በዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት- የኢትዮጵያን ቱሪዝም የማሳደግ ጥረት

ቱሪዝም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ እድገት እንዲመዘገብ አስተዋፆ ከሚያበረክቱ ዋና ዋና ዘርፎች መካከል አንደኛው ነው። በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ገቢ /ጂዲፒ/ ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን የዓለም የቱሪዝም ደርጅት (UNWTO) ጥናት ይጠቁማል። 10 በመቶ የሚሆነው የስራ እድልና 30 በመቶ የሚሆነው የወጪ ንግድ የሚፈጠረውም በዚሁ ዘርፍ ምክንያት እንደሆነ ጥናቱ ይጠቁማል።

ቱሪዝም የዓለማችንን የኢኮኖሚ እድገት ከማፋጠኑም ባሻገር ሁሉንም በእኩልነት ለማካተትና የጋራ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችል አማራጭ እንደሚፈጥርም ይሄው የድርጅቱ ጥናት ያመለክታል። በዚህም ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ (በአካል ጉዳትና በመሳሰሉት) ዜጎችና የተለያየ የሙያ ዘርፍ እና ክህሎት ያዳበሩ ባለሙያዎችን የሚያሳትፍ አካታች እድገት (inclusive growth) የሚያመጣ ዘርፍ ነው።

ለዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት ዋንኛው ምሰሶ የአየር ንብረት ለውጥን በኃላፊነት መከላከል እንደሆነ ይገለፃል። በዚህ ረገድም እንደ ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት መረጃ ዘርፉ ከሚፈጥራቸው በጎ ተፅዕኖዎች ውስጥ አንዱ አየር ንብረት እንዲጠበቅና ተፈጥሮ እንዳይራቆት ማድረግ መሆኑን ይጠቁማል። በዚህ ሂደት ውስጥ የተፈጥሮ ቱሪዝምን በማበረታታት፣ በዓለም ቅርስነት በመመዝገብ፣ እንክብካቤ እንዲደረግ ብሎም የተፈጥሮ ሚዛን እንዲጠበቅ አዎንታዊ ድርሻ ይወስዳል።

በዛሬው ርእሳችን በስፋት የምንዳስሰው ሌላኛው የቱሪዝም አዎንታዊ ተፅእኖ በዓለም አቀፍ ገፅታ ግንባታ፣ ትብብርና ዲፕሎማሲ ላይ ያበረከተውን አስተዋፆ ነው። ዘርፉ ሀገራት ያላቸውን የተፈጥሮ፣ ታሪክ፣ ባህል እና ልዩ ልዩ የመስህብ እሴቶች በትብብር ለመጠበቅና ለማሳደግ እንዲችሉ በር ከፋች መሆኑ የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጥናት ያመለክታል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ግዙፍ ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን ልዩ ትኩረት መስጠቷን መንግሥት ይገልጻል፡፡ በዚህም ቱሪዝም በአጠቃላይ የ ሀገር ውስጥ ምርት እድገት (GDP) ላይ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች (ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማእድንና አይሲቲ) ውስጥ አንዱ ሆኖ እየተሰራበት ነው።

በዚህም በመዳረሻ ልማት፣ በቅርስ ጥገና፣ በገበያ ልማትና መስህቦችን በማስተዋወቅ ረገድ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በጥቂት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን ቱሪዝም አቅጣጫ የቀየሩ ታላላቅ የመዳረሻ ልማት ግንባታዎች ስኬትም የዚሁ ጉዞ አካል ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ሲገለፅ ይደመጣል።

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀምና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅእኖው ከፍ ካለው የቱሪዝም ዘርፍ ድርሻ ለመውሰድ ከሚያስችሏት እርምጃዎች ውስጥ ዋንኛው ዓለም አቀፍ አጋርነት፣ ትብብር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሆነ ይጠቀሳል። በዚህ ረገድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች መኖራቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ክፍል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው ይናገራሉ። ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ቱሪዝምን በሚመለከት ለማምጣት የታሰበውን ስር ነቀል ለውጥ የሚያግዙ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ከተለያዩ አገራት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ያመለክታሉ።

በያዝነው ዓመት ከልዩ ልዩ አገራት ጋር በቱሪዝም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተሻሉ ውጤቶች መመዝገባቸውንም የሚናገሩት አቶ አለማየሁ ጌታቸው፤ በልምድና ተሞክሮ ማጋራት፣ በትብብር በመስራትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ ስምምነቶች እንደተደረጉም ይገልፃሉ። በቅርቡም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናንሲሴ ጫሊ በቼክ ሪፐብሊክ ያደረጉትን የሁለት ቀናት ግንኙነት ያነሳሉ። በዚህ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ የቱሪዝም ግንኙነት ጥረት ውስጥ የተገኙትን ውጤቶችም በዝርዝር ይገልፃሉ።

‹‹አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በቼክ ሪፐብሊክ የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት አድርገዋል›› የሚሉት መሪ ስራ አስፈፃሚው ጉብኝቱ በኢትዮጵያ እና በቼክ መካከል እየተጠናከረ የመጣውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በቱሪዝም ዘርፍም ለማጠናከር ያለመ መሆኑን መግለጻቸውን ይናገራሉ። ሚኒስትሯ በቆይታቸውም ከቼክ ሪፐብሊክ የባህል ሚኒስትር ሚስተር ማርቲን ባታ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ የሁለቱ ሀገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተወያዩባቸውን አጀንዳዎች ወደ ተግባር ለመቀየር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያስረዳሉ። በዚህም ብሔራዊ ሙዚየሞቻችን መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ በማመላከት በአፈፃፀሙ ላይ ዝርዝር ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንደሚሉት፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ በዋናነት ኢትዮጵያ በዘርፉ የተሻለ እድገት ካስመዘገቡና የተሻለ የአሰራር ሥርዓት ከዘረጉ ሀገራት ጋር በትብብር መስራት እንድትችል መንገድ መጥረግ መሆኑን በማንሳት የሚኒስትሯ የቼክ ሪፐብሎክ ጉዞም ይህንን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ያብራራሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ መነሻ ቼክ ሪፐብሊክ ያላት ብሄራዊ ሙዚየም ከዓለም ምርጥ ሙዚየሞች መካከል አንዱ ሲሆን፣ 206 አመት እድሜ ያለው ፣ከ20 ሚልዮን በላይ የሙዚየም ስብስቦችን የያዘ በዓመትም ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ጎብኝዎች በላይ የሚጎበኙት ድንቅ ሙዚየም ነው፡፡ ሚኒስትሯ የሀገሪቱ ቱሪዝምና ብሄራዊ ሙዚየም አደረጃጀት ከቼክ ሪፐብሊክ ምርጥ ተሞክሮ ለመጋራት ከብሄራዊ ሙዚየም ዳይሬክተር ጀነራል ሚስተር ሚካኤል ሉከስ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።

‹‹የመሪዎቹን ውይይት ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በቼክ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ሙዚየሞች መካከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል›› የሚሉት መሪ ስራ አስፈፃሚው፤ ይህንን ስምምነት መሬት ላይ ለማውረድ ያለመ ተጨማሪ ውይይትና ስምምነት በቱሪዝም ሚኒስትሯ አማካኝነት መደረጉን ይናገራሉ። በስምምነቱ መሰረት በአቅም ግንባታ መስክ፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ሙዚየም ለማዘመን በሚደረገው ጥረት እንዲሁም የተለያዩ የሙዝየም ስብስቦችን በጊዜያዊ ኤግዚቢሽን መልክ በልውውጥ በየሀገራቱ ለማሳየትና አብሮ ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱን ይገልፃሉ። በተጨማሪም ሚኒስትሯ በዲቩር ክራሎቭ ሳፋሪ ፓርክ የሥራ ጉብኝትና ውይይት ማድረጋቸውንም አቶ አለማየሁ አስታውቀዋል።

ፓርኩ በአፍሪካ ብቻ የሚገኙትን በተለይ ዘራቸዉ የጠፋና እየጠፋ ባለ የዱር እንስሳት ዙሪያ አተኩሮ የሚሰራና ሳይንሳዊ ጥናት የሚያደርግ ሲሆን በሳፋሪው ከ2000 በላይ የዱር እንስሳት ያሉትና በዓመትም እስከ ስድስት መቶ ሺህ ሰዎች የሚጎበኙት ፓርክ ነው።

ከፓርኩ ኃላፊዎች ጋር በተደረገው ውይይት ሁለቱን ሀገሮች የበለጠ ለማስተሳሰር እንዲቻል በዱር እንስሳት ጥበቃና እንክብካቤ፣ በዘርፉ የሚደረግ ጥናት እንዲሁም ለአደጋ ለተጋለጡ የዱር እንስሳት መጠለያ ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል። ይህም በቀጣይ ከዱር እንስሳት ባለስልጣን ጋር በሚፈረም የመግባቢያ ስምምነት ወደ ስራ የሚገባ እንደሚሆን የህዝብ ግንኙነት ክፍል መሪ ሥራ አስፈፃሚው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዲፕሎማሲ በያዝነው ዓመት ውጤታማ ግንኙነት መፍጠር እንደቻለች የሚናገሩት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፣ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ይጠቅሳሉ። በዚህም የጆርዳን የቱሪዝም ሚኒስትር መከራም ሙስጠፋን በሀገር ውስጥ በመቀበል ሁለቱ ሀገራት በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እና የልምድ ልውውጥ ማድረግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከአምባሳደር ናንሲሴ ጫሊ ጋር መወያየታቸውን ይናገራሉ። በተለይም በቱሪዝም ኢንቨስትመንት፣ በፕሮሞሽን፣ በቅርስ ጥበቃ እና በጤና ቱሪዝም ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን ያስረዳሉ።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ በሀይማኖት ቱሪዝም እና ጤና ቱሪዝም ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ውይይቶችን ከተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ማድረጋቸውንም መጥቀሳቸውን ገልጸው፣ በከተማዋ ያሉ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ማድረግ መቻሉንም ያነሳሉ።

መሪ ሥራ አስፈጻሚው ጆርዳንና ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ለሁለት ቀን በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረጉት ሚኒስትሩ መናገራቸውን አንስተው፤ አጋርነትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የቱሪዝም ዘርፍ አንዱ መሆኑን መናገራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን መግለጻቸውንም አስታውቀዋል። ከጆርዳንና ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር የቱሪዝም ዘርፍን በተመለከተ ከተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባሻገር በያዝነው ዓመት ሌሎች ተጨማሪ የሁለት እዮሽ ስምምነቶች መደረጋቸውን የሚገልፁት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ለእዚህም ከቱርክ ጋር የተደረገውን ስምምነት እንደ ምሳሌነት ያነሳሉ።

የሕዝብ ግንኙነት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ አምባሳደር ናንሲሴ ጫሊ ከቱር ከመጣው የልኡካን ቡድን ጋርም በጽህፈት ቤታቸው መወያየታቸውን አስታውሰው፤ የቱርክ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መጋበዛቸውን ገልጸዋል። የቡድኑ አባላትም በአቅም ግንባታ፣ በጤና ቱሪዝም፣ ቪላ ቱሪስት ማረፊያ ቦታዎች ላይ የዘርፉን ልምዳቸውን ማካፈልና የልምድ ልውውጥ የማደረግ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን ተናግረዋል።

ከቱርክ በተጨማሪ ዘንድሮ ከልዩ ልዩ አገራት ጋር ቱሪዝምን መሰረት ያደረጉ በርካታ ስምምነቶችና ትብብሮች መደረጋቸውን በመጥቀስም፣ የኢትዮጵያን ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ የጎላ ድርሻ እንዳላቸው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከ10 አንዱን የሥራ እድል የመፍጠር አቅም ያለው የቱሪዝም ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ ጉልህ ተፅእኖ እንዲኖረው ትኩረት ሰጥቶት እየሰራበት መሆኑ ይታወቃል። በተለይ የአዳዲስ መዳረሻ ልማት ትግበራዎች ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ በስፋት ተከናውነዋል። በዚህም እንደ ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ሃላላ ኬላ እና መሰል በተፈጥሮ ቱሪዝም ላይ ያተኮሩ አዳዲስ መዳረሻዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የቱሪስት ፍሰት ወደ ኢትዮጵያ የመሳብ አቅም እንዳላቸው ታምኖበታል። ይሁን እንጂ ከቱሪዝም መሰረተ ልማት ግንባታው ጎን ለጎን የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶችና መልካም እድሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

አቶ ጌትነት ይግዛው በቱሪዝም ሚኒስቴር የኮንቬንሽን ቢሮ መሪ ስራ አስፈፃሚ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ መንግሥት በሁለትዮሽ ግንኙነት ፣ በባለብዙ የዲፕሎማሲ መድረኮች በመገኘት እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች በማስተዋወቅና የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ ስትራቴጂ ቀርፆ መስራት እንዳለበት ይናገራሉ። በዚህ ጥረት ውስጥ የግል ዘርፉን በባለቤትነት ሊያሳትፍ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከ500 በላይ ቱር ካምፓኒዎች፣ ከ700 በላይ ሆቴሎች እንዲሁም በርካታ የቱሪዝም ምርት አቅራቢዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ጌትነት፤ እነዚህ ባለድርሻዎች የበኩላቸውን ተፅእኖ ማሳረፍ የሚችሉበት አደረጃጀት መፍጠር ቢቻል በቱሪዝም ፕሮሞሽንና ዲፕሎማሲ ሥራ ላይ ጉልህ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ገልጸውልናል።

ሚኒስትሯ አምባሳደር ናንሲሴ ጫሊ በቼክ ቆይታቸው ከሀገሪቱ የቱሪዝምና የሙዚየም ባለስልጣናት ጋር መክረዋል

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You