የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን በየዓመቱ ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ውስጥ አንዱ የሆነው የግል የበላይነት የአቋም መለኪያ ሳምንቱን ሙሉ ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ረፋዱ ላይ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ዘንድሮ ከአምናው በተሻለ ሁኔታ የሴቶች ተሳትፎ እንደጨመረም የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ሃላፊ የሆነው አቶ ዮናስ ካሳሁን በተለይ ለዝግጅት ክፍላችን ገልፆልናል፡፡
‹‹በአዲስ አበባ የሚገኙ ክፍለ ከተሞች፣የግል ተወዳዳሪዎች እንዲሁም ከክልል ተጋባዥ የሆኑ ተወዳዳሪዎች አሳትፏል፡፡ የዘንድሮው ውድድር መቶ አስር ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ሆነውበታል›› ያለው የፅህፈት ቤት ኃላፊው ለሁሉም ክፍት የሆነ የአቋም መለኪያ ውድድር እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በዚህም በኮርስ፣አዋቂ ማውንቴን፣ ታዳጊ ማውንቴን እንዲሁም በሴቶች ማውንቴን የነጥብ ውድድሮች ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የሴቶች ተሳትፎ ከመጨመሩም ባሻገር የአዲስ አበባ ፖሊስ አዲስ ክለብ በማቋቋሙ ይህን ውድድር ተጠቅሞ አዳዲስ ታዳጊዎችን ለመመልመል እድል አግኝቷል፡፡
‹‹የሚመዘገበው ነጥብ በግል ለተወዳዳሪው የሚያዝ ነው›› ያለው አቶ ዮናስ በኮርስ ውድድር ከኤሌክትሪክ ክለብ በግል የተወዳድረው እስራኤል ጴጥሮስ በ62 ነጥብ የዛሬውን የመጨረሻ ውድድር ሳይጨምር እየመራ ይገኛል፡፡ አዲሱ መኮንን እና ሃምዛ አብደላ ከአካዳሚ 60 ነጥብ በማስመዝገብ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በአዋቂ ማውንቴን ውድድር ደግሞ ተማም እስራኤል እና አማኑኤል ዳጨው 88 እኩል ነጥብ በማምጣት እየመሩ ነው፡፡ በሴቶች ማውንቴን በረከት መኮንን በ21 ነጥብ እየመራች ስትገኝ በሁለተኝነት ቅድስት ይመር ከአካዳሚ ሃና ቡልቡላ እንዲሁም ትግስት ወንድም ዓለም በተመሳሳይ በ18 ነጥብ ይከተላሉ፡፡ በታዳጊ ወንዶች ማውንቴን ውድድር ሀብታሙ አየለ ከኦሮሚያ በ33 ነጥብ በአንደኝነት ሲመራ ዮሃንስ ተስፋዬ በተመሳሳይ ከኦሮሚያ እና ናትናኤል አጥናፉ በ29 ነጥብ ይከተላሉ፡፡ አሸናፊዎቹ ዛሬ በሚደረገው አጠቃላይ ውድድር ላይ የሚያመጡት ነጥብ ተደምሮ የሚለዩ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 19/2011
ዳግም ከበደ