የክለቦች ደካማ አደረጃጀት በኢትዮጵያ የእግር ኳስ እድገት ላይ ትልቁ እንቅፋት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት እነዚሁ ክለቦች «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንደሚባለው ብሂል አብዛኞቹ በመንግሥት ዳረጎት እየተሰፈረላቸው የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ እግር ኳሱ የተሻለ እድገት እንዲኖረውና ክለቦች ሕዝባዊ መሠረት እንዲላበስ የሚያስችል ስልት በፌዴሬሽኑ እና ስፖርቱን በሚመሩት ተቋማት አለመፈጠሩ ሌላው መሰናክል እንደሆነ የስፖርቱ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡
የዝግጅት ክፍላችን ባሳለፍነው ሳምንት የሊግ አደረጃጀት እና ክለቦች የሚገኙበትን ነባራዊ ሁኔታ በሚመለከት ሰፋ ያለ ዳሰሳ አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ የእግር ኳስ ክለቦች ከአመሰራረታቸው አንስቶ በፖለቲካ ተፅእኖ ውስጥ የሚያልፉ መሆናቸው የሚያሳዩ መረጃዎችን ጠቃቅሰን አልፈን ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አብዛኞቹ ክለቦች በመንግሥት እና በልማት ድርጅቶች የሚተዳደሩ በመሆናቸው እራሳቸውን በፋይናንስ ሊደግፉ እና በነፃነት ሊመሩ የሚችሉበት ቁመና ላይ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ጥናትም ጠቁመናል፡፡ የፋይናንስ ግልፅነት እና ተጠያቂነት ችግርም ሌላኛው የሊጉ የአደረጃጀት ፈተና መሆኑንም አንስተናል፡፡
የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ ባስቀመጣቸው መለኪያዎች ሲቀመጡ አሁን ያሉት ክለቦች የክለብነት መስፈርት አያሟሉም፡፡ የስፖርታዊ፣ የመሠረተ ልማት፣ የአስተዳደርና የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ እንዲሁም የሕጋዊ መስፈርቶችን ተከትሎ አገር ውስጥ ያሉ ክለቦችን ሲለኩ አብዛኛዎቹ «ክለብ» ለመባል የማይበቃ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ነው የተለያዩ ሰነዶች የሚያመለክቱት፡፡ በተጨማሪም አዲስ አደረጃጀት ማለትም የአክሲዮን እና የሊግ ካምፓኒ አደረጃጀትን ተረድቶ ተግባራዊ የማድረግ ዝግጁነት እንደሌላቸውም መረዳት ይቻላል፡፡ አንዳንድ የስፖርት ባለሙያዎች እንደ ዳንቴል የተወሳሰበውን የእግር ኳስ ፈተና በጥልቀት መታየት ይኖርበታል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡
በዛሬው የእሁድ ገፅ የስፖርት አምዳችን ችግሮቹን ከላይ ጠቆም እንዳደረግነው ሁሉ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ክለቦችን ለመመስረት እና ለማስተዳደር ምን ዓይነት መስፈርቶች ሊሟሉ ይገባል? የአገራችን ክለቦች ቁመና ከዚህ መስፈርት አንፃር ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሚለውን ጉዳይ በስፋት እንዳስሳለን፡፡ ጉዳዩን በጉልህ ለማየት እንድንችል «FIFA club licensing Regulation» ወይም የፊፋን የክለቦች ፍቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር ሕግ እንደ ማንፀሪያ እንጠቀማለን፡፡
ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ የክለቦች ፍቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር ሥነ ሥርዓትን እንዲሁም መስፈርት ፈር የሚያስያዝ ሕግ በዋናነት ያወጣበት ምክንያት በአገር አቀፍ እና በኢንተርናሽናል ደረጃ የሚካሄዱ የሊግ ውድድሮችን በተሻለ ደረጃ እንዲከናወኑ፤ እግር ኳስ በማህበረሰቡ ውስጥ ተወዳጅነቱ ጠብቆ ዘላቂ እንዲሆን፤ ክለቦች የሚያንቀሳቅሱት ፋይናንስ ግልፅ አሠራር እንዲኖረው ለማድረግ፤ የክለቦቹ መስራቾች እና ባለቤቶች በግልፅ እንዲታወቁ እንዲሁም የቁጥጥር ሥርዓታቸው ግልፅ እንዲሆን ነው፡፡ በዚህ አግባብ ዓለም ላይ ውጤታማ የሆኑ የሊግ ውድድሮች እና ተሳታፊ ክለቦች ተፈጥረዋል፡፡ እግር ኳስም ከስፖርቶች ሁሉ ልቆ ተወዳጅነቱ በዓለም ላይ ግዘፍ ነስቷል፡፡ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ግን ከዚህ እውነታ ተቃራኒ ነው፡፡
የአገራችን ክለቦች በፊፋ መስፈሪያ
አንድን የእግር ኳስ ቡድን ክለብ የሚያሰኘውን ደረጃ የሚያሟላበት እና እግር ኳሱን በበላይነት ከሚመራው ፌዴሬሽን ፍቃድ የሚያሰጠው ስፖርታዊ መስፈርት ‹‹sport criteria›› አሟልቶ ሲገኝ ነው፡፡ የመጀመሪያው ስፖርታዊ መስፈርት ክለቦች ታዳጊዎችን የሚያፈሩበት ፕሮጀክት ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚገልፅ ሲሆን በዚህ ውስጥ ታዳጊዎች በታክቲክ እና ቴክኒክ እንዲሁም በስነልቦና አንፆ ማፍራት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ከስፖርታዊ ክሎት በተጨማሪ የቀለም ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ማመቻቸት እና መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ከህክምና የማሰልጠኛ ሜዳን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርታዊ ቁሶችንም በበቂ ሁኔታ ማሟላት ይኖርበታል፡፡ ታዳጊዎችን በዚህ መንገድ ቀርፆ ማውጣትም ክለቡ ለዋናው ቡድን መጠናከር ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው፡፡ ለእግር ኳስ እድገትም ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡
ከላይ በጠቀስነው መስፈርት መሠረት አብዛኛዎቹን የአገራችንን ክለቦች ስንመለከታቸው እጅግ ወርደው እናገኛቸዋለን፡፡ ለይስሙላ በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ያሉ ታዳጊዎችን በፕሮጀክት መንገድ አቅፈው ቢይዙም ነገር ግን ዓለም አቀፍ መስፈርትን ባሟላ መንገድ ለእግር ኳስ ፍቅር እና ፍላጎት ያላቸውን ታዳጊዎች የሚያንፅ ፕሮጀክት የላቸውም፡፡ በእርግጥ ይህን መሰል ፕሮጀክት ከፍተኛ ገንዘብ እና ፕሮፌሽናል ባለሙያ የሚፈልግ ቢሆንም ቅሉ የረጅም ጊዜ ውጤታማነትን አስበው ታዳጊዎችን ለማፍራት ጥረት ሲያደርጉ አይስተዋልም፡፡ በተለይ ክለቦች ለዋናው ቡድናቸው ተጫዋቾች የሚከፍሉትን ዓመታዊ ደመወዝ እና መሰል የተጋነኑ ወጪዎች ስንመለከት በእርግጥ ይህን ማድረግ ተስኗቸው ይሆን? የሚል ምፀታዊ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ በመሆኑም ፊፋ ባወጣው መስፈርት የታዳጊ ፕሮጀክት መስፈርት ስንመዝናቸው ደረጃ ውስጥ እንኳን ሊያስገባቸው የሚችል አቋም ላይ አለመሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡
ሌላኛው መስፈሪያ መሠረተ ልማት ነው፡፡ የተሟላ የስፖርት መሠረተ ልማት ለአንድ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ክለብ ዋናና አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ ደረጃውን የጠበቀ የልምምድ እና የመጫወቻ ስታዲዮም ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚህ ጋር የታዳጊዎች ካምፕን ጨምሮ አስፈላጊ የሚባሉ የመሠረተ ልማት መስፈርቶችን ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡ አሁን አሁን የስፖርቱ አፍቃሪ ማህበረሰብ ውድድሮችን በተሟላ እና ምቾት ባለው ስታዲዮሞች መመልከት ይፈልጋል፡፡ ገንዘቡን እና ጊዜውን ሲያፈስም ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ክለቦች የደጋፊዎቻቸውን እና የስፖርት አፍቃሪዎችን ፍላጎት ሊያሟላ በሚችል መንገድ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ሊያሟሉ ይገባል፡፡
በዚህ መመዘኛ የአገራችን ክለቦች የት ደረጃ ላይ ናቸው ብለን ስንጠይቅ አሁንም የምናገኘው ምላሽ ‹‹እጅግ ዝቅተኛ ነው›› የሚል ነው፡፡ በቂ ገበያ የማፈላለግ እና የፋይናንስ አቅም የማጠናከር ሥራ ሰርተው የተሟላ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን የማከናወን አቅም ያላቸው አይደሉም፡፡ የግል ንብረታቸው የሆኑ ስታዲዮሞች የላቸውም፡፡ በጣት በሚቆጠሩ ክለቦች ጅምር እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም ቅሉ ሁሉም መንግሥት በገነባቸው ሜዳዎች ላይ ነው ጨዋታዎቻቸውን የሚያካሂዱት፡፡ ይሄም ቢሆን ፊፋ ባስቀመጠው ዘመኑን የሚመጥኑ ሜዳዎች ደረጃ ስንመለከተው ለልኬት እንኳን የማይመጥን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
አፈር እና ድንጋይ ብቻ በሞላቸው ሜዳዎች ላይ የሊግ ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡ ይሄ ደግሞ የክለቦቹንም ሆነ የሊጉን ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ይገኛል፡፡ በተለይ እግር ኳሱ አንድ ቦታ እንዲቆም እና እንዳያድግ እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ውስብስብ ችግሮች መካከል የስፖርት መሠረተ ልማት ቀዳሚውን ይዛሉ፡፡ እንደ አገር በዚህ ዘርፍ ላይ እየተሰራ ያለው ክንዋኔ እንደ በጎ ጅምር ቢወሰድም በክለቦች ደረጃ ግን እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡
ሦስተኛው የክለቦች መመዘኛ መስፈርት ‹‹የክለብ አስተዳደር እና አመራር›› ነው፡፡ አሁን አሁን የእግር ኳስ ክለቦች ከስፖርታዊ እንቅስቃሴያቸው በላይ ትልቁን ትኩረት የሚስቡት በሌሎች አትራፊ ሥራዎች ላይ መሰማራታቸው እና አቅማቸውን ማጎልበታቸው ነው፡፡
ዓለም ላይ ስኬታማ የሆኑ ክለቦች አስተዳደራቸው ጠንካራ በመሆኑ ኢኮኖሚያቸውን እጅግ ሲያፈረጥሙ እና የስፖርቱን ደረጃ ዙሩን በማክረር ሲመሩት እንመለከታለን፡፡ የገበያ ስልታቸው እጅግ ጠንካራ ከመሆኑም ሌላ የፋይናንስ፣ የመዝናኛ እና የሚዲያ ክፍሎችን በማጠናከር የክለቦቻቸውን ኃያልነት እና ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ሥራ ይሰራሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የፋይናንስ ነፃነታቸውን ማወጅ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም በፕሮፌሽናል ደረጃ ተመዝግበው ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ክለቦች አስተዳደራቸው በጠንካራ ባለሙያዎች እና አመራሮች የሚተዳደር መሆን አለበት፡፡
በዚህ መስፈርት የምንቃኛቸው የአገራችን ክለቦች የሚገኙበት ደረጃ አሳዛኝ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ክለቦቹ በአማተር የሚመሩ እንዲሁም ብቁ ባለሙያዎች የሌላቸው ናቸው፡፡ ደካማ የገበያ ስልት የሚከተሉ እንዲያውም ከመንግሥት ተመፅዋችነት ያልተላቀቁ ናቸው፡፡ በተለይ በርካታ ደጋፊ ያላቸው ክለቦች አጋጣሚውን ወደገበያ ቀይረው እራሳቸውን ማጠናከር የተሳናቸው ናቸው፡፡ የእውቀትም የተነሳሽነትም ችግሮች በነዚህ ክለቦች ላይ ይስተዋላል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀማቸውም ዘመኑን ያልዋጀ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን አይችሉም፡፡ ውድድሮችን ለማድረግ የሚያስችል የግል አቅም አይፈጥሩም፡፡ ይህ ደግሞ ከላይ ለጠቃቀስናቸው ችግሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አጋልጧቸዋል፡፡
ለመጠቅለል
ፌዴሬሽኑ በአድራጊ ፈጣሪነት በሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የሚገኙ ክለቦች የአመራርነት እና የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ እግር ኳሱን እና የአገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ የሚያደርጉ ሕጎች እና ደንቦችም አይዘጋጁም፡፡ ውድድሮች እንዴት እንደሚመሩ የሚያሳይ አጠቃላይ ሰነዶችም እንዲሁ፡፡ ይህ በተዘዋዋሪ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ ክለቦች እንዳይፈጠሩ እንቅፋት ሆኗል፡፡ በፊፋ የክለቦች ደረጃ አወጣጥ መስፈርት ስንመዝናቸውም ‹‹ክለብ ለመባል የሚያበቃ›› አቋም ላይ አይገኙም፡፡ ይባስ ብሎ አሁን ላይ እግር ኳስ ሜዳዎች እና ቡድኖች የብጥብጥ እና የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ዋንኛ ምሳሌዎች እየሆኑ ነው፡፡ ጭርሱኑ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› የሚባለው ይህን ጊዜ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 19/2011
ዳግም ከበደ