ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተከርስቲያን በኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክ ውስጥ ግዙፍ ስፍራ የያዘች ጥንታዊት የእምነት ተቋም እንደሆነች ይታወቃል። የኢትዮጵያ በርካታ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ ሥነልቦናዊ ውቅርም ከዚሁ ጋር በእጅጉ ቁርኝት አለው። ይህንን እውነታ አጉልተው ከሚያሳዩ አስረጂዎች ውስጥ ዘመናትን ያስቆጠሩ ቅርሶች፣ ሥነ ጽሑፎች፣ የሥነ ጥበብ ውጤቶች ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ሀብቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ኢትዮጵያን በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ቅርሶች በተለይ በዓለም መድረክ ላይ ስናስተዋውቅ ጥንታዊቷ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያበረከተቻቸውን፣ ዛሬም ድረስ ጠብቃ ያቆየቻቸውን ሀብቶች ደምረን ነው። የላሊበላ፣ አክሱም ጽዮን፣ የይምርሀነ ክርስቶስ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በርከት ያሉ ጥንታዊ ገዳማት፣ የብራና መጽሐፍት፣ የጥንት ቁሳዊ ሀብቶች እና ሌሎችም የማይዳሱና የሚዳሰሱ ቅርሶችን ይዘን ነው።
በዓለማችን ላይ በርካታ ጎብኚዎች ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው ቅርሶችን ለመመልከት ወደ ተለያዩ ሀገሮች ይጓዛሉ። ከእነዚህ ተመራጭ ስፍራዎች መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ነች። በግዕዝ የተፃፉ ድርሳናትን፣ የአያት ቅድመ አያቶቻችንን የሥልጣኔ ጥበብ የያዙ ብራናዎችን፣ የኪነ ሕንፃ ጥበብ፣ ተፈጥሮ እና ሃይማኖታዊ ምስጢራትን ሀገራችን ኢትዮጵያ በብዛት ይዛለች። አያሌ ቅርሶችም በወራሪዎች ከሀገር ውስጥ ተዘርፈው በዓለማችን ታላላቅ ሙዚየሞች ሲገበኙ ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህን በገንዘብ የማይተመኑ ታላላቅ ቅርሶችን እነዚህ አካላት በኩራት ሲያስጎበኙ ይስተዋላሉ፡፡ ኢትዮጵያም እነዚህን የማንነቷ መገለጫ ቅርሶች ለማስመለስ በርካታ ጥረቶች እያደረገች መሆናን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ከርስቲያን ለዓለማችን ካበረከተቻቸው ሀብቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ኪነ ሕንፃ እና ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች ይገኛሉ። አብዛኞቹ ክፍለ ዘመናትን ወደኋላ የተሻገሩ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በርከት ያሉ አስርተ ዓመታትን ያስቆጠሩ ናቸው።
ከእነዚህ የእምነት ተቋማት (በኪነ ሕንፃ ቅርስ ከሚመደቡት) ውስጥ 92 ዓመታትን እድሜ ያስቆጠረው የመንበረ ፀባዎት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይገኝበታል። የዛሬ የባሕልና ቱሪዝም ዓምዳችንም በዚህ የእምነት ስፍራ የኪነ ሕንፃ ቅርስ ላይ ያተኩራል። ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ለማንሳት የወደድንበት ዋንኛው ምክንያትም በአራት ኪሎ እምብርት ላይ የሚገኘው ካቴድራሉ እያደረገ ያላው የቅርስ ጥገና መርሐ ግብር ነው።
ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በኪነ ሕንፃ ውበቱ ማራኪ መሆኑ ተመስክሮለታል። የአምልኮ ሥነሥርዓት ከሚፈፅሙት ምዕመናን ውጪ በየእለቱም ከውጪም ሆነ ከሀገር ውስጥ በርካታ ጎብኚዎች ሊጎበኙት ወደ ስፍራው ይጎርፋሉ። በኢትዮጵያ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ታዋቂ ሰዎች ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ እንዲያርፉ የሚደረጉትም በዚህ ታላቅ ስፍራ ነው። ለጎብኚዎች ልዩ ትርጉም ካላቸው የጉብኝት ቦታዎች አንዱም ይህ እንደሆነ ይነገራል። የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትም ኪነ ሕንፃውን በቅርስነት መዝግቦት ልዩ ትኩረትና ጥበቃ እንዲደረግለት በትብብር እየሠራ ይገኛል።
ካቴድራሉ በአሁኑ ወቅት በቤተክርስቲያኗና በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጥገና እየተደረገለት ነው። የጥገና ሂደቱ ምን ላይ እንደደረሰ በቅርቡ በተሰጠ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፤ የካቴድራሉ ጥገና በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት የመንበረ ፀባዎት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሚያዚያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው በዚህ መግለጫ ላይ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ሲራክ አድማሱ የኪነ ሕንፃ እድሳቱን አሁናዊ ሁኔታ በማስመልከት እንዳስታወቁት፤ አንድ ሀገር ሃይማኖት፣ ታሪክና ቅርስ ከሌለው ማንነቱ በሌሎች ዘንድ ሊታወቅ አይችልም። ቅርሶች ያለፈውን፣ ነባሩንና ተተኪውን ትውልድ የሚያገናኙ የትውልድ ድልድዮች ናቸው። ኢትዮጵያም ንዋይ ሊተምነው የማይችል የታሪክና የቅርስ ግምጃ ቤት ናት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በውስጧ በርካታ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ቅርሶች በመያዝ በሀገር በቀል እውቀቶቿ ለሀገሪቱ የሥልጣኔ ዐሻራ መሆን ችላለች። ለእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ቅርስና ልዕልና መነሻ በመሆን ትልቁን አስተዋፅዖ እያበረከቱ ከሚገኙት መካከልም ከቤተክርስቲያኗ የፈለቁት ሀብቶች መሆናቸው ዛሬም ሕያው ምስክሮች ናቸው።
‹‹የቀደሙት አባቶች ያቆዩትንና ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ እንድትታወቅ ያደረጉትን ቅርሶች ትናንት በነበሩበት ሁኔታ እንዲቆዩ ሊጠበቁና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል›› ያሉት አስተዳዳሪው፤ ከእነዚህ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው የመንበረ ፀባዎት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለካቴድራሉ ግንባታ መሠረት የተጣለው በወቅቱ ንጉሥ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አማካኝነት በ1924 ዓ.ም. መሆኑን አስታውሰው፣ ይሁን እንጂ በፋሺስት ወረራ ጊዜ ለአምስት ዓመታት ግንባታው ተቋርጦ ቆይቷል ብለዋል። ከድል በኋላም ንጉሡ ዳግም ሥራው ተጀምሮ በከንቲባ ከበደ ተሰማ ተቆጣጣሪነት ግንባታው በ1936 ተጠናቅቆ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ተጀምሯል ያሉት አስተዳዳሪው፣ የግንባታው ሙሉ ወጪ የተሸፈነውም በንጉሡ አማካኝነት መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ አስተዳዳሪው ገለፃ፤ ካቴድራሉ በእድሜ እርዝማኔ ምክንያት እድሳት ሳይደረግለት በመቆየቱ ውስጣዊና ውጫዊ የሕንፃው አካል ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ቅርሱን ለችግር የሚያጋልጠው ሆኖ ተገኝቷል። ሁለንተናዊ ውበቱን፣ ቅርሱንና ይዘቱን እንደጠበቀ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ከቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በሀገሪቱ ባሉ ታዋቂ የቅርስ ጥናት ባለሙያዎች አማካኝነት ጥልቅ ጥናት ለአንድ ዓመት ከ4 ወር ተደርጎለታል። ግኝቱን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት የእድሳቱ ሥራ ተጀምሮ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው።
‹‹ካቴድራሉ በርካታ ቅርፃ ቅርፆች ያሉትና ውድ ከሆኑ የተለያዩ ቁሳቁስ የተገነባ ነው›› ያሉት አስተዳዳሪው፤ እድሳቱን ለማከናወን በቅርስ እድሳት የካበተ ልምድ ካለው ቫርኔሮ ከተባለ ድርጅት ጋር 172/ የአንድ መቶ ሰባ ሁለት/ ሚሊዮን ብር የሥራ ውል ስምምነት መፈፀሙን ይናገራሉ። ክንውኑም በተፋጠነ መልኩ እየሄደ እንደሆነ ጠቅሰው፣ እድሳቱ በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንዳይስተጓጎል በታሪኩና በቅርሱ ለማይደራደረው በሀገር ውስጥና በውጪ ለሚገኘው ኢትዮጵያዊ ማሳወቅ ማስፈለጉን ያብራራሉ።
አብዛኛው ማኅበረሰባችን ካቴድራሉ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም እንዳለው፣ ምንም አይነት እርዳታ እንደማያስፈልገው አርጎ ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ የተዘገበበት ሁኔታ እና ከዚህ በመነሳትም ድጋፍ ለማድረግ ፍቃደኛ አለመሆኑ እየታየ ያለበት ሁኔታ የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደቱን ከምናስበው በላይ እጅግ ውስብስብ እና ፈታኝ አድርጎብናል ሲሉ አስተዳዳሪው ጠቁመዋል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው ያስፈለገበት አንደኛው ምክንያት ይሄው እንደሆነም ይናገራሉ።
ከተሳሳቱ ግንዛቤዎች መካከል ካቴድራሉ ዙሪያ ያሉትን ሕንጻዎች የካቴድራሉ ንብረት አድርጎ የመቁጠር ፣ ብዙ ባለሀብቶች የሚረዱት አድርጎ ማሰብ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። ስለሆነም በሀገር ውስጥም፣ ከሀገር ውጪም ያሉ ኢትዮጵያውያን ካቴድራሉ በዙሪያው ምንም አይነት የሚያከራየውና ገቢ የሚያገኝበት ሕንጻ እንደሌለው ፣ ዙሪያውን ያሉ ነዋሪዎች በልማት ምክንያት በመነሳታቸው ከሌሎች ከተማ ዳር አካባቢ ካሉ አብያተ ክርስቲያናት ያነሰ ገቢ እንዳለው እንዲረዱላቸው አስገንዝበዋል፡፡
አስተዳዳሪው ጥገናው ከሦስት ወር በኋላ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ ጠቅሰው፣ ሥራው ሲጠናቀቅ በውሉ መሠረት የሚከፈል ጠፍቶ ያልተገባ እና ያልተፈለገ ችግር ውስጥ ላለመግባት ሕዝቡ የከተማዋ ታላቅ ቅርስ ለሆነው ካቴድራል እድሳት ማጠናቀቂያ የሚውል የገቢ ማሰባሰብ ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ አስተላልፈዋል። እድሳቱን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 85 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በጥገናው እስካሁን ከተሠሩት ሥራዎች የመጀመሪያው የእድሳትና ጥገና ሥራ ነው፡፡ ከካቴድራሉ ሕንፃ መስቀል አንስቶ እስከ መሠረት ማጠናከር ድረስ በሚገኙ ሥራዎች መካከል ከተከናወኑ ሥራዎች ውስጥ የመዋቅር እድሳት በምድር ቤት ውስጥ የሚገኙ ምሰሶዎች ማጠናከር፣ የሚዛን ወለል ሙሉ ለሙሉ አፍርሶ የመሥራት ተግባር፣ የሕንፃው መካከለኛ ክፍል ላይ ከፍ ብሎ የሚገኘውን ስፍራና የውጪ ግድግዳ እድሳት፣ የልስን ሥራ፣ የውስጣዊ ክፍል ስዕል እድሳትና ሌሎችም ተሠርተዋል።
በኪነ ሕንፃ እድሳት ዘርፍ ደግሞ የሁለት የደውል ቤቶችና መስቀሎች እድሳት መሠራቱን የተናገሩት አስተዳዳሪው፣ የትልቁ መስቀል (ዶም) እንዲሁም የመካከለኛውና ትልቁ (ዶም) ጣሪያ የመዳብ ጥገና፣ የድንጋይ ጌጦች የመጀመሪያ አጠባ፣ የወንጌላውያንና የመላዕክት የሐውልት ቅርፃ ቅርፆች ፅዳት፣ የስዕል ጥገና ሥራ፣ የፍሳሽ መስመር ጥገና፣ የኤሌክትሪክ መስመር ጥገና፣ የዓውደ ምሕረት የባዞላ ንጣፍ መቀየር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አስተዳዳሪው ባለፉት 18 ወራት ወስጥ ከላይ የተዘረዘሩት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀው፤ እነዚህም ከመሠረታዊው የቅርስ እድሳት ሥራዎች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ይናገራሉ። ቀጣይ ሥራውም በየጊዜው በባለሙያዎች ክትትል እየተደረገለት እስከ ፍፃሜው ድረስ እንደሚገልፅ አስታውቀዋል። በሂደቱም የሕንፃ ጥገና ሥራው 75 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
በእድሳቱ ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮች መኖራቸውን የሚያነሱት አስተዳዳሪው፤ የመጀመሪያው በውሉ መሠረት ሥራው ተጠናቅቆ የሚያልቅበት የጊዜ ገደብ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም እንደነበረም ተናግረዋል። የዶም ኮፐር ቀለም እና የውጪያዊ ግድግዳ ቀለም፣ ሞዛይኮች፣ መብራቶችና ጄነሬተር ከውጪ ሀገር የሚመጡ መሆናቸውን አመልክተው፣ እነዚህን ለማስገባት የውጪ ምንዛሪ እጥረት ማጋጠሙን ይናገራሉ። ምንዛሪውን ለማግኘት ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ቢቀርብም ለማግኘት መቸገራቸውን ይገልፃሉ። በዚህ ምክንያትም ጥገናው የሚጠናቀቅበት ጊዜ እንዲራዘምና ሦስት ወራት የጊዜ ገደብ እንዲጨመር መደረጉን ያስረዳሉ።
የካቴድራሉን እድሳት በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡት አስተዳዳሪው ለሥራው የሚውል መዋዕለ ንዋይ የማሰባሰብ መርሐ ግብርን የተመለከተ ጉዳይም አንስተዋል። ለዚህ ተብሎ የተቋቋመው ኮሚቴ ገንዘብ ለማሰባሰብ የተለያዩ ስልቶችን እየተጠቀመ እንደሆነ ገልፀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የመጀመሪያው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራና የገንዘብ ማሰባሰቢያ ቁስቀሳ ሥራ ነው። ሌላው ከአዲስ አበባ ባሕል ቱሪዝምና ኪነጥበብ ቢሮ ጋር በመተባበር በስካይ ላይት ሆቴል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን በማድረግ እስካሁን ድረስ 90 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ ተችሏል። በኢንተር ኮኒቲኔንታል ሆቴል መሰል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ሥራ ተዘጋጅቷል። ይህ መርሐ ግብር በቀጥታ ስርጭት በመገናኛ ብዙኃን ገንዘብ የማሰባሰብ እቅድን ያካተተ ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም