ጥናትና ምርምር – ለዘላቂ ቱሪዝም ልማት

ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ሥራ ሊውሉ የሚችሉ የአያሌ ቅርሶች፣ ድንቅ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ባህሎች፣ ፓርኮች፣ የዱር እንስሳትና የመሳሰሉት ሀብቶች ባለጸጋ ናት:: ከእነዚህ የቱሪዝም ሀብቶች መካከልም ከ16 የማያንሱት በዓለም ቅርስነት በዩኒስኮ ተመዝግበዋል::

እነዚህን የቱሪዝም ሀብቶች ለመጎብኘትም በርካታ የውጭ ቱሪስቶች ወደ ሀገሪቱ ይመጣሉ:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችም እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች በስፋት መጎብኘት ጀምረዋል::

ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን ይህን እምቅ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት ዘርፉን በቀጣይ የሀገር ምጣኔ ሀብት ምሰሶ አድርጎ ከያዛቸው አምስት ግዙፍ ዘርፎች መካከል እንዲካተት አርጎታል:: መንግሥት ይህን በማድረግ ብቻም አላቆመም:: ሀገሪቱ በውጭም በሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ሊጎበኙ የሚችሉ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ቢኖሩም፣ ቱሪስቶችን ይስባሉ፤ ቆይታቸውን ያረዝማሉ ያላቸውን በርካታ አዳዲስ የቱሪስት መደረሻዎችን በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች አልምቶ ወደ ሥራ አስገብቷል፤ እያለማም ይገኛል::

የቱሪስት መዳረሻ ልማቶቹ የሚያስፈልጋቸውን የሠለጠነ የሰው ሃይል ለማሟላት በቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ከሚሰጡ ሥልጠናዎች በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማትም በሰው ሃይል ልማቱ ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው::

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት በመንግሥት ከተሰጡት ተልእኮዎች መካከል ትምህርትና ሥልጠና ዋናውና አንዱ ነው። ሌላው የጥናትና እና ምርምር፣ የማማከር ሥራ እና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ነው። በትምህርትና ሥልጠና ሥራው ተማሪዎችን በመደበኛነት እየተቀበለ የሚያስተምር ሲሆን፣ በዘርፉ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፤ ምርምርና ጥናቶችን እያካሄደ በመንግሥት የተሰጡትን ተልኮዎች እየፈጸመ ይገኛል::

ኢንስቲትዩቱ በየአመቱ የጥናት እና ምርምር ጉባኤ ያካሂዳል:: ዘንድሮም በቅርቡ ለ13ተኛ ጊዜ ይሄው ጉባዔ ተካሂዷል:: ጉባዔው በተለያዩ ምሁራን ጥናት እና ዝግጅት የተደረገባቸው አራት የምርምር ውጤቶች ቀርበውበታል::

በጉባዔው ላይ እንደተጠቆመው፤ ጥናትና ምርምር ውጤቶች ለእንድ ሀገርና ማህበረሰብ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ ለመስጠት ያስችላሉ፤ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓትን ለማሻሻልም ጉልህ ሚና አላቸው::

‹‹ቀጣይነት ያለው ቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲን መገንባት›› በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ይህ ጉባዔም የዘላቂ ቱሪዝም ልማት ግንባታ ጉዳይ ሲታሰብ በዘርፉ የሚደረጉ ምርምሮች ሚና የጎላ መሆኑ ተጠቁሞበታል::

በጉባዔው ላይ የተገኙት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ እንደገለጹት፤ የምርምር ሥራን ባህል ማድረግ ቴክኖሎጂንና የሥራ እድልን ለመፍጠር ያግዛል:: የምርምር ሥራ ለአንድ ሰሞን ተደርጎ የሚተው ሳይሆን፣ ተልዕኮን በላቀ ደረጃ ለማከናወን የሚረዳ መሆን ይኖርበታል::

የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ በቱሪዝም ዘርፍ በዋናነት ሥልጠናዎች ፣ የጥናትና ምርምርና እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ይሠራሉ:: የጥናትና ምርምር ተቋሙ በየአመቱ በሚያዘጋጀው መድረክ ጥናቶች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ዘንድሮም በዚህ መድረክ ላይ አራት ትናቶች ተመርጠው ቀርበዋል::

ኢንስቲትዩቱ በቱሪዝም ዘርፉ የሚያስፈልገውን የሰው ሃይል እያሠለጠነ ወደ ዘርፉ እንደሚያሠማራ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ሰዓትም በኢንስቲትዩቱ እየተሠራ ያለና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ጥናት መኖሩን ምክትል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል:: ይህ ጥናት ዘርፉ ምን ያህል የሰው ሃይል ይፈልጋል? ከማሠልጠኛ ተቋማት ምን ይጠበቃል? በሚል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል በመላው ሀገሪቱ የተደረገ ጥናት ነው ብለዋል::

በጥናት እና ምርምር ጉባኤዔው የቅርስ ጥበቃ እና አስተዳደር ፣ ቅርሶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ያላቸው ተጠቃሚነት ፣ ለቅርሶች በሚደረግ ጥበቃ የማህበረሰብ ተሳትፎ አስፈላጊነት ፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን የቱሪዝም ዘርፉን የሠለጠነ የሰው ሃይል ማቅረብ ፣ የቱሪዝም ሀብትን በሚገባ ማስተዋወቅ እንዲሁም ሀገር በቀል እውቀቶችን በሥልጠና ሥርዓት ውስጥ ማካተት የሚሉ ጉዳዮች በጉባዔው ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡ ምሁራን በዋናነት ያነሷቸው ሃሳቦች ናቸው :: ዘላቂነት ያለው ቱሪዝምን እንዴት መገንባት ይቻላል ፣ የባለድርሻ አካላት ሚና ምን መምሰል አለበት በሚል የተዘጋጁ ጥናቶች በቀረቡበት በዚህ መድረክ ላይ ፣ በኢንስቲትዩቱ የተጋበዙ እንግዶች እና የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል::

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ የማይዳሰሱ እና የሚዳሰሱ ቅርሶች በሚል 11 የሚሆኑ ቅርሶችን አስመዝግባለች:: የእነዚህ ቅርሶች መመዝገብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ጎብኚዎችን ከእስከ አሁኑም በላቀ መልኩ ወደ ሀገሪቱ እንዲመጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል:: ከቅርሶች ጋር ተያይዞ የተካሄደው ጥናትና ምርምር ያለው ፋይዳም ከፍተኛ ነው::

በሀገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ለሀገር ውስጥም ሆነ የሌላ ሀገር ጎብኚዎች ምርጫቸው የሚያደርጓቸው በዓመት ቀላል የማይባል የጎብኚ ቁጥርን የሚያስተናግዱ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ቅርሶች እንዳሉ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ቅርስ ባለበት ሁኔታ ጠብቆ ማቆየት እና ማስተዳደር እንደሚገባ ተመልክቷል::

ቅርስን ጠብቆ በማቆየት እና ማስተዳደር በኩል ሃላፊነቱ ቅርስን እንዲያስተዳድር ሃላፊነት የተሰጠው አካል መሆን እንደሌለበት የተገለጸ ሲሆን፣ ቅርሱ የሚገኝበት አካባቢ ማህበረሰብ ጨምሮ የአካባቢው አስተዳደር ሃላፊነት እንዳለባቸው በመድረኩ በቀረበው ጥናትም ታይቷል:: በአፍሪካም ሆነ በሀገራችን ቅርሶችን የማስተዳደር እና ጠብቆ የማቆየት ክፍተት በተቋማት ላይ እንደሚታይ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ቅርሶች በአንድም በሌላም መንገድ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ ተጠቁሟል::

ቅርሶች በምን ምክንያት ሊጎዱ ይችላሉ በሚል ጥያቄዎች ተያይዘው ተነስተዋል:: ለእዚህ ከተሰጡ ምላሾች መካከልም የሕዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ በህብረተሰቡ ዘንድ እየጨመረ የመጣው የመሠረተ ልማት ፍላጎት፣ በከተማ ግንባታ ወቅት የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች መጨመር የሚሉት ይጠቀሳሉ:: እነዚህን አገልግሎቶች የቱሪስት መዳረሻ ናቸው በሚባሉ ሥፍራዎች ውስጥ ማሟላት አጠያያቂ እንዳልሆነም ተጠቁሞ፣ ሥራዎቹ በቅርሶች ላይ ጉዳት በማያስከትል መልኩ መከናወን እንዳለባቸውም ተመልክቷል::

ሌላኛው ቅርሱን ለመጠበቅ እና ለማቆየት የሚደረጉ ጥንቃቄዎችና የሚካሄዱ ጥገናዎች የአካባቢው ማህበረሰብ ያለውን ሀገር በቀል እውቀት መጠቀምን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን የማድረግ አስፈላጊነትም ተጠቁሟል፤ ይህ እንዲሆን የሚመለከተው አካል ፈቃድ አስፈላጊ ነው የሚል ሃሳብ ተነስቷል::

በመድረኩ እንደተጠቆመው፤ ህብረተሰቡ በእቅራቢያው የሚገኘውን ቅርስ ፣ ከባቢያዊ ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችል እና በራሱ ቅርሱን የሚጠብቅበት ዘመናትን የተሻገረ እውቀት አለው:: ይህን አቅም በሚገባ ለመጠቀም ባለድርሻው አካል ቅርሱን ለመጠበቅ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የህብረተሰቡን የባለቤትነት ስሜት በመረዳት ለማህበረሰብ ተሳትፎ ዋጋ መስጠት ይገባዋል::

ህብረተሰብ ተኮር የቱሪዝም ልማት ሌላው በመድረኩ የተነሳ ርእሰ ጉዳይ ነው:: ይህ አይነቱ የቱሪዝም ልማት በተለይ ቅርስ ያለበት አካባቢ የሚኖር ህብረተሰብ ቅርሱን እየጠበቀ እና እየተንከባከበ ከቅርሱ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ማድረግ የሚያስችል አሠራር ነው:: የቱሪዝም ልማት የአካባቢውን ማህበረሰብ ከቱሪዝም ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆን የለበትም::

ሌላው በመድረኩ የቀረበው ጥናት በሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ያተኮረው ነው:: ኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሀገር በቀል ሀብት በብዛት ያላት ሀገር እንደመሆኗ በቱሪዝሙም ዘርፍም እንዲሁ የሀገር በቀል አውቀቶች ባለጸጋ ናት:: ይህን ሀብት በመጠቀም በኩል ግን ብዙም አልተሠራም::

በሀገር በቀል እውቀቶች ላይ የተካሄደው ጥናትም የሀገር በቀል እውቀቶችን ፋይዳ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ዘርፍ ማካተትን ታሳቢ ያደረገ ነው:: ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት የጥናቱ አቅራቢ ሲያብራሩ እንዳሉት፤ በቱሪዝም ዘርፉ ለሀገር በቀል እውቀቶች እየተሰጠ ያለው ትኩረት አናሳ ነው :: እንደ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ያሉ ተቋማትና ሌሎች ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሠለጠነ የሰው ሃይልን የሚያቀርቡ ማሠልጠኛ ተቋማት በሚሰጧቸው የሥልጠና መስኮች ላይ የሀገር በቀል እውቀት /የሀገር ውስጥ ምግብ አዘገጃጀትና የመሳሰሉት/ አለማካተታቸው እንደ ማሳያ ተነስቷል::

ሀገር በቀል እውቀቶችን በማሠልጠኛ ተቋማት ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ ብዙ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል ያሉት አቅራቢው፣ መተግበር ግን እንደሚቻል ነው ያስታወቁት:: እነዚህ ሀገር በቀል እውቀቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ መሆናቸውንም በመጥቀስ፣ በእነዚህ ላይ ጥልቅ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል::

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች ላይ ጥናት በማድረግና በእዚህ ሀገር በቀል እውቀት ላይ የራሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅለት በማድረግ፣ እውቀቱን በማሠልጠኛ ተቋማት ሥልጠና ሥራ ላይ በማካተት ቢሠራ በዓለም የንግድ ውድድር ላይ በሚገባ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተጠቁሟል:: በሀገር በቀል እውቀት ላይ የተጠናከሩ ጥናቶችን በማድረግ በገበያው ላይ ጠንካራ አቅርቦትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ መሆን ይቻላል ተብሏል::

ሀገር በቀል እውቀቶችን መመዝገብ ፣ የሥራ እድል መፍጠር የሥልጠና ሰነድ ማዘጋጀት ፣ እና ሠልጣኞች ከሀገር በቀል እውቀቶች ጋር እንዲተዋወቁ ማድረግ ይገባል የሚል ምክረ ሃሳብም ተሰጥቷል::

ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩቱ እነዚህን ሀገር በቀል እውቀቶች በሚገባ በማስጠናት ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ለማድረግ በተለያዩ የባህል ምግቦች ላይ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥናት በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንንም የሥራ እድል መፍጠሪያ ለማድረግ በሥልጠና በማካተት ለመስጠት እንዲያስችል ለማድረግ እየሠራ ይገኛል ተብሏል::

በመድረኩ ላይ እንደተጠቆመው፤ እየተጠናቀቀ ባለው 2016 በጀት ዓመት ኢንስቲትዩቱ የስምንት ክልሎችን ባህላዊ ምግቦች ለማጥናት አቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአምስቱን ክልሎች አጥንቷል:: ጥናት የተደረገባቸው ምግቦችም የስልጤ ፣ ሀዲያ ፣ ወላይታና ኮንሶ ባህላዊ ምግቦች ናቸው:: እነዚህ ጥናት የተደረገባቸውን ባህላዊ ምግቦች የጥናት ሰነድ ወደ ሥልጠና በማካተት ምግቦቹ ደረጃቸውን በጠበቁ ሆቴሎች የሚዘጋጁበትን ሁኔታ ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ ነው::

በመድረኩ ላይም ሀገር በቀል እውቀቶችን በመተመለከተ ከባህላዊ ምግቦች ባሻገር በባህላችን ውስጥ ያሉ የእንግዳ አቀባበል ፣ አለባበስ ፣ ባህል እና ሙዚቃ ማሰብ ከታዳሚያን የተነሱ ሃሳቦች ናቸው ::

የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ እና ሀገር የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ በዘርፉ የተሠማሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን ደረጃውን የጠበቀ ማድረግ ፣ እንደ ሀገር ያሉትን ሀብቶች በሚገባው ልክ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሀብቶችን ማስተዋወቅ እና ገቢ እንዲያመጡ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቅሷል ::

ሀገሪቱ ከቱሪዝም ሀብት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ በሚሰሩ ሥራዎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ከሀገር ውጪ የሚመጡ ጎብኚዎችን ለመሳብ ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን የበለጠ ለመሳብ መሥራት እንደሚገባም ተመላክቷል::

በመድረኩ ላይ በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ እንደ ክፍተት ተደርገው የተነሱት በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት የጸጥታ ችግሮች ፣ ጎብኚዎች ሊሄዱባቸው በሚችሉ እና የቱሪዝም ሀብት በሚገኝባቸው ቦታዎች የመሠረተ ልማት አለመሟላት ፣ ረጅም ዓመት ላስቆጠሩ ቅርሶች የሚደረገው ጥበቃ ጉድለት እንደ ችግር ተጠቅሰዋል::

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You