ዓለም አቀፍ መድረኮች – ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት

ሀገሮች ቱሪዝምን መሠረት ያደረጉ በርካታ ዓለም አቀፍ የንግድ ዓውደ-ርዕይና ትርዒቶችን ያዘጋጃሉ። የቱሪዝም መስህብ ያላቸው ሀገራትም ጎብኚዎችን ለመሳብና ገፅታ ለመገንባት በእነዚህ ዓለም አቀፍ መሰናዶዎች ላይ ይሳተፋሉ። ባሕላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና መሰል እሴቶቻቸውን (የቱሪዝም መዳረሻዎቻቸውን) የሚገልፁ ማስታወቂያዎችና ዝግጅቶችን በማሰናዳትም ተደራሽነታቸውን ለማስፋት ይጥራሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም የንግድ ትርዒቶችና ዓውደ-ርዕይ ዝግጅቶች ተቀባይነታቸው እየጨመረ መጥቷል። ቱሪስቶች የጉብኝት እቅድ ለማውጣትና በቂ መረጃ ለማግኘት በእነዚህ መሰናዶዎች ላይ ትኩረታቸውን ያደርጋሉ። ሀገራቱም አስጎብኚዎች፣ የቱሪዝም ተቋማትን እና መሰል ባለድርሻዎችን በትርዒቶቹ ላይ በማሳተፍ አስፈላጊ የሚሏቸውን መረጃዎች ተደራሽ ያደርጋሉ። ይህ ጥረት ለዓለም አቀፍ የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ተቋማት ይገልፃሉ።

በዓለማችን በቱሪዝም ትርዒትና ዓውደ-ርዕይ ከሚታወቁ ቀዳሚ ዝግጅቶች መካከል በየዓመቱ መጋቢት ወር ላይ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚካሄደው አይ.ቲ.ቢ በርሊን /የዓለም ትልቁ የቱሪዝም ኤክስፓ/ ተጠቃሽ ነው። ይህ ዓለም አቀፍ ዓውደ-ርዕይ እ.ኤ.አ በ1966 ስያሜውን ይዞ ከአምስት ሀገራት በተውጣጡ ዘጠኝ ተሳታፊዎች የተጀመረ ነው። እስከ እ.ኤ.አ 2019 ድረስ በተመዘገበው መረጃ መሠረትም በየዓመቱ በመሰናዶው ላይ ሁለት መቶ ሺ የሚደርሱ ጎብኚዎች ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም የቱሪዝም ሀብቶቿን ለማስተዋወቅ በዚህ ዝግጅት ላይ በአስጎብኚ ድርጅቶች፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም በቱሪዝም ሚኒስትር በመወከል ትሳተፋለች። ዘንድሮም በበርሊን ጀርመን የተካሄደው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኤግዚቢሽን (ITB) በይፋ ሲከፈት ኢትዮጵያ መሳተፏን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል። ይህ ኤግዚቢሽን በመላው ዓለም የሚገኙ ስመጥር የቱሪዝም ኩባንያዎችና ሀገራት የቱሪዝም አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ እንደመሆኑ ኢትዮጵያም የዚህ እድል ተጠቃሚ ለመሆን ተሳታፊ መሆኗን አስታውቋል።

በዓውደ-ርዕዩ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ተገኝተው ኢትዮጵያ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት እያከናወነች ያለችውን የመዳረሻ ልማትና የቱሪስት መስሕቦችን አስተዋውቀዋል። ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋርም ለመሥራት የሚያስችላቸውን ውይይት ማድረጋቸውን የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ጌታቸው ለዝግጅት ክፍላችን መረጃ አስታውቀዋል።

በዘንድሮው የበርሊኑ አይ.ቲ.ቢ ዓውደርዕይ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ የሀገር ውስጥ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪዎች ተሳትፈዋል፤ ኢትዮጵያ አይ.ቲ.ቢን ጨምሮ የቱሪዝም መስሕቦችን ለማስተዋወቅ በተለያዩ ጊዜያት በበርካታ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕዮች ላይ ተሳትፋለች።

እውቅ ዝግጅቶች በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተመራጭ ከመሆናቸውም በላይ በርካታ ቱሪስቶችን ለማግኘትና መስሕቦችን ለማስተዋወቅ ሁነኛ አቅሞች ናቸው። በእነዚህ ታዋቂ ዓውደ-ርዕዮች ውስጥ የቫንኮቨር ዓለም አቀፍ የጉዞ ኤክስፖ፣ የኒዮርክ ታይምስ የጉዞ ትርዒት፣ የላስ ቬጋስ የጉዞ ወኪሎች ፎረምና የዓለም የጉዞ ገበያ በለንደን ይገኙበታል።

አቶ ጌትነት ይግዛው በቱሪዝም ሚኒስቴር ኮንቬንሽን ቢሮ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ጊዜያት የቱሪዝም መስሕቦቿን በዓለም አቀፍ አውደ ርዕዮች ላይ ስታስተዋውቅ ሀገሪቷን በመወከል ይታወቃሉ። በርከት ባሉ መሰል ዝግጅቶች ላይ ይሳተፋሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኤክስፖዎችንና የንግድ ዓውደ-ርዕዮችን ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚካሄዱት ባሕላዊ ገበያዎች ይመስሏቸዋል። ነጋዴዎች ምርቶቻቸውን ለመሸጥ እነዚህን ባሕላዊ ገበያዎች እንደሚጠቀሙት ሁሉ ኢትዮጵያም በታዋቂ የንግድ ትርዒቶች፣ ኤክስፖዎችና ዓውደ ርዕዮች ላይ ተሳታፊ በመሆን የቱሪዝም ሀብቶችን፣ ባሕላዊ እሴቶችን፣ ታሪካዊ ቦታዎችንና መሰል የዘርፉ ሃብቶችን ለማስተዋወቅ እንዲሁም ጎብኚዎችን በመሳብ ጥቅሎችን ለመሸጥ እንድትችል ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡

በእነዚህ ዓውደ-ርዕዮች ላይ የገበያ ስልቶችን ተጠቅሞ የኢትዮጵን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅና የቱሪዝም ምርቶችን ለመሸጥ እድል የሚከፍት ነው የሚሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ አራት አይነት የገበያ አይነት ወይም መንገዶች መኖራቸውን ይናገራሉ። የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ያሏትን ባሕላዊ እሴቶችና ምርቶች፣ ታሪካዊ ስፍራዎችና የመስሕብ መዳረሻዎችን የሚወክሉ ምርቶችን ጥራት ባለው መንገድ በዓውደ-ርዕዮቹ ላይ ማቅረብ እንደሆነ ይገልፃሉ።

አቶ ጌትነት እንደሚናገሩት፤ ከገበያ ስልቶቹ በኢንተርናሽናል የቱሪዝም ኤክስፖና ዓውደ-ርዕዮች ላይ ተግባራዊ የሚደረገው ሁለተኛው ተግባር ማስተዋወቅ ነው፡፡ ለኢትዮጵያም አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ ባሕላዊ እሴቶች፣ የቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍ አገልግሎቶችን፣ ሌሎች የዓለም ሀገራትና ጎብኚዎች የማያውቋቸውን የቱሪዝም መስሕቦች ለማስተዋወቅ በር ይከፍታል፡፡

ሌላው በገበያ ስልት ውስጥ የሚጠቀሰው ቦታ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች አስተዋውቆ ቱሪስቶችን በብዛት ለማግኘት የሚቻልበትን ትክክለኛ ስፍራ መለየት እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህ ሳይንሳዊ ስልት አንፃር በዓለም በጉብኝት ባሕላቸው የሚታወቁት ምዕራባውያን፣ በኤሺያና ሌሎች አሕጉራት በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ዓውደ-ርዕዮች የኢትዮጵያን እሴቶችና የመስሕብ ሀብቶች ማስተዋወቅ ትክክለኛው አማራጭ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያም ሀብቶቹን በጥራት ማስተዋወቅ በሚቻልባቸው ኤክስፖ፣ ዓውደ-ርዕይና ትርዒቶች ላይ በተደጋጋሚ መቅረብ እንደሚጠበቅባት ያስረዳሉ። የኢትዮጵያን የመስሕብ ስፍራዎች የሚጎበኙ ሁሉ አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ለማድረግና ለማስተዋወቅ መድረኮቹ ጠቃሚ ስፍራዎች መሆናቸውን አቶ ጌትነት ይገልፃሉ።

በዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕዮች ላይ በሆቴል ዘርፍ የሆቴል ባለቤቶች እንዲሁም በአስጎብኚ ድርጅቶች (tour operators) አማካኝነት ኢትዮጵያ መወከል ይገባታል የሚሉት አቶ ጌትነት፤ እንደየቱሪስቱ ፍላጎትና ባሕሪ የተፈጥሮ ቱሪዝም፣ የባሕል ቱሪዝም፣ በታሪክና ቅርስ ላይ መሠረት ያደረጉ ጥቅሎችን አዘጋጅተው ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የማስተዋወቅ ሥራ መተግበር እንደሚገባቸው ይናገራሉ። ይህን መሰል ተግባር ለማከናወን ደግሞ እንደ አይቲቢ በርሊን ያሉ ታዋቂ ዓለም አቀፍ መድረኮች ተመራጭ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

‹‹ከአስር ዓመት በፊት ኢትዮጵያ 12 በሚደርሱ ዓለም አቀፍ የገበያ መድረኮች ላይ ተሳትፋ ነበር›› የሚሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ አሁን ግን ቁጥሩ በጣም ዝቅ ብሎ አይ.ቲ.ቢ በርሊንና የዓለም የጉዞ ገበያ በለንደን ላይ ብቻ እየተሳተፈች እንደሆነ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ መሰል ዓለም አቀፍ መድረኮችን መሳተፍ የጀመረችው የቱሪዝም አባት ተብለው በሚታወቁት አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ አማካኝነት ከ1970ዎቹ ጀምሮ እንደነበርም ይገልፃሉ። ይህ ልምድ እየቀነሰ መምጣቱ ተገቢ አለመሆኑን አስገንዝበው፤ ዳግም ሊነቃቃ እንደሚገባ ይመክራሉ።

መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንደሚያብራሩት፤ በታላላቅ ዓውደ-ርዕዮቸ ላይ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስሕቦች ለማስተዋወቅ በትክክለኛው ቦታ ተገቢ ባለሙያ መጠቀምም አስፈላጊ ነው። ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብት በፍፁም ሙያዊ ሥነ-ምግባርና በጥልቅ እውቀትና መረጃ ታግዞ ለቱሪስቶች ማስተዋወቅና ውጤት ማምጣት ይቻላል። የተቋም ግንባታ አስፈላጊ ቢሆንም ትክክለኛና ተገቢ ባለሙያዎችን ማሳተፍ የማይቻል ከሆነ በመሰል መድረኮች ላይ መሳተፍ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

አቶ ጌትነት ከ12 ዓለም አቀፍ የማስተዋወቅ መድረኮች ወደ ሁለት የተወረደበት ምክንያት በተለያየ ጊዜ የሚፈጠረው የአደረጃጀት ለውጥ ተፅዕኖ መሆኑን ይገልፃሉ። መድረኮቹ ላይ በመሪነት ይሳተፍ የነበረው መዋቅር አንድ ጊዜ በባሕልና ቱሪዝም ሌላ ጊዜ ደግሞ በቱሪዝም ድርጅትና በቱሪዝም ኢትዮጵያ በሚሉ ስያሜዎች በየጊዜው የመዋቅር ለውጥ እያመጣ መደራጀቱና አለመረጋጋቱ በቋሚነት፣ በጥራትና በብዛት የንግድ ትርዒቶቹ ላይ ኢትዮጵያ ተሳታፊ እንዳትሆን እንቅፋት መፍጠሩን ያስረዳሉ።

መንግሥት በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅና የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ የግል ዘርፉን በባለቤትነት ሊያሳትፍ እንደሚገባ የሚናገሩት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ ይህን ማድረግ ካልተቻለ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አዳጋች መሆኑን ነው ያስረዱት።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከ500 በላይ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ከ700 በላይ ሆቴሎች እንዲሁም በርካታ የቱሪዝም ምርት አቅራቢ ባለቤቶች መኖራቸውን ገልፀው፤ እነዚህ ባለድርሻዎች የበኩላቸውን ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉበት አደረጃጀት መፍጠር እንደሚጠበቅበት ይናገራሉ። በተለይ በኮቪድ ወረርሽኝና በልዩ ልዩ ሰው ሠራሽ ግጭቶች የተዳከሙትን የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች መደገፍና ማነቃቃት አንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ። ይህ ሲሆን የኢትዮጵያን ሀብት ማስተዋወቅና የቱረስት ፍሰቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ይገልፃሉ።

የኮንቬንሽን ቢሮው መሪ ሥራ አስፈፃሚው አቶ ጌትነት በበርካታ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም የጉዞ ዓውደ ርዕዮች ላይ ከመሳተፍ ባሻገር መሰል ዝግጅቶችንም በኢትዮጵያ ውስጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ። ይህ ዝግጅት ዓለም አቀፍ ደረጃውን ከጠበቀና ሌሎች ሀገራትንም ያሳተፈ ከሆነ በቀላሉ የመስሕብ ሀብቶችን በዚሁ በኢትዮጵያ ማስተዋወቅና ጎብኚዎችን በብዛት መሳብ እንደሚቻል ያስረዳሉ። ሆኖም በቅድሚያ ትላልቅ የኮንቬንሽን ማዕከላትን መገንባት ያሉትንም ደረጃቸውን ማሳደግ ተገቢ መሆኑን ያነሳሉ።

አዲስ አበባ 200 በላይ ዲፕሎማት ያላት እንዲሁም የአፍሪካ መዲና እንደሆነች የሚያነሱት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ ይሁንና ግዙፍ መድረኮችን ለማዘጋጀት የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ የኮንቬንሽን ማዕከል እስካሁን በሚፈለገው ልክ መገንባት አለመቻሏን ያስረዳሉ። ይህንን ተግዳሮት መፍታትና ልክ እንደ አይ. ቲ.ቢ በርሊን እንዲሁም ሌሎች ታላላቅ የቱሪዝም የንግድ ትርኢቶችን በቋሚነት ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ። ይህን ማድረግ ሲቻል የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገራት በሚፈለገው ልክ ማስተዋወቅ እንደሚቻል ያስገነዝባሉ።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You