የሰላም ሚኒስቴር “ሚዲያ ለሰላም” በሚል መሪ መልእክት ዛሬ በካፒታል ሆቴል ከጋዜጠኞች፣ የሚዲያ አመራሮችና አክቲቪስቶች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልና የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዚን ፌሎሺፕ ፕሬዚዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴ፣ ታዋቂ ግለሰቦች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የውይይት መድረኩን ሚኒስትሯ በንግግር የከፈቱት ሲሆን “ኢትዮጵያውያን ከብዙኅነታችን መካከል የሀሳብ ብዙኅነት አንዱ ነው፤ ነገር ግን የሀሳብ ልዩነቶቻችን ማፈጸሚያ መሰረቱ ደግሞ ሰላማዊ ሊሆን ይገባል” ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ሙፈርያት ሚዲያ በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ነው፤ ሀገር ለመገንባትም ለማፍረስም አቅም አለው ያሉት ሚኒስትሯ ሚዲያውን በኃላፊነት በመጠቀም ለሀገሩ ቀናኢ የሆነነና ተግቶ የሚሰራ፤ ልዩነቶችን በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎቱም አቅሙም ያለው ማኅበረሰብ ለመፍጠር መሥራት ከሚዲያው እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
በአገሪቱ እየታዩ ያሉ አለመግባቶችና ግጭቶችን አስመልክቶም ግጭቶችን ከማቀንቀን ይልቅ የማኅበረሰቡ እሴት ውስጥ የሚገኙ የሰላም ገጾችን እየገለጣችሁ ያልተዳሰሱ በጎ እሳቤዎችንና ተግባራትን ማሳየት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ግጭቶች በሚዘገቡበት ጊዜም የሚፈቱበትን መፍትሔዎች ጭምር አመላካች በሆነ መንገድ በመዘገብ አቀጣጣይ ከመሆን ይልቅ የመፍትሔው አካል መሆን ላይ ደፈር ብሎ ሊሰራ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በውይይት መድረኩ “የሰላም ጋዜጠኝነት እንደ አማራጭ” በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መመህር ረ/ፕሮፌሰር ጌታቸው ድንቁ (PhD)፣ “ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትና የጥላቻ ንግግር መስፋፋት ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው” በሚል ርዕስ አቶ ታምራት ደጀኔና አቶ ዳዊት ከበደ እንዲሁም የህግ ልዕልናና የአገራችን ሰላምን አስመለክቶ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መመህርና በአ.አ.ዩ. የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር አቶ ወርቁ ያዜ የመወያያ ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን አቅርበዋል፡፡