ስግብግቡ፣ ዘራፊውና ነፍሰበላው ጁንታ የተዘረጋለትን የሰላም እጅ ነክሶ በተለይም ከለውጡ ዘመን ወዲህ የሴራ፣ የጭፍጨፋና የግጭት ፊት አውራሪ ሆኖ ኖሯል። ለንጹሀን የትግራይ ሕዝቦች ክብርና ደህንነት ሲባል የሚያከናውናቸው የጥፋት ተግባራት በዝምታ መታለፋቸውም የልብ ልብ ሰጥቶትና ጫፍ የነካ መታበይ ውስጥ ከቶት ራሱን ወደማጥፋት ለሚያደርስ ግብዝነት ዳርጎታል።
ከውልደቱ ጀምሮ ሴራ፣ አፈናና ግድያ ባህሪው የሆነው ይህ ቡድን በመላ አገሪቱ በተቀሰቀሰ ሕዝባዊ አመጽ ዓይንህ ለአፈር ተብሎ ሲተፋና ከሥልጣን ሲባረር በሕግ ፊት ሊያቆመው የሚችል ሺህና ሺህ ምክንያቶች ቢኖሩም ለውጡን በይቅርታ መንፈስ ለመምራትና እንደ አገር ከመጣንበት የአሳሪና ታሳሪ ታሪክ ለመውጣት በደሎቹ ሁሉ በይቅርታ መንፈስ ተሰርየውለት እንደነበር አይዘነጋም።
ይሁንና ሞኝ ሲያከብሩት የፈሩት ይመስለዋል እንደሚለው ብሂል ይህ ጸረ ሕዝብ ኃይል በሕዝብና በመንግስት የተደረገውን ይቅርታና ትዕግስት ከፍርሃት በመቁጠርና መቀሌን እንደመማጸኛና አይነኬ መሸሸጊያ ከተማ በመቁጠር በአደባባይ ሕግና ሕገ መንግሥትን የጣሱ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱ ጸሐይ የሞቀው እውነታ ነው። ለዓመታት የሰራው ግፍና ዝርፊያ ወደ መቀሌ እንዲጓዝ ያስገደደው ይህ ኃይል የሽብር ማስተርማይንድ በመሆን አገርና ሕዝብን ለሰቆቃ የዳረጉና ደም ያስለቀሱ የጥፋት ተግባራትን በማቀድ፣ በማስፈጸምና በመፈጸም ተሰማርቶ ቆይቷል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዓብይ አህመድ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በቅርቡ ለፓርላማ ባደረጉት ማብራሪያ ከለውጡ ወዲህ ባሉ ዓመታት በአገሪቱ ከተከሰቱ ግጭቶች ጀርባ ጁንታው መኖሩን አረጋግጠዋል። ይህ ጸረ ሰላም ኃይል እነዚህን ግጭቶች እየፈጸመና እያስፈጸመ መንግሥትን ሕግን የማስከበር አቅም የለውም ብሎ ሲከስስና በትግራይ ክልል ላይ ግጭቶች አልተከሰቱም እያለ ሲዘባነን
መኖሩም አይረሳም።
ከዚህ የምንረዳው የዚህ የጁንታ ቡድን የህልውናው መሰረት ሴራ፣ ዘረፋ፣ ግጭትና ጭፍጨፋ መሆኑን ነው። ይህ ደግሞ ቡድኑ ከሰብዓዊነት የራቀና ሰይጣናዊ ባህሪን የተላበሰ መሆኑን ያሳያል። ሲገድል፣ ሲያሰቃይና ሲዘርፍ ለአንድ ቀን ትውስ ያላለውን አገር ወዳዱን የትግራይ ሕዝብ ለጥፋቱ ምሽግ አድርጎ ለመጠቀም የሚያደርገውን ሙከራ ለተመለከተም የቡድኑን አፍረተቢስነት በቀላሉ እንዲረዳ ያደርገዋል።
ይህ ጁንታ ለዓመታት ሲፈጽማቸው የነበሩ ጸረ-ሰላምና ጸረ-ሕዝብ ተግባሩ አልበቃ ብሎትም ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ/ም የአገር ደጀንና መከታ በሆነውና ከ20 ዓመታት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ የትግራይን ሕዝብና የአገርን ሉዓላዊነት ከወራሪ ሲጠብቅ በኖረው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ላይ አስቀድሞ ባዘጋጃ ቸው የጥፋት ኃይሎች የባንዳነት ጥቃት ሰንዝሯል። ምንም እንኳን ይህ ጥቃት የጁንታው ራስን የማጥፋት ውሳኔ ቢሆንም ተግባሩ ግን መላ ኢትዮጵያውያንን በከፍተኛ ደረጃ አስቆጥቷል።
ይህ የጁንታው የባንዳነት ተግባር በተለይም ጨዋውንና ለአገር ሉዓላዊነት ዕድሜ ልኩን ውድ ህይወቱን በመስዋዕትነት ሲያቀርብ የኖረውን የትግራይ ህዝብ አንገት ያስደፋም ነበር። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ጁንታው ጥቃት የፈጸመው በኢትዮጵያ ላይ ስለነበር ነው። በተለይም ከህይወቱና ከአካሉ መስዋዕትነት ባሻገር ካለችው ደመወዝ ላይ እየቀነሰ ለትግራይ ወንድሞቹና እህቶቹ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያና መሰል መሰረተ ልማቶችን ባስገነባውና በአጨዳና በአንበጣ ወረርሽኝ ወቅት የሕዝብ ክንድ በሆነው የሰሜን ዕዝ ላይ ይህን መሰል ጥቃት መሰንዘሩ የጁንታውን አረመኔነትና ባንዳነት እርቃኑን ከማስቀረቱም በላይ በሕዝብ እንዲተፋ አድርጎታል።
ይህ የጁንታው የባንዳነት ተግባርና የአገር ክህደት ያስቆጣው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ ያለምንም ንጹኃን ጉዳት ጁንታውን በጥቂት ቀናት ጠራርጎ የመጨረሻ ምሽጉ ከነበረው መቀሌ ጭምር ሸሽቶ እንዲፈረጥጥ አድርጎታል። አሁን ላይ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ይህን አጥፊ ቡድን እግር በእግር እየተከታተለ ለሕግ ለማቅረብ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ከዚህ የጁንታው ተግባርና ከተገኘው ድል አንድም የትዕቢት፣ የሴራና የጭካኔ መጨረሻው ውርደትና ወድቀት መሆኑን በሌላም በኩል ኢትዮጵያዊነትና እውነት ሁሌም አሸናፊ መሆናቸውን የተመሰከረበት ነው!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2013