በጋዜጣው ሪፖርተር
አንድ የውጭ ሀገር ሰው ከአንድ ኢትዮጵያ ወጣት አስጎብኚ ጋር ሲወያዩ አሰጎብኚው «እኛ ኢትዮጵያውያን ባህላችንን ጠባቂ ነን ።ሐይማኖተኛነታችን፣ ሥነ-ምግባራችን፣ ታማኝነታችን ፣ ቃል አክባሪነታችን ፣ አነጋገራችን፣ ቋንቋችን … ወዘተ የተለየ ነው» እያለ ብዙ ነገር ይዘረዝርለታል ።ጎብኚው ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሩ ሊመለስ ሲል «እንዴት ነው ታዲያ ሀገራችንን እንዴት አየሃት?» በማለት አስጎብኚው ጠየቀው።
ጎብኚውም «የነበረው ባህል ደስ ይላል» ሲል መለሰለት። አስጎብኚው ቆጣ ብሎ «እንዴት የነበረው ትላለህ?» ሲል መለሰለት «ያልከውን አይነት ኢትዮጵያዊነትን ባንተ ውስጥ አላየሁትማ ።ምላስህ ላይ እንጂ የነገርከኝ ኢትዮጵያዊ ባህል በህይወትህ ውስጥ ሳትናገር የሚናገር፣ ሳትጠቅስ የሚጠቀስልህን ባህል ባንተ ውስጥ አላየሁም» በማለት እንደመለሰለት ይነገራል፡፡
ይህን ያለበት ምክንያት አስጎብኚው በተግባር ልዩ መሆኑን ሊያሳየው ባለመቻሉ ነበር። እኛስ ስለባህላችን በምንናገረው ልክ እየኖርንበት ይሆን? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ሆነብኝ። ምክንያቱም ሰብዓዊ የሆነው ኢትዮጵያዊው ጠባያችን በውስጣችን ቢኖርም በምግባራችን ሲገለፅ አይስተዋልምና!
ባህል እንደ ታሪክ የሚጠቀስ ሳይሆን በህይወታችን ልንኖርበት የሚገባ ነገር በመሆኑና ባህል በመሆን ህይወት ውስጥ ህያው ይሆናልና ነው ።በምሳሌ የተንደረደርኩት ካለምክንያት አልነበረም ስለወጣትነትና ባህል ጥቂት ለመጨዋወት በማሰቤ ነው።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በአንድ ወቅት ቤተ መዛግብትና ቤተመፃህፍት ኤጀንሲ እና የዓለም ሰላም እና እርቅ ድርጅት ጋር በመሆን የህዝበ ገለፃ (ፐብሊክ ሌክቸር) «ወጣትነትና ስነ-ምግባር በኢትዮጵያ» በሚል ርእስ አካሂዶ ነበር።
በእለቱም«ስነ-ምግባርና ወጣትነት ድሮና ዘንድሮ» በፕሮፌሰር ፍሰሃፅዮን መንግስቱና «ባህል፣ ስነ-ምግባርና ወጣትነት በኢትዮጵያ» በሚሉ ርእሶች በወጣት ፀጋአብ ለምለም ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርቦ ነበር። ከቀረቡት የውይይት መነሻ ፅሁፎች መካከል በወጣት ፀጋአብ ለምለም በቀረበው ፅሁፍ ላይ ተመስርተን ባህልና ወጣትነት ላይ አተኩረን እንጨዋወታለን፡፡
የሰው ልጅ በኑሮ ሂደት ውስጥ ካሉት ሁለንተናዊ መገለጫዎች አንዱና ዋነኛው ባህሉ ነው ።ባህል የሰው ልጅ ማንነቱ መገለጫም ነው ።ህዝቦች በሚኖሩበትና ለመኖር በሚያደርጉት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ ተግባራት ውስጥ ባህልና እሴቶች የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው ።በተለይ ህዝባዊና ማህበረሰባዊ ባህሎችና እሴቶች በግለሰቦችና እያንዳንዱ የህዝብ አካል ውስጥ ያላቸውና የሚኖራቸው ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው ።
ይህ ተፅዕኖ ሂደት እንደመሆኑ መጠን ሊነሳ፣ ሊወድቅ፣ ሊቀየር፣ ሊለወጥ፣ ሊረሳ፣ ሊጠፋ … ወዘተ ይችላል ምክንያቱም ጊዜና የተለያዩ ሁነቶች ለዚህ ሊዳርጉት ይችላሉና፡፡
ባህልን ከዘርፍ አንጻር በአራት ከፍለን ልንመለከተው እንችላለን ።ሥነ- ጽሑፋዊ ጥበቦች፤ እይታዊ ጥበቦች፤ትዕይንታዊ ጥበቦች እና የዕደ ጥበብ ናቸው ።የሰው ልጅ በነበረው፣ ባለውና ለወደፊቱም እስካለ ድረስ በሚኖረው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ነበረኝ፣ አለኝና ይኖረኛል የሚለው ነገር ባህሉንና ዕሴቱን ነው፡፡
ባህሉንና ዕሴቱ የማንነቱ መገለጫዎች ናቸው ።መገለጫው ደግሞ የአኗኗር ሁኔታውን ከሌላው በተለየ መልኩ እንዲታይ ያደርገዋል ።የባህል እሴቶች መዳበር ለሀገር የሚኖረው ሁለንተናዊ ፋይዳ ከፍተኛ ነው ።ፋይዳውም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ነው ።አሁን የቴክኖሎጂና የግሎባላይዜሽን (ሉዓላዊነት) ዘመን ላይ እንደመሆናችን መጠን ትልቁ ፈተና ያለው ከዚህ ጋር አብሮ የመራመድ፣ ተፅዕኖን የመቋቋም፣ የማሳደግና የማስፋት፣ጠብቆ የማቆየት እንደሚሆን ይታመናል፡፡
ዋናው የትኩረት ነጥብም “የሰው ልጅ በህብረተሰብ ውስጥ የሚይዘው” ይሆናል ።የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጡሮች በተለየ መልኩ የራሴ የሚለው ባህል አለው ።ይህ ባህሉ ትላንት የነበረ፣ ዛሬም ያለው እንዲሁም የሰው ልጅ በህይወት እስካለ ድረስ አብሮት የሚኖር ሀብቱ ነው ።ይህ ሀብት በጊዜ ሂደት ሊረሳ፣ ሊያድግ፣ ሊለወጥ፣ ሊሰፋ፣ ሊዳብር፣ ሊቀየር፣ሊበረዝ ይችላል ።የሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤው ጋር እንዲሁ እየተለዋወጠ እንደ ሄደ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
እንደ የማህበረሰብ ሳይንስ አጥኚዎች እምነት ባህል ሰዎች አካባቢያቸውን ለማሸነፍ እና ለኑሮ የተመቸ እንዲሆን ለማድረግ ያዳበሩት የህይወት መመሪያ ነው ።ይህም የህይወት መመሪያ የባህሉ ባለቤት የሆኑ ሰዎች በተግባቦት የሚጋሯቸው ዕውቀቶች፣ ሀሳቦች፣ እሴቶች፣ ምልክቶች፣ አስተሳሰቦች፣ እምነቶች እንዲሁም የማህበረሰቡ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ሀብቶችን ያጠቃልላል ።በሌላ በኩል «ባህል ህዝብ በማህበረሰብ ውስጥ፤ ህዝብ በጋራ ኑሮው ውስጥ፤ የሚማረው፣ የሚፈጥረው እናም የሚያካፍለው አስተሳሰብ እና ጠባይ ነው፡፡
ባህል አንድን ህዝብ ከሌላው ይለየዋል ማለትም ልዩ ያደርገዋል ሲባል የህዝብን ዕምነት፣ መመርያ፣ ቋንቋ፣የእምነት ክንውኑን፣ ስነ ጥበቡን፣ ቴክኖሎጂውን፣ አለባበሱን፣ የምግብ አሰራሩን፣ የዕቃ መገልገያውን፣ ሐይማኖቱን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስርአቱን ያካትታል ።ባህል በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚጫወተው ሚና እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡
የባህል ዕሴቶች የምንላቸው በባህል ውስጥ ያሉንን ሀብቶች ነው ።እነዚህ ሀብቶች የሚጨበጡና የማይጨበጡ፤ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ብሎም የሚታዩና የማይታዩ ናቸው ።ባህላዊ ዕሴቶች በተለያየ መንገድ ይገለጻሉ አልያም ይታያሉ፡፡
ባህላዊ ዕሴቶች መገለጫዎች የሀይማኖት በዓላት፣ ህዝባዊ በዓላት፣ታሪካዊ ቦታዎችና መዳረሻዎች፣ አልባሳት፣ኪነጥበብ ስራዎች፣ ስነ ጽሑፍ፣ የአመጋገብ ስርአት፣ የሐዘን ስርአት፣ የጋብቻ ስርአት፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣የቤት አሰራር፣ ሙዚቃና የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ አጨፋፈርና አዘፋፈን፣ ዜማዎች፣ ሰላምታ፣ ማህበራዊ ግንኙነቶች፣ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች፣ የማስታወቂያ ስራዎች፣ አርክቴክቸር፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ የልብስ ፋሽኖች፣ፊልምና ቪዲዮ ቀረጻ፣ ድምጽና ምስል ሥራዎችን፣ ግራፊክስ ዲዛይን፣ የትምህርትና የመዝናኛ ሶፍትዌሮች፣ትዕይንታዊ ጥበባትና መዝናኛዎች፣ ቴሌቪዥን፣ የሬዲዮና የኢንተርኔት ሥርጭቶች፣ ሕትመትን ወዘተ የሚያጠቃልሉ ናቸው፡፡
በሌሎች ሀገሮች ዘንድ የሚታወቀው ኢትዮጵያዊ ጠባይ “ፈሪሃ ፈጣሪ፤ ትሕትና፤ ርኅራሄ፤ ታማኝነት፤ ቃል ኪዳን መጠበቅ (ቃሉን አክባሪነት)፤ እንግዳ ተቀባይነት፤ እውነተኛነትና ሐቀኝነት ቃሉን አያጥፍም፤ በራሱ ይመሰክራል፤ቅጣት የሚያስከትልበትም ቢሆን ያደረገውን አይክድም፤ በነፍስ ግዳይ የተያዘ ቢሆን እንኳ (ቢያናድደኝ ቢዝትብኝ ገደልኩት ይላል እንጂ «አልታየሁም» በማለት የሚያከራክርና የሚያጓትት ነገር አያመጣም፡፡) በማለት ነው የሚታወቀው።
ባህልን ማወቅ ለወጣቶች እጅግ አስፈላጊ ነው ።ምክንያቱም ከትውልድ ትውልድ ይሸጋገር ዘንድ ሰፊ ቁጥር ያለው ወጣት የማይተካ ሚና አለው ።ከትውልድ ትስስር፣ ከተስፋ፣ ከሁለንተናዊ እንቅስቃሴ፣ ከማስተዋወቅ፣ ከሀገር ተረካቢነት፣ ከእውቀት፣ ከማንነት ወዘተ አንጻር የሚታይ ይሆናል ።ሁለንተናዊ አቅሙን የመገንቢያ አማራጭ መንገድ ነው፡፡
ለወጣቶች የባህል ልማት ኢንዱስትሪ ማለት የተቀናጀ ህዝቦች የተሳተፉበት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንደመሆኑ መጠን፤ የባህል ኢንዱስትሪም እንዲሁ ህዝቦች የሚሳተፉበት የተቀናጀና በደንብ የተደራጀ ባህላዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማለት ነው ።ይህ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም ለአገልግሎት፣ ለምርት፣ ለስርጭት፣ ለግንባታና ለምርት ግብይት ሊሆን ይችላል፡፡
እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ገለጻ “የባህል ኢንዱስትሪ ማለት ባህል ነክ የሆኑ እውቀቶችን፣ ክህሎቶችንና ሀብቶችን በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ ባህላዊ የምርት ውጤቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ሲሆኑ መሰረታቸውም ባህላዊ ዕውቀቶችና ፈጠራዎች ናቸው” መሆናቸውን ያስቀምጣል ።ሀገራት እንደየራሳቸው ሁኔታ የባህል ኢንዱስትሪያቸውን በተለያየ መንገድ ይከፍሉታል፡፡
ይኸውም ሥነ – ጽሑፋዊ ጥበቦች ድርሰቶች(ልብ ወለዶችና ኢ- ልቦለዶች)፣ ግጥሞች፣ ተውኔቶች፣ ሥነ ቃሎች፣ መነባንቦች … ወዘተ ናቸው ።እይታዊ ጥበቦች የሥዕል፣ የፎቶ ግራፍ፣ የምልክት ስራዎች፣ የፊልም፣ የድራማ፣ የጭውውት፣ የኪነ – ህንጻ ስራዎች፣ የፋሽን፣ የዲዛይን፣ … ወዘተ ናቸው ።
ትዕይንታዊ ጥበቦች በትዕይንት የተሞሉ የሙዚቃ፣ የትያትር፣ የውዝዋዜ፣ የጭፈራ፣ ባህላዊ የሐዘንና የደስታ መገለጫዎች የሆኑ ተግባራት፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ የቅዳሴና መሰል የሐይማኖት በዓላት መገለጫዎች በዚህ የሚካተቱ ይሆናል፡፡
የዕደ ጥበብ ሙያ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ሰው በነጠላም ይሁን በቡድን በመሆን ልዩ ተስጥኦውን በመጠቀም ለዕለት ተዕለት የሚውሉ ቋሚና አላቂ የሆኑ ቁሳዊ ምርቶችን የሚያመርትበት ሙያ ተኮር ዘርፍ ነው ።በዚህ ዘርፍ የእንጨትና የቆዳ፣ የቅርጫት፣ የስፌት፣ የቀርከሃ፣ የሽመና እንዲሁም የጌጣ ጌጥ ስራ ወዘተ ያጠቃልላል፡፡
የግሎባላይዜሽን ተጽዕኖ (በእምነት፣በእውቀትና በድርጊት) የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ከውስጥ ይልቅ ወደ ውጭ መሆን፤ ያለን ንቃተ ህሊናና ግንዛቤ ያልሰፋ መሆን፤ ለባህል ያለን ግንዛቤ ከኃላቀርነት ጋር ማያያዝ፤ ኢትዮጵያዊ ጠባያትን መዘንጋትና አለመላበስ፤ የአነጋገርና የአለባበስ ስርዓታችን መዛባት፤ (ከአነጋገር ይፈረዳል ከአያያዝ ይቀደዳል፤ ከአፍ የወጣ ቃል ከእጅ የወደቀ እንቁላል፤) ለዚህም ስድቦቻችንና አካሄዳችን ማሳያ ነው ።ለዚህም ማሳያው የወንጀሎች መበራከት፣ ኢትዮጵያዊ ጠባያት መደብዘዝ … አጀንዳችን ፍሬከርሲኪ መሆኑ መዝናኛችን የውጭ ሀገር ወሬዎች ላይ ማተኮሩ ወዘተ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
የሚያሳዝነው – የሚያሳፍረው – የሚያስቆጨው ለምን? እንዴት? ስለምን እንደሚኖር? የመጪ ዓመት እቅዱን ትርጉም ባለው መልኩ የማያውቅ ወጣት ስለአንድ እግር ኳስ ተጫዋች ማንነት፣ ታሪክ፣ ሀሳብ፣ ዕቅድ፣ትውልድም፣ ምርጫ (የምግብና አልባሳት)፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ … በደንብ ጉዳዬ ብሎ፤ ያገባኛል ብሎ ይከታተላል ።
የመረጃና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ያለብን ውሱንነት፤ (የማህበራዊ ድረገፆች፣ የሞባይል፣ የኢንተርኔት…ወዘተ አጠቃቀማችን) የሌሎች መጠቀሚያ መሆን፤ (በቲሸርት፣ በጥቅስና በምልክት …) እንደ ወረደ መቀበልና የውጭ አምላኪነት አባዜ፤ ለራሳችን እንኳ ጊዜ ያለመኖር፡፡
ስለህይወታችን የምናስብበት፣ የምንመራመርበት፣ የምንጠይቅበትና የምንገመግምበት ጊዜ ያለመኖር። ትርጉም ያለው የንባብ ባህላችን ደካማ መሆኑ፤ ትምህርት ለዕውቀት ሳይሆን ለወረቀት ብቻ መሆኑ፤ በዚህም ጥናትና ምርምር ስራዎች ደካማነት፤ አፋዊ – ባህል አክባሪነት ተጠቃሾች ናቸው።
መፍትሔዎች
የመንግስት ድጋፍን ማሳደግ፤ የሐይማኖት አባቶችና የአረጋውያን ሚናን ከፍ እንዲል መስራት፤ ዕውቀትን ማሳደግና ማስፋት፤ የባህል ኢንቨስትመንት ማበረታታት፤ የተለያዩ ባህል ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ቡድኖችን (think tank group) እንዲበራከቱ ዕድል መስጠት፤ ባህልን በስርአት ትምህርት ውስጥ ሰፊ ቦታ እንዲኖረው ማድረግ፤ በተለያየ ትምህርት ቤቶች ከታችኛው ክፍል እስከ ከፍተኛ ተቋማት ድረስ የባህል ክበባትን ማቋቋም፤የማህበረሰብ የባህል ልማት መርሃ ግብር መቅረጽ ባህል ተኮር የፈጠራ ክህሎት ማዳበሪያ ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል።
እንዲሁም የባህል ኢንዱስትሪ ትብብር መርሐ ግብር የባህል ኢንዱስትሪ ጥናትና ምርምር ተቋም ማቋቋም፤ የባህል ማዕከላትና ተቋማትን ማስፋፋትና ማጠናከር የአዕምሮአዊ ንብረት ጥበቃ አፈጻጸምን ማሻሻልና የማስተዋወቅ ስራ መስራት ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያን ባህል ኢንዱስትሪ የተመለከተ ድረ ገጽ መክፈት ግብረ ገብነትና የባህል ትምህርት በትምህርት ስርዓት ውስጥ ማካተት፤ ትርጉም ያለው የንባብ ባህልን ማሳደግ፤ እራሱን የሚያውቅና እራሱን የሚሆን ትውልድ ማበራከት፤ ምክንያታዊና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ወጣትን ማብዛት፤ በሀገራችን የባህል ኢንዱስትሪ ዞን ማቋቋም – – – ወዘተ ወሳኝነት አለው።
በተለይም በእምነት፣ በእውቀት፣ በድርጊት ላይ ሰፊ ሥራ መስራት አስፈላጊ ይሆናል ።ይህንንም ለማድረግ በዕውቀት የዳበረ፣ ችግር ፈቺና መፍትሔ ፈላጊ የሆነ ትውልድን ትርጉም ባለው የንባብ ባህልን በማስፋትና በማዳበር ማበራከት አስፈላጊ መሆኑ ጊዜና ወቅቱ የሚጠይቀው ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2013