
አብርሃም ተወልደ
የሀገሮች ወይም የህዝቦች ታሪክ በተለያዩ ፈርጆች በሚገለጽ የማንነት ክፍለ ወሰን ተቆራኝተው የሚኖሩ ህያው ሰዎች ወይም ተከታታይ ትውልዶች እንደ ማህበረሰብ በሚጋሩት ህይወት ካወሱት፣ከሆኑት፣ከፈለጉት፣ካለሙት በመነጨ ያጋጠማቸውን ወይም ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ በሚሏቸው ሁኔታዎች ዙሪያ የወሰዷቸው እርምጃዎች ውጤት ነው።ይህን ደግሞ በተወሰነ ሀገራዊ፣አካባቢያዊ፣ ዓለማዊ እና እምነታዊ መቼት ውስጥ ሆነው የሚያከናውኑት ነው።
ከዚህ አኳያ ሲታይ ታሪክ በአንድ በኩል የህዝቦች ተግባር ውጤት ሲሆን፣በሌላም በኩል ይህንኑ መልሶ የሚያቀጣጥል ሂደት ነው። በዚህም ከኅብረተሰብ የአንድ ወቅት ደግሞም ተወራራሽ የሆነ የማያቋርጥ እንቅስቃሴ የተነሳ ታሪክ እንደ ጅረት ተያይዞ የሚፈስ እንጂ እንደ ኩሬ በድንበር ተገድቦ የረጋ ወይም የተቀመጠ አይደለም።
ዘሪሁን ተሾመ “ኩርኩራ” በሚለው መጽሐፉ አንደጠቀሰው የሰው ልጅ ከእንስሳት የሚለየው ባለታሪክ በመሆኑ ብቻ አይደለም። ታሪክን አስቦና መርጦ በየዘመኑ የሚፈጥር ፣ ይህን አድርጎም በተረከበው ላይ የሚያክል የቀደምቶች ቅርስና ውርስ ነው፤በሚል ዝግ ተቀባይነት እና ወራሽነት ራሱን አለማሰሩ ነው። ይህ ሳይሆን ሲቀር የነገ መሰረትን እውን ማድረግ ባለመቻል አደራውን ፤ኃላፊነቱን እና ተረኛ አባትነቱን ያልተወጣ ይሆናል።
የዚህ ሁሉ ምክንያት የትናንት ውርስን ከዛሬ ህይወቱ … ሊያየው ከሚችለው የነገ እጣ ፈንታው ጋር አቀናጅቶ ሊያዘምንና ሊመርጥ በሚያስችል አስተሳሰባዊ ቅኝት የሚጠበቅበትን የሃሳብ ፍተሻ በማካሄድ ወደ ተግባር መለወጥ አለመቻሉ ነው። እኛም ባዛሬው ሳምንቱን በታሪክ አምዳችን እንደ ጅረት ከሚፈሰው ታሪክ አንዱን እንካችሁ ብለናል። ይህም ከህዝቦች የተግባር ውጤት ከሚገኘው የታሪክ ፈርጅ አንዱ ነው – ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል።
ሆስፒታሉን ኢትዮጵያውያን አዋጥተው እንደገነቡት ይገለጻል። ሰፊ ራእይ ተሰንቆ የተገነባ ሆስፒታልም ነው። በጊዜ ሂደትም በተለያየ ጊዜ ወደ ስልጣን የመጡ መንግሥታት የተለያዩ የማስፋፊያ ስራዎችን ያከናወኑለት እንደመሆኑም ግዙፍ ሆስፒታል ለመሆን በቅቷል።
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከዛሬ 47 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ህዳር 24 ቀን 1966 ዓ.ም ነበር። የሆስፒታሉ ግንባታ ተጠናቆ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተመረቀው ጥቅምት 24 ቀን 1966 ዓ.ም እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። አገልግሎት መስጠት የጀመረው በወሩ ሕዳር 24 ቀን 1966 ዓ.ም ነበር። በ1950 ዎቹ መጨረሻ እንደተጀመረ የሚነገረው የሆስፒታል ግንባታ፣ የፈሰሰበት መዋዕለ ንዋይ ደግሞ 21 ሚሊየን 605 ሺህ 399 ብር ነው።
ሆስፒታሉ መጀመሪያ “የልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል” እየተባለ ነበር የሚጠራው።ልዑል መኮንን ወደ አዳማ ሲጓዙ መንገድ ላይ ባጋጠማቸው የትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ልጅ ናቸው። በኋላ በደርግ ዘመን ይህ ስሙ ተሽሮ ከ1968 ዓ.ም አንስቶ “ጥቁር አንበሳ” ተብሎ መጠራት ጀመረ።
“ጥቁር አንበሳ” በጣሊያን ወረራ ወቅት ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈሉ እና በ1928 ዓ.ም የተመሠረተው የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት የመጀመሪያዎቹ ምሩቆች የነበሩ ወጣት ዓርበኞች የትግል ስም ነው።ሆስፒታሉ በዚህ ስም እንዲጠራ የተደረገው የእነዚህ ለጋ ወጣቶች ጀግንነትንና የአገር ፍቅር ስሜት ለትውልድ እንዲተላለፍ ታስቦ እንደሆነ ይነገራል።
ሐሙስ ህዳር 27 ቀን 1966 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ “የልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል ስራ ጀመረ” በሚል ርዕስ ይዞት በወጣው ዘገባ “በኢትዮጵያና በመላው ምሥራቅ አፍሪካ በትልቅነትና በዘመናዊነት ተወዳዳሪ የሌለው የልዑል መኮንን ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ለበሽተኞች በሩን በመክፈት አገልግሎት መስጠቱን ቀጥሏል።”ሲል አስነብቧል።
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተገነባው 500 አልጋዎች እንዲኖሩት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ስራ የጀመረው በ 150 አልጋዎች ብቻ ነበር። ዛሬም 67 በመቶ ነጻ ህክምና የሚሰጠው ሆስፒታሉ ሲመሰረት 25 አልጋዎች ነጻ ህክምና ለሚሰጣቸው ችግረኞች መድቦ ነበር።
ሆስፒታሉ ስራ የጀመረው በኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ መንግሥታት መካከል በተደረገ ስምምነት በሁለቱ አገራት የህክምና ባለሙያዎች ጥምረት ነው።አገልግሎት መስጠት የጀመረው በ 18 ሐኪሞች ሲሆን ከእነዚህ የህክምና ባለሙያዎች መካከል ስድስቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። በወቅቱ በሆስፒታሉ ከነበሩት 25 ነርሶች 12ቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ የስዊዝ ነርሶች ነበሩ።በተጨማሪም 22 ኢትዮጵያውያን “ድሬሰሮች” ነበሩት።
የሆስፒታሉ አልጋዎች ሦስት ደረጃዎች ነበሯቸው። አንደኛ ደረጃ አልጋ እንደ ክፍሉ ይዞታ ከ30 እስከ 50 ብር እንዲሁም ለሁለተኛ ደረጃ አልጋ ደግሞ 12 ብር ይከፈል ነበር። በእነዚህ ሁለት የአልጋ ክፍሎች የሚታከሙ ታካሚዎች ለሚያገኙት የህክምና አገልግሎት ተጨማሪ ክፍያ ይፈጽማሉ።
ሦስተኛ ደረጃ አልጋ ክፍል ግን ለየትኛውም አይነት የህክምና አገልግሎት የሚውል ነበር፤ ለአልጋው በድምሩ በቀን የሚከፈለው 10 ብር ነበር። ተመላላሽ ታካሚዎች ለምዝገባ የሚከፍሉት የሦስት ብር ክፍያ ሁሉንም አይነት የላብራቶሪ ምርመራ ጭምር የሚያካትት ነበር።
በሁሉም ደረጃ የመኝታ ክፍሎች ውስጥ በእያንዳንዱ አልጋ አጠገብ የሬዲዮ ዜናዎችና ሙዚቃ ለመስማት ለሚፈልጉ ታካሚዎች ሁሉ ቴፖች ተዘጋጅተውላቸው ነበር። ታዲያ የአንደኛው ፍላጎት የሌላውን ጸጥታ እንዳያውክ በሚልም በጆሮ ላይ የሚደረጉ የማዳመጫ መሳሪያዎች ተዘጋጅተውላቸዋል።
የሆስፒታሉ ክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረ ህይወት ከወራት በፊት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ፣ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲመሠረት አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 25 ሚሊዮን አካባቢ ነበር የሚገመተው። በዚያ ዘመን ዘመናዊ ሕክምናን የመጨረሻው አማራጭ ተደርጎ ነበር የሚታሰበው።
በወቅቱ ኢትዮጵያውያን ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ የሕክምና ዘዴዎችን ነበር የሚያዘወትሩት። ስለዚህም ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ተገልጋዮች ቁጥር በጣም ውስን ነበር። ሆስፒታሉ ስምንት ወለሎች ቢኖሩትም አልጋ የነበረው ግን እስከ አምስተኛ ፎቅ ድረስ ብቻ ነበር። ያኔ ሕንፃው ከበቂ በላይ በመሆኑ ከስድስተኛ እስከስምንተኛው ፎቅ ድረስ ያሉት ክፍሎች ባዶ ነበሩ።
አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር የሚገኘው ሆስፒታሉ በየጊዜው የአልጋዎቹን ቁጥር እያሳደገ መጥቶ አቅሙን አሟጥጦ በመጠቀሙ ትርፍ የሚባል ክፍል የለውም። ከመሬት ጀምሮ እስከ ስምንተኛው ፎቅ ድረስ በአልጋ ተሞልቷል።በዋነኝነት አገልግሎት የሚሰጠው የደሃ ደሃ ለሆኑ ዜጎች ነው ማለት ይቻላል። 67 ከመቶ የሚደርሱት ታካሚዎች ከሚኖሩበት አካባቢ የደሃ ደሃ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ሠርፍኬት ይዘው የሚመጡ ናቸው።
ዛሬ ጥቁር አንበሳ 1 ሺ 100 ገደማ ከጀማሪ እስከ ሰብስፔሻሊስት ደረጃ ያሉ ሀኪሞችንና 930 ነርሶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 3ሺህ400 ሠራተኞች አሉት፤በበርካታ ዘርፎች ህክምና የሚሰጥ ግዙፍ ሆስፒታል ሆኗል። በሌሎች የህክምና ተቋማት የማይሰጡ የካንሰር ሕክምናዎች በአብዛኛው ተሟልተው የሚገኙበት ብቸኛ ሆስፒታል ነው። ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ የካንሰር ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በሁሉም የሕክምና ዘርፎች በውስጥ ደዌ፣ በሕፃናት፣ በማሕፀንና ፅንስ፣ በቀዶ ሕክምና እንዲሁም በሌሎች የሕክምና መስኮችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የካንሰር ሕክምናዎች ይሰጣል። በድንገተኛ አገልግሎትም በዓመት እስከ 40 ሺህ ሰዎች ይታከማሉ። የአጥንት ሕክምና አገልግሎትም እየሰጠ ይገኛል። በአጥንት ሕክምና ረገድ ሰው ሠራሽ መገጣጠሚያዎችን የመትከል አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም ነው።
ባሳለፍነው ዓመትም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስለ ህክምና ተቋሙ ባስነበበው ዘገባ ተቋሙ የህክምና ተቋም እንደሆነ ጠቅሶ በተጓዳኝ የሚሠራቸው ሥራዎችም እንዳሉትም ያትታል። ሆስፒታሉ ለራሱና አገሪቱ የጤና ተቋማት በመስኩ የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት መልስ በመስጠት ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው።በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ 6ሺ500 የሚደርሱ ተማሪዎችን ያስተምራል።
በድህረ ምረቃ የስፔሻሊቲና ሰብስፔሻሊስት ትምህርትም ሀኪሞችን በማፍራት ላይ ይገኛል።በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ከሚገኙ ተቋማት ምርምር በመሥራትና በማሳተም ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የአንደኛነት ደረጃን ተቆናጧል።
ሆስፒታሉ አሰራሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዘመነ በመምጣት ለተገልጋዮቹ ዘመኑን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት በሚያደርገው ጥረት ብዙ መሻሻሎችን ያሳየ ቢሆንም፣የአንዳንድ የህክምና መሳሪያዎች አለመሟላትና የመድሃኒት እጥረት ያልተቀረፉ ችግሮቹ ሆነው ዘልቀዋል። በሆስፒታሉ ውስጥ መሠራት ካለበት የላቦራቶሪ ቴስት ሜኑ 16 በመቶው እየተሰራ አይደለም።የመድኃኒት አቅርቦቱም ከ65 እስከ 70 በመቶ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2013