መሠረተ ልማት ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ቅርንጫፎችን ማለትም መንገዶች፣ ወደቦች፣ ድልድዮች፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ መጋዘኖች፣ የውሃ ተፋሰሶች፣ የኃይል ማመንጫዎች፣ የባቡር ሃዲዶች፣ ልዩ ልዩ የመገናኛ አውታሮች፣ የውሃና ፍሳሽ ተቋሞች፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችና የመሳሰሉትን ያካተተ ነው።
በመሠረተ ልማት ውስጥ የሚጠቃለሉ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ተቋሞች የአንድን ሀገር ቁሳዊ ሀብት በማሳደግ ረገድ የሚጫወቱት ሚና አይተኬ መሆኑም እሙን ነው። ኢትዮጵያ በዓለም ከሚገኙ ድሃ አገሮች ከሚባሉት አንዷ ብትሆንም ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት በርካታ ትላልቅ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል። በርግጥ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ህዝቦች አሁንም በርካታ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ሲያነሱም ይደመጣል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በህዝብ ገንዘብ የተገነቡ ወሳኝ መሰረተ ልማቶች የአንድን ቡድን ፍላጎት ለማሳካት ብቻ ሲወድሙ ማየትም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ የሆነና ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነው፡፡
በቅርቡ ዘራፊው የጁንታ ቡድን በኢፌዴሪ መከላከያ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃ መውሰድ ሲጀምር ጁንታው እራሱን ለማትረፍ ሲፈረጥጥ በክልሉ የሚገኙ የውሃና የኤሌክትሪክ መስመሮችን፣ ድልድዮችን፣ የአክሱም የአየር ማረፊያን ጨምሮ ሌሎች በርካታ መሰረተ ልማቶችን አውድሞ መሄዱ የሚታወስ ነው።
የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ ጎብኚዎች የአክሱም ጽዮንን ለመሳለምና የአክሱም ሃውልቶችን ለመጎብኘት የኢትዮጵያን አየር መንገድንና የአክሱም አየር ማረፊያን እንዲሁም በየብስ በኩሉ ያሉ ድልድዮችን አቆራርጠው ምኞታቸውን ሲያሳኩ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን መሰረተ ልማቶች አሁን ማግኘት አንችልም፡፡ የህዝብ ጠላት የሆነው ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ባደረሰው ውድመት ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋልና፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ጽንፈኛው ዘራፊና የህዝብ ጠላት የሆነው ቡድን ያፈረሰውን መሰረተ ልማት የህዝብ ልጅ የሆነው መከላከያ ሰራዊት እየጠገነ ህግ የማስከበሩን እርምጃ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በዚህም ይህ ፅንፈኛ ቡድን ለትግራይ ህዝብ የማያስብ ከመሆኑም ባለፈ ሀገር ከሃዲ መሆኑን ጭምር ያስመሰከረበት ጭምር እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ በአመፅና በወታደራዊ ሃይል ስልጣኑን ማራዘም ያሰበው ይህ ጁንታ ድል እየተደረገ ሲሸሽ በማይካድራ በንፁሃን ዜጎች ላይ ያደረሰው ግፍ ታሪክ የማይረሳው ሆኖ ቀርቷል፡፡ በዚህ ያላበቃው ይህ ጁንታ ከ526 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባውን የአክሱም አየር ማረፊያን በግሬደር በማረስ አውድሞ ሸሽቷል፡፡ ቡድኑ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ከፈፀመው ግፍ ባሻገር በክልሉ የሚገኙ የመሰረተ ልማት አውታሮችን “እኔ ካልበላሁት ጭሬ ልበትነው” በሚል ብሂል እያወደመ ሽሽቱን ቀጥሏል፡፡ የህዝብ ሀብት የሆኑት የወደሙ መሰረተ ልማቶችም የህዝብ ሀብት በሆኑት መከላከያ ሰራዊት መልሰው እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡
ታዲያ ህዝብ የሚገለገልባቸው እነዚህ ጠቃሚ መሰረተ ልማቶች ሲወድሙ ከማውገዝ በዘለለ ለነገ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መልሶ መገንባትም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የመንግስትና የባለድርሻ አካላት ኃላፊነትም ጭምር ነው፡፡ እነዚህ የህዝብና የሀገር ሀብት በሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ላደረሰው ጥፋት ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ተጠያቂ እንዲሆንና ለህግ እንዲቀርብ እየተሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
በዋናነት ልንገነዘብ የሚገባው በኢትዮጵያ መሰረተ-ልማትን በፍትሃዊነት ማዳረስ ተገቢ ከመሆኑም አልፎ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እንደሚረዳ ነው። በዚህም መንግስት አጥፊዎችን በህግ ቁጥጥር ስር በማዋል በሀገሪቱ ፍትሃዊ የአገልግሎትና መሰረተ-ልማት ስርጭት መኖሩን ማረጋገጥ ቀዳሚ ስራው እንደሆነም ተገልጿል።
መንግሥት መሰረተ ልማቶችን በማሟላት፤ ለወጣቱ የሥራ እድል በመፍጠር በተለይም ደግሞ የጀመረውን ህግን የማስከበር ሥራ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ በማድረግ የትግራይ ህዝብ በተለይም ወጣቶች ጥረውና ግረው ከድህነት የሚወጡበትን ዕድል ለመፍጠር በቀጣይ የሚሰራ ይሆናል።
ጁንታው በህዝብና በመንግሥት መሰረተ ልማቶች ላይ ያደረሰውን ውድመት ለማቋቋም ጊዜያዊ አስተዳደር ከመመስረት ባለፈ ክልሉን ከሌሎች ክልሎች ጋር የሚያገናኙትን ድልድዮች መልሶ በመገንባት የህዝብን ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ሥራም ይሰራል፡፡ እነዚህን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ወደ ቦታቸው የመመለሱ ሥራ በተለይም የትግራይን ህዝብ ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ ማህበራዊ መሰረታቸው ትግራይ ክልል የሆኑ ፓርቲዎች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በጋራ በመስራት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግም ግድ ይላቸዋል።
በክልሉ ሥራውን የጀመረው ጊዜያዊ አስተዳደር ሰሞኑን በጁንታው የወደሙ የመሰረተ ልማቶች ላይ የመልሶ መገንባት ስራዎችን አጠናክሮ ከመቀጠሉም በላይ የትግራይ ህዝብ በጁንታው አጥቶት የነበረውን መሰረተ ልማት ለማሟላት አበክሮ እየሰራ ይገኛል! ይህም የትግራይን ህዝብ ከጁንታው በመገላገል የሚሰራ ሥራ እንደመሆኑ ፋይዳው እጅግ የጎላ ነው!
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012 ዓ.ም