ባለፈው ሐሙስ ነው፡፡ በጠዋት ወደ ሥራ ቦታ የሚያደርሰኝ ተሽከርካሪ ውስጥ እያለሁ መገናኛ ‹‹ዲያስፖራ›› አደባባይ ፊት ለፊት ለማውረድና ለመጫን ተሽርካሪው ቆመ፡፡ ጉዞውን ሊጀምር ሲል ግን በመስኮት በኩል ያሉ ሰዎች ግርግር አበዙ፤ መስኮቱን ከፍተው አሻግረው እያዩ የሚስቀው ይስቃል፤ የሚበሳጨው ይበሳጫል፡፡
ሳነብ የነበረውን መጽሔት አጠፍኩና እኔም ወደሚያዩት ነገር አንገቴን ስቀስር አንድ ጎልማና አንዲት በግምት የ10 ዓመት የምትሆን ሴት ልጅን ፖሊስ ይዟቸዋል፡፡ ዙሪያውን የከበባቸው ሰውም ግማሹ ይስቃል ግማሹ ያዝናል፡፡ እግዜር ይስጠው አሽከርካሪያችንም የወሬ ጥማታችንን እንወጣ ዘንድ ዝም አለን፡፡
እርግጠኛ ነኝ ይሄኔ የገመታችሁ የአስገድዶ መድፈር ድርጊት ነው፤ ያ ቢቀር እንኳን ጾታዊ ትንኮሳ ሳይመስላችሁ አይቀርም፡፡ ኧረ በፍፁም ስላችሁ! ደግሞስ የ10 ዓመት አካባቢ አዳጊ ምኗ ይተነኮሳል? ለነገሩ በዜና ከምንሰማው አንጻር ይሄ እንኳን የሚጠበቅ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ግን አስገድዶ መድፈርም ሆነ ጾታዊ ትንኮሳ አልነበረም፡፡
ግድንግዱ ጤነኛ ጎልማሳ ልጅቷን ሊለምንባት እያስተኛት ነበር፡፡ ቀደም ብለው ድርጊቱን ካዩ ሰዎች እንደተረዳሁት ገና አነጣጥፎ ሊያስተኛት ሲል ነው አሉ ፖሊስ የደረሰበት፡፡ ፖሊስ ግን ሁሌም እንዲህ ዓይነት ክትትል ቢያደርግ!
ፖሊስ ሆዬ ለካ ድርጊቱን ሲያይ(ጾታዊ ትንኮሳ መስሎትም ይሆናል) ሁለቱም ጤነኛ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ የአተኛኘቱንና በሽተኛ የመምሰሉን ነገር በደንብ ሲያሳያት ፖሊስ እያየ ነበር፡፡ ልክ አነጣጥፎና እንደ በሽተኛ አለባብሶ እንደጨረሰ ፖሊስ አንገቱን ያዘው፡፡
እሷንም እሱንም አገላብጦ ሲያይ፤ እሱም በሬ መጎተት የሚችል ወጠምሻ፣ እሷም ፈጣሪዋ ይመስገንና ምንም ያልሆነች ድንቡሽቡሽ ልጅ ናት፡፡ ይህን ያየ ፖሊስ ሰውየውን ሲገላምጥ ሰውየው ከአፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ጭራሽ የምን አገባችሁ ክርክር ጀመረ (የፈሲታ ተቆጢታ)፤ ሊያመልጥ ሁሉም ሞክሮ ነበር፡፡
በዚህ እየተከራከሩ ሳለ አሽከርካሪያችን ‹‹ምነው እንግዲህ ይበቃችኋል!›› ብሎ ጉዟችንን ጀመርን፡፡ ለማንኛውም የሆነውን ነገር ዓይተናል፤ አውቀናል፡፡ ምናልባት ፖሊስ ምን እንደሚ ያደርገው አይታወቅም፡፡
እንግዲህ ፖሊስ ምንም ያድርገው ምን እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች የእውነት ነበሩ ማለት ነው(እኔ እኮ አላምንም ነበር)፡፡ በእርግጥ በሀሜት ደረጃ እሰማለሁ(ማየት ማመን ሆነ እንጂ)፡፡ ቤንዚንና የተለያዩ ቀለማቀለም እየተቀቡ ቁስለኛ ሆነው የሚለምኑ እንዳሉ ይወራል (ምነው ተዋናይ በሆኑና ይሄን ወቀሳ የበዛበት ፊልም ባስመሰገኑት!)
ልመናን ልመና ያነሳዋልና ሌላ የልመና ገጠመኝ ትዝ አለኝ(እንዳትሰለቹ እለምናች ኋለሁ)፡፡ ይሄ እንኳን አንድ ጓደኛዬ የነገረኝ ነው(ደግሞ እኮ ይሄም መቼቱ መገናኛ መሆኑ ነው)፡፡ አንዲት ሴትዮ ከአንድ ዓመት በፊት መንታ ልጆች ይዛ ያያል፤ በዚያ ባለፈ ቁጥር ልቡ ይሰበራል፡፡ በመሃል ቦታ ቀይራ ይሁን ስለለመደው ልብ ባለማለቱ አንድ ዓመት ያህል አላያትም፡፡ በቅርቡ ግን ያችው ሴትዮ እዚያው ቦታ ላይ ሌላ ልጆች ይዛ አየ፡፡
አንድ ዓመት ሁሉ ቆይታ ባያድጉ እንኳን ከእነዚህ ያነሱ አይሆኑም ነበር፡፡ የሴትዮዋ ነገረ ሥራ ገረመውና የብዙ ለማኞች ታሪክ እንደዚያ መሰለው፡፡ ልመና መደበኛ ሥራ እየሆነ ነው፡፡ የተለያየ የአሠራር ስልት እየተቀረጸለት መሰማራት ሆኗል፡፡ ጤነኛው እንዲህ እያደረገ ሲለምን የተቸገረውስ ምን ያድርግ?
የአካል ጉዳተኛ ሆነው ከማንም ያላነሰ (እንዲያውም የተሻለም) የሚሠሩ እያሉ ሙሉ ጤነኛው ግን እንዲህ ያደርጋል፡፡ የምር ይሄንማ ፖሊስ መከታተል አለበት፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ጤነኛ ሲለምን ነበር የማዝነው(አሁን ግን አናደዱኝ)፡፡ ጤነኛ የሚለምነው ያለምክንያት አይደለም፤ በጣም ቢቸግረው ነው፡፡ በዚያ ላይ ጤነኛ እኮ ማንም አይሰጠውም በሚል ያሳዝነኝ ነበር፡፡ እንዲህ በማጭበርበር ሲሆን ግን ያበሳጫል፡፡ የምር ለተቸገረ እኮ ማንም ይሰጥ ነበር፡፡
እዚህ ላይ ለማኞቹ ብቻ አይደሉም ጥፋተኛ፤ ልጆቻቸውን የሚያከራዩት እንጂ (መቼም በኪራይ ቢሆን ነው)፡፡ ቆይ ግን ምን ዓይነት የወላድ አንጀት ነው? ከዚህ ይልቅ ቢያንስ ራሷ እናቷ ብትለምን አይሻልም? ወይስ እናትየዋ ሌላ ሥራ ይዛ ልጅን መለመኛ መስጠት ተጨማሪ ገቢ ይሆን? የእናት ሆድ ይህን ያደርጋል ብሎ ማሰብ ይከብዳል!
እግረ መንገዳችንን አንድ ሃሳብ እናንሳ፡፡ እነዚህ መንገድ ላይ መለመኛ የሚሆኑ ሕፃናት ያለዕቅድ የተወለዱ ናቸው፡፡ ‹‹ኑሮዋ ሳይስ ተካከል እንዴት ጎዳና ላይ እያለች ትወል ዳለች?›› የሚል ፈራጅ አይጠፋም፡፡ ይሄ ጥያቄ በሁለት ምክንያት ትክክል አይሆንም፡፡ አንደኛ ሕፃናቱ የተወለዱት ጎዳና ላይ ከወጣች በኋላ አይደለም(ምናልባት የሚሆንም ይኖራል)፡፡ ጎዳና ላይ የወጣችው ከወለደች በኋላ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ጥፋቱ የሴቷ ሳይሆን የወንዱ ነው፡፡
ትዳር አገኘሁ ብላ፣ ሕይወትን ያሻሻለች መስሏት፣ የሰው ልጅ ማህበራዊ ሕይወት የሚያምረው በትዳር ነውና የወግ ማዕረጉን ለማድረግ ስትል አንዱን ሰካራም ታገባለች፡፡ ልጅ ከተወለደ በኋላ አብሮ መኖሩ ጎዳና ላይ ከመለመን የከፋ ይሆናል፡፡ ጎዳና ላይ ያሉት በአደባባይ ስለታዩ እንጂ ወደ ሴተኛ አዳሪነት የሚገቡትም ቀላል አይደሉም፡፡
በእርግጥ ይሄ ጥፋት የወንዱ ብቻ ነው ማለትም ላይሆን ይችላል፡፡ እንደየ ባህሪያቸው ችግሩ ከእሷም ሊመጣ ይችላል፡፡ አለፍ ሲል ደግሞ የሁለቱም ጥፋት ላይሆን ይችላል፡፡ በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ያለው መሰናክል ብዙ ነው፡፡ ተዋደው ተፈቃቅረው እየኖሩም ድንገት አስገዳጅ ሁኔታ ይከሰታል፡፡ እንዲያውም ጎዳና ላይ የሚያወጣው እንዲህ ዓይነቱ ድንገተኛ የሚያለያይ ነገር ሲፈጠር ነው፡፡
በከተማችን ውስጥ ብዙ ዓይነት ልመና አለ፤ ከምንም በላይ ግን ሕፃናት ይዞ ልመና በጣም ልብ ይሰብራል፡፡ ሕፃን ልጅ ተርቦ እንደማየት ውስጥን የሚረብሽ ነገር የለም፡፡ በዋናነት ድህነት ቢሆንም ግን የችግሮቹ ምክንያት ድህነት ብቻ አይሆንም፡፡ ከግል ባህሪ ጋር ተያይዞም ሊፈጠር ይችላል፡፡
በአካባቢዬ የማውቀው አንድ ገጠመኝ ነግሪያችሁ ሃሳቤን ልቋጭ! ባልዬው ሰካራም ነው፤ ሌላ ሴት ጋር ይሄዳል እየተባለ ይታማል፡፡ በዚህም ሚስቱ በጣም ትቀናለች፡፡ እንደ አካባቢው ነዋሪ ቤታቸው ከማንም የተሻለ እንጂ ያነሰ አይደለም፡፡ በሰውዬው ባህሪና በእሷ ቅናት ምክንያት መግባባት አልቻሉም፡፡ ዕለት ከዕለት ይጣላሉ፡፡ በዚሁ ምክንያት ገና ጡት ያልተወ ሕፃን ጥላ ምኑንም ወደማታውቀው አዲስ አበባ ስትሄድ ከመንገድ ተያዘች፡፡
ያቺ ሴት ሄዳ ቢሆን ኑሮ ከልመና ወይም ከሴተኛ አዳሪነት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበራትም፡፡ ማህራዊ ሕይወታችንም ችግር አለበት ማለት ይህ ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 19/2011
ዋለልኝ አየለ