ እንዲማሩ ለማድረግ የቻልኩትን እሞክራለሁ ትላለች፡፡
ለእሷ ኢትዮጵያ የ13 ወር ፀጋ ባለቤት ብቻ ሳትሆን የዓመት ሙሉ በጋ የዓመታት ሙሉ ክረምት እመቤት ነች፡፡ ፀደይ መጥቶ የታረመው፣ መኸር መጥቶ ታጭዶ ተወቅቷልና ክረምት እስኪመጣ ቁጭ ብለን እንጠብቅ ብሎ ይሉት ብሂል በእርሷ ዘንድ ዋጋ የለውም፡፡ ዓመት ሙሉ ማሳዋ ላይ የማትታጣ የደቡብ ኮኮብ ነች፡፡
ወይዘሮ ያይንአበባ አስፋው ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው ደቡብ ክልል አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ላንቴ ቀበሌ ነው፡፡ ዕድሜዋ 32 ሲሆን የሁለት ሴት ልጆች እናት ናት፡፡ ወይዘሮ ያይንአበባ አስፋው ከዚህ በፊት በንግድ ሥራ ተሠማርታ ንግዱ አላዋጣ ያላት ግለሰብ ነበረች፡፡ ታዲያ ይህን የንግድ ሥራ በመተው የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ ወደ ሙዝና ቲማቲም ልማት ፊቷን አዞረች:: ያሰበችውን ለማሳካት ብጣሽ መሬት ባይኖራትም እንኳን በአካባቢው የሚደረገው ከአርሶ አደሮች መሬት የመከራየት ልማድን እንደ ጥሩ አጋጣሚ መውሰድ እንደምትችል ገብቷት ነበርና በዚያ መልኩ ጀመረችው፡፡
በዚህ ሃሳቧ ገፋችበትና ከአርሶ አደሮች መሬት ተከራይታ በትንሹም ቢሆን ቲማቲም ማምረት ጀመረች:: የምርቱንና የገበያው ሁኔታ በማየት በየጊዜው ከአርሶ አደሮች በኪራይ የያዘችውን መሬት አሰፋች፡፡ ከንግዱ አለመሳካት በኋላ ሙሉ ለሙሉ የአርሶ አደርነት ህይወት ውስጥ የገባችው በዚሁ አጋጣሚ ነበር፡፡ ይህም ህይወቷ የተሻለ ብሩህ ተስፋ እንዲኖረው አኗኗሯም የተቃና እንዲሆን አስችሏታል፡፡
ከአርሶ አደሮች መሬት የምትከራየው እንዲህ ነው፤ ከመሬቱ ባለቤት ጋር ውል ትገባለች ከዚያም መሬቱ በዋናነት ቲማቲምና ሙዝ ይመረትበታል፡፡ ተከራይ ማለትም ወይዘሮ የያይንአበባ ለሁለት ዓመት ያህል ቲማቲም ካመረተች በኋላ በሦስተኛው ዓመት ሙዝ ይተከልበታል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አከራዩ አርሶ አደር እና ተከራዩዋ ከሚመረተው ሙዝ እኩል እየተካፈሉ ይቀጥላሉ፡፡
ምርቱ የማያቋርጥና ተከታታይ ነው፡፡ ዓመቱን ሙሉ ይመረታል፡፡ የአንዱ አዝመራ ሲሰበሰብ ከሥር ሌላው እንዲተካ ይደረጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የውሃ ፍላጎታቸውን ዓባያ በተባለው ሐይቅ ላይ መሥርተዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ብላ ወይዘሮዋ እንዳነሳችው ዛሬ የደረሰና የሚለቀም የቲማቲም ምርት አለኝ፤ ይህ ከሳምንት በኋላ ሌላ ይተከልበታል፤ በዚህ ሁኔታ ሌላውም ይቀጥላል ትላለች::
ከሐይቁ በውሃ መሳቢያ አማካኝነት ውሃ በማውጣት ለመስኖ ምርታቸው ይጠቀማሉ፡፡ እንዲያውም የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ነገር ብዙ ጊዜ ያማርራቸዋል፡፡ እንደወይዘሮዋ ገለፃ ውሃ መሳቢያ ሞተሮች መንግሥት የሚያስመጣቸው ሲሆኑ ነዳጅ የማይበሉና ቶሎ የማይበላሹ ይሆናሉ፤ ከነጋዴ የሚገዟቸው የውሃ መሳቢያ ሞተሮች በየጊዜው የሚበላሹ በመሆናቸውና ነዳጅ ከመጠን በላይ የሚበሉ ስለሆኑ ወይዘሮዋን ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ሥራ የተሠማሩ ሌሎች አርሶ አደሮችንም ያማረረ ጉዳይ ነው፡፡
እንዲያውም አጋጣሚ ሆኖ ይህ ቃለ መጠይቅ በተደረገበት ጊዜ የጋሞ ዞን ከፌዴራል መንግሥት ያመጣቸውን የውሃ መሳቢያ ሞተሮች በማህበር በኩታ ገጠም በማምረታችን ምክንያት በመስጠታችን እንጂ የውሃ መሳቢያ ችግራችን በጣም የከፋ ነበር ስትል በሥራዋ ላይ ሳንካ ስለፈጠረባት ችግር ተናግራለች፡፡
ለምታመርተው ምርት የምትጠቀመው በተለይም ለቲማቲም ምርቷ ዳፕና ዩሪያ የሚባሉትን የአፈር ማዳበሪያ አይነቶች ሲሆን ለሙዝ ምርቷ ደግሞ ፍግ ከየቦታው በማስጫን ትጠቀማለች፡፡ ወይዘሮዋ ይህን ስታደርግ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ላንቴ ቀበሌ ግብርና ባለሙያው ተገቢ ሙያዊ ድጋፍ ያደርግላት እንደነበር አልሸሸገችም፡፡
ወይዘሮ ያይናአበባ በአካባቢው እንደሚደረገው ሁሉ ቲማቲም የሚትሸጠው በሳጥን እየተለካ ነው:: አንዱ ሳጥን 65 ኪሎ ግራም ያህል ቲማቲም የሚይዝ ሲሆን በአንድ ሄክታር 1ሺህ200 ሳጥን ይመረታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ቲማቲም በየሦስት ወሩ ነው የምታመርተው፡፡አሁን ማለትም በህዳር መገባደጃ ላይ እየተለቀመ ያለ ቲማቲም አላት፤ ይህ ቲማቲም መስከረም ላይ የተተከለ ነው፡፡
ህዳር ላይ የሚተከለው ደግሞ ጥር መጨረሻ ላይ ይለቀማል፡፡ ወይዘሮዋ በዓመት ለአራት ጊዜ ያህል የቲማቲም ምርት ታመርታለች፡፡ እንደምትለውም በአቅም እጥረት ምክንያት የቲማቲሙ ፍል ከሌላ ቦታ የሚመጣ በመሆኑ እንጂ በእርሻ ቦታው ፍሉን ማፍያ ሥፍራና ቴክኖሎጂው ቢገኝ በዓመት ከዚህ በላይ በሆነ ፍጥነት ቲማቲም ማምረት ይቻላል፡፡
የቲማቲም ችግኝ ከደብረ ዘይት ጀነሲስ ፋርሚንግ አስመጥታ ለዚያውም አንዷን ችግኝ አምስት ብር ገዝታ ነው የምታመርተው፡፡ ይህም እጅግ በጣም ውድ መሆኑን ትገልጻለች። ይህን ለማምረት አቅም ስለሚጠይቅ እንጂ በራሴ ማፍላት ብችል በቀላሉ ትርፋማ መሆን እችል ነበር ትላለች፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ግን በአካባቢዬ የቲማቲም ምርትን ደፍሬ እየሠራሁ ያለሁት እኔ ነኝ በማለት በኩራት ትናገራለች፡፡
ወይዘሮ ያይኔአበባ በማሳ ላይ የምታሳልፈውን ጊዜ እንዲህ በማለት ትገልፃለች፤ ለእኔ የምርት ስብሰባ ወቅት የሚባል የተለየ ጊዜ የለኝም፡፡ አንዱን ለቅሜ ጨርሼ ሌላው ይተከላል፤ በሌላውም መሬት ይህንኑ ሂደት እቀጥላለሁ፡፡ የቲማቲም ምርቱ እንደዚህ ያለ ሂደት ሲሆን የሙዝ ደግሞ በየሃያ ቀኑ የሚቆረጥ ስለሆነ ፋታ የሚሰጥና የምርት መሰብሰቢያ ጊዜ የሚባል ልዩ ጊዜ የለኝም፡፡
ሁልጊዜም ምርት የመሰብሰብና የመትከያ ጊዜ ነው፡፡ ከአርሶ አደሩ ተከራይቼ የምሠራበት 19 ሄክታር መሬት እጄ ላይ አለ፡፡ መሬቱን ስከራየው ለሁለት ዓመት ይሰጡኛል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የሚመጡትን አሥር ዓመታት ከአከራዩ አርሶ አደር ጋር የተመረተውን ምርት እኩል እንካፈላለን፡፡ ይህ ማለት አንድ ሄክታር መሬት ያከራየኝ አርሶ አደር እኔ ለሁለት ዓመት ቲማቲም ካመረትኩ በኋላ ቀጣዮቹን አሥር ዓመታት ሙዝ ተክዬ ሙዙን በየጊዜው ምርቱን እኩል እንካፈላለን ማለት ነው፡፡
ወይዘሮዋ ከምታለማው የሙዝ ምርት አሁን ላይ በጣም ጥሩ ምርት እያገኘች ነው፡፡ ከሁለት ሄክታር በየሃያ ቀናት ውስጥ አንድ መኪና ሙዝ ቆርጣ ለገበያ ታቀርባለች፡፡ ይህም በአማካይ 73 ኩንታል አካባቢ ይሆናል፡፡ ከፍተኛ የምርት መጠን የምትጠብቀው ከሙዝ ምርቷ ነው፡፡ የሙዝ ምርት በጣም ጥሩ ምርት፤ ተከታታይና የማያቋርጥ ሲሆን በዚያ ላይም የገበያው ሁኔታ ታይቶ ስለሚቆረጥ ለኪሳራ አይዳርግም፡፡ ያም ሆኖ ግን የገበያ ትስስር እንደሌላት ትናገራለች፡፡
በዚህም ምክንያት ለደላላ አላስፈላጊ ወጪ እንድታወጣ ተገድዳለች፡፡ ያመረትነው ምርት ደላላ ሳይገባው በቀጥታ ለተጠቃሚው ወይም ለህጋዊ አከፋፋይ እንዲደርስ ቢደረግ የዋጋ ንረትም አይኖርም ትላለች። አሁን ባለው ሁኔታ በአንድ መኪና 1ሺህ500 ብር ድረስ ለደላሎች እንደምትከፍል ትገልፃለች፡፡
‹‹የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል ያደርጉልኛል:: ከሙያ ድጋፍም ባሻገር ብድር እስከማመቻቸት ድረስ ቃል ገብተውልኛል፡፡ ሆኖም ከአካባቢው አርሶ አደሮች ሴት ሆኜ ይህን ያህል ሥራ የሠራሁት እኔ ነኝ፡፡ ብዙ ችግሮችን አልፌ አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለሁ፡፡ አሁን ከተማ ላይ ቪላ ቤት ሰርቻለሁ፤ ከዚህም በተጨማሪም ሲኖትራክ መኪና ገዝቻለሁ፡፡
ይህ እንግዲህ በብልህነት አጋጣሚዎችን በመጠቀሜ ጭምር የተገኘ ሀብት ነው::›› ነው ስትል የስኬቷን ምንጭ ታስረዳለች። ለምሣሌ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በኮሮና ምክንያት ሰዎች ፈርተው ቲማቲም አልተከሉም ነበር፡፡ እኔ ግን የራሴን ጥንቃቄ በማድረግ ቲማቲም ማምረቴን በመቀጠሌ በወቅቱ በጥሩ ዋጋ መሸጥ ችያለሁ፡፡ ይህን ሁሉ ማድረግ የቻልኩት በአራት ዓመት የአርሶ አደርነት ዘመኔ ነው፡፡ አሁን ሁለት ሄክታር ኩታ ገጠም መሬት ላይ ያለ ሙዝ እየተሸጠ ያለው አንድ ሚሊየን ብር እና ከዚያ በላይ ነው፡፡ እኔ ደግሞ 15 ያህል ሄክታር ሙዝ አለኝ፡፡
በዚህ ብናሰላ እንኳን ወደ ሰባት ሚሊየን ብር አለኝ ማለት ነው፡፡ ሌሎቹ ሲደመሩ ወደ 12 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ሃብት አለኝ ፡፡ በአካባቢው ጥሩ ልማት እያለማሁ ቢሆንም ይህንን ሁሉ ሳደርግ የተደረገልኝ ድጋፍ በቂ አይደለም፡፡ በራሴ ተነሳሽነት ከአርሶ አደሮች ላይ እርሻ ኮንትራት ይዤ፤ ራሴ አሳርሼና ሌሎች የሚያስፈልጉ ውድ የሚባሉ እንደ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች አይነት ገዝቼ ነው የጀመርኩት ትላለች፡፡
መንግሥት ሴት ያበረታታል ሲባል እንሰማለን፡፡አሁን እንደማየው ከሆነ ከወንዶች እኩል ተሯሩጬ እየሠራሁ እንጂ ማንም ድጋፍ ያደረገልኝ አካል የለም፡፡ በእርግጥ የውሃ መሳቢያ ሞተር በማህበሩ ውስጥ ቅድሚያ እንድገለገል ዕድል ተሰጥቶኛል፤ ይህ ጥሩ ነገር ቢሆንም ለሴቶች ግን ከዚህ በላይ የሆነ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
መንግሥት የሚያመጣቸው የውሃ መሳቢያ ሞተሮች በአንድ ሰዓት ውስጥ አንድ ሄክታር መሬት ያጠጡልናል፡፡ የነዳጅ ፍጆታቸውም ዝቅተኛ ነው፡፡ስለዚህ መንግሥት የውሃ መሳቢያ ሞተር በነፃ ባይሰጥ እንኳን ጥራት ያላቸው እቃዎች በመንግሥት በኩል በብድር እንኳን ማቅረብ ቢችል ጥሩ ነው፡፡ ይህ ቢመቻች ብድሩንም እየሠሩ መክፈል ይቻላል፤ አሁን የሥራ ፍላጎቱና መነሳሳቱ አለ፡፡
ሴትነት ከምንም ነገር አያግድምና መክሊታችሁን ለይታችሁ ስሩ ስትል ትመክራለች።‹‹ እኔ ምሳሌ ልሆን የምችል ሴት ነኝ፤ የሁለት ልጆች እናት ነኝ፤ ልጆቼን ጥሩ ትምህርት ቤት አስተምራቸዋለሁ፤ አስጠኝም ቀጥሬላቸዋለሁ፡፡ በሞተር እርሻ ቦታዬ ሄጄም ለምርቶቼ አስፈላጊውን እንክብካቤ አደርጋለሁ፡፡ በአካባቢው ያሉ ሰዎች ታዲያ በዚህ ሁኔታ ይገረማሉ፤ ይደነቃሉ›› ትላለች::
ወይዘሮ ያይንአበባ ለ40 ያህል ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥራለች፡፡ ሌሎች በአካባቢው ያሉ ችግረኛ ህፃናትንም ትምህርታቸውን እንዲማሩ ትረዳለች፡፡ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ለመከላከያ ሰራዊት አንድ መኪና ሙዝ ማበርከቷን ነግራናለች፡፡
ለምትጠቀሙበት ሐይቅ ምን ዓይነት እንክብካቤ ታደርጋላችሁ ያልናት ወይዘሮ ያይንአበባ እንዲህ በማለት ሃሳቧን አጠቃላለች፡፡ ከዓባያ ሐይቅ ውሃ ስንጠቀም ሐይቁ ሳይጎዳ እንዲሆን የግብርና ባለሙያዎች እየመጡ ይከታተላሉ፤ ይቆጣጠራሉ፡፡
በአካባቢው የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ነዳጅ ዘይት እንዳይፈስ እና ሌሎች ባዕድ ነገሮችን እንዳንጥል ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም የውሃ ማጠጫ ሰዓታችን ውስን እንዲሆን ተነግሮን በዚያ መሠረት እስከ ስድስት ሜትር ርቀት የውሃ መሳቢያ አስቀምጠን ነው ውሃውን የምንጠቀመው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2013